ሱባዔያችን በረከት የሚያሰጥ ይሁን

እንኳን ለእመቤታችን የትንሣኤና ዕርገት በዓል በሰላም አደረሳችሁ – አደረሰን፡፡

በእንዳለ ደምስስ

ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምሮ ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከት እናገኝ ዘንድ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከደነገገቻቸው ሰባቱ አጽዋማት መካከል ፍልሰታ ለማርያም ጾምን ስንጾም ቆይተናል፡፡ ከጾሙ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ሥርዓት ሊበጅላቸውና “ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሉ አበው ሊስተካከል ይገባል ያልኩትን በሐመር መጽሔት ፳፻፲፩ ዓ.ም መንገደኛው ዓምድ ላይ ያሰፈርሁትን ጽሑፍ ለዛሬ ለድረ ገጹ ቢሆን ብዬ አቅርቤዋለሁ፡፡ መልካም ንባብ፡፡

እንደምን ሰነበታችሁ? መንገደኛው ነኝ፡፡ እነሆ ከእመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም በረከትን በመሻት በፍልሰታ ለማርያም ሱባዔ ለመያዝ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም በታነጸውና በቤተ ክርስቲያናችን ከሚታወቁ ታላላቅ ገዳማት በአንዱ ከዋዜማው ጀምሮ ተገኝቻለሁ፡፡

ለሱባኤ የሚያስፈልጉኝን የጸሎት መጻሕፍትና አልባሳት በቦርሳ አድርጌ በጀርባዬ አዝዬ፣ የጸበል መቅጃ አነስተኛ ጀሪካን፣ ሽንብራና በሶ በፌስታል አንጠልጥዬ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ሔጄ ተሳለምኩ፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ምእመናን እንደ እኔ በረከት ፍለጋ፣ በጾም በጸሎት ተወስነው ከአምላካቸው ከእግዚአብሔር ለመገናኘት፣ የልቦናቸውን መሻት ይፈጽምላቸው ዘንድ ለመማጸን ያለማቋረጥ ወደ ገዳሙ ይጎርፋሉ፡፡

በበጎ አድራጊ ምእመናን እንደታነጹ የሚታወቁት የወንዶችና የሴቶች የሱባዔ መያዣ በአቶች(አዳራሾች) ከቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ውጪ በስተ ምሥራቅና በስተ ምዕራብ ሽንጣቸውን አርዝመው ለመስተንግዶ በራቸውን ከፍተዋል፡፡ በበሮቹ መግቢያና መውጫዎች የሚገቡና የሚወጡ ምእመናን ግርግር አካባቢውን የገበያ ውሎ አስመስሎታል፡፡ ሁሉም ይጣደፋል፡፡ ግርግሩን እየታዘብኩ ለሱባዔ ወደ ገዳሙ መምጣቴን ለማሳወቅና ቦታ እንዲሰጠኝ ለመጠየቅ ወደ አስተናጋጆቹ ሔድኩ፡፡ ማንነቴን የሚገልጽ መታወቂያ በማቅረብ አስመዝግቤ ወደተመደብኩበት የወንዶች አዳራሽ አመራሁ፡፡

ገና ከቀኑ ስምንት ሰዓት ቢሆን ነው፡፡ አዳራሹ በመጋረጃ መሐል ለመሐል ተከፍሎ በርካታ ምእመናን እንዲያስተናግድ ተደርጎ ተዘጋጅቷል፡፡ ወለሉ ሙሉ ለሙሉ ምንጣፍ ተነጥፎበታል፣ ቀድመውኝ የመጡ ምእመናን የራሳቸውን ምንጣፍ፣ ካርቶን፣ ከምንጣፉ በላይ ደርበው አንጥፈዋል፡፡ አብዛኛው የአዳራሹ ሥፍራ ተይዟል፡፡ ቦታ ፍለጋ ዓይኖቼን አንከራተትኳቸው፡፡ ቢያንስ አምስት ሰው ሊያስተናግድ የሚችል ቦታ እንዳለ አስተዋልኩ፡፡ የሚመቸኝን ቦታ ከመረጥኩ በኋላ ጓዜን አስቀምጬ ምንጣፍ ዘረጋሁ፡፡

ራሴን ካረጋጋሁ በኋላ አዳራሹን ከላይ እስከ ታች በዐይኖቼ ቃኘሁት፡፡ አብዛኛው በአዳራሹ ቦታ ይዘው ያሉት ወጣቶች ናቸው፡፡ አልፎ አልፎ ግን በጎልማሳነት ዕድሜ ላይ ያሉ፣ በሕመም ምክንያት በአስታማሚ የሚረዱ ሰዎችም አብረውን አሉ፡፡ ከሁሉም ግን ትኩረቴን የሳበው  በስተቀኝ በኩል ግድግዳውን ተደግፈው ከአንድ ሱባዔ ከሚይዝ ሰው የማይጠበቅ ፌዝና ቀልድ ላይ ያተኮረ የወጣቶቹ ድርጊት ነው፡፡ ገና ከዋዜማው እንዲህ ከሆነ ጥቂት ሲቆይ ለጸሎትም እንኳን እንደምንቸገር መገመት አላዳገተኝም፡፡ እኔም አላርፍም እነሱን መከታታል ጀመርኩ፡፡ እየተቀላለዱ ይሳሳቃሉ፡፡

የልጆቹ ሁኔታ ስላላማረኝ ነጠላዬን መስቀልያ ለብሼ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ሔድኩ፡፡ አሁንም የቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር በጸበልተኛና ሱባኤ በሚገቡ ምእመናን ግርግር እንደተሞላ ነው፡፡ ያሰብኩትን ሱባዔ በሰላም አስጀምሮ በሰላም እንዲያስፈጽመኝ ተማጸንኩ፡፡ ጠዋት የጸበል መጠመቂያ ቦታውን በመፈለግ እንዳልደናበር ወደ አንድ ጸበልተኛ ጠጋ ብዬ “ጸበል መጠመቂያው የት ነው?” ብዬ ጠየቅሁት፡፡

በጣቱ ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ እያመለከተኝ “በዚህ በኩል ነው፡፡ ቢያንስ አራት ወይም አምስት ደቂቃ ብቻ ቢወስድ ነው” አለኝ፡፡ በደንብ ሲያስተውለኝ እንግዳ መሆኔን በመረዳት “ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የመጣኸው?” አለኝ፡፡

“አዎ፡፡” አልኩት፡፡

“ወንድሜ ራስህን በደንብ መጠበቅ አለብህ፡፡ በእግዚአብሔር ወይም በእመቤታችን እንዳታማርር፡፡ የሰው ፍላጎቱ ብዙ ነው፡፡ ለበረከት የሚመጣ እንዳለ ሁሉ ለስርቆትና ለክፉ ነገር የሚመጣም አለ፡፡ ጸበል ስትጠመቅ ያወለቅኸውን ልብስ ይዞብህ፣ ወይም ለብሶብህ የሚሔድም አይጠፋም፡፡ ንብረትህን በደንብ መጠበቅ አለብህ፡፡ እንዲህ ስልህ ለነፍሳቸው ያደሩ፣ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ያስገዙና ስለሌሎች የሚኖሩ የሉም እያልኩህ አይደለም፡፡ ሥፍራው ታላላቅ ተአምራት የሚከናወንበት የጽድቅ ሥፍራ ነው፡፡ ጠንክሮ መጸለይ ነው” አለኝ በትሕትና፡፡

“እሺ ወንድሜ፡፡ እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡ የመጣሁት ከእመቤታችን በረከት ለማግኘት ነው፤ ለዚህም እግዚአብሔር ይረዳኛል፡፡” በማለት አመስግኜ ተሰናበትኩት፡፡ “ብዙ ኃጢአት ባለችበት የእግዚአብሔር ጸጋ ትበዛለች” የሚለው የቅዱስ ኤፍሬም የሰኞ ውዳሴ ማርያም ጸሎት ትዝ ብሎኝ እየተገረምኩ አንድ ጥግ ድንጋይ ላይ ተቀመጥኩ፡፡

ሰርክ ላይ ጸሎት፣ የወንጌል ትምህርት እንዲሁም ምሕላ ተደረገ፡፡ ሱባዔው ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ምእመናን ሥነ ምግባር በተሞላበት ሁኔታ የመጡበትን ዓላማ አሳክተው እንዲመለሱ፣ የበረከቱ ተሳታፊም እንዲሆኑ በመምህራን ማሳሰቢያ ተሰጠ፡፡

የሰዓታት ጸሎት መርሐ ግብር እስኪጀመር ድረስ ሁሉም ወደየበአቱ በማምራት በሶውን በጥብጦ፣ ቆሎውን፣ ሽምብራውን ቆርጥሞ የበረታ በጸሎት ሲጠመድ ሌላው ዕረፍት አደረገ፡፡ አንዳንዶች ከአሁኑ አርምሞ ጀምረዋል፡፡ አዳራሹ ውስጥ በቡድን ሆነው የመጡት ጓደኛማቾች ድምጻቸውን ይቀንሱ እንጂ መቀላለዳቸውን አላቋረጡም፡፡ በጸሎት ለተጠመደ ኅሊናን ይሰርቃሉ፡፡

ከሌሊቱ ዐራት ሰዓት ሲሆን የቤተ ክርስቲያኑ ደወል ተደወለ፡፡ አንዱ አንዱን እየቀሰቀሰ ተያይዘን ወደ ቤተ መቅደሱ አመራን፡፡ ካህናት አባቶች ሰዓታት ቆመዋል፡፡

ቤተ መቅደሱ የቻለውን ያህል ምእመናንን አስተናግዶ ሌላው ውጪ ሆኖ ብርዱን ተቋቁሞ ይጸልያል፡፡ ሰዓታት እንደ ተጠናቀቀ ንጋት ላይ የኪዳን ጸሎት፣ ስብሐተ ነግህ ቀጠሉ፡፡ ጨለማው ለብርሃን ሥፍራውን ሲለቅ ውዳሴ ማርያምና ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ እንደ ቅደም ተከተላቸው ቀርበው የቅዳሴ ሰዓት እስኪደርስ ጸበል ለመጠመቅ እሽቅድድም በሚመስል ፍጥነት ይራወጣሉ፡፡

ጸበል መያዣ ባለ አምስት ሊትር ጀሪካን ይዤ ወደ ጸበሉ ስፍራ ሰዎችን ተከትዬ ሔድኩ፡፡ ግርግሩ ዕረፍት ይነሣል፡፡ እንደማንኛውም ሰው ወረፋ ያዝኩ ነገር ግን በጉልበታቸው የተመኩ ወጣቶች እየተጋፉ፣ የዕድሜ ባለጠጋ የሆኑትን አረጋውያንን እየገፉ ተጠምቀው ለመውጣት ይጣደፋሉ፡፡ ሰልፉ ተረበሸ፡፡ ችግሩ ከሚያስተናግዱ ወንድሞች በላይ ሆነ፡፡ በሴቶችም በኩል መጠነኛ ግርግሩ ቀጥሏል፡፡ በዚህ መካከል የሚወድቅ፣ ንብረቱ የሚዘረፍ ቁጥሩ በርካታ ነው፡፡ የምእመናን ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም እስከ ስድስት ሰዓት ሳይጠመቅ የተመለሰ አልነበረም፡፡

ከቅዳሴ በኋላ ዕረፍት የሚያደርጉ እንዳሉ ሁሉ ተፈትተው የተለቀቁ ይመስል ከበአታቸው እየወጡ በቡድን፣ በቡድን እየሆኑ በየጫካው ለፌዝና ለቀልድ ጊዜያቸውን የሰጡ ምእመናንም አሉ፡፡ ነገር ግን የመጡት ለሱባዔ ነው፡፡

እንዲህ እንዲህ እያልን ነሐሴ ፲፮ ቀን ድረስ ቆየን፡፡ የእመቤታችን ትንሣኤ ተበሠረ፡፡ ከቅዳሴ በኋላ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን የእመቤታችንን ትንሣኤ እንደ ልጇ ትንሣኤ ያክብሩት ብላ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት እንደ ሠራች በስፋት አስተማሩ፡፡ የሱባዔውንም መጠናቀቅ አወጁ፡፡

ቤተ ክርስቲያኗ ከጥሉላት ምግቦች ተከልክሎ የቆየውን ምእመን የጾም መፍቻ ብላ ያዘጋጀችው ማዕድ በየአዳራሹና በድንኳኑ ታደለ፡፡ እኔ ካለሁበት አዳራሽ ውስጥ ካሉት ምእመናን መካከል “አንበላም እስከ ነሐሴ ፳፩ ቀን ጾማችንን እንቀጥላለን” በማለት የመለሱት ይበዛሉ፡፡ ግራ ተጋባሁ፡፡ የቀረበላቸውን ተቃምሰው ጓዛችን ሸክፈው ወደወጡበት ቤታቸው ለመመለስ የሚጣደፉ ምእመናንም ቁጥር ብዙ ነው፡፡ እኔ ግን አንድ ቀን እረፍት አድርጌ በማግስቱ ለመሔድ ስለወሰንኩ የቀረበልኝን ማዕድ በላሁ፡፡

የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በመጣሱ ቅር ተሰኘሁ፡፡ ቤተ ክርስቲያን “የእመቤታችንን ትንሣኤ እንደ ልጇ ትንሣኤ አክብሩ” እያለች ይህንን ተላልፈው የእመቤታችን ትንሣኤ በሚከበርበት ወቅት እጾማለሁ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አልገባኝም፡፡ “ቤተ ክርስቲያን ሁለት ዓይነት ሥርዓት አላት እንዴ?” እያልኩ ከራሴ ጋር ሙግት ገጠምኩ፡፡ አንድ ነገር ወሰንኩ፡፡ አባቶችን ማማከር፡፡

ጥቂት ዕረፍት አድርጌ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር በመግባት አባቶችን ፈለግሁ፡፡ ውዳሴ ማርያምና ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜን ላለፉት ቀናት በጣፋጭ አንደበታቸው ሲተረጉሙ የነበሩት አባት ከቤተ መቅደስ ሲወጡ አገኘኋቸው፡፡ ቀረብ ብዬ ሰላምታ ከሰጠኋቸው በኋላ ጥያቄዬን አቀረብኩ፡፡

በትኩረት እየቃኙኝ “ልጄ ቤተ ክርስቲያን የሠራችው ሥርዓት ማፋለስ ኃጢአት ነው፡፡ እውነት ነው ቤተ ክርስቲያን የእመቤታችን ትንሣኤ እንደ ልጇ ትንሣኤ ያክብሩት ብላ ሠርታለች፡፡ ነገር ግን ምእመናን ሲጥሱት እንመለከታለን፡፡ ከዚህ በፊትም በስፋት አስተምረናል፡፡ የበለጠ በረከት ለማግኘት ነው” እያሉ የሚጾሙ ምእመናን ቁጥር በርካታ ነው፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፡፡ አንዳንድ ምእመናን ቢነገራቸውም አይሰሙም፡፡ ግዝት አይደለም መጾም እንችላለን ይሉሃል፡፡ አንዳንድ አባቶችንም ስታነጋግር ምን ችግር አለው ይሉሃል፡፡ ነሐሴ ፳፩ ቀንም ታቦት አውጥተው ያከብራሉ፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፡፡” አሉኝ ጥያቄው የእኔ ብቻ ሳይሆን የእሳቸውም ጥያቄ እንደሆነ በሚገልጽ ምላሽ፡፡

“ታዲያ ሥርዓት የሚሽሩትን ከገዳሙ ለምን አታስወጡም” አልኳቸው፡፡

ለጥቂት ሰከንዶች በመገረም እያዩኝ፡፡ “ልጄ እኔ የዚህ ሥልጣን የለኝም፡፡ በተቻለኝ አቅም ልጆቼን በሔዱበት ሁሉ የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት እንዳይጥሱ አስተምሬአቸዋለሁ፡፡ ካለ እኔ ፈቃድም አያደርጉትም፡፡ አሁን አንተ የምትለኝን ገዳሙ የራሱ አስተዳደር አለውና እነሱን ጠይቅ” ብለው መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ አስተዳደሩን ለማግኘት ያደረግሁት ጥረት ሳይሳከ ቀረ፡፡

ሁላችንም ምክንያት የምናደርገው ሌሎችን ነው፡፡ ለምን ብለን ግን አንጠይቅም፡፡ ፈቃጁ ማነው? ማን እንደሆነ አይታወቅም፡፡ አንዱ ወደ አንዱ ያሻግርሃል፡፡ በጣም ተበሳጨሁ፡፡ ወደ አዳራሹ ተመለስኩ፡፡ ብዙ ሰዎች ሱባኤያቸውን ቀጥለዋል፡፡ በመብላቴ እኔን እንደ ደካማና ኃጢአተኛ አድረገው የቆጠሩኝ መሰለኝ፡፡ ሕሊናዬ አላርፍ አለኝ፡፡

አዳራሹ ውስጥ ካሉት መካከል ለረጅም ሰዓት ቆሞ በመጸለይና በመስገድ መንፈሳዊ ቅናት ወደ ቀናሁበት ወንድም ጠጋ ብዬ ጥያቄዬን አቀረብኩለት፡፡ “ጾሙ አልተጠናቀቀም ወይ?” ነበር ጥያቄዬ፡፡

“በረከት ለማግኘት ስል እስከ እመቤታችን ዕረፍት መታሰቢያ ቀን ድረስ እቆያለሁ፡፡” አለኝ፡፡

“ለምን? ሥርዓት መጣስ አይሆንብህም?” አልኩት፡፡

“መብቴ እኮ ነው፡፡ ከመብላት አለመብላት ይሻላል፡፡” አለኝ፡፡

“እንዴት እንዴት አድርገህ ነው የምትተረጉመው? ቤተ ክርስቲያን የእመቤታችንን ትንሣኤ ከነሐሴ ፲፮-፳፩ ቀን እንደ በዓለ ሃምሳ ያክብሩት በማለት መደንገጓን ምነው ዘነጋህ? ለመሆኑ ሱባኤው እስከ ነሐሴ ፳፩ ቀን መቆየት የተጀመረው መቼ ነው?” አልኩት፡፡

“በቅርብ ይመስለኛል፡፡ ግን ምን ችግር አለው? ቀኖና ነው፡፡ ቀኖና ደግሞ ይሻራል፣ ይስተካከላል፡፡ አባታችን ይህንን ሲናገሩ ሰምቻለሁ” አለ በድፍረት፡፡

“ማናቸው አባትህ?” አልኩት ዐይን ዐይኑን እየተመለከትኩ፡፡

“ባሕታዊ እከሌ ናቸዋ” አለኝ፡፡

በጣም አዘንኩ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ተዘንግቶ፣ ቀድሞ አባቶች የሠሩትን ሥርዓት በባህታዊ ነኝ ባዮች ሲሻር ያሳዝናል፡፡

“ለመሆኑ ማነው የሚሽረውና፣ የሚያስተካክለው?” አልኩት እልህ እየተናነቀኝ፡፡

“ቤተ ክርስቲያን ናታ፡፡”

“የቤተ ክርስቲያን መብት ከሆነ አንድ ባሕታዊ ይህንን የመሻር ምን ሥልጣን አለው? ለምእመኖችዋ ውሳኔውን ማሳወቅ ያለባት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ እሷ ደግሞ አባቶች የሠሩትን ሥርዓት የምታጸና እንጂ የምታፈርስ አደለችም፡፡” አልኩት በንዴት፡፡

“አንተ እንደፈለግህ፡፡ እኔ ግን የባሕታዊ አባቴን ድምጽ እሰማለሁ፡፡ በቃ አትጨቅጭቀኝ፡፡” በማለት በኩርፊያ ጥሎኝ ሄደ፡፡

ለመሆኑ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሲጣስ አደብ የሚያስገዛው ማነው? ለማንስ አቤት እንበል? ሱባኤያችን በረከት የሚያሰጥ ይሆን ዘንድ ምን እናድርግ? ሱባኤ ሔጄ ይህንን ታዘብኩ፡፡ እናንተስ ምን ትላላችሁ?

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *