ቀዳም_ሥዑር
ከመምህር አዲሱ በዛብህ
የማይሞተው አምላካችን በፈቃዱ ቅድስት ነፍሱን ከሥጋው ከለየ በኋላ ሰማይና ምድር የማይችሉት አምላካችን እኛን ያስነሣ እና ነጻነትን ይሰጠን ዘንድ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን ነጻ ሲያወጣ በአካለ ሥጋ ከመለኮቱ ያለመለያየት በመቃብር ሦስት ቀን ሦስት ሌሊት ሙስና መቃብር ሳያገኘው ቆይቷል።
ይህንን ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስ ሲያስረዳ እንዲህ ይላል”ነፍሱን በሲኦል አልተወም ሥጋውም ሙስና መቃብርን አላየም መለኮቱ ከሁለቱም አልተለየም ሁለንተናው ከነፍስ ጋር በሲኦል ነበር። በሲኦል ለጻድቃን የምሥራችን አበሠረ፤ ሁለንተናው ከሥጋ ጋር በመቃብር ነበር እንጂ በቦታው ሁሉ ምሉእ ነውና” (ሃይ. አበ ዘቄርሎስ ፸፩፥፲፭-፲፮)
ለሁላችን የማያልፍ ድኅነትን ፣ ሥርየተ ኃጢአትን ፣ ቅድስናን ፣ አሸናፊነትን እና ይቅርታን ይሰጠን ዘንድ ሞታችንን ሞተ፤ የገባልንን ቃል ኪዳን ፈጸመ። “ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል።” እንዲል። (ማቴ፲፪፥፵)
ጌታችን ከዐርብ ሠርክ እስከ እሑድ መንፈቀ ሌሊት ድረስ ሦስት ቀን ሦስት ሌሊት በመቃብር ዐርፏል። እነዚህ ቀንና ሌሊት የራሳቸው ትርጉም አላቸው። የነገረ ክርስቶስ መጽሐፍ ጸሐፊ መጋቤ ሐዲስ ክቡር ዶክተር ሮዳስ ታደሰ ስለ ሦስት ምክንያት እንደሆነ ይጠቅሳሉ: –
፩. ለአዳም ፣ ለሔዋን ፣ ለሕፃናቱ ሊክስ
፪. ለሥጋ ፣ ለነፍስ ፣ ለደመ ነፍስ ሊክስ
፫. ሞትን ፣ ፍዳን ፣ ኃጢአትን ሊያጠፋ ጌታችን ሦስት ቀን ሦስት ሌሊት በመቃብር ዐርፏል። (ነገረ ክርስቶስ፡ ገጽ፻፸፰)
ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት
ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሠ መቃብር ፫ ቀንና ፫ ሌሊት አደረ፡፡ ይኸውም ነቢዩ ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ እንዳደረው (ት/ዮና ፪÷፩-፪) ራሱም መድኀኔ ዓለም ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በ፫ ኛው ቀን አነሣዋለሁ ብሏል፡፡ (ዮሐ. ፪፥፲-፳፪) የተሰቀለ ዐርብ ፮ ሰዓት፤ ነፍሱን ከሥጋው የለየው ዐርብ ፱ ሰዓት ፤ ወደ መቃብር የወረደው ዐርብ ፲፩ ሰዓት ፤ የተነሣ ቅዳሜ ለእሐድ አጥቢያ ሌሊት ፮ ሰዓት ነው፡፡ ይህ ፫ ቀንና ፫ ሌሊት እንዴት ተባለ? ቢሉ የመጀመሪያው ብርሃኑን “ቀን” ጨለማውን “ሌሊት” በማለት የሚቆጠረው አቆጣጠር ነው፡፡ ይኸውም
ሦስቱ ቀኖች: –
🕕 ዐርብ ከነግህ/ጠዋት እስከ ቀን ፮ ሰዓት ብርሃን ነበር
🕘 ከ፱ ሰዓት እስከ ሰርክ ብርሃን ነበር
🕛 ቅዳሜ መዐልት/ቀን
ሦስቱ ሌሊቶች: -
🕕 ዐርብ ከቀን ፮ ሰዓት እስከ ቀን ፱ ሰዓት አምላክ በመስቀል ላይ ሳለ ጨለማ ሆነ
🕛 ዐርብ ለቅዳሜ ሌሊት
🕛 ቅዳሜ ለእሁድ ሌሊት
ሌላው በዕብራውያን የቀን አቆጣጠር መሠረት ዓርብ ሌሊቱን እሑድ ቀኑን ይስቡና ይቆጠራል፡፡
ይኸውም: – ሌሊቶቹ
ሐሙስ ለዐርብ
ዐርብ ለቅዳሜ
ቅዳሜ ለእሑድ
ቀኖቹ ደግሞ
ዐርብ ቀኑን
ቅዳሜ ቀኑን
እሁድ ቀኑን ቆጥሮ ነው፡፡
ጌታችን ቀድሞ አዳምን፤ ሔዋንን ዐርብ ፈጥሮ ቅዳሜ እንዳረፈ ሁሉ አሁንም ያጡትን ገነትን ባጡበት ዐርብ ዕለት ሰጥቶ ቅዳሜ በመቃብር አርፎባታል ስለዚህም የተለየችቅዳሜናት።
➢ አራቱ ስያሜዎች፦
፩. ቀዳም ሥዑር
ሥዑር ማለት የግእዝ ግስ ሆኖ በአማርኛ የተሻረ ማለት ሲሆን በአንድ ላይ ሲነበብ የተሻረ_ቅዳሜ የሚል ትርጓሜ እናገኛለን። ምክንያቱ እንደ ቀደመቺቱ ሰንበት የማናርፍባት ይልቁንም ደቀመዛሙርቱን አብነት አድርገን በጾም በኀዘን ሕማሙን እያሰብንባት የምናሳልፋት ቀን በመሆኗ ቀዳም ሥዑር ተብላለች።
፪. ዐባይ ሰንበት
አምላካችን ሃያ ሁለቱን ሥነ ፍጥረት ፈጥሮ እንዳረፈባት የማዳኑንም ሥራ በመስቀል ላይ ፈጽሞ በአዲስ መቃብር ዐርፎ ውሎባታልና ዐባይ ሰንበት ተብላለች።
፫. ቅዱስ ቅዳሜ
በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን አድኖባታል ፣ ሲኦልን በዝብዟል ፣ ምርኮን ለራሱ ጨምሯል ፣ ዲያብሎስን አሳፍሯል ፣ የዕዳ ደብዳቤያችንን ደምስሷል ከሌሎች ቀናት ሁሉ የተለየች በመሆኗ ቅዱስ ቅዳሜ ተብላለች።
፬. ለምለም ቅዳሜ
በዚህ ዕለት በኖኅ ዘመን የጥፋቱ ውኃ ማለቁን የሰላም አብሣሪ ርግብ ለኖኅ ቄጤማ እንዳመጣችለት አሁንም የጥፋቱ ሞት ራቀልን ፣ ከሞት ወደ ሕይወት ተሸጋገርን ፣ አንቀጸ ገነት ተከፈተልን ሲሉ ካህናት አባቶቻችን የቅዳሜው የነግህ ጸሎት ከተጠናቀቀ በኋላ ለምእመኑ ለምለም ቄጤማ ስለሚሰጡ እኛ ምእመናንም በግንባራችን ላይ አድርገን ትንሣኤውን ስለምናከብር ለምለም ቅዳሜ ተብላለች።

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!