ሰሙነ ሕማማት (ሰኞ)

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰሙነ ሕማማትን ከሌሎቹ የዐቢይ ጾም ሳምንታት በተለየ ሁኔታ ጌታችን መድኃኒታችን ኢያሱስ ክርስቶስ ለመከራ ተላልፎ የተሰጠበትንና አዳምና ልጆቹን ያድን ዘንድ በዕለተ ዓርብ በፈቃዱ በመስቀል ላይ መሰቀሉን በመስበክ ሕማሙንና ስቃዩን እያሰበች በጾም፣ በጸሎትና በሐዘን ታከብረዋለች፡፡ ምንባባቱ፣ የዜማ ክፍሎቹ ሁሉ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም በደል ሳይገኝበት አይሁድ በምቀኝነት ተነሣስተው ያደረሱበትን ስቃይ፣ በመስቀል ላይ እርቃኑን በቀራንዮ አደባባይ እንደ ሰቀሉት፣ ሞቱንና ወደ መቃብር መውረዱንና በሦስተኛውም ቀን ሞትን በሥልጣኑ ድል ነሥቶ መቃብር ክፈቱልኝ፣ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል በራሱ ሥልጣን ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱን፣ በትንሣኤውም ትንሣኤአችንን እንዳበሰረ የሚነገርበት ነው፡፡

በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት በሰሙነ ሕማማት ከጸሎተ ሐሙስ በስተቀር ቅዳሴ አይቀደስም፤ ስብሐተ ነግህ አይደረስም፤ ጸሎተ ፍትሐት አይጸለይም፤ ጸሎተ አስተስርዮም አይደረግም፣ ጥምቀተ ክርስትናም አይፈጸምም፡፡ እነዚህም አስቀድሞ በዕለተ ሆሣዕና ይከናወናሉ፡፡ በተጨማሪም በሰሙነ ሕማማት ምእመናን መስቀል እንደማይሳለሙት ሁሉ መጨባበጥ፤ መሳሳምና የትከሻ ሰላምታ መለዋወጥን አይፈጽሙም፡፡ ሰላምታ የማንለዋወጥበት ምክንያት አይሁድ ጌታን ለመስቀል ሰኞ እና ማክሰኞ መከሩ አልሰመረላቸውም፡፡ ምክራቸው የተፈጸመው ረቡዕ ነው፡፡ ማንኛውም ክብረ በዓል በዚህ ሳምንት ቢውል ከትንሣኤ በኋላ ይከበራል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰሙነ ሕማማት ባሉት አምስት ቀናት ማለትም ከሰኞ እስከ ዓርብ ስቅለቱ ያከናወናቸውን ሥራዎች ቅድሚያ ሰጥተን በዚህ ጽሑፋችን ከፋፍለን እንመለከታለን፡፡ 

ሰኞ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ሆሣዕና ለኢየሩሳሌም ቅርብ ወደሆኑት ወደ ደብረ ዘይትና ወደ ቤተ ፋጌ ደርሶ በተናቁትና ሮጠው ማምለጥ በማይችሉት በአህያይቱና ውርንጫይቱ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ሕዝቡ እና ሕፃናቱም ልብሳቸውን እያነጠፉ፣ የወይራና የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው “ሆሣዕና በአርያም፤ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው” እያሉ አመስግነውታል፡፡ “ከልጆችና ከሕፃናት አንደበት ምስጋናን አዘጋጀህ” ተብሎ እንደተጻፈ እያመሰገኑት ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ በዚያም ታላላቅ ተአምራትን አድርጎ፣ በቤተ መቅደስ የሚሸጡንና የሚገዙትን ሁሉ አባረረ፤ የገንዘብ ለዋጮችና ርግብ ሻጮችን መደርደሪያና ወንበር ገልብጦ “ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል ተብሎ ተጽፏል እናንተ ግን የሌባና የቀማኛ ዋሻ አደረጋችሁት” አላቸው፡፡ ትቷቸውም ወጥቶ ወደ ቢታንያ ሄዶ እንዳደረ ቅዱስ ማቴዎስ ይተርክልናል፡፡ (ማቴ. ፳፩፥፩-ፍጻሜ)

በማግሥቱም (ሰኞ) ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ከተማ ሲመለስ ተራበ፡፡ ከቅጠል በስተቀር ፍሬ ያልተገኘባትን ዕፀ በለስ አግኝቶ ፍሬ አልባ ሆና ነገር ግን ቅጠል ብቻ ሆና አግኝቷታልና “እንግዲህ ወዲህ ለዘለዓለም ፍሬ አይኑርብሽ” በማለት ረገማት፤ ወዲያም በለሲቱ ደረቀች፡፡ (ማቴ. ፳፩፥፲፰-፲፱) 

ጌታችን መድኃኒታችን ኢያሱስ ክርስቶስ አምላክ ሲሆን፣ ከሦስቱ አካላት በሥጋ ማርያም ማኅፀን በኅቱም ድንግልና ገብቶ በኅቱም ድንግልና ተወልዶ፣ በሥጋ ተገልጦ በዚህች ምድር ላይ እየተመላለሰ ሲያስተምር “የእኔስ መብል የላከኝን የአባቴን ፈቃድ አደርግ ዘንድ፤

ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” ብሎ ተናግሯል (ዮሐ. ፬፥፴፬)፡፡ ታዲያ ጌታችን ለምን ተራበ?

ቅዱስ ማቴዎስ እንደተራበ ሲገልጽ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ደግሞ ቀድሞ በትንቢቱ “እግዚአብሔር ለዘለዓለም አይራብም፤ አይጠማም፤ አይደክምም” ብሏል (ኢሳ. ፵፮፥፳፭)፡፡ ይህን እንዴት ያስታርቁታል ቢሉ፡- ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ “በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ፤ ይህም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፡፡ ሁሉም በእርሱ ሆነ፤ ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ ምንም የሆነ የለም፡፡”  ሲል ጽፏል (ዮሐ. ፩፥፩-፫)፡፡ ሰማያውያን መላእክት እንዳይራቡ አድርጎ የፈጠረ፤ እስራኤልን ገበሬ በማያርስበት፣ ዘር በሌለበት፣ ዝናብ በማይጥልበት ምድረ በዳ የመገበ፤ ድኅረ ሥጋዌ በአምስት አንጀራና በሁለት ዓሣ ከአምስት ሺሕ የሚበልጡ ሰዎችን የመገበ ጌታ “ተራበ” ተብሎ ሲነገር እጅግ ይደንቃል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው በመሆኑ አልተራበም፣ አልተጠማም አንልም፡፡ የጌታችን ረኃብ ግን የድህነት (የማጣት) አይደለም፡፡ የክርስቶስ ረኃቡ የበለስ ፍሬ ሳይሆን ከሰው ልጆች ዘንድ ሃይማኖትና የመልካም ሥነ ምግባርን ፍሬ አፍርተው አለማግኘቱን ለማጠየቅ ነው፡፡ ለዚህም “ተራበ” ተባለ፡፡ በዚህም ምክንያት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእሥራኤል (አይሁድ) የፈለገውን ባለማግኘቱ ጉባኤ አይሁድን ረግሟል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በአይሁድ ጉባኤ የነገሠውን ኃጢአት፤ በበለስ አንጻር መርገሙን ሲገልጽ “በበለስ አንጻር ኃጢአትን ረገማት” ብሏል፡፡ እስራኤልም ጌታችን የጠበቀባቸውን ፍሬ ባለማፍራታቸው ተረግመዋል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እስራኤል ከፍቅር ይልቅ እርግማን እንዳገኛቸው፤ አሕዛብ ደግሞ የቃሉን ትምህርት ሰምተው የእጁን ተአምራት አይተው ያመኑበትን የእግዚአብሔር የጸጋ ልጁ ለመሆን መብቃታቸውን መስክሯል፡፡ በተጨማሪም “አሕዛብ በእግዚአብሔር ቸርነት አበባ ሰበሰቡ፤ በአይሁድ ዘንድ ግን እሾሁ ተረፈ፤ ይኸውም የሃይማኖት ጉድለት ነው” ብሎ ተርጕሞታል፡፡ እሾኽ የእርግማን፤ አበባ የእግዚአብሔር ጸጋ ልጅነት ምሳሌ ነው፡፡

ጌታችን ወደ መቅደስ ሕይወታችን ቢመጣ ምን ያገኝ ይሆን? ፍሬ ወይስ ቅጠል? የእግዚአብሔር ቃል “ለንስሓ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤” ይለናልና እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገውን የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ አፍርተን እንገኝ ዘንድ ዘወትር መትጋት ይገባል፡፡ (ማቴ. ፫፥፰፤ ገላ. ፭፥፳፪)፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *