ሥርዓተ ሰሙነ ሕማማት

በሊቀ ጠበብት ሐረገወይን አገዘ

ክፍል ሁለት

ጸሎተ ሐሙስ፡-

በብሉይ ኪዳን የቂጣ በዓል የሚለውን ትርጉም ከመሰጠቱ በተጨማሪ ጌታችን ምሥጢረ ቁርባንን ከምሥጢረ ጸሎት ጋር አዋሕዶ የገለጠበት ዕለት ስለሆነ ታላቅ የምሥጢር ቀን ነው፡፡

በዚህ ዕለት ስግደቱ፣ ጸሎቱ፣ ምንባባቱ እንደተለመደው ይከናወናሉ፡፡ ለየት ያለው ሥርዓት መንበሩ/ታቦት/ ጥቁር ልብስ ይለብሳል፣ ጸሎተ ዕጣን ይጸለያል፣ ቤተ ክርስቲያኑ በማዕጠንት ይታጠናል፡፡

በዘጠኝ ሰዓት ዲያቆኑ ሁለት ኩስኩስቶችን ውኃ ሞልቶ ያቀርባል፣ አንዱ ለእግር፣ አንዱ ለእጅ መታጠቢያ፡፡ ጸሎተ አኰቴት የተባለ የጸሎት ዓይነት ተጸልዮ፣ ወንጌል ተነቦ ውኃው በካህኑ /በሊቀ ጳጳሱ/ እጅ ተባርኮ የሕጽበት እግር ሥርዓት ከካህናት እስከ ምእመናን፣ ከወንዶች እስከ ሴቶች በካህኑ አስተናጋጅነት ይከናወናል፡፡

ሥርዓተ ኅጽበቱ የሚከናወነውም በውኃ ብቻ ሳይሆን የወይራና የወይን ቅጠልንም ለሥርዓቱ ማስፈጸሚያነት እንጠቀምባቸዋለን፡፡ ምሥጢሩም የሚከተለውን ይመስላል፡፡

ወይራ ጽኑዕ ነው፡፡ ክርስቶስ ጽኑዕ መከራ መቀበሉን ከማስረዳቱ በተጨማሪ እኛም /የሚያጥበውና የሚታጠበው ክርስቲያን/ መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነን ለማለት ነው፡፡ የወይኑ ቅጠል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወይን የተመሰለ ደሙን አፍስሶ ለምእመናን ሕይወት መጠጥ ይሆናቸው ዘንድ መስጠቱን ለማዘከር ነው፡፡ (ማቴ.፳፮፥፳፮)፡፡

ይህም ሥርዓት ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ያሳየውን የተግባር ትምህርት ለምእመናን ለማሳየት ነው፡፡ (ዮሐ.፲፫፥፲፬)፡፡ሊቃውንትም በቀኝና በግራ “ሐዋሪያቲሁ ከበበ እግረ አርዳኢሁ ሐፀበ” እያሉ ይዘምራሉ፡፡ ይህ ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ሥርዓተ ቅዳሴው ተከናውኖ ቅዱስ ሥጋውን፣ ክቡር ደሙን ምእመናን ይቀበላሉ፡፡

የጸሎተ ሐሙስ ቅዳሴ፡-

ቅዳሴው የሚከናወነው በተመጠነ ድምጽ ነው፡፡ ደወሉ የጸናጽል ድምጽ ነው በቀስታ ስለሚጮህ ነው፡፡ የድምጽ ማጉያ አይጠቀሙም፤ ምክንያቱም ዲያቆኑና ካህኑ ዜማውን በቀስታ የሚሉት ይሁዳ በምሥጢር ጌታችንን ማስያዙን ለመጠቆም ሲሆን በሌላ በኩል የዘመነ ብሉይ ጸሎት ዋጋው ምድራዊ እንደነበር ለማስታወስ ነው።

በመቀጠል ክቡር ይእቲ፣ ዕጣነ ሞገር ዝማሬ የተባሉ የድጓ ክፍሎች ተዘምረው አገልግሎቱ ይጠናቀቃል፡፡ ሕዝቡም ያለ ኑዛዜና ቡራኬ ይሰናበታሉ፡፡

ዕለተ ዐርብ ነግህ፡-

ዕለተ ዐርብ የአዳምን ነጻነት ለመመለስ የአዳምን ዕዳ በደል አምላካችን የተሸከመበት ዕለት፣ የኀዘን ዕለት፣ የድኅነት ዕለትም ነው፡፡ በዚሁ ዕለት ሁሉም ነገር እንደተለመደው ይከናወናል፡፡ መሪው እዝል ይመራል፣ ሕዝቡ ይከተላል፣ አራቱ ወንጌላት ይነበባሉ፡፡ በየመሐሉ “ወጸቢሆ ተማከሩ ሊቃነ ካህናት፤ ሲነጋም ሊቃነ ካህናት ተማከሩ” የሚለው ዜማ በመሪ፣ በተመሪና በሕዝብ ተሰጥዎ ይከናወናል፡፡  ምንባቡም፣ ስግደቱም፣ ድጓውም እንደአለፈው ይቀጥላል።

በሦስት ሰዓት፡-

ሥዕለ ስቅለቱ፣ መስቀሉ፣ ወንጌሉ፣ መብራቱ፣ ጽንሐሑ በመቅደሱ በር ላይ ይዘጋጃል፤ ዲያቆኑ በቃለ ማኅዘኒ በሚያሳዝን ቃል ግፍኦሙ እግዚኦ ለእለ ይገፍኡኒ ይላል፡፡ ካህናቱና ምእመናኑም በዜማ እየተቀበሉ ይሰግዳሉ፡፡ ምስባክ ተሰብኮ አራቱ ወንጌላት ይነበባሉ፡፡ በየመሐሉ የሰዓቱ ድጓ ይቃኛል፡፡

ስድስት ሰዓት፡-

የዕለቱ መሪ እዝል ይመራል፣ ሦስቱ ካህናት ጽንሐሑን ይዘው ከርቤ እያጠኑ ዲያቆናት መብራት እያበሩ ለመስቀልከ ንስግድ እያሉ ያዜማሉ፣ ምእመናንም ዜማውን እየተቀበሉ ይሰግዳሉ፡፡ ከዚያም ዲያቆኑ ቀነውኒ እደውየ ወእገርየ የሚለውን ምስባክ ሰብኮ አራቱ ወንጌላት ይነበባሉ፣ በየመሐሉ ድጓው ይዜማል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ምእመናን ይቀመጣሉ፣ ሦስቱ ካህናት ጥቁር ልብስ ለብሰው በሚያሳዝን ዜማ አምንስቲቲ ሙኪርያ አንቲ ፈሲልያሱ፣ ጌታዬ ሆይ ስለ እኔ ሞትህ ወዮ እኔ ልሙትልህ እያሉ ሦስት ጊዜ ያዜማሉ፡፡

ሕዝብ ይቀበላል፣ በዚያው አያይዘው ተዘከረነ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ እያሉ በዜማ ይጸልያሉ ሕዝቡ ይቆማል ሥርዓተ ስግደቱም ይከናወናል፡፡

በዘጠኝ ሰዓት፡-

ሌላው እንደተለመደው ሆኖ ኦ ዘጥዕመ ሞተ በሥጋ ሦስት ጊዜ ካህናቱ በዜማ ይሉታል፣ ምእመናኑም ይቀበላሉ፡፡ ምስባክ ተሰብኮ አራቱ ወንጌላት ይነበባሉ፣ ስግደት እንደተለመደው ነው፡፡ በሦስት ሰዓት፣ በስድስት ሰዓት፣ በዘጠኝ ሰዓት፣ ወንጌላቱ ተነበው እንዳለቁ ለምእመናን ትምህርት ወንጌል ይሰጣል፡፡ ይህ ግን እንደ ቋሚ ሥርዓት ሳይሆን እንደ ሁኔታው አመቺነት ነው፡፡

አሥራ አንድ ሰዓት፡-

ካህናት በአራቱ ማዕዘን ቁመው አራት መቶ እግዚኦታ ያደርሳሉ፣ ዕለቱን የሚመለከቱ መዝሙራት ተመርጠው ይነበባሉ፡፡ ንሴብሖ እየተባለ ቤተ መቅደሱን በመዞር በከበሮ በጸናጽል በሕማሙ ያዳነን እግዚአብሔር ይመሰገናል፡፡ ዑደት የሚደረገው ሥነ ስቅለቱን በመያዝ ነው፡፡ ምእመናን በሰሙነ ሕማማት የሠሩትን ኃጠአት እየተናዘዙ በካህናት አባቶች ንስሓ ይቀበላሉ፣ በወይራ ቅጠልም ቸብ ቸብ ይደረጋሉ፤ የመከራው ተሳታፊዎች መሆናቸውን ለመግለጥ ነው፡፡ ወይራ ጽኑዕ ነው፣ የተቀበልከው መከራም ጽኑዕ ነው እኛም ይህን መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነን ለማለት ነው፡፡ በታዘዙት መሠረትም ስግደታቸውን ያጠናቅቃሉ፡፡

ከዚያ በኋላ በካህኑ ኑዛዜ ምእመናን ወደ ቤታቸው ይሰናበታሉ፡፡ መስቀል መሳለም አሁንም የለም፣ የቻለ ከሐሙስ ጀምሮ አሊያም ከዐርብ ማታ ጀምሮ እስከ ዕለተ ትንሣኤው ድረስ ያከፍላል/ይጾማል/፡፡ የተጀመረውም በዕለተ ስቅለቱ በሐዋርያትና በእመቤታችን እንደሆነ አበው ያስተምራሉ፡፡

ቀዳም ሥዑር፡-

የማትጾመዋ ቅዳሜ ስለምትጾም “ሥዑር/የተሻረች/ ትባላለች፣ በዓል መሻርን ግን አያመለክትም፡፡ ቀዳም ሥዑር በጾም ምክንያት የተሻረችው ቀዳሚት ሰንበት በሰንበት ሌሊት ሥርዓቱ የሚጀምረው በመኀልየ ሰሎሞን ምንባብ ነው፡፡ ማኅሌቱም እዝሉ እየተቃኘ፣ እየተመለጠነ፣ እየተዘመመ፣ እየተመረገደና እየተጸፋ ያድራል፡፡ ጠዋት አቡን መሥዋዕት ውዳሴ ማርያም ዜማ ተደርሶ ወለመልአከ ሕይወትሰ ሰቀልዎ በሚለው ሰላምታ ይጠናቀቃል፡፡ ገብረ ሰላም በመስቀሉ እየተባለ እየተዘመረ ቄጤማውም ቤተ መቅደሱን ዞሮ በካህኑ ተባርኮ ለምእመናን ይታደላል፡፡

የቄጠማው አመጣጥና ምሥጢርም ከአባታችን ከኖኅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ምድር በማየ አይኅ /በጥፋት ውኃ/ በጠፋችበት ወቅት የኖኅ ታማኝ መልእክተኛ ርግብ የውኃውን መጉደል ያበሰረችው ቄጠማ ይዛ በመግባት ነው፡፡

ዛሬም ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች የኃጠአት ውኃ ጎደለ፣ የኃጠአት ውኃ ጠፋ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻነት ተሰበከ፣ ታወጀ በማለት ካህናት ቄጠማ ይዘው ምእመናንን ያበስሩበታል፡፡ በአጠቃላይ ሥርዓተ ሕማማት ብለው የተለየ ሥርዓት አውጥተው አባቶቻችን ተግተው ያቆዩልንን ሥርዓተ መላእክት ልንጠብቀውም ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *