በሁለት ወገን የተሳላችሁ ሁኑ!

ዲ/ን ስንታየሁ አለማየሁ

ሰው በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል የተፈጠረ፣ ነገር ግን ከሁሉ የሚልቅ ዕፁብ ድንቅ ፍጥረት ነው። ከአፈር መፈጠሩ ሲታይ “ታስበው ዘንድ ሰው ምንድነው?” ፤ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል መፈጠሩ ሲታይ ደግሞ “ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አሳነስኸው፤ የክብርና የምስጋና ዘውድ ጫንህለት፥ በእጆችህም ሥራ ላይ ሾምኸው” ማለቱ የእግዚአብሔርን ቸርነት ሁሉን በአግባቡና በሥዓቱ ፈጥሮ የሚገዛ አምላክ መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡ (ዕብ. ፪፥፮-፯)

እግዚአብሔር ሰውን በዚህ በሚያስደንቅ ሁኔታ ከ፬ቱ ባሕርያተ ሥጋ (ከአፈር፣ ከነፋስ፣ ከእሳትና ከውኃ) እና ከ ፫ቱ ባሕርያተ ነፍስ (ሕያዊት፣ ለባዊት፣ ነባቢት) ፈጥሮ ፍጥረትን ሁሉ እንዲጠብቅ፣ እንዲገዛ አድርጓል። የሥጋ ባሕርያት እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ቢሆኑም እንኳ በሰው ላይ ተስማምተውና ጸንተው የፈጣሪን ከሀሊነት አሳይተዋል ። ስለዚህም የሰው ልጅ ስንል የነፍስ እና የሥጋ ተዋሕዶ ማለታችን ነው። የሥጋንና የነፍስን ሚዛን አስማምቶና ከኃጢአት ርቆ የሚኖር ሰው እርሱ በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ ነው።

በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ በሁለቱም በኩል መሥራትና የታለመለትን ውጤት ማስገኘት ይችላል።  ማለትም መቁረጥ ከሆነ መቁረጥ፣ መጥረብ ከሆነ መጥረብ… ፤ እንዲሁ ሰው ነፍሱንና ሥጋውን በእግዚአብሔር ቃል፣ በመልካም ምግባርና ሃይማኖት በመጠበቅ ከገለጠ እርሱ በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ ነው። ምክንያቱም በእምነት የተገለጠ ክርስትና ነፍሳትን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ያደርሳልና።

ነፍሳችን ከእግዚአብሔር ከተቀበለችው አንዱ ጸጋ ዐዋቂነት ነው። በእምነት በጎ ሥራን ለመሥራት ዕውቀት ያስፈልጋል። በእምነት፣ በዕውቀትና በጥበብ እንደ ባለ አእምሮ ከተመላለስን ለዓለም ምሳሌ ሆነን በክብር በጨለማው ውስጥ እናበራለን። ነገር ግን ዕውቀታችንና ጥበባችን ከእግዚአብሔር ከለየን፤ እግዚአብሔር በሐዋርያው ላይ አድሮ እንደ ነገረን “እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱ መጠን እንዲሁ እግዚአብሔር ይህን የማይገባውን ይሠሩ ዘንድ ሰነፍ አእምሮን ሰጣቸው” እንዲል ይገሥጸናል። (ሮሜ. ፩፥፳፰)

በሁለት በኩል መሳል ለምን ያስፈልጋል?

በሁለት በኩል መሳል የሥጋን ባሕርይ ለነፍስ በማስገዛት የእግዘብሔርን ስም በመቀደስ ክብሩን እንዲወርስ ያደርጋል። ሰዎች በሁለት በኩል መሳላቸው ከራስ አልፈው ለሌሎች ነፍስ መዳን ምክንያት ይሆናሉ። እንዴት ቢሉ፡- የእግዚአብሔርን ቃል በማስተማር፣ በመምከር፣   በማሳመን ብዙዎችን ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ይመልሳሉ። ሃይማኖትንና ምግባርን አስተባብረው በርትተው በመሥራትም የተራበ ያበላሉ፣ የተጠማ ያጠጣሉ፣ የታረዘ ያለብሳሉ፣ አልፎ ተርፎም ለብዙዎች አርአያ ይሆናሉ፡፡ ለዚህ ነው ታላቁ አባት ብፁዕ አቡነ ሺኖዳ “ለራሱ ብቻ የኖረ ሰው አልኖረም ማለት ነው” ያሉት። ሰው በሕይወቱ የእግዚአብሔርን ቃል ከመማር በተጨማሪ የዓለምን ፍልስፍናና ዕውቀት ማወቅ ተገቢ ነው። እንዲህ ሲሆን ለሁሉም በሚገባው ቋንቋ ነገረ እግዚአብሔር አስተምሮ ለመንግሥቱ ያቀርባልና።

“እግዚአብሔር የለም” በሚሉ ሰዎች ፊት እግዚአብሔር መኖሩን እነርሱ በደረሱበት የዕውቀት ልክ ገልጦ ሲመሰክር “ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ” የሚለውን ሽልማት ይጎናጸፋል፡፡ (ማቴ. ፲፥፴፪) በመንግሥቱም እንደ ፀሐይ ደምቆ ያበራል። ሰዎች በመንፈሳዊም ሆነ ዓለማዊ ሕይወታቸው በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ ሲሆኑ ተልእኳቸው በስኬት ይታጀባል፤ ከራሳቸው አልፎ ወደ ሌሎችም ይሻገራል። ለዚህ ነው “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ” የተባለው ። (ማቴ. ፭፥፲፫)

ጨው ከራሱ አልፎ ለሌላው ጣዕም ይሰጣል፤ አልጫውንም ያጣፍጣል። በሁለት ወገን የተሳለ ሰውም በምግባሩና በሃይማኖቱ ለሌላው የሕይወት መዓዛ ይሆናል “በሚድኑትና በሚጠፉት ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነንና፤ የሞት መዓዛ የሚገባቸው ለሞት፤ የሕይወት መዓዛ የሚገባቸውም ለሕይወት ናቸው” (፪ኛቆሮ ፪፥፲፭) እንዲል። የምድር ጨው (Nacl) የተገነባው ከሁለት መሠረታዊ ንጥረ ነገሮች ማለትም ከሶዲየም(Na) እና ክሎሪን(Cl) ሲሆን ሁለቱም ለብቻቸው  ለሰው ልጅ ጸር ናቸው። ነገር ግን ሁለቱ አንድ ሲሆኑ ከራስ አልፈው ለሌላ ጣዕም ይሆናሉ። ሰውም መንፈሳዊውን እና ዓለማዊው ሕይወቱን አዋሕዶ ሲገኝ በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ ይሆናል፡፡ ከራሱ አልፎ በሥጋም በነፍስም ለሌላው ይጠቅማል።  ከሁሉም በላይ እግዚአብሔርን በመፍራት የሕሊናውን ሚዛን ይጠብቃል፡፡ ምክንያቱም “የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው”ና፡፡ (መዝ.፻፲፩፥፲)

መንፈሳዊ አገልግሎትን ከትምህርት ጋር እንዴት ማጣጣም ይቻላል?

መንፈሳዊ አገልግሎት በእግዚአብሔር ለተለየ አገልግሎት መመረጥ እንደ መሆኑ መጠን ከትምህርት፣ ከመደበኛ ሥራችን እና ሌሎች ማኅበራዊ ሕይወታችን ጋር አጣጥሞ መጓዝ ያስፈልጋል፡፡ ለአገልግሎት መጠራታችንን ከተረዳን ከሌሎች ተግባራቶቻችን ጋር በጊዜ ለክተንና አስማምተን በዕቅድ ራሳችንን መምራት ይገባል፡፡ “… አሁንም በፊቱ ትቆሙና ታገለግሉት ዘንድ አገልጋዮቹም ትሆኑ ዘንድ እግዚአብሔር መርጧችኋልና ቸል አትበሉ” ሲል እግዚአብሔር በነቢዩ ሕዝቅያስ ላይ አድሮ እንደተናገረ፡፡ (፪ኛ ዜና. ፳፱፥፩-፲፩፤ ማቴ. ፱፥፱) መመረጥ መልካም እንደሆነ ሁሉ ለተመረጡበት አገልግሎት ታምኖ መገኘትና ማገልገል ከአንድ መንፈሳዊ አገልጋይ ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን አገልግሎታችን ፍሬ እንዲያፈራ ሌሎች ከምናከናውናቸው ተግባራት ጋር ማስማማት ግድ ይላል፡፡

መንፈሳዊ አገልግሎት የሚከናወነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡ አገልግሎቱ የመንፈስ ቅዱስ እንጂ የሰው አለመሆኑን ማመን ተገቢ ነው። በሰው ጥበብ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ረዳትነት፣ ዕውቀትና ብቃት ብቻ የሚከናወን አይደለም፡፡ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ስንጠይቅ መንፈሳዊው አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ለሕይወታችን ለሚያስፈልጉን ነገሮች ሁሉ መቃናት ወሳኝ ነው፡፡ “ካለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም” ብሎናልና፡፡ (ዮሐ. ፲፭፥፭) ስለዚህ የምናከናውናቸውን ተግባራት በጊዜ ለክተንና መድበን ሁሉንም በአግባቡና በሥርዓት ማስኬድ ይጠበቅብናል፡፡ በተለይም ወጣቶች ይህንን ከተረዱ በመልካም አገልግሎታቸው እና ልዩ ልዩ ተግባራት  ለሌሎች አርአያ መሆን እንችላሉ፡፡

ወጣትንነትን ስንመለከት የእሳትነት ዘመን እንደ መሆኑ መጠን ስሜታዊነት ጎልቶ የሚታይበት ጊዜ ነው፡፡ በተለይም በግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ውስጥ አገልግሎትን ከመደበኛ ትምህርት ጋር አጣጥሞ መጓዝ ላይ በርካታ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ራስን በዕቅድ አለመምራት ነው፡፡ ዕቅድ ሲታቀድ ደግሞ በጊዜ ተለክቶ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ቁርጠኛ መሆንን ይጠይቃል፡፡ በተለይም በበርካታ ወጣቶች ላይ የሚታየውን ስሜታዊነት ማረቅ የሚቻለውና ለተጠሩለት አገልግሎት እንዲሁም ለመደበኛ ትምህርት አስፈላጊውን ጊዜ ሲሰጡ   ነው፡፡

በመጀመሪያ የሚያስፈልጉትንና የማያስፈልጉትን መለየት ይገባል። ቀጥሎም አሁን

ከሚያስፈልገው በመነሣት ሁሉንም በቅደም ተከተል መዘርዘር ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም፡-  ጊዜ የሚባል በጣም ውድ የእግዚአብሔር ስጦታ አለና። ጊዜ በአግባቡ ከተጠቀምንበት ወርቅ ነው፡፡ ለሁሉም ጊዜው አለውና “ለሁሉ ዘመን አለው፤ ከፀሐይ በታችም   ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው፡፡” (መክ. ፫፥፩) እንዲል ጠቢቡ፡፡ ጊዜ የለኝም! ነገ አገለግላለሁ!  ነገ እሠራለሁ! ማለት ለተጠሩለት አገልግሎት ታማኝ ሆኖ አለመገኘትን ያመለክታልና ምክንያት ከመደርደር ይልቅ በተገቢ ጊዜና ሰዓት ተገቢውን አገልግልሎት መፈጸም ይገባል፡፡ በምንም ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ብንሆን እንኳን ሁሉን በተገቢው መንገድ አቀናጅተን እንሠራለን፤ እናገለግላለን፡፡ በሐዋርያው ቃልም እንዲህ እንላለን” … አገልግሎት ስላለን አንታክትም” (፪ቆሮ. ፬፥፩)፡፡

እዚህ ላይ ቆም ብለን ራሳችንን አንድ ነገር እንጠይቅ፡- ጊዜ የሚያንሰኝ ለምንድነው? ለትምህርቴስ? ለአገልግሎቴ ለጓደኞቼ የምሰጠው ጊዜ ምን ያህል ነው? ለቤተሰቦቼስ? ለማኅበራዊ ሚዲያስ? … በአጠቃላይ ምን ምን እያከነወንኩ ነው ጊዜዬን የምጨርሰው? በእውኑ ለአገልግሎት ጊዜ የለኝምን? እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ያስፈልጋል፡፡ ከመለስን

የሚጠቅመንና የሚጎዳንን ከለየን በኋላ ሁሉን በጊዜው እንሥራ፤ “የሚሻለውን ሥራ

እንድትመረምሩና እንድትፈትኑ ክርስቶስ በሚመጣበት ቀን ያለ እንቅፋት ቅዱሳን ትሆኑ   ዘንድ” (ፊል.1፩፥፲) እንዲል፡፡ የሚጠቅመንን ማድረግ ስንጀምር ዕለት ዕለት ያለመታከት

በአግባቡ ካጠናን የሚጠበቅብንን ሁሉ በሰዓቱ ካከናወንን ጊዜ በምንም ሁኔታ ሊያጥረን

አይችልም። በተለይም ደግሞ ተማሪዎች   አንዱ ለእግዚአብሔር የምናቀርበው አሥራታችን

ጊዜ ነው። በዚህ ታምነን ከተገኘን ለነፍሳችን ስንቅ ለሥጋችን ስኬትን እናገኛለን።

በሚገባ ጊዜያችንን ተጠቅመን ትምህርታችንን ከተማርንና እርሱን ካገለገልን በማያልቅ በረከት ይባርከናል፤ በሁለት ወገን የተሳልን ሰይፎች ሆነንም እንወጣለን፡፡

አምላከ ቅዱሳን ለተጠራንበት አገልግሎት ታምነን በሥጋም በነፍስም ተባርከን ስሙን ለመቀደስ መንግሥቱንም ለመውረስ ያብቃን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *