ረቡዕ
ከመምህር ተሾመ ግዛው
እያንዳንዱ የሰሙነ ሕማማት ዕለታት ስያሜ እንዳላቸው ዕለተ ረቡዕም ራሱን የቸለ ምሥጢራዊና ታሪካዊ ትርጒም አለው፡፡ ይህም እንደሚከተለው በዝርዝርእንመለከታለን።
የምክር ቀን (ምክረ አይሁድ)
አይሁድ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስሰ ክርስቶስን የሚይዙበትን መንገድ ይፈልጉ ነበር፤ በመካከላቸው ምንም ዓይነት ልዩነት እንኳን ቢኖር ለኃጢአት ሥራ ግን ተባበሩ፡፡ ፰ት ለተለያየ አላማ የተቋቋመ ማኅበር (ስምንቱ ቤተ አይሁድ) ፦ ሊቃነ ካህናት፣ መገብተ ምኲራብ፣ ኃጥኣን መጸብሓን፣ ጸሓፍት ፈሪሳውያን፣ ሰዱቃውያን፣ ረበናት (መጽሓፈ ሰዓታት ንባቡና ትርጓሜው ሮዳስ ታደሰ ገጽ ፬፻፸፭)
ረበናት የሕዝቡን ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ዕሤት ይጠብቃሉ ተብለው የተሾሙ ነበሩ፤ ነገር ግን ሕዝቡን ከመጥቀም ይልቅ የሚጎዳ ተግባር ላይ ተጠመዱ፤ ንጉስ ክርሰቶስን ለመስቀል በእለተ ረቡዕ ተማከሩ፤ ደሙም በላያቸው ላይ እንዲሆን በራሳቸው ላይ የሞት ፍርድን ፈረዱ። ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እንደ ገለጸው ‹‹ማኀበራነ አይሁድ ተመድበሉ ለሰቂለ አምላክ ተማሐሉ፣ የአይሁድ ማኅበራት ተሰባሰቡ አምላክን ለመስቀል ተማማሉ›› ይች ዕለት የአዳም የመዳን ተስፋ፣ የነቢያት ትንቢታቸው ፍጻሜ እንዲያገኝ በቤተ አይሁድ ምክር የጸናበት እንዲሁም ለጨለማ አበጋዞች የኀዘን ዳራ የሰፋበት ነው፡፡
በዚህ ዕለት ጌታ ለሞት ተላልፎ እንዲሰጥ አይሁድ መክረው የተነሱበት አንዲሁም አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእጃቸው የሚወድቅበት መንገድ ከይሁዳ ጋር ዘዴ የዘየዱበት ዕለት በመሆኑ የቤተ ክርስቲያነችን ሊቃውንት ዕለቱ ከበዓለ ኀምሳ በስተቀር ዐመቱን ሙሉ በጾም እንዲታሰብ ሠርዓት ሠርተዋል።
የንስሓ ዕለት
ንስሓ ለሰው ልጅ ከበድል የሚነጻበት የነፍስ ሳሙና ነው፡፡ ቅዱሰ ኤፍሬም ሰለንስሓ እንዲህ ይለናል ‹‹ጌታ ሆይ ወርቅ ትሰጠኝ ዘንድ አለምንህም ወርቅ ክፉዎች የሚፈልጉት ንዋይ ነውና፡፡ ሀብትና ንብረትም አልለምንህም፤ እነርሱም ድኅነትን የሚያስገኙ አይደሉም፡፡ ይቅርታን ማግኘት ከወርቅ ይልቃል፡፡››
ጌታቾን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሠራቸው ድንቅ ሥራዎች ቅዱስ መጽሐፍ ማርያም ባለ ሽቶዋ በሚንቋትና ኃጢአተኛነቷን በየሄዱበት በሚመሰክሩባት ሴት ይቅርታን ያደረገበት ቀን ነው፡፡
ከቀናት ሁሉ ቅዱስ ተብለው የሚጠሩ ዕለታት ነፍስና ሥጋን የሚያነጹ ልዩ ዕለታቶች አሉ፡፡ ማርያም ለንስሓ የተነሳችበት ዕለት ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ በኀዘንና በትካዜ የውስጧን ማንነት የሚያሳያትን በዓይነ ኅሊና ፊት እንጅ ለኃጢአትና ለበደል በሚያቆማት መስታወት ፊት ብቻ አልነበርም፡፡
ከዓይነ ሥጋ ዕይታ በመውጣት በዓይነ ኅሊና የታያት የክብር ዙፋን በመናፈቅ ውድና ክቡር የሆነ ሽቱ ፍለጋ ነበር የወጣችው፤ በወጣችበት ጊዜም ቀላል የማይባል ፈተና ገጥሟት ነበር፡፡ እርሱን ተቋቍማ ነገሥታት ይቀቡት የነበረውን እጅግ የከበረ ልዩ ሽቱ ፍለጋ ተንከራተተች፤ ፈልጋም ባገኘች ጊዜ በውድ ገንዘብ ገዛችው፡፡
የሽቱ ታሪክ በቤተ ክርስቲያናችን እንዲህ ይተረካል፡-
ሰባ ሰገል ለሕጻኑ የገበሩት ከጥንት አባቶቻቸው የመጣ ታሪክ እንዳለው ሁሉ ሽቱውም ልዩ ታሪክ አለው፡፡ ዳዊትና ሰሎሞን ይቀቡት የነበረዉ ውድ ሽቱ ሳይሆን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በወርኀ ስደቷ ጥጦስና ዳክርስ የተባሉ ሽፍቶች ነበሩ፤ እነዚህ ሽፍቶች የሕጻኑን ልብስና ጨማ ከዘረፉ በኋላ ፈያታዊ ዘየማን ሕጻኑን በመታቀፍ ሸኝቶት ነበር፤ የሕጻኑ ወዝም በሽፍታው ልብስ ይቀራል፤ ልዩ ጠረንም ነበረው፤ እንድታጥብለትም ለእናቱ ሲሰጣት ሽታው እስካሁን ከምታውቀው ሽቱ ሁሉ የተለየና በአንድ ተራ ሰው ቤት ሊገኝ የማገባው መሆኑን አውቃ ለነጋዴ ሸጠችው፤ ያ ነጋዴም የሚገዛው ሰው እስኪያገኝ ድረስ በልዩ ቦታ አስቀምጦት ነበር፤ ማርያም እንተ ዕፍረት በመጣች ጊዜ በውድ ዋጋ ሸጠላት፡፡
ማርያም እንተ ዕፍረት ይህንን የገዛችው ሽቱ ለክርሰቶስ እንዲገባ ዐውቃ የስምዖንን ዛቻና ግፊት ሳይበግራት በጽናት ተቋቍማ ወደ ክርስቶስ ቀርባ በፊቱ አቀረበችለት፡፡ በዐይኖቿም ዕንባ አፍሳ እግሮቹን አጠበችው፤ በዕንባዋ ያጠበችው እግሮቹም በጨርቅ ሳይሆን በውብ ፀጉሮቿ ነው እግሮቹን ያበሰችው፡፡
ያን ጊዜ ማርያም እንተ ዕፍረት በጌታ ዘንድ ከእንባዋ የተነሳ ይቅርታን አገኘች፤ ከበደል እስራትም ተፈታች፤ ከ፴፮ቱ ቅዱሳት አንስትም ተቆጠረች፤ በቅዱሱ ዕለትም ቅድስናን ተቀበለች፡፡ (ሉቃ. ፯፥፴፯-፶)
ማርያም እንተ ዕፍረት እግዚብሔር የሰጣትን ውበትና መልክ ለቅድስና ሳይሆን ለኃጢአት አውላው ነበርና፤ ብዙዎቹ በእርሷ ውበት ተማርከው ገንዘባቸውን ጨረሱ፤ ትዳራቸውን አፈረሱ፤ ክቡር የሆነውንም የክርስቶስ ቤተ መቅደስ አረከሱ፤ በኃጢአት ዓለም እራሳቸውን አዋረዱ፤ ማርያም ግን ከዚህ ሁሉ ጥፋትና በደል በኋላ ወደ ቀልቧ ተመለሰች፤ ሁሉም ከንቱ መሆኑና በሚያልፈው ዓለም የማያልፈውን ክብር መግዛት ፈለገች፡፡
በማርያም እንተ ዕፍረት የሚከተሉትን የሕይወት ለውጥ እንመለከታለን፡-
ለኃጢአት ትጠቀመው የነበረውን መስታወት ለጽድቅ ማያ አደረገቸው፤
ለዝሙት ይውሉ የነበሩ ልብሶቿ ለክብር ሆኑ፤
ለዝሙት ይዘረጉ የነበሩ እጆች ለጽድቅ ተዘረጉ፤
ለዝሙት ይንበረከኩ የነበሩ እግሮቿ ለስግደት ተንበረከኩ፤
የጎልማሳ ቀልብን ሰብረው በመንገድ የሚያስቀሩ ዓይኖቿ የንስሓ እንባን አነቡ፤
ወደ ኃጢአት የእራት ግብዣ የሚገሰግሱ እግሮቿ ለክብር እንግድነት በቅድስና የእራት ግብዣ ቦታ ገሰገሱ፤
የጎልማሶች እጅ መንሻ በምትቀበልበት እጆቿ የተለየ ሽቱ ለነገሥታት እንደሚገባው ንጉሠ ነገሥት ለሆነው ለክርስቶስ አቀረበች፡፡
ይህች ዕለት ለእርሷ የተቀደሰ ሐሳብን ያሰበችበት፣ ያባከነችውን ጊዜ የምትክስበት፣ ለኃጢአት መኳኳል ትጠቀምበት የነበረውን ጊዜ ለጽድቅ ያደረገችበት ቅዱስ ዕለት፤ ከዓለም ሁካታና ጩኸት የተለየችበት ቅድስት እለት ናት፡፡
ዛሬ እኛ ከነበርንበት ውደቀት ለመውጣት ብዙ ምክንያች እንደረድራለን ያለንበትን ቦታና በዙሪያችን ያሉ ሰዎችን ከውደቀታችንም ላለመነሳት ምክንያት እናደርጋቸዋለን፡፡ ከዚህች ብርቱና ቆራጥ ሴት የምንማረው ለበጎ ተግባር ቁርጥ ውሳኔ መወሰንና ፈጥኖ በተግባር ማዋልን ነው። ያኔ ታላቅ የሕይወት ለውጥ በኑሯችን ይከሰታል።
ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!