ቅዱስ ቂርቆስ ወቅድስት ኢየሉጣ
በቀሲስ ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮ ሐምሌ ፲፱ ቀን የሚከበረው ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ቅድስት ኢየሉጣን እና ልጁዋን ቅዱስ ቂርቆስን ከፈላ ውኃ የታደገበት(ያዳነበት) የሚታሰብበት በዓል ነው፡፡
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ፡- ”ይትአየን መልአከ እግዚአብሔር አውዶሙ ለእለ ይፈርህዎ ወያድኅኖሙ ጣዕሙ ወታእምሩ ከመ ኄር እግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል ያድናቸውማል፤ እግዚአብሔር ቸር እንደሆነ ቅመሱ ዕወቁም‘(መዝ.፴፫፥፯) በማለት እንደመሰከረው፡፡
በዘመነ ሰማዕታት በሮማውያን ቄሳሮች አማካይነት በክርስቲያኖች ላይ የግፍ ዓዋጅ በመታወጁ ስለ ክርስትናቸው ደማቸው በየሜዳው እንደ ጎርፍ እየፈሰሰ፣ አጥንታቸው እየተከሰከሰ ጭካኔ በተመላበት ሁኔታ እንደ በግ እየታረዱ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር በመሆን ጸኑ፡፡ ስለ ስሙ የተሰውት በየቀኑ ቁጥራቸው እጅግ በርካታ ሲሆኑ የቀሩት ደግሞ ተሰደዱ፡፡ ከተሰደዱት ክርስቲያኖች መካከል ደግሞ ቅድስት ኢየሉጣ አንዱዋ ናት፡፡
ቅዱስ ቂርቆስ ዕድሜው የሦስት ዓመት ሳለ እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ ከሮሜ ወደ ሌላ ሃገር(ኢቆንዮን) ሸሽታ ይዛው ሄደች፤ በዚያም የሸሸችውን መኮንን(እለእስክንድሮስ) አገኘችው። የሚያውቋትም ሰዎች ሸሽታ እንደመጣች ስለተረዱ ለመኮንኑ ነገር ሰሩባት። መኮንኑም ቅድስት አየሉጣን አስጠራትና ስለምታመልከው አምላክ ጠየቃት። ቅድስት ኢየሉጣም፡- ”መኮንን ሆይ፡ ዕድሜው ሦስት ዓመት የሆነው ሕፃን አለ፤ አማልክቶችህን ማምለክ መልካም እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ያስረዳን ዘንድ እርሱን ጠይቅ” አለችው።
ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስም ወደ አለበት ጭፍራውን ልኮ ወደ እርሱ አስመጣው ሕፃኑንም ፊቱ ብሩህና ደስተኛ እንደሆነ አየውና “አንተ ደስተኛ ሕፃን ሆይ እንዴት ነህ?” አለው። ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስም መለሰለት፣ እንዲህም አለው፡- “አዎ እኔ በጣም ደስተኛ ነኝ ደስታዬም ተጠብቆልኛል ላንተ ግን ሐዘንና ለቅሶ ጥርስ ማፋጨትም ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስም ለዝንጉዎች ተድላ ደስታ የላቸውም ብሏልና” አለው።
እግዚአብሔር አምላክ ኃይልንና ንግግርን ሰጥቶታልና በዚያ ለተሰበሰቡት ሰዎች እስኪደነግጡ ድረስ ስለሚያመልክው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ተናገረ። ቅዱስ ቂርቆስም ንጉሡን መኳንንቱንና ጣዖታቱን ረገማቸው ከብርታቱም የተነሣ አደነቁ፡፡
መኮንኑም በአፈረ ጊዜ እጅግ ዘግናኝና ከባድ በሆነ ስቃይ ታላላቆች እንኳ የማይችሉትን አስጨናቂ በሆነ ልዩ ልዩ መከራ አሰቃየው። እናቱ ቅድስት ኢየሉጣንም ከእርሱ ጋር እንደ እርሱ በጣሙን አሰቃያት። እግዚአሔብሔር ግን ያለ ምንም ጉዳት ያነሳቸው ነበር። ብዙዎች አሕዛብም ይህን አይተው አደነቁ፡፡ ክብር ይግባውና በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት አምነው በሰማዕትነት ሞቱ።። የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀበሉ።
በሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ላይም የመንፈስ ቅዱስ ፀጋ አደረበት። ታላላቅ ድንቅ ተአምራቶችንም ያደርግ ነበር። ብዙዎች በሽተኞችንም ያድናቸው ይፈውሳቸው ነበር። ይህንን ያየው መኮንኑም በታላቅ የናስ ጋን ውስጥ ውኃ ጨምረው በእሳት ያፈሉት ዘንድ አዘዘ። የፍላቱም ድምጽ እንደ ክረምት ነጎድጓድ ሆነ ድምጹም በጣም ያስተጋባ ነበር። ይህን ያየችና የሰማች እናቱ ቅድስት ኢየሉጣም ፍርሃትና የሃይማኖት ጉድለት ታየባት። ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ግን እናቱ ቅድስት ኢየሉጣን ሁኔታዋን አይቶ ወደ አምላኩ እግዚአብሔር ጸለየ።
ያን ጊዜ ልዑል እግዚአብሔር ልቧን ወደ ሰማይ አሳርጎ ለቅዱሳን ሰማዕታት የተዘጋጁ የብርሃን ማደሪያዎችን አሳያት። ቅድስት ኢየሉጣም እንደገና በሃይማኖቷ ጸናች። እግዚአብሔር አምላኳንም አመሰገነችው። ልጇን ሕፃኑን ቅዱስ ቂርቆስንም “ልጄ ሆይ አንተ ከእንግዲህ አባቴ ነህ እኔም ልጅህ ነኝ በሥጋ ብወልድህና እናትህ ብሆንም በሃይማኖት እንድጸና በምክርህ እና በጸሎትህ ስለ እኔም ባቀረብከው ልመና በሃይማኖት ወልደኸኛልና” አለችው።
መልሳም ቅድስት ኢየሉጣ ለልጇ “ያች የተወለድክባት ዕለት ቀኗ የተባረከችና የተቀደሰች ናት” አለችውና ተጋድሎአቸውን እንዲፈጽሙ ቁርጥ ውሳኔ እንዳደረገች ነገረችው። እሱም ስለ እናቱ እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡ የመኳንንቱ ጭፍሮችም እሳት ወደ አለበት ጋኖች ውስጥ ቅዱስ ቂርቆስንና እናቱን ቅድስት ኢየሉጣን በጨመሯቸው ጊዜ የውኃው ፍላት እንደ ክረምት ነጎድጓድ ድምጹ ይሰማ የነበረና ወደ ላይ ፲፬ ክንድ ያህል ይፍለቀለቅ የነበረ ቢሆንም የክርስቶስ ባለሟሎች የሆኑት ቅዱስ ቂርቆስ እና ቅድስት ኢየሉጣ ሲጣሉበት ወዲያውኑ ቀዘቀዘ። ከእግዚአብሔር የታዘዘ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወርዶ የእሳቱን ኃይል አቀዝቅዞታልና።
ከራስ ጸጉራቸው እስከ እግር ጥፍራቸው የለበሱት ሰናፊል ሳይቀር የውኃው ፍላት እና የናሱ ብረት ግለት ሳይነካቸው በሰላም በሚፍለቀለቀው የውኃ ፍላት ውስጥ በደስታ ሲመላለሱበት የሚሆነውን ለማየት የተሰበሰቡ ሁሉ በመገረም ያዩ ነበር፡፡ ብዙ አሕዛብም ባዩት ተአምር በቅዱስ ቂርቆስና በቅድስት ኢየሉጣ አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ፡፡ ከንጉሡ ጭፍሮችም ብዙዎች ያመኑ ቢሆኑም ያላመኑት ያመኑትን በቁጣ ተነሣስተው በሰይፍ ገደሉአቸው፡፡ ብዙዎችም ሰማዕትነትን ተቀበሉ፡፡
ይህን ያየ መኮንኑም ይባስ እልህ ውስጥ ስለገባ ሥጋቸው ተቆራርጦ እስከሚወድቅ ድረስ በመቃጥን ውስጥ አድርገው አንዲጎትቷቸው አዘዘ። ከእግዚአብሔርም የታዘዘ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል አዳናቸው። ጨካኙ ንጉሥ በታላቅ ስቃይ ያሰቃያቸው ዘንድ አስቦ እስኪመክር ድረስ መኮንኑ በወህኒ ቤት ዘጋባቸው። በዚህን ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስን አረጋጋው፤ አጽናናው ስሙንም ጠርተው መታሰቢያ ለሚያደርጉለትም በረከትን እንደሚያገኝና ሌላ ብዙ ቃል ኪዳን ሰጠው። ለቅድስት ኢየሉጣም እንዲሁ ቃል ኪዳን ሰጥቶ አጽናናት፡፡ በወህኒም እንዲቆዩ ተደረገ፡፡
በሌላ ጊዜ መኮንኑ ከመካነ ምኩናኑ ተቀምጦ ቅዱስ ቂርቆስን ካለበት አስጠርቶ “የተመለስከው መመለስ አለን?” አለው:: ቅዱስ ቂርቆስም አይሆንም አልመለስም” አለው:: ጋሻ ጃግሬውን ጠርቶ ”ንሳ በሰይፍ ቅጣው” አለው:: በሰይፍ መታው፡፡ ጌታም ነፍሱን ከመካነ ዕረፍት ሥጋውንም ነጥቆ በሠረገላ ኤልያስ አኑሮለታል:: እናቱ ቅድስት ኢየሉጣንም እንዲሁ በሰይፍ እንዲቆርጡዋት አዘዘ፡፡ እርሱዋም እንደ ልጅዋ በጽናት ስለ ክርስቶስ መስክራ ሁለቱም እናትና ልጅ በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ ዕረፍት መታሰቢያ በዓላቸውም ጥር ፲፭ ቀን ይከበራል፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን የሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስና የእናቱ የቅድስት ኢየሉጣ በረከታቸውና ረድኤታቸውን ያድለን አሜን።
ምንጭ፡- ስንክሳር ሐምሌ ፲፱፣ ገድለ ቅዱስ ቂርቆስ ወኢየሉጣ)
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!