“በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል” (ኤፌ ፪፥፳)
በኃይለ ኢየሱስ ዘጼዴንያ
ክፍል -ሁለት
የሐዋርያት ጾም ስያሜና ቀኖናዊ መሠረቱ
ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣበትን መለኮታዊ ዓላማ አጠናቆ ወደ ባሕርይ አባቱ ከማረጉ በፊት ቅዱሳን ሐዋርያትን ሰብስቦ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፤ ያዘዝኋቸውን ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴ፳፰÷፲፱ -፳) በማለት ታላቁን ተልእኮ አዟቸው ነበር፡፡
በፍርሃት ውስጥ ሆነው ይህንን መለኮታዊ አደራ የተቀበሉት ሐዋርያት ለአገልግሎት ከመሰማራታቸው በፊት ከፍርሃታቸው የሚያላቅቃቸው፤ የሚያጽናናቸው እና የሚያበረታታቸው እንዲሁም ከሐሰተኛው ዓለም ለይቶ ወደ እውነት ሁሉ የሚመራቸው ሰማያዊ ኃይል ያስፈልጋቸው ነበርና “አንትሙሰ ንበሩ ሀገረ ኢየሩሳሌም እስከ ትለብሱ ኃይለ እም አርያም፤ እናንተ ግን ከአርያም ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ቆዩ፡፡”(ሉቃ ፳፬÷፵፱) የሚል ትእዛዝ ተነግሯቸው ተስፋም ተስጥቷቸው ነበር፡፡
በተስፋውም መሠረት ኢየሩሳሌም በማርቆስ እናት በማርያም ቤት ሁሉም ተሰብስበው በጸሎት እየተጉና በአንድ ልብ ሆነው ይህንን ሕያው ተስፋ በመጠባበቅ ሳሉ ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን መካከል በተነሣ በኀምሳኛው ቀን ባረገ በዐሥረኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ እሳት ወረደላቸው፤ የፍርሃት መንፈስ ተወግዶ በምትኩ ደፋሮችና በብዙ ቋንቋዎች የሚናገሩ ሆኑ፤ በሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ስብከትም በአንድ ቀን ሶስት ሺህ ነፍሳት አምነው ተጠመቁ፡፡
ዕለቱም የቤተ ክርስቲያን መመሥረት እውን የሆነበትና አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበት ስለነበር የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን ተባለ፡፡ (የሐዋ. ፪÷፩-፵፯) የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተገልጦ ፍርሃትና ስጋታቸው የተወገደላቸው ቅዱሳን ሐዋርያት ለወንጌል አገልግሎት ከመሠማራታቸው በፊትና ሕገ ወንጌልን ከማስተማራቸው አስቀድሞ አገልግሎታቸው እንዲቃና፤ መንፈስ ቅዱስ እንዳይለያቸውና የመንፈስ ቅዱስን ምሪትና ኃይል ለመቀበል ሱባኤ ያዙ፡፡ ይህም ጾም “ጾመ ሐዋርያት” ወይም “የሰኔ ጾም” ተባለ፡፡ የሰኔ ጾም ለምን ተባለ ቢሉ ከክረምቱ መግባት ቀደም ብሎ ከወርኃ ሰኔ ጀምሮ የሚጾም በመሆኑ የሰኔ ጾም በሚል ስያሜ ይጠራል፡፡
ሐዋርያት የአገልግሎት መጀመሪያ የሆነውን ጾም ሲፈጽሙም ዓለምን በወንጌል ጨውነት ያጣፍጡ ዘንድ የሚያገለግሉበትን ክፍለ ዓለም ዕጣ በመጣጣል ዕጣው ወደ ደረሳቸው የአገልግሎት ቦታ መሰማራታቸውን የቤተ ክርስቲያን የታሪክ መዛግብትና ሊቃውንት አባቶቻችን ያስረዳሉ፡፡
ጾመ ሐዋርያት “የቀሳውስት ጾም” ወይስ የክርስቲያኖች ሁሉ ጾም?
የሐዋርያትን ጾም አንዳንዶች “የቀሳውስት ጾም ነው” ሲሉት ይሰማል፡፡ ይህም ከአሰያየሙ ጋር የተያያዘ ብዥታን በመጠቀም ላለመጾም የሚፈልጉ ወገኖች ያመጡት አስተሳሰብ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች “የሐዋርያት” የሚለውን ቃል ብቻ በመውሰድ ጥንት ይህንን ጾም ሐዋርያት ብቻ እንጂ ሕዝቡ አልጾመውም፤ ዛሬ ደግሞ በሐዋርያት እግር የተተኩ ካህናት (ቄሶች) ናቸውና ጾሙም የእነርሱ ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡
ቤተክርስቲያን ግን ይህን የአዋጅ ጾም ጳጳስ፣ ቄስ/መነኩሴ፣ ዲያቆን፣ ሰንበት ተማሪ ምእመን ሳትል በ፵ እና በ፹ ቀን የተጠመቀና ዕድሜው ከሰባት ዓመት በላይ የሆነው ሁሉ እንዲጾም ዐውጃለች፡፡ እኛም እነርሱን ተከትለን፣ በእነርሱ ሥርዓት በመመራት፣ በሐዋርያት ላይ ያደረው የመንፈስ ቅዱስ ጸጋና ሀብት በእኛም ላይ እንዲያድርብን በየዓመቱ ጾመ ሐዋርያትን ሌሎችንም አጽዋማት አክብረን መጾም እንደሚገባን በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ተወስኗል (ፍት.ነገ. ፲፭÷ ፭፰፮)፡፡
የሐዋርያት ጾም የሁላችንም ጾም ነው!!
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል” እንዳለ (ኤፌ ፪÷፳) በሐዋርያት መሠረትነት ላይ ለታነጽን ለእኛ ለክርስቲያኖች የሐዋርያት ጾም የእኛም ጾም ነው፡፡ ጾሙንም የምንጾመው የሐዋርያትን በረከት ለመሳተፍ፣ እነርሱ ድል ያደረጉትን ዓለም እንድናሸንፈው አምላካችንን ለመማጸን ነው፡፡ በዚህ ጾም ሐዋርያት ሁሉን ትተው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መከተላቸው፣ ዓለምን ዞረው ማስተማራቸውና ስለ ቅዱስ ስሙ በጽናትና በጥብዐት መከራ መቀበላቸው ይዘከራል፡፡ ምእመናን እና ካህናትም የቅዱሳን ሐዋርያትን መንፈሳዊ ተጋድሎ በማሰብ በዘመኑ ሁሉ በፍቅር በተዋበ መታዘዝ እንፈጽም ዘንድ ይገባል፡፡ (ፊልጵ. ፪÷፲፪) ከልብ ንስሓ በመግባት፣ ከምጽዋትና ከጸሎት ጋር፣ እግዚአብሔር ደስ በሚሰኝበት መንገድ ከግብዝነት ሕይወት በጸዳ መልኩ እንጹም፡፡ ከጸሎትና ከምጽዋት ጋር በሚገባ ጾመን ከራሳችንን እና ከእግዚአብሔር አምላካችን ጋር የምንታረቅበት ሱባኤ ያደርግልን ዘንድ፤ የቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያት በረከትና ጸሎት አይለየን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!