ራስን መግዛት
በመ/ር በትረ ማርያም አበባው(የመጻሕፍተ ብሉያትና የመጻሕፈተ መነኮሳት መምህር)
ራስን መግዛት ማለት ራስን ከክፉ ነገር መጠበቅ፣ ሰውነትን መቆጣጠር፣ ራስን ከኃጢኣት ማራቅ ማለት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በላከው መልእክቱ ራስን መግዛት የመንፈስ ፍሬ እንደሆነ ገልጧል። (ገላ. ፭፥፳፪)
ቅዱስ ጴጥሮስም በ(፪ኛ ጴጥ.፩፣፮) “በበጎነትም ዕውቀትን በዕውቀትም ራስን መግዛትን ራስንም በመግዛት መጽናትን በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችነትን መዋደድ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ” ብሎ ስለ ራስን መግዛት ተናግሯል።
ራስን መግዛት ለምን? ብለን ስንጠይቅ በዋናነት ራስን ከኃጢኣት ለመጠበቅ ነው። ኃጢኣት በሦስት መንገድ ይሠራል። ይኸውም በኀልዮ (በማሰብ)፣ በነቢብ (በመናገር) እና በገቢር (በድርጊት) ነው። ኀልዮ በመጽሐፈ መነኮሳት ትርጓሜ ላይ እንደተጻፈው ሁለት ደረጃዎች አሉት። እኒህም ነቅዐ ኀልዮ እና ቁርጽ ኀልዮ ናቸው።
ነቅዐ ኀልዮ ማለት የሰው ልጅ በአምስቱ የስሜት ሕዋሳቶቹ ማለትም (መዳሰስ፣ ማሽተት፣ ማየት፣ መስማት፣ መቅመስ) አማካኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ የሚታሰበው ቅጽበታዊ ሐሳብ ነው። ይህን በስሜት ሕዋሳታችን አማካኝነት ያሰብነውን ቅጽበታዊ ሐሳብ ደጋግመን በሕሊናችን ስናመላልሰው ደግሞ ቁርጥ ኀልዮ ይባላል። በሕሊናችን የታሰበውን ሐሳብ ስንናገረው ደግሞ ነቢብ ይባላል። ያሰብነውን ሐሳብ እና የተናገርነውን ነገር ወደ ተግባር ስናውለው ደግሞ ገቢር ይባላል። ስለዚህ በሦስቱም መንገድ ኃጢኣት ወደ ሰውነታችን እንዳይገባ ራሳችንን መግዛት አለብን ማለት ነው።
በኀልዮ (በማሰብ) የሚመጣ ኃጢኣት እንዳይጥለን ከፈለግን የስሜት ሕዋሳቶቻችንን መቆጣጠር ነው። ይህም ማኅሌታዊው ቅዱስ ያሬድ “ዐይን ይጹም ዕዝንኒ ይጹም፣ እምሰሚዐ ኅሡም፤ ዓይን ክፉ ነገር ከማየት፣ ጆሮም ክፉ ነገር ከመስማት ይከልከል” ያለው ነው። የሰው ልጅ ዓይኑን ክፉ ነገር እንዳያይ ከተቆጣጠረው፣ ጆሮውንም ክፉ ነገር እንዳይሰማ፣ እጁን ክፉ ነገር እንዳይዳስስ፣ አፉን ክፉ እንዳይናገር፣ አፍንጫውን ክፉ እንዳያሸት ከተቆጣጠረው በኀልዮ የሚመጡ ኃጢአቶችን መቀነስ ይችላል።
ክፉ የሚባለው የእግዚአብሔርን ሕግ የሚያስሽር ሁሉ ነው። አንድ ሰው ዝሙትን የሚያሳስብ ንግግር በጆሮው ከሰማ ወይም ዝሙትን የሚያሳስብ ነገር በዓይኑ ካየ ከዚያ ቀጥሎ “ነቅዐ ሀልዮ” ይከተለዋል። ይህም ወደ ቁርጥ ሀልዮ ያድጋል። (ማቴ. ፭፣፳፷)
“እኔ ግን እላችኋለሁ ሴትን ዐይቶ የተመኛት ሁሉ ፈጽሞ በልቡ አመነዘረባት” ይላል። ማመንዘር ደግሞ ከ፲ሩ ሕግጋት አንዱ የሆነውን (ዘጸ. ፳፥፳፬) “አታመንዝር” የሚለውን ሕግ አስሽሮ ወደ ሲኦል የሚመራ ነው። ስለዚህ የሰው ልጅ ፍጻሜያቸው የእግዚአብሔርን ሕግ የሚያስሽሩ ነገሮችን ከማየት፣ ከመስማት፣ ከመዳሰስ፣ ከማሽተት እና ከመቅመስ ራሱን መከልከል አለበት ማለት ነው።
በተጨማሪ ነገራተ እግዚአብሔርን በማሰብ፣ ነገረ ስቅለቱን ሁል ጊዜ በማሰብ፣ ጣዕመ መንግሥተ ሰማያትን እና ምረረ ገሐነመ እሳትን አዘውትሮ በማሰብ ከክፉ ሐሳብ እንላቀቃለን። በእርግጥ አንዳንድ ሐሳቦች ለብዙ ዘመናት ይፈትኑን ይሆናል። ነገር ግን እኛም እነዚያን ለማራቅ ተስፋ ሳንቆርጥ እስከ መጨረሻው መታገል ይገባል። የስሜት ሕዋሳቶቻችንን ከክፉ ነገር መጠበቅ ብቻ ሳይሆን በምትኩ መንፈሳዊ ነገርን ልናይባቸው፣ ልንሰማባቸው፣ ልንዳስስባቸው፣ ልንናገርባቸው ይገባል።
ዐይን ቅዱሳት ሥዕላትን፣ መንፈሳዊ መጻሕፍትን ይመልከት። “…የእግዚአብሔርን መድኃኒት እዩ” እንዲል (፪ኛዜና. ፳፣፲፯)፡፡ “ኑ የእግዚአብሔርን ሥራ እዩ” (መዝ. ፷፮፣፭)፡፡ ጆሮ የእግዚአብሔርን ቃል ይስማ። “ቃሌን ስሙ” (ዘኊ. ፲፪፣፮) እንዲል። አፋችን እውነትን ይናገር። “የእግዚአብሔርን ምሥጋናና ኃይሉን ያደረገውንም ተአምራት ተናገሩ” (መዝ. ፸፰፣፬) እንዲል።
በነቢብ (በመናገር) ከሚሠሩ ኃጢአቶች መከልከል የምንችለው ባለመናገር ነው። “ከቃልህ የተነሣ ትጸድቃለህና ከቃልህም የተነሣ ትኮነናለህና” (ማቴ. ፲፪፣፴፯) እንዲል። መጽሐፈ መነኮሳት ላይ ያለ አንድ ታሪክ አለ። ይኸውም በአንድ ወቅት ሙሴ ጸሊምን ሰዎች መጥተው ክፉ ክፉ ቃል ተናገሩት። እርሱም ምንም ሳይመልስ ዝም አለ። በኋላ ደቀ መዛሙርቱ አባታችን ያንን ሁሉ ክፉ ክፉ ቃል ስትሰደብ ምንም አልተሰማህም ወይ? ብለው ይጠይቁታል። እርሱም ሲመልስ “በእርግጥ ስሰደብ መልሰህ ስደባቸው መልሰህ ስደባቸው የሚል ስሜት መጥቶብኝ ነበር፤ ነገር ግን እንዳልናገር አፌን ተቆጣጠርኩት” ብሏቸዋል፡፡ (መጻሕፍተ መነኮሳት)፡፡
ንጽሐ ሥጋ የሚጀመረው በአርምሞ ነው። አርምሞ ማለትም ክፉን ቃል አለመናገር ማለት ነው። አንድን ነገር ከመናገራችን በፊት ነገሩን በቃለ እግዚአብሔር ሚዛንነት ለክተን እንናገር። አለበለዚያ ግን ዝም እንበል። “አቤቱ ለአፌ ጠባቂ፣ ለከንፈሮቼም ጽኑዕ መዝጊያን አኑር” (መዝ.፻፵/፻፵፩፣፫) እንዲል። ሌላውን ሰው የማያሳዝን ቃል ልንናገር ይገባል። እኛም ተናግረን የምንጠቀምበት ሰሚውም ሰምቶ የሚጠቀምበትን ነገር ልንናገር ይገባናል። እንዲህ ስናደርግ ራሳችንን ገዛን ይባላል።
በገቢር (በድርጊት) ከሚመጡ በደሎች ለመራቅ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ በመሸሽ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ዮሴፍ በጲጥፋራ ሚስት የተፈተነውን ፈተና ያመለጠው በመሸሽ ነው። (ዘፍ. ፴፱፣፯) “ከዚህ በኋላ የጲጥፋራ ሚስት በዮሴፍ ላይ ዓይኗን ጣለች። ከእኔም ጋር ተኛ አለችው” እንዲል። አስተውሉ ዮሴፍ የተጠየቀው የገቢር ኃጢአትን እንዲሠራ ነው። ነገር ግን ዮሴፍ እግዚአብሔርን አልበድልም ብሎ ሸሽቶ አምልጧል። በዚህም ምክንያት “እግዚአብሔርም ከዮሴፍ ጋር ነበረ ምሕረትንም አበዛለት” ተብሎ ተጽፎለታል። (ዘፍ. ፴፱፣፳፩)
ስለዚህ በጠቅላላው ራስን መግዛት ማለት እኛን ከእግዚአብሔር ከሚለዩን ነገሮች መከልከል፣ ኃጢኣት ወደ ሰውነታችን እንዳይገባ መቆጣጠር ነው። ስለሆነም የሰው ልጅ ሥጋዊ ፍላጎቱ ወይም ስሜቱ የሚገዛው ሳይሆን ሥጋዊ ፍላጎቱን ወይም ስሜቱን የሚገዛ መሆን አለበት። “ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባርያ ነው”።(ዮሐ.፰፣፴፬)
አስተውል ሰው ኃጢአተኛ ከሆነ የኃጢአት ባርያ ይሆናል እንጂ የራሱ ገዢ አይሆንም። “በሚሞት ሥጋችሁ ኃጢአት አይንገሥ” (ሮሜ.፮፣፲፪) እንዲል። ራሳችንን ካልገዛን በራሳችን ሌላ ኃጢአት ይነግሥብናል። ሌላው ራስን መግዛት የሚባለው ከኃጢአት መራቅ ብቻ ሳይሆን መልካም ሥራንም መሥራት ነው። “እንግዲህ በጎ ለማድረግ ዐውቆ ለማይሠራው ኃጢአት ነው” (ያዕ. ፬፣፲፯)። ይህም ማለት በጎ ትምህርትን፣ በጎ ዕውቀትን ገንዘብ አድርገን ወደ ተግባር ካልለወጥነውም ኃጢአት ይሆንብናል። አንድ ንጉሥ ወይም ገዢ የሚመሰገነው ሕዝቡን ከውጭ ወራሪ ከውጭ ጠላት በመጠበቁ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡን በመልካም አስተዳደርም በማስተዳደሩ ነው። ስለዚህ ማንኛውም የሰው ልጅ ራሱን ሲገዛ ከኃጢአት መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ጽድቅንም መሥራት ይኖርበታል።
ራስን ለመግዛት ጾም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። ሊቁ “ኀዲገ መብልእ ለዘተክህሎ፣ ሐራዊ በጸብእ ኢይኄይሎ ወንጉሥ በላእሌሁ ኢሀሎ፤ ምግብን መተው የቻለን ሰው ወታደር በጠብ አይችለውም። በእርሱም ላይ ንጉሥ የለም” ብሏል። ይህም ማለት ሰው ሲጾም ሲጸልይ በራሱ ላይ የተሾመ የራሱ ንጉሥ ይሆናል ማለት ነው። ሰው ራሱን ከገዛ ዓለምን መግዛት ይችላል። ስለዚህ ክፉ ከማሰብ፣ ክፉ ከማድረግ፣ እንዲሁም ክፉ ከመሥራት በመጠበቅ ራስንም በመግዛት ለእግዚአብሔር የምንመችና እንደ ቃሉም የምንመላለስ ሆነን መገኘት ከእኛ ኦርቶዶክሳውያን ይጠበቃል፡፡
ራስን በመግዛት ከክፉ ተጠብቀን የመንግሥቱ ወራሾች ያደርገን ዘንድ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ አሜን፡፡
እግዚአብሔር ይስጥልን
አሜን ተሻለ እናመሰግናለን።
ለሌሎች እንዲደርስ ያድርጉልን።
ቃለ ሕይወት ያሰማልን
አሜን በላይ እናመሰግናለን።
ሌሎች እንዲያዩት ያጋሩልን።