ቃና ዘገሊላ

ይህ በዓል ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ከዘጠኙ ንዑሳን በዓላት መካከል አንዱ ሲሆን ይህም ጥር ፲፪ቀን ይውላል፡፡ የቃና ዘገሊላ ጥንተ ነገሩ ወይም ታሪኩ የተፈፀመው የካቲት ፳፫ ቀን ነው፡፡ ነገር ግን አባቶቻችን የውኃን በዓል ከውኃ በዓል ጋር ለማክበር ብለው የየካቲቱን በዓል ወደ ጥር ፲፪ አምጥተውታል፡፡ ይህም ውኃ ወደ ወይን የተለወጠበትን በዓል ከጌታ ጥምቀት በዓል ጋር በማስተሳሰር ለማክበር ነው፡፡ (ስንክሳር ዘጥር ፲፪)

“በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሠርግ ነበረ፥ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፤ ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሠርጉ ታደሙ። የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት፡- “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” አለችው። ኢየሱስም፡- “አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም” አላት። እናቱም ለአገልጋዮቹ፡- “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” አለቻቸው። አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፥ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር። ኢየሱስም፡- “ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው” አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው። “አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት” አላቸው፤ ሰጡትም። አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውኃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ፡- ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል?” አለው። ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።”(ዮሐ. ፪፥፩-፲፩)።

ሦስተኛ ቀን ምንድን ነው?

፩. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው ጥር ፲፩ ቀን ነው፡፡ ወዲያውኑ እንደተጠመቀ ሳይውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄደ፤ ፵ ቀንና ፵ ሌሊት ጾመ፤ ጾሙ የካቲት ፳ ቀን ቅዳሜ ይፈጸማል፡፡ ለእሁድ ሦስተኛ ቀን የካቲት ፳፫ ቀን ማክሰኞ በሦስተኛው ቀን ሠርግ ነበር፡፡

ሦስተኛ ቀን የሚለው፡-

  • የመጀመሪያ ቀን የሚባለው ዘመነ አበው፤ አዳም፤ እነአብርሃም፤ ይስሐቅ አበው የነበሩበት ዘመን ሲሆን፤
    •  ሁለተኛ ቀን የሚባለው ዘመነ ኦሪት ነው፤ እነሙሴ የነበሩበት ዘመን፣
    •  ሦስተኛ ቀን የተባለው ዘመነ ሐዲስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነበት ዘመን ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ሠርግ የሆነው።

፪.ጌታችን  ፊልጶስን  አግኝቶ  “ተከተለኝ”  ካለበትና  ፊልጰስም  ጓደኛውን  ናትናኤልን  ከጠራበት  ዕለት  ሦስት  ቀን በኋላ ተአምሩን አደረገ  ነው፡፡ (ዮሐ. ፩፥፵፬) 

፫.በነገው ደግሞ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር። ያለውን እሑድ (ዮሐ. ፩፥፴፭)፣ በነገው ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊወጣ ወደደ፥ ፊልጶስንም አገኘና ተከተለኝ አለው (ቁ.፵፬) ያለውን ሰኞ ብሎ በመተርጐም ማክሰኞ  ተአምሩን  በቃና  አደረገ  የሚል  ነው፡፡

፬. የእኛ ቤተ ክርስቲያን የበለጠ  የምታስተምረው አገባብ ደግሞ ጌታችን  በዮሐንስ  እጅ ከተጠመቀ በኋላ  ሳይውል  ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሔዶ የጾመውን ዐርባ ቀንና ሌሊት  እንደ  አንድ  ቀን በመቁጠር ከዚያ  መልስ  ተአምራቱን አደረገ  የሚል  ነው፡፡ (ቃና ዘገሊላ፤ ዲ/ን ሔኖክ ኃይሌ)

ዐርባ ቀንና ሌሊት እንደ አንድ ቀን እንዴት ይቆጠራል? ቢባል ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ልማድ ስለሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ማቴዎስ “ጌታችን ከግብፅ ስደት መልስ ወደ ናዝሬት መጥቶ ኖረ” ብሎ ከጻፈ በኋላ ቀጥሎ በዚያም ወራት መጥምቁ ዮሐንስ፡- መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ ብሎ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ ብሎ ጽፎአል፡፡ (ማቴ. ፪፥፳፫፤ ፫፥፩) በሁለቱ ዓረፍተ ነገሮች መካከል የሃያ አምስት ዓመታት ልዩነት  አለ፡፡ ብዙውን እንደ አንድ መቁጠር የመጻሕፍት ልማድ ስለሆነ “በዚያ ወራት” ብሎ ጻፈ፡፡ ይህ የትርጓሜ አገባብ የበለጠ ትርጒም የሚሰጥ ነው፡፡ ከማንኛውም መንፈሳዊ  አገልግሎትና ተአምራት በፊት  መጾምና  መጸለይ

እንደሚቀድም ያስተማረንም  ከቃናው  ተአምር በፊት በገዳመ ቆሮንቶስ በመቆየቱ ነው፡፡

የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች

  • ቤተ ዘመድ ናትና ተጠርታ።
  • እመቤታችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋዊ ዕድገቱ እንደምትቀድመው ሲያጠይቅ። እንኳን የእርሱ እናት ትቅርና ዮሐንስ መጥምቁም በ፮ ወር ይቀድመው ነበር፡
  • አስቀድማ የነበረችውንና ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን በፊት የኖረችውን ድንግል ማርያምን ሳናውቅ ኢየሱስን እናውቃለን ማለት አይቻልም ሲል፡፡

ወይኑ ባለቀ ጊዜ “ወይን የላቸውም” አለች፡፡

የወይኑን ማለቅ ለእመቤታችን ማን ነገራት? ሙሽራው ወይስ ከሠርገኞቹ መካከል አንዱ? ለዚህ ምንም ዓይነት መልስ እንደማይሰጥ ግልጽ ነው፡፡ ድንግል ማርያም ግን ራሷ ነበር ያወቀችው፤ ነቢይት ናትና፡፡ ስለሆነው እንዲሁም ስለሚሆነው ታውቃለች፤ ቅዱስ ዘካርያስና ቅድስት ኤልሳቤጥ ካመሰገኗት በኋላ “ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብጽዕት ይሉኛል” ማለቷ ወደፊት ስለሚመጣው ትውልድ ነበር የተናገረችው፤ ይህ ነቢይነቷን የሚገልጽ ነው፡፡ (ሉቃ. ፩፥፵፰-፵፱)

ኢሳይያስ በትንቢቱ “ወደ ነቢይቱ ሄድኩ ጸንሳም ነበር” (ኢሳ. ፰፥፩) የሚላት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ነው፡ በሶርያ የነበረው ንጉሥ በኢየሩሳሌም ያለውን ንጉሥ ሊወጋ (ሊገድል) በፈለገ ጊዜ በእልፍኝ ሆኖ የሚመክረውን ምክር ነቢዩ ኤልሳዕ ኢየሩሳሌም ሆኖ ይመለከትና ያውቅ ነበር፤ ኢየሩሳሌም ሆኖ በሶርያ የሚደረገውን እያየ ነበር፡፡ ስለዚህም የኢየሩሳሌሙን ንጉሥ “ከቤትህ እንዳትወጣ ሶርያውያን ሊገድሉህ ይፈልጋሉ” (በ፩ኛ ነገ. ፮፥፰) እያለ ይመክረው ነበር፡፡ ምን ዓይነት ጸጋ እንደሆነ አስቡት፤ ኢየሩሳሌም ሆኖ በሶርያ የሚደረገውን ነገር ማወቅ፡፡ ታዲያ በዘመነ ብሉይ የነበሩ ነቢያት እንዲህ የርቀቱን ነገር የሚያውቁ ከሆነ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የዶኪማስን የቤት ችግር፤ የወይን ማለቅ ብታውቅ ብትረዳ ምን ይደንቅ። የመለኮት እናትም እንዴት ጸጋው ይበዛላት፤ እንደ እመቤታችንስ ጸጋው የበዛለት በዘመነ ብሉይ ማን ነበር። “ጸጋን የተመላሽ ድንግል ሆይ ደስ ይበልሽ” የተባለች ድንግል ማርያም አይደለችምን?

“ከአንቺ ጋር ምን አለኝ”

፩. “ያልሽኝን እንዳልፈጽምልሽ ምን የሚከለክለኝ ነገር አለ” ሲል ነው፡፡ “እናትና አባትህን አክብር፤ ለእናትና ለአባትህ ታዘዝ” ያለ አምላክ እናቱን ሂጂልኝ፤ ወግጅልኝ አላት ሲባል አያሳፍርም? ይህማ እንዳይሆን “ለእናቱ እየታዘዘ አደገ” ወንጌል ይል የለምን፡፡ (ሉቃ. ፪፥፶፩)

፪. ውኃውን ጠጅ አድርግላቸው ብትዪኝ አይሆንም እልሽ ዘንድ ውኃውን ጠጅ ላላደርግላቸው ከሠርግ ቤት ተጠርቼ መጥቻለሁን? ውኃውን ጠጅ ላደርግላቸው ነው።

፫. በአምላክነቱ አገብሮ ተአዝዞ እንደሌለበት ለማጠየቅ

“ጊዜዬ ገና አልደረሰም”

፩. ሥራውን የሚሠራበት ጊዜ አለውና በቀትር የሚሠራውን በሠለስት አይሠራም፤ በሠለስት የሚሠራውን በነግህ አይሠራምና።

፪. ወይኑ ከእንስራው ፈጽሞ አላለቀም ነበር። ያለውን አበርክቶት ቢሆን ያኑ አበረከተው ተብሎ ተአምራቱ ድንቅ ባልተባለ ነበርና።

፫. ይሁዳ ወጥቶ ነበርና ከተአምራቱ ቢለየኝ ከሞቱ ገባሁበት እንዳይል።

፬. ለዓለም ቤዛ የምሆንበት፣ በመስቀል ላይ የምሰቀልበት ሰዓቱ ገና ነው ሲል ይህን ተናገረ። (ትርጓሜ ወንጌል ዘዮሐንስ ፪፥፬)

የሠርጉ ባለቤት ማን ነበር?

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሙሽራው ማን እንደሚባል እና ሙሽራዋም ማን እንደሆነች የሚገልጽ የለም። በግብረ ሕማማት ረቡዕ ምሽት ሦስት ሰዓት ምንባብ ላይ በሚገኘው ተዓምረ ኢየሱስ የሙሽራው ስም ዶኪማስ እንደሆነ ይናገራል። ስለ ሙሽራዋ ግን ምንም አይገልጽልም። የተዓምሩ ክፍል እንድህ ይላል፦

“ናትናኤልም ባቲላስ በሚባል አገር ሳለ ይህችውም በገሊላ አውራጃ የምትገኝ የቃና ምድር ናት። በዚያች በቃና ሠርግ በተደረገ ጊዜ ጌታችን ወደ ሠርጉ ግብዣ ይመጣና ይባርካቸው ዘንድ ናትናኤል ለምኖ እንዲያመጣው ዘመዶቹ ማለዱት፤ የሙሽራውም ስሙ ዶኪማስ ይባላል። እርሱም የዮካን ልጅ ነው። ናትናኤልም ወደ ጌታ ኢየሱስ ሂዶ “ጌታችን ሆይ የአባቴ የወንድም ልጅ ወደሆነው ወደ ዶኪማስ ሠርግ ትመጣልን ዘንድ የሠርጉንም ቤት ትባርክ ዘንድ እለምንሃለሁ” አለው። ጌታችን ኢየሱስም ጥሪውን ተቀብሎ አብሮ ወደ ሠርጎ ቤት ሄደ። ወደዚያም በገባ ጊዜ በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች ክብርት እመቤታችን ማርያም እና ሰሎሜ ወደ ሠርጉ ይመጡ ዘንድ ሰው ተላከ እነሱም መጡ” ይላል። (ተአምረ ኢየሱስ)

በተአምረ ኢየሱስ አገላለጽ ሙሽራው የሐዋርያው የናትናኤል አጎት የዮካን ልጅ ዶኪማስ ነው። ሌላው ወንጌላዊው የቅድስት ሰሎሜን መገኘት ያልጻፈ ቢሆንም ከድንግል ማርያም ጋር በሠርጉ ቤት ታድማለች። ይህን መሠረት በማድረግ ትርጓሜ ወንጌል የእመቤታችንን በሠርጉ መገኘት “ቤተሰብ ነች” በማለት ይገልጻል። (ትርጓሜ ወንጌል ዘዮሐንስ ፪፥፩)

የቅዱስ ሚካኤል በዓል እንዴት አብሮ ይከበራል?

ቅዱስ ሚካኤል እስራኤል የተባለ ያዕቆብ ከወንድሙ ከኤሳው ጋር ተጣልቶ ፈርቶ ሳለ የረዳው እና ዮርዳኖስን አሻግሮት ወደ እናቱ ወንድም ወደ ላባ ሄደ። ያዕቆብ የአጎቱን ልጆች ልያንና ራሔልን አግብቶ ብዙ ገንዘብ እና ልጆች አፈራ። በኋላም ከንብረቱ እና ከልጆቹ ጋር ቅዱስ ሚካኤል መንገድ እየጠረገና እያቀና ወደ አገሩ በሰላም መለሰው። ወንድሙ ኤሳውም በፍቅር ተቀበለው። ቅዱስ ሚካኤል ለያዕቆብ ዮርዳኖስን ከፍሎ ያሻገረበትን መታሰቢያ “የውኃን በዓል በውኃ” ለማክበር አባቶች ሥርዓት ሠርተው እናከብራለን።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *