“በሚሞት ሰውነታችሁ ኃጢአትን አታንግሡአት” (ሮሜ. ፮፥፮)
በእንዳለ ደምስስ
ኃጢአት የሚለው ቃል “ኃጥአ” ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም፡- አጣ፣ መገፈፍ፣ መነጠቅ ማለት ነው፡፡ አዳም አባታችን ለሰባት ዓመታት በገነት ፍጥረታትን እየገዛና እያዘዘ በተድላና ደስታ ሲኖር በምክረ ከይሲ ተታሎ አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስ በላ፣ ኃጢአትንም በራሱ ላይ አነገሣት፣ የእግዚአብሔርንም ትእዛዝ ተላለፈ፡፡ በዚህም ምክንያት ክብሩን አጣ፣ ጸጋውም ተገፈፈ፣ በእግዚአብሔር የተሰጠውንም የገዢነት ሥልጣን ተነጠቀ፣ እስከ መረገምም አደረሰው፡፡ “ከእርሱ እንዳትበላ ከአዘዝኩህ ከዚያ ዛፍም በልተሃልና ምድር በሥራህ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤ እሾህና አሜከላ ታበቅልብሃለች፣ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ፤ ወደ ወጣህበት ምድር እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ ትበላለህ፣ አፈር ነህና ወደ አፈርም ትመለሳለህና” ተብሎ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ፣ ገነትን ያህል ቦታ አጣ፤ወደ ምድረ ፋይድም ተባረረ፡፡ ዘለዓለማዊ ሆኖ የተፈጠረው የሰው ልጅ በራሱ ላይ ኃጢአትን አንግሧልና ዘለዓለማዊነትን አጣ፤ ይህ ፍርድ የኃጢአት ሥራ ያስከተለው ውጤት እንደሆነ እንረዳለን፡፡
አዳም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መተላለፉን በተረዳ ጊዜ ኃፍረቱን ይሸፍን ዘንድ ቅጠልን አገለደመ፣ ተሸሽጎም በደሉ ዕረፍት ነስቶት በጸጸት አለቀሰ፡፡ (ዘፍ. ፲፯-፲፱) እግዚአብሔር ፍርዱ እውነተኛ ነውና ሞት በምድር ላይ ነገሠ፡፡ አዳምም ከነበረው ክብር ወረደ፤ “የኃጢአት ትርፍዋ (ደመወዝዋ) ሞት ነውና” (ሮሜ. ፮፥፳፫) ተብሎ እንደተጻፈ በወዙና በላቡ ይበላ ዘንድ እሾህና አሜኬላውን እየመነጠረ ምድርንም እየቆፈረ ሕይወቱን ለማቆየት ታገለ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ፍጹም ቸር ነውና የአዳምን ንስሓ ተመልክቶ “አምስት ቀን ተኩል ሲሆን ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ” (ቀሌ. ፫፥፱) ባለው አምላካዊ ቃሉ መሠረት አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ይህንን ዓለም ያድን ዘንድ ተወለደ፡፡
መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስም “እነሆ የዓለሙን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፡፡ ከእኔ በፊት የነበረ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል ብዬ ስለ እርሱ የነገርኋችሁ ይህ ነው፤ እርሱ ከእኔ አስቀድሞ ነበርና፡፡ ነገር ግን እስራኤል እንዲያውቁት ስለዚህ እኔ በውኃ ላጠምቅ መጣሁ፡፡” (ዮሐ. ፩፥፳፱-፴፩) ሲል የመሠከረለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገባው ቃል መሠረት በዚህ ምድር ላይ ተመላለሰ፡፡ ወንጌልን አስተማረ፣ ድውያንን ፈወሰ፣ በቀራንዮ አደባባይ በመስቀል ላይ ተሰቀለ፣ ሞተ፣ ተቀበረ፣ በትንሣኤውም ትንሣኤያችንን አወጀ፡፡ አዳምና ልጆቹንም ወደ ቀደመ ክብራቸው መለሰ፡፡
እግዚአብሔር ኃጢአትን እንጂ ኃጢአተኛን አይጠላምና የተከፈለልንን ዋጋ አስበን እንደ ቃሉም ተጉዘን፣ የተሰጠንን ክብር ጠብቀን መገኘት ከእኛ ከኦርቶዶክሳውያን ይጠበቃል፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በላከው መልእክቱ “በሚሞት ሰውነታችሁ ኃጢአትን አታንግሡአት” (ሮሜ ፮፥፮) ሲል የሚያሳስበን፡፡
ኃጢአት ከእግዚአብሔር አንድነት ይለያል፣ ሥጋንና ነፍስን ያጎሳቁላል፣ በመጨረሻም ወደ ሞት ያደርሳል፡፡ በተለይም በርካታ ወጣቶች ይጉዳቸው ወይም ይጥቀማቸው ሳያመዛዝኑ ሁሉንም የመሞከር ችግር በከፍተኛ ደረጃ ስለሚታይባቸው በቀላሉ ኃጢአትን ለመለማመድ ይፈጥናሉ፡፡ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ወጣትነትን የእሳትነት ዘመን መሆኑን ታስተምራለች፡፡ ይህንን የእሳትነት ዘመንን በመንፈሳዊነት ማረቅ፣ መግራት ካልተቻለ ጥፋቱ ከራስ አልፎ ቤተሰብን፣ ማኅበረሰብንና ሀገርን እንዲሁም ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ይጎዳል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለመንፈስ ልጁ ጢሞቴዎስ “አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ጸንተህ ኑር፤ ከማን እንደተማርኸው ታውቃለህና” (፪ጢሞ. ፫፥፲፬) እንዲል ከእግሩ ሥር ቁጭ ብሎ በመማሩ፣ የሚያከናውናቸውን መንፈሳዊ ተግባራት ሁሉ በማገዝና በመሳተፍ መንፈሳዊነትን ገንዘብ አድርጓልና ወጣትነቱን ተጠቅሞበታል፡፡ ከእግሩ ሥር ቁጭ ብሎ ሲማርና ሲያገለግለው የነበረው ደቀ መዝሙሩ ዴማስ ግን የወጣትነት ስሜቶች ተገዢ ሆኖ ለዓለም እጁን በመስጠት፣ ብልጭልጯ የተሰሎንቄ ከተማ ማርካው ከአገልግሎቱ አሰናክላ ጥላዋለች፤ ኃጢአትንም በራሱ ላይ አነገሣት፡፡ “ዴማስ ይህንን የዛሬውን ዓለም ወድዶ እኔን ተወኝ፤ ወደ ተሰሎንቄም ሄደ” (፪ጢሞ. ፬፥፲) እንዲል ፡፡
የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎቻችንም በወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚገኙ በመሆኑ ከቤተሰብ የሚርቁበት፣ በራስ መተማመን የሚያዳብሩበት፣ ለዓለሙም ሆነ ለመንፈሳዊው ዓለም ራሳቸውን አጋልጠው የሚሰጡበት ጊዜ ላይ በመሆናቸው በማስተዋል ራሳቸውን ሊመሩ ይገባል፡፡ ሥጋዊ ፍላጎትና የጓደኛ ግፊት ሳይበግራቸው ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ የሚታገላቸውን የኃጢአት ቀንበር አሽቀንጥረው በመጣል በመንፈሳዊ ሕይወት መታነጽ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዲያብሎስ ዙሪያቸውን አጥሮ ከመንገዳቸው ሊያስወጣቸው እንቅልፍ እንደሌለው በመረዳት ከምን ጊዜውም በላይ በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደትና በአገልግሎት በመትጋት ድል ሊነሡት ይገባል፡፡ “እንግዲህ ዐዋቂዎች ሁኑ፣ ትጉም፣ ጠላታችሁ ጋኔን የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና፡፡ እርሱንም በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት” በማለት ቅዱሰ ጳውሎስ እንዳስተማረው፡፡ (፩ጴጥ. ፭፥፰-፱)
በሁለቱም ወገን ማለትም ዓለማዊውን ጥበብ በመንፈሳዊ ጥበብና ዕውቀት በመግራት ሀገርንና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለመጥቀም ትክክለኛ ጊዜው የወጣትነት ጊዜ ነው፡፡ ይህን ጊዜ በዋዛ ፈዛዛ ማሳለፍ ስለማይገባ ከእግዚአብሔር የተሰጠንን የወጣትነት የዕድሜ በረከት ልንጠቀምበት ያስፈልጋል፡፡ “በሚሞት ሰውነታችሁ ኃጢአትን አታንግሡአት” (ሮሜ. ፮፥፮) ተብለን እንደተማርን መንፈሳዊነትን ለጽድቅ አገልግሎት በማዋል ዓለም ከዘረጋችውና ካጠመደችው የኃጢአት ወጥመድ ልንርቅ ይገባል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!