ቃናዘገሊላ

መ/ር ዮሴፍ በቀለ

የቃና ዘገሊላ በዓል ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ከዘጠኙ ንኡሳን በዓላት መካከል አንዱ ሲሆን በዓሉም ጥር ፲፪ ቀን ይውላል፡፡ በዓሉ መከበር የነበረበት የካቲት ፳፫ ነበር፤ ነገር ግን የካቲት ላይ ጾም ስለሚሆን “የውኃን በዓል ከውኃ ጋር” ሲሉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ወደ ጥር ፲፪ ቀን አምጥተው አንድ ላይ እንዲከበር አድርገዋል፡፡

ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ “በሦስተኛውም ቀን የገሊላ ክፍል በምትሆን በቃና ሰርግ ሆነ፤ የጌታችን እናትም በዚያ ነበረች፡፡ ጌታችን ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ፡፡” በማለት ይገልጻል፡፡ በሰርጉም እናት ከተጠራ በኋላ ልጅ ይጠራልና የተወደደ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ከመምህር ደቀ መዝሙርን መነጠል አይገባምና ደቀ መዛሙርቱም ከጌታችን ጋር ተጠሩ፡፡

የሰርጉ ወይን ጠጁ ባለቀ ጊዜም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም‘ አለችው፡፡ እርሱም “አንቺ ሆይ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ፤ ጊዜዬ ገና አልደረሰም” አላት፡፡ እርሷም ለአሳላፊዎቹ “የሚላችሁን አድርጉ” አለቻቸው፡፡ (ዮሐ. ፪፥፩-፭) አሳላፊዎቹም ጋኖቹን ሞሉ፡፡ ውኃውም በተአምር የወይን ጠጅ ሆነ፡፡ በዚህም የድንግል ማርያም ምልጃ ተገለጸ፡፡

ሦስተኛ ቀን ምንድን ነው ቢሉ?ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው ጥር ፲፩ ማክሰኛ ቀን ነው፡፡ ወዲያውኑ እንደተጠመቀ ሳይውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄደ፡፡ በዚያም ፵ ቀንና ፵ ሌሊት ጾመ፤ አርባው ቀን ቅዳሜ የካቲት ፳ ይፈጸማል፡፡ እሑድ ገብቶ ያድራል፡፡ አርባውን ቀን እንደ አንድ አድርጎ እሑድን ለአርባው ቀን ሳኒታ (ማግስት) አለው፡፡ በማቴዎስ አምስቱን ዘመን እንደ አንድ አድርጎ ወበውእቱ ማዋዕል (በዚያን ዘመን) እንዳለ፡፡ ጾሙ የካቲት ፳ ቀን ይፈጸምና እሑድንና ሰኞን ውሎ የካቲት ፳፫ ቀን (በሦስተኛው ቀን) የገሊላ ክፍል በምትሆን በቃና በሰርግ ቤት ከእናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም እና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዶኪማስ ቤት ተገኝቷልና በሦስተኛው ቀን አለ፡፡

 “ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?” ያላትስ ምን ማለቱ ነበር? “ያልሽኝን እንዳልፈጽምልሽ ምን የሚከለክለኝ ነገር አለ?” ሲል ነው፡፡ “እናትና አባትህን አክብር፤ ለእናትና ለአባትህ ታዘዝ” ያለ አምላክ ለእናቱ እየታዘዘ አድጓልና ለነቀፋ ሳይሆን “አንቺ እናቴ ጠይቀሽኝ ምን የማላደርግልሽ ምን ነገር አለ?” ለማለት እንጂ፡፡ (ሉቃ. ፪፥፶፩)

“ጊዜዬ ገና አልደረሰም” ያለው ወይኑ ከእንስራው በደንብ ካለቀ በኋላ ውኃ ሞልተው የጌታን ተአምር እንዲታይ ለማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም ወይኑ በደንብ ሳያልቅ ከዚያው ላይ ቢሞላው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ተአምር አይታወቅም፤ ያንኑ አበረከተው በተባለ ነበር እንጂ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወይኑ ሁሉ ካለቀ በኋላ ግን ውኃ ተሞልቶ ወይን ሲሆን ተአምሩ ይታወቃል፤ ይገለጻል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በቃና ዘገሊላ ያደረገው የተአምራቱ መጀመሪያው ነው፤¸ክብሩንም ገለጠ፣ ደቀ መዛሙርቱም አመኑበት” ተብሎ ተጽፏል፡፡ (ዮሐ. ፪፥፲፩)  

በሰርገኛው ቤት ብቻ አይደለም ወይን የጎደለው፤ ሁላችንም ወይን የለንም የሕይወት እንስራችን ጎደሎ ነው፡፡ ይህ እንስራ (ጋን) የሚሞላው በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በቅዱሳን ምልጃ አማካኝነት ነው፡፡ እርሷ ከሌለችበት በፍጹም ሊሞላ አይችልም። ይህም በቅድሚያ ምልዕተ ጸጋ የሆነች እመቤታችንን መያዝ፤ ለምን ቢሉ እግዚአብሔር ከእርሷ ጋር ነውና፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነውና ብሏታል፤ እርሷን ከያዝን በምልጃዋ ጎዶሏችን ይሞላል፤ ለዘመናት ደክመናል ነገር ግን ያለ እርሷ እንስራችን ባዶ ነው፡፡ ስለዚህ እመቤታችን በምልጃዋ ትሙላልን፤ ፍቅሯን ታሳድርብን፡፡ በዚህም ምክንያት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ቃና ዘገሊላ ጥር ፲፪ ቀን በድምቀት ታከብረዋለች፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *