በስመ አብ ወወልድ ወንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡ አሜን

በመላው ዓለም የተስፋፋውን የኮሮና ወረርሽኝ ለመግታት ከኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ

ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ መግለጫ

በሀገራችን በኢትየጵያ በገጠር፣ በከተማና በመላው ዓለም ለምትገኙ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን በሙሉ!

ወቅታዊ የሰው ልጅ ሥጋት በመሆን በመላው ዓለም በፍጥነት በተስፋፋው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ዓለም አቀፍ ሥጋት ስለተከሰተ መንግሥታት ሀገርን ከጥፋት፣ ሕዝቡን ከሞት ለመጠበቅ አዋጆችን እያወጡ ይገኛሉ፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት ለመታደግ እምነትና ቀኖናን ጠብቆ ሃይማኖታዊ መመሪያ የመስጠት ሐዋርያዊ ኃላፊነት አለባት፡፡

ስለዚህ ቀሚ ሲኖዶስ የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት መሠረተ እምነትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ጠብቆ ለሁሉም ካህናትና ለሕዝበ እግዚአብሔር ደኅንነት ሲባል የሚከተሉትን መመሪያዎች አስተላልፏል፡-

  1. በሰሙነ ሕማማት እንደምናደርገው የእርስ በርስ መሳሳም ቀርቶ ራስን ዝቅ በማድረግ እጅ መንሳት ወይም በእማሄ ሰላምታ በማቅረብ እንዲፈጸም፣
  2. ወረርሽኙ በሰዎች መሰባሰብ የሚስፋፋ ስለሆነ ማናቸውም መንፈሳዊ ጉባኤያት፣ የትምህርት ክፍለ ጊዜያት፣ ወደ ገዳማትና አድባራት የሚደረጉ ጉዞዎች እና ምእመናን የሚሳተፉባቸው ታላላቅ መርሐ ግብሮች ለጊዜው እንዲቋረጡ፣
  3. ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገባም ሆነ አስፈላጊ በሆነበት በጊዜ ሁሉ እጆቻችንን በመታጠብና ዘርዘር ብሎ በመቆም ሥርዓተ አምልኮ እንዲፈጸም፣
  4. ዓመታዊ የንግሥ ክብረ በዓላት በቅደሴና በማኅሌት ታስበው ክብረ በዓላቱ በሌላ ጊዜ እንዲከበሩ፣
  5. የጉንፋን ምልክት ያለባቸው ለሌሎች እንዳያስተላልፉ በቤታቸው በጥንቃቄ ተለይተው በጸሎትና በሕክምና እንዲቆዩ፣ ከቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ አገልግሎትም በልዩ ሁኔታ እንዲያገኙ፣
  6. በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የተስፋ ልዑክ በመሆን እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ተደራጅቶ ተልእኮውን በአስቸኳይ እንዲጀምር፣
  7. ሥርዓተ ቅዳሴን በተመለከተ፡-
  • በቤተ መቅደስ ቀዳስያን በሆኑት ልዑካን ብቻ ሥርዓተ ቅዳሴው እንዲፈጸምና ሌሎች አገልጋዮች በቅድስቱ ዘርዘር ብለው በመቆም እንዲያገለግሉ፣
  • በዕለቱ ለሚቆርቡ ምእመናን አረጋውያን፣ ለወጣቶችና ለሕፃናት የፈረቃ ተራ በማዘጋጀት ቆራቢዎች ብቻ ወደ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ገብተው ዘርዘር ብለው በመቆም እንዲያስቀድሱ፣
  • ሌሎች ምእመናን በአጸደ ቤተ ክርስቲያን ቢያንስ ሁለት የትልልቅ ሰው እርምጃ ያህል በመራራቅ ቆመው እንዲያስቀድሱ፣
  • የቅዳሴ ጠበል በየግል መጠቀሚያ ምእመናን በየቆሙበት ቦታ በጥንቃቄ እንዲሰጥ፣
  • ሌሎች ከቅዳሴ ጋር የተያያዙ ዝርዝር የአፈጻጸም ጉዳዮችን ግብረ ኃይሉ አዘጋጅቶ በቅዱስ ሲኖዶስ በማጸደቅ ለአህጉረ ስብከት በሚልከው መመሪያ መሠረት ተግባራዊ እንዲደረግ፣
  1. ከሥርዓተ ቅዳሴ በተጨማሪ እንደ ስብሐተ ነግሕ፣ ሰዓታት፣ ቁመተ ማኅሌት፣ ጥምቀተ ክስትና፣ ጸሎተ ፍትሐት፣ የመሳሰሉ አገልግሎቶች ለሥርዓቱ በሚያስፈልገው ቁጥር ብቻ እና ውሱን ሊቃውንት በተራ እንዲፈጸም፣
  2. ወረርሽኙ ከዓለም እንዲጠፋ ካህናት ብቻ በቤተ መቅደስ፣ በዐውደ ምሕረትና በአፀደ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ጸሎተ እጣን በማድረስ ማዕጠንት እንዲፈጽሙ፣
  3. በማኅበራዊ ግንኙነት በደስታ፣ በሐዘን፣ በእድር፣ በሥርዓተ ቀብር አፈፃፀምና በመሳሰሉት መሰባሰቦች በሽታው እንዳይሰራጭ አገልግሎቱ በውስን የሰው ቁጥር በጥንቃቄ እንዲፈጸም፣
  4. ምእመናን ራሳቸውን እየጠበቁ በቫይረሱ የተጠቁና አገግመው የወጡ ወገኖችን፣ እንዲሁም በውጭ ሀገር ዜጎች ላይ ከሃይማኖትና ከምግባር የወጣ መገለልና ጥቃት እንዳይደርስባቸው በክርስቲያናዊ ፍቅርና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት እንክብካቤ እንዲደረግላቸው፣
  5. ለነዳያንና ለተቸገሩ ወገኖች አስፈላጊው ማኅበራዊ እና ቁሳዊ እገዛ በሁሉም አጥቢያዎች እንዲደረግ፣
  6. ቤተ ክርስቲያንን ከማይወክሉና ቀኖናዊ ካልሆኑ አሳሳች መረጃዎች በመቆጠብ ሊቃውንት፣ ካህናት፣ መምህራን፣ ሰባክያን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚሰጡ መመሪያዎችን በየአጥቢያችሁና አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ እንድትፈጽሙ እና እንድታስፈጽሙ ተወስኗል፣

በአጠቃላይ በሽታው እስካሁን ለተያዙት፣ በጊዜያዊ ማቆያ ለሚገኙት በሙሉ እግዚአብሔር አምላካችን ምሕረቱን እንዲሰጥልን እንጸልያለን፣

በመላው ዓለም ዜጎቻቸውን በበሽታው ለተነጠቁ ሁሉ መጽናናቱን እንዲሰጥልን ያረፉትንም እንዲምርልን እግዚአብሔርን በጸሎት እንጠይቃለን፣

በመላው ዓለም የምትገኙ ወገኖቻችን የራሳችሁንና የሌሎች ሕይወት ከወረርሽኙ እንዲጠብቅ እንዲሁም የበሽታው ሥርጭት እንዲቆም መንፈሳዊና ማኅበራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ እያሳሰብን የተሰጡት መመሪያዎች ወረርሽኙ እስኪጠፋ ድረስ የጸኑ እንዲሆኑ በጥብቅ እናስታውቃለን፡፡

ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱና በይቅርታው ብዛት ዓለማችንን ከጥፋት የሰውን ልጅ ሁሉ ከመከራ ሞት ይጠብቅልን፡፡ አሜን፡፡

ወስብሐተ ለእግዚአብሔር!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ/ም አዲስ አበባ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *