ሥርዓተ ሰሙነ ሕማማት

ከሊቀ ጠበብት ሐረገወይን አገዘ

ሥርዓት ምንድነው?

“ወንድሞች ሆይ ከእኛ የተቀበለው ወግ ሳይሆን ያለ ሥርዓት ከሚሔድ ወንድም ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን” (፪ኛ ተሰ.፫፥፮)፡፡

ሥርዓት የሥነ ፍጥረት ሕይወት ምሕዋር፣ መቆጣጠሪያ መሣሪያ ነው፡፡ የመዓልቱ በሌሊት የሌሊቱ በመዓልት በመሠልጠን ሥርዓተ ዑደትን እንዳይጥስና የመዓልቱ በመዓልት፣ የሌሊቱ በሌሊት እየተመላለሰ ዕለታዊ ግብሩን እንዲያከናውን ማንኛውንም ፍጡር ፈጣሪው በሥርዓት አሰማርቶታል፡፡(መዝ.፩፻፳፭፥፲፱-፳፬)፡፡

በተለይ መንፈሳውያን ልዑካን መንፈሳዊውን ተልእኮ ያለ ሥርዓትና ሕግ ማካሔድ እንደማይችሉና እንደማይገባም ሐዋርያው ሲያስተምር “ያለ ሥርዓት ከሚሔድ ወንድም ተለዩ” አለ፡፡

ስለሆነም በሰሙነ ሕማማት የሚከናወኑ ሃይማኖታዊ እሴቶች ከዚህ ኃይለ ትምህርት የተገኙ መሆናቸውን እያሰብን በሰሙነ ሕማማት የሚከናወኑ የሕማማት ሥርዓቶችን ቀጥለን እንመለከታለን፡፡

ሰሙነ ሕማማት፡-

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከዕለተ ትንሣኤ በፊት ያለውን ሳምንት ሰሙነ ሕማማት በማለት ታከብረዋለች፡፡ የዚህ ስያሜ መነሻም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መከራው፣ ሕማሙና ሞቱ የሚዘከርበት፣ ከአዳም እስከ ክርስቶስ የነበረው የዓመተ ፍዳ የዓመተ ኩነኔ ወቅትም የሚታሰብበት ስለሆነ ሰሙነ ሕማማት ተብሏል፡፡ የዚህ ጾም መነሻም በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ ተደንግጓል፡፡ ጥንታዊ ቀዳማዊ መሆኑም ይታወቃል፡፡

በሕማማት የማይፈቀዱ፡-

በዚህ በሰሙነ ሕማማት ሳምንት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለየት ያለ የአገልግሎት ሥርዓት ሠርታለች፡፡ ከጸሎተ ሐሙስ በቀር ቅዳሴ አይቀደስም፣ የዘወትር የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት የሆነው ጥምቀተ ክርስትና፣ ሥርዓተ ፍትሐት፣ ሥርዓተ ማሕሌት፣ ሥርዓተ ተክሊልና ሌሎችም የተለመዱ አገልግሎቶች አይካሔዱም፡፡ በመስቀል መባረክ፣ ኑዛዜ መስጠትና መቀበል፣ እግዚአብሔር ይፍታህ ማለት የለም፡፡ በአጠቃላይ ከዓመት እስከ ዓመት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አማካይነት ለምእመናን ይሰጡ የነበሩ መንፈሳውያት አገልግሎቶች አቁመው በሌላ ወቅታዊ ማለትም የጌታችን ሕማሙን፣ መከራውን፣ መከሰሱን፣ መያዙን፣ ልብሱን መገፈፉን፣ በጲላጦስ ዐደባባይ መቆሙን፣ መስቀል ላይ መዋሉን፣ ሐሞት መጠጣቱን እና ሌሎችም ለኃጢአተኛው የሰው ልጅ ሲባል የተከፈለውን ዕዳ በሚያስታውሱ አገልግሎቶች ይተካሉ፡፡

እነዚህንም ሥርዓታዊና ምሥጢራዊ የሰሙነ ሕማማት አገልግሎቶች ከዕለተ ሰኑይ እስከ ቀዳም ሥዑር ድረስ እንዴት እንደሚከናወኑ በአጭር በአጭሩ እንመለከታለን፡-

ዕለተ ሰኑይ/ሰኞ በነግህ፡-

ከሁሉም በፊት የዕለቱ ተረኛ አገልጋይ ቃጭል እየመታ ሦስት ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑን ይዞራል፡፡ የሰባቱ ቀን ውዳሴ ማርያም፣ አንቀጸ ብርሃን፣ መዝሙረ ዳዊት በሙሉ ይጸለያል፡፡ በዕለቱ ተረኛ መምህር/መሪ ጌታ የዕለቱ ድጓ ይቃኛል፡፡ ድጓው ከዐራቱ ወንጌላት ምንባብ ጋር እንዲስማማ ሆኖ ነው የሚቃኘው፡፡ ድጓውን እየተቀባበሉ እያዜሙ ይሰግዳሉ፡፡ የድጓው መሪ መምህር ሰኞ በቀኝ ከሆነ ማክሰኞ በግራ በኩል ባለው መምህር ይመራል፡፡ እንዲህ እየተዘዋወረ ይሰነብታል፡፡ ድጓው ሦስት ጊዜ እየተመላለሰ ከተዘለቀ በኋላ፡-

      ለከ ኀይል ክብር ወስብሐት

      ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም

       አማኑኤል አምላኪየ ለከ ኀይል

       ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እከ ለዓለመ ዓለም

       ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ ለከ ኀይል

       ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም

      ኀይልየ ወጸወይንየ ውእቱ እግእዚየ

       እስመ ኮንከኒ ረዳኢየ እብል በአኮቴት

እየተባለ በቀኝ በኩል ስድስት፣ በግራ በኩል ስድስት ጊዜ እየተዜመ ይሰገዳል፡፡ በድምሩ ፲፪ ጊዜ ማለት ነው፡፡ በዚያው ልክ አቡነ ዘበሰማያት በዜማ/በንባብ/ ይደገማል፡፡ ከዚያ በመቀጠልም፡-

       ለአምላክ ይደሉ ክብር ወስብሐተ ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም

       ለሥሉስ ይደሉ ክብር ወስብሐተ ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም

      ለእዘዙ ይደሉ ክብር ወስብሐተ ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም

      ለመንግሥቱ፣ ለሥልጣኑ፣ ለምኩናኑ፣ ለኢየሱስ፣ ለክርስቶስ፣ ለሕማሙ ይደሉ

እያሉ በቀኝ በግራ እየተቀባበሉ ይሰግዳሉ፡፡ በመቀጠል የነግሁ ምንባብ መነበብ ይጀምራል፡፡ በመጨረሻም ተአምረ ማርያምና ተአምረ ኢየሱስ ይነበባሉ፡፡ ከዚያ ከዳዊት መዝሙር ምስባክ ተሰብኮ የሰዓቱ ወንጌል ከተነበበ በኋላ ጸልዩ በእንተ  ጽንዓ ዛቲ የተባለው በካህኑ ሲነበብ ምእመናንም አቤቱ ይቅር በለን እያሉ በመስገድ ይጸልያሉ፡፡

ከዚያም ሁለተኛው ሥርዓተ ስግደት ይጀመራል፡፡ ዜማው የሚጀምረው አሁንም በቀኝ በግራ በመቀባበል ነው፡፡ አንዱ ይመራል፣ ሌላው ይቀበላል፡፡ እንዲህ በማለት፡-

      ኪርያላይሶን/፭ ጊዜ/በመሪ በኩል

      ኪርያላይሶን /፪ ጊዜ/ ዕብኖዲ ናይን በተመሪ በኩል

      ኪርያላይሶን ታኦስ ናይን

      ኪርያላይሶን ማስያስ ናይን

      ኪርያላይሶን ኢየሱስ ናይን

      ኪርያላይሶን ክርስቶስ ናይን

     ኪርያላይሶን አማኑኤል ናይን

     ኪርያላይሶን ትስቡጣ ናይን

በዚሁ መልኩ አንድ ጊዜ ከተዘለቀ በኋላ እንደገና ይደገማል፡፡ በመጨረሻም በቀኝ በግራ በማስተዛዘል አርባ እንድ ጊዜ እየተዜመ ይሰገዳል፡፡ ከላይ የተገለጹት የጌታችን ኅቡአት ስሞች ናቸው፡፡ ኪርያላይሶን ማለት አቤቱ ይቅር በለን ማለት ነው፡፡

በመቀጠል መልክአ ሕማማት በሊቃውንቱ ይዜማል፡፡ ከዚያም ካህኑ ፍትሐት ዘወልድ፣ ጸሎተ ቡራኬ፣ ወዕቀቦሙ፣ አ ሥሉስ ቅዱስ፣ ኦ ማኅበራኒሁ ለክርስቶስ፣ ነዋ በግዑ የተሰኙ ምንባባትን እያፈራረቁ ያነባሉ፡፡ ካህኑም በጸሎታቸው ፍጻሜ ፵፩ ጊዜ ኪራላይሶን በሉ ብለው መልእክት ያስተላልፋሉ፡፡ ሕዝቡም መልእክቱን ተቀብሎ ይጸልያል፡፡ ዲያቆኑም “ሑሩ በሰላም እግዚአብሔር የሀሉ ምስሌክሙ፣ ንዑ ወተጋብኡ ውስተ ቤተ ክርስቲያን በጊዜ ሠለስቱ ሰዓት ብሎ ያሰናብታል፡፡

አሁን የተመለከትነው ሥርዓት ሰኞ በነግህ/በጥዋት/ የሚከናወን ነው፡፡ በ፫፣ በ፮፣ በ፱፣ በ፲፩ ሰዓት የሚከናወነው ሥርዓትም አሁን በተመለከትነው መሠረት ነው፡፡ የሚለያዩት ምንባባቱ ብቻ ናቸው፡፡ የሰሙነ ሕማማት ዜማም ከሰኞ እስከ ረቡዕ ግእዝ፣ ሐሙስ አራራይ፣ ዐርብና ቅዳሜ እዝል ነው፡፡ አሁን በተመለከትነው መሠረት ሰኞ፣ ማክሰኛ፣ ረቡዕ ከምንባባቸው በቀር ከላይ በተመለከትነው አኳኋን ሥርዓታቸው ይፈጸማል፡፡

ይቆየን፡፡

ምንጭ፡- ከስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፣ ከመጋቢት ፳-፳፬ ቀን ፳፻፪ ዓ.ም

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *