ሰባቱ የመስቀል ላይ ጩኸቶች
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአይሁድ በይሁዳ አማካይነት ተላልፎ ከተሰጠበት ሐሙስ ምሽት ጀምሮ ስቃይ ሲያጸኑበት ቆይተዋል፡፡ በዕለተ ዐርብም ይሰቅሉት ዘንድ አስከ ቀራንዮ መስቀል አሸክመው የተለያዩ ጸዋትወ መከራ እያጸኑበት ወስደውታል፡፡ በመሰቀል ላይ በሁለቱ ወንበዴዎች መካከል ከተሰቀለበት ሰዓት ጀምሮም የተናገራቸው ቃላት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን “ሰባቱ የመስቀል ላይ ጩኸቶች ወይም “ሰባቱ አጽርሐ መስቀል” በማለት ሰይማ ታስባቸዋለች፡፡ እነርሱም በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱ ሲሆን ቀጥለንም በዝርዝር እንመለከታቸዋለን፡-
፩ኛ. “ኤሎሄ ኤሎሄ ላማሰበቅታኒ፤ አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ”፡–
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ በዘጠኝ ሰዓት የተናገረው ቃል እንደሆነ በወንጌል ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡ “በዘጠኝ ሰዓትም ጌታችን ኢየሱስ ኤሎሄ ኤሌሄ ላማሰበቅታኒ ብሎ በታላቅ ቃል ጮኸ፡፡ይኸውም አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ? ማለት ነው፡፡ በዚያም ቆመው የነበሩት በሰሙ ጊዜ ይህስ ኤልያስን ይጠራል አሉ” (ማቴ.፳፯፥፵፭) እንዲል፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ ብሎ የተናገረበት መሠረታዊ ሐሳብ፡- ያችን የድኅነት ቀን ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን በኋላ ያለችውን ዕለተ ዓርብ በተስፋ ይጠባበቅ የነበረውን አዳምን ወክሎ እንደሆነ አበው ያስረዳሉ፡፡ (ማቴ.፳፯፥፵፭ አንድምታ ትርጓሜ)፡፡ በመሆኑም አምላኬ አምላኬ ያለው በአዳም ተገብቶ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁም አምላኬ አምላኬ ያለው ሰውነቱን ሲገልጥ ነው፡፡ ይህም ፍጹም አምላክነቱንና ፍጹም ሰውነቱን ማለት ነው፡፡
፪ኛ. “ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ”፡–
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደል ሳይኖርበት እንደ በደለኛ ተቆጥሮ በሁለት ወንበዴዎች መካከል ነበር የተሰቀለው፡፡ “ከእርሱ ጋርም ሁለት ወንበዴዎችን አንዱን በቀኙ አንዱን በግራው ሰቀሉ፡፡ መጽሐፍ ከዐመፀኞች ጋር ተቈጠረ ያለው ተፈጸመ” (ማር.፲፭፥፳፯) ይላልና፡፡
በቀኝ በኩል የተሰቀለው ወንበዴ ጌታችንን “አቤቱ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ›” አለው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም መልሶ እንዲህ አለው “እውነት እልሃለሁ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ፡፡” (ሉቃ.፳፫፥፵፫)፡፡
፫ኛ. “አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ”፡–
“ያን ጊዜም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድምጹን ከፍ አድርጎ አባት ሆይ ነፍሴን በአንተ እጅ አደራ እሰጣለሁ ብሎ ጮኸ፤ ይህንም ብሎ ነፍሱን ሰጠ” (ሉቃ.፳፫፥፵፮)፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ “አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” በማለት የተናገረው ቃል የተሰቀለው እርሱ እግዚአብሔር ወልድ እንደሆነና የአብ የባሕርይ ልጁ እንደሆነ ያሳያል፡፡
፬ኛ. “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው”፡–
ምንም በደል ሳይኖርበት አይሁድ በክፋት ተነሳስተው መከራ አጸኑበት፤ ያን ሁሉ የግፍ ግፍ በጭካኔ የተሞላ መከራ ሲያደርሱበት ልባቸውን ዲያብሎስ ስላደነዘዘው የሚራራ ልብ አጡ፡፡በዚያንም ጊዜ መምህረ ይቅርታ ቸሩ አምላካችን ለሠቃዮቹ “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው አለ” (ሉቃ.፳፫፥፴፬)፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደለኞች ይቅርታን ያገኙ ዘንድ ይቅር በላቸው አለ፡፡ ልመናውንም ያቀረበው ወደ ባሕርይ አባቱ ነው፡፡ ከባሕርይ አባቱ ጋር ደግሞ በባሕርይ፣ በሕልውና፣ በአገዛዝ፣ በፈቃድ አንድ ናቸው፡፡ እንዲሁም የሰውን ባሕርይ ባሕርይ አድርጎ ፍጹም ሰው እንደሆነ ሲያስረዳ ነው፡፡ይህም በደለኞችን ከራሱ ጋር ያስታረቀበት የፍቅር ድምጽ ነው፡፡
አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅርበላቸው ማለቱ አባት ሆይ ብሎ የባሕርይ ልጅነቱን ከመግለጹ በተጨማሪ ይቅር በላቸው ማለቱ ጠላትን ይቅር ማለት የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ የመሆኑ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ምክንያቱም ጠላቶቻችሁን ውደዱ ብሎ ያስተማረ እርሱ ብቻ ነውና፡፡
፭ኛ. “እነሆ ልጅሽ፤ እናትህ እነኋት”፡–
“ጌታችን መድኀኒታችንን ኢየሱስም እናቱንና የሚወደውን ደቀ መዝሙሩን ቆመው ባያቸው ጊዜ እናቱን ‘አንቺ ሆይ እነሆ ልጅሽ’ አላት፡፡ ከዚህም በኋላ ደቀ መዝሙሩን ‘እናትህ እነኋት’ አለው፡፡ ከዚያችም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ተቀብሎ ወደ ቤቱ ወሰዳት” (ዮሐ.፲፱፥፳፮)፡፡ ደቀ መዝሙሩ ተብሎ የተጠቀሰው ጌታችን ይወደው የነበረ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊው ነው፡፡ ይህንንም የጻፈው እርሱ ነው (ዮሐ.፳፩፥፳፬)፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ቢሆንም ሐሙስ ማታ እረኛው ሲያዝ ከተበተኑት በጎች ጋር አብሮ አልሸሸም፡፡ በዚያች በአስጨናቂዋ ሰዓት ከጌታችን ጋር እስከ እግረ መስቀሉ ተጓዘ፡፡የክርስቶስ ፍቅር ፍርሃቱን ሁሉ አርቆለት የአይሁድን ቁጣና ዛቻ ሳይፈራ ጸንቶ በመቆሙ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለእኛ ሁሉ እርሱ በኩል ተሰጠችን፡፡ እናታችን ድንግል ቅድስት ማርያም ሁል ጊዜም ቢሆን ከእግረ መስቀሉ ሥር ለሚገኙ፣ ልባቸው ቀራንዮን ለሚያስብ ሁሉ እናት እንድትሆን እነርሱም ልጆቿ እንዲሆኑ በቅዱስ ዮሐንስ በኩል ተሰጥታናለች፡፡
በመሆኑም “እነሆ ልጅሽ፤ እናትህ እነኋት” የሚለው የመስቀሉ ቃል በመስቀል ላይ የተከፈለልንን ዋጋ አስበን በእርሱ አምነን በምግባር ታንጸን እንደ ፈቃዱ በምንኖር ክርስቲያኖችና ለድኅነታችን ምክንያት በሆነች በእመ አምላክ በቅድስት ድንግል ማርያም መካከል የእርሷ እናትነት፣ የእኛ ልጅነት የተመሠረተበት የፍቅር ቃል ነው፡፡
፮ኛ. “ተጠማሁ”፡–
“ከዚህም በኋላ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ሁሉ እንደ ተፈጸመ ባየ ጊዜ የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ‘ተጠማሁ’ አለ” (ዮሐ.፲፱፥፳፰)፡፡
ውኆችን በእፍኙ የሰፈረ፣ የባሕር አሸዋን የቆጠረ፣ ውኆችንም ጠርቶ በምድር ፊት ላይ የሚያፈሳቸው፣ የባሕር ጥልቀትንና ዳርቻን የወሰነ፣ የኤርትራን ባሕር እንደ ግድግዳ ያቆመ አምላክ “ተጠማሁ” ብሎጮኸ፡፡ (ኢሳ.፵፥፲፪፣አሞ.፱፥፮)፡፡
“የተጠማ ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ በእኔም የሚያምን መጽሐፍ እንደ ተናገረ የሕይወት ውኃ ምንጭ ከሆዱ ይፈልቃል” (ዮሐ.፯፥፴፯) በማለት እርሱ የሕይወት ውኃ እንደሆነ ተናገረ፡፡ አምላክ ሲሆን “ተጠማሁ” ብሎ መጮኹ ስለ ምንድንነው ብለን ቅዱሳት መጻሕፍትን ስንመረምር፡- አንደኛ የመከራውን ጽናት፣ ከሚነገረው በላይ መከራውን እንዳጸኑበት የሚያሳይ ሲሆን፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ እርሱ የተጠማው የሰውን መዳን ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በዚያን ወቅት እንኳ ከክፉ ሥራው ተመልሶ የሚጸጸት፣ የሚራራ፣ ንስሓ የሚገባ ሰው በማጣቱ መድኃኒት እርሱ ቀርቦ ሳለ የሰው ልጅ ባለማስተዋሉ ወደ እርሱም በፍቅር ባለመቅረቡና ባለመመለሱ ተጠማሁ አለ፡፡
፯ኛ. “ሁሉ ተፈጸመ”፡–
”ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስም ሆምጣጤውን ቀምሶ ሁሉ ተፈጸመ አለ፡፡ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን ሰጠ” (ዮሐ.፲፱፥፴)፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕተ ዐርብ በመስቀል ላይ ሳለ ‘ተፈጸመ’ ብሎ መናገሩ ብዙ ትርጉም ያለው ቃል ነው፡፡ እነርሱም፡-
በነቢያት ስለ እኔ የተነገረው ትንቢት፣ የተመሰለው ምሳሌ፣ በቅዱሳን አበው የተቆጠረው ሱባኤ፣ ጊዜው ደርሶ የአዳም ተስፋ ተፈጸመ፡፡
የሰው ልጅ በዲያብሎስ አገዛዝ በሞትና በጨለማው ሥልጣን፣ በአጋንንት ወጥመድ ታስሮ የሚኖርበት የፍዳ ዘመን አለቀ ተፈጸመ፡፡
በእግዚአብሔርና በሰው፣ በመላእክትና በሰው፣ በሰማይና በምድር መካከል ቆሞ የነበረው የጥል ግድግዳ ፈረሰ፣ የተጻፈው የዕዳ ጽሕፈት ተደመሰሰ፣ የሰው ልጅ ዕዳ በደል ተከፈለ በአምላክ የቤዛነት ሥራ ሁሉ ተፈጸመ ማለት ነው፡፡
እነዚህ ከአንድ እስከ ሰባት የጠቀስናቸው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መራራውን መከራ እየተቀበለ የተናገራቸው የመጨረሻ ቃላቶቹ ናቸው፡፡ ወደዚህ ዓለም ሰው ሆኖ የመጣበትን ዓላማ አከናውኖ ሲጨርስ በመጨረሻ “ተፈጸመ ኵሉ” በማለት ነፍሱን ከሥጋው ለየ፡፡ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶም በሲኦል ባርነት ለነበሩት አዳምና ልጆቹ ነጻነትን ሰበከላቸው፡፡ በአካለ ሥጋ ደግሞ ወደ መቃብር ወርዶ ሙስና መቃብርን አጠፋልን፡፡
የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!