ቅድስት (የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት)
ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓ ድርሰቱ በዐቢይ ጾም ለሚገኙት ሳምንታት ማለትም በየሳምንቱ ለሚውሉት እሑዶች መዝሙር አዘጋጅቶላቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት እያንዳንዱ እሑድ በመዝሙሩ ስም ይጠራል። ባለፈው ሳምንት “ዘወረደ”ን እንዳቀረብን ሁሉ በዚህ ዝግጅታችን ደግሞ ሁለተኛውን ሳምንት ቅድስትን እንመለከታለን፡፡ ፡፡
የዐቢይ ጾም ሁለተኛው እሑድ ቅድስት ተብሎ ተሰይሟል። ቅድስት የሚለው ቃል ግሱ “ቀደሰ” ሲሆን “ለየ፣ አከበረ፣ መረጠ የሚል ትርጉም ሲኖረው፤- ቅድስት ማለት የተለየች፣ የተመረጠች፣ የከበረች ማለት ነው። ቅዱስ የሚለው ቃል እንደ የአገባቡ ለፈጣሪም ለፍጡርም ያገለግላል። ለፈጣሪ ሲነገር እንደ ፈጣሪነቱ ትርጉሙ ይሰፋል፣ ይጠልቃል፡፡ ለፍጡር ሲነገር ደግሞ ቅድስናውን ያገኙት ከራሱ ከእግዚአብሔር ነው፡፡ “ያዘጋጃቸውን እነርሱን ጠራ፤ የጠራቸውንም እነርሱን አጸደቀ፤ የአጸደቃቸውንም እነርሱን አከበረ፡፡” እንዲል፡፡ (ሮሜ. ፰፥፴)
ዕለተ ሰንበት ቅድስት መባሏ በሰዎች እና በእግዚአብሔር መካከል ለቅድስና ሕይወት ምልክት ማስታወሻ እንድትሆን ነው። በባሕሪይው ቅዱስ የሆነ አምላክ ዓለምን የማዳን ሥራውን የጀመረበትን፣ ፅንሰቱን፣ እንዲሁም የማዳን ሥራውንም አጠናቆ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ዘለዓለማዊ ሕይወትን ያበሰረበትን ትንሣኤውን የምናስብበት በመሆኑ የዕለቱ ቅድስና፣ የፈጣሪን ቅዱስ ተግባር የምናደንቅበት፣ የዋለልንን ውለታ ከፍ ከፍ እያድረግን እርሱን የምናመሰግንበት ዕለት ነው። ይህም እኛን ወደ በለጠ የቅድስና ሕይወት የሚያሸጋግረን በመሆኑ የእግዚአብሔርን ጥልቅ ፍቅር በየጊዜው እንድናስብና በፍቅሩም እንድንኖር ያግዘናል፡፡
ዕለተ ሰንበት ነገረ እግዚአብሔር በተለየ ሁኔታ የሚዘከርባት ናትና “የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ” (ዘፀ. ፳፥፰) ተብሏል፡፡ የሰንበትን ቀን አስቀድሞ የቀደሰ፣ የባረከ ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ “እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው፣ ቀደሰውም፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ ዐርፎአልና“እንዲል፡፡ (ዘፍ. ፪፥፫)
“እንግዲህ የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ” የተባለው እግዚአብሔር አስቀድሞ የባረከውን የቀደሰውን እኛ ድጋሚ የምንቀድስ የምንባርክ ሆነን ሳይሆን በዕለተ ሰንበት ራሳችንን በተለየ ሁኔታ ለቅዱስ ተግባር እንድንለይ፣ ለሥጋችን ከምንፈጽማቸው ተግባራት ይልቅ ለተግባረ ነፍስ እንድናደላ ያስረዳናል። ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት፤ ሐሤትን እናድርግ፥ በእርስዋም ደስ ይበለን።” እንዳለው (መዝ. ፻፲፯፥፳፬)
በዕለተ ሰንበት የምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት ይባረካል፣ ይቀደሳል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ “አንቀጸ ብፁዓን” በመባል የተጠቀሱትን መፈጸም ለክርስቲያን ሁሉ ይገባል፡፡ (ማቴ. ፭፥፩-፲፪) በዚህ ታሳቢነት ዕለቱም ዕለተ ቅድስና መሆኑን ለማጠየቅ ቅድስት ተብሏል። “እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” (ዘሌ. ፲፱፥፪) ተብለናልና ቅድስት በተባለች ዕለተ ሰንበት ወደ ቤተ ክርስቲያን በመገስገስ ቅዳሴ በማስቀደስ፣ ቃለ እግዚአብሔር በመስማት፣ የታመመን፣ የታሠረን በመጠየቅ፣ በአጠቃላይ የቅድስና ሥራዎችን እንድንሠራ ለእኛ ለክርስቲያኖች ታዘናልና ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ የቅድስና ሕይወት መሠረቱ የእግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዝ መጠበቅና ማድረግ ሆኖ ሳለ ለመቀደስ የእኛ መሻት፣ መፈለግ ወሳኝ ነው።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!