ቁስቋም ማርያም
ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ወደ ግብፅ እንደሚሰደድ “ወይወርድ እግዚእነ ውስተ ምድረ ግብፅ እንዘ ይጼዐን ዲበ ደመና ቀሊል፤ ጌታችን በፈጣን ደመና (በእመቤታችን ጀርባ) ተጭኖ ወደ ግብፅ ይወርዳል” ብሎ በተናገረው ትንቢት መሠረት ስደትን ለመባረክ፣ የግብጽን ጣኦታት ያጠፋ ዘንድ ተሰዷል፡፡ (ኢሳ. ፲፱፥፩)
ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስም የጌታችንን ስደት በተመለከተ “የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ “ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይሻዋልና ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ምድረ ግብፅ ሽሽ፤ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ኑር” በማለት እንደ ጻፈው ቅዱስ ዮሴፍ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ከልጇ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እንዲሁም ሰሎሜን ይዞ ወደ ግብፅ ተሰዷል፡፡ (ማቴ. ፪፥፲፫)
ነገር ግን ጊዜው ሲደርስ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ግብፅ ይሰደዱ ዘንድ እንደነገራቸው ሁሉ ፵፪ ወራት (ሦስት ዓመት ከስድስት ወራት) ሲፈጸም የሄሮድስ መሞት እና ወደ ኢየሩሳሌም ይመለሱ ዘንድ “የሕፃኑን ነፍስ የሚሹ ሞተዋልና፥ ተነሥተህ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ” በማለት ነግሯቸዋል፡፡ (ማቴ.፪፥፲፱-፳፩) በዚህም መሠረት ኅዳር ፮ ቀን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተመለሱበትን ቀን በድምቀት ታከብረዋለች፡፡
ደብረ ቁስቋም በደቡብ ግብፅ የሚገኝ ተራራ ነው፡፡ ወደ ግብፅ ከተሰደደች በኋላ አሳዳጅ የነበረው ሄሮድስ በመሞቱ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከስደት ሲመለሱ ያረፉበት ቦታ ነው፡፡ ይህ ቁስቋም ተራራ ጌታችን ብዙ ተዓምራት የፈጸመበት በመሆኑ ተባርኳል፤ ተቀድሷልም፡፡ ይህ ተራራ የተቀደሰ ስለመሆኑ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ታኦፊሎጎስ በድርሳነ ማርያም እንዲህ ብሏል፤ “ይህም ከሀገሮቹ ሁሉ ተራሮች የሚበልጥ (የተለየ) ከፍ ያለ ተራራ ነው፡፡ በውስጡ ቅዱስ አግዚአብሔር ያድራል፡፡ ይህንን ተራራ የእግዚአብሔር ልጅ ወዶታል፤ አክብሮታልምና፤ ከዓለም ሀገሮች ሁሉ ከተቀደሰች እናቱ ጋር አድሮባታልና፡፡ ከመላእክት ቤት ያድር ዘንድ አልወደደም፤ ቢታንያንም አልመረጠም፤ ከተራራው ላይ ባለች ገዳም ቤት ውስጥ አደረ እንጂ፤ ነቢዩ ዳዊት፤ የጽዮንን ተራራ ወደደ፤ በአርያምም መቅደሱን ሠራ” እንዳለ፡፡
ሊቁም በመቀጠል ሙገሳውን እንዲህ ሲል ገልጿል፤ “አንተ ተራራ ሆይ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሆንህ ጊዜ በኪሩቤልና በሱራፌል መካከል ፍጹም ደስታ ተደረገ፡፡ የመላእክት ሠራዊት ቅዱስ የሆነ ፈጣሪያቸውንና ጌታቸውን ይታዘዙ (ያገለግሉ) ነበር፡፡ አንተ ተራራ ሆይ ያደረብህ ጌታችን ስለሆነ ከተራሮች ሁሉ ከደብረ ሲናም ይልቅ ከፍ ከፍ አልህ፤ ጌታችን በደብረ ሲና ባረፈ ጊዜ ፍጹም ደስታ፣ ታላቅ ብርሃንም በሆነ ጊዜ መቅረብና መመልከት ከሙሴ በቀር የቻለ የለም፡፡ እርሱም ቢሆን ፊቱን ማየት አልቻለም፡፡ ሥጋ ለባሽ ሁሉ እርሱን ዐይቶ በሕይወት መኖር የሚቻለው የለምና፡፡ እኛ ግን አየን፤ ከዚህ ማደሩንም ተረዳን፤ ዳግመኛም ንጽሕት በሆነች በማርያም ዘንድ አየነው፡፡ ቅድስት ከሆነች ከእመቤታችን ማርያም ዘንድ በቤተልሔም ስለ እኛ በተዋሐደው ሥጋ በጨለማና በሞት ጥላ ሥር ያለን እኛን ከቸርነቱና ሰውን ከመውደዱ የተነሣ መጥቶ አዳነን፤ ከዓለም ሁሉ ይልቅ ጣዖትን በማምለክ ሲበድሉም ወደ ግብፅ ሀገር ወርዶ በእነርሱ ላይ የመለኮትነት ብርሃኑን በማብራት ታላቅ የሆነ ክብሩን ገለጠ፡፡” እመቤታችን ቅድስት ማርያምም ከጌታችን ኢየሱስ ጋር በዚህም ተራራ ስድስት ወራት ዐርፈዋል፡፡ (ድርሳነ ማርያም)
ኅዳር ፮ ቀን የሚነበበው የመጽሐፈ ስንክሳር ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ዳግመኛም በኋላ ዘመን ሐዋርያትን በደብረ ቁስቋም ሰብስቦ፤ ታቦትንና ቤተ ክርስቲያኑን አክብሮ የቊርባን መሥዋዕትንም ሠርቶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን እንደ ሰጣቸው፤ ጌታችንም ካረገ ከብዙ ዘመናት በኋላ በኅዳር ፮ ቀን “አስተጋብኦሙ እግዚእነ ለሐዋርያቲሁ ቅዱሳን ውስተ ዝንቱ ደብረ ቊስቋም ወቀደሰ ታቦተ ወቤተ ክርስቲያን ወሠርዐ ቊርባነ ወመጠዎሙ ሥጋሁ ቅዱሰ ወደሞ ክቡረ፤ በዚህ በደብረ ቊስቋም ቅዱሳን ሐዋርያቱን ሰበሰባቸው፤ ታቦትንና ቤተ ክርስቲያንንም አክብሮ የቊርባን መሥዋዕትንም ሠርቶ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ሰጥቷቸዋል” ይላል፡፡ (ስንክሳር ኅዳር ፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!