“ሞት በጥር፤በነሐሴ መቃብር”

ሞት በጥር፤ በነሐሴ መቃብር”

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በ፷፬ ዓመቷ ጥር ፳፩ ቀን ፵፱ ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም ማረፏን ነገረ ማርያም ያስረዳል፡፡ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ማረፍን የተመለከቱት ቅዱሳን ሐዋርያትም ሊቀብሯት ወደ ጌቴሴማኒ ይዘዋት ሲሔዱ አይሁድ “እንደ ልጇ ተነሣች፤ ዐረገች እያሉ እንዳያውኩን በእሳት እናቃጥላት” ብለው በክፋት ተነሣሡ፡፡ ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊም አጎበሩን ይዞ ሊያወርዳት ሲል የእግዚአብሔር መልአክ ሁለት እጆቹን ቀሰፈው፡፡ የአይሁድን ክፋት የተመለከተው አምላካችን ቅዱስ እግዚአብሔር እመቤታችንን ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስን አስከትሎ በደመና ነጥቆ በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጣት፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያትም እመቤታችን ያለችበት ቦታ እንዲገለጥላቸው ባረፈች በስምንተኛው ወር ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ገብተው እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ጀመሩ፡፡ ከዚህ ላይ “ስምንት ወር ሙሉ ምን ይዘው ቆይተው ነሐሴ ላይ ሱባዔ ገቡ?” የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ከስብከተ ወንጌል፣ ከጾም፣ ከጸሎት፣ ከገቢረ ተአምራት፣ ተለይተው እንደማያውቁ መንፈሳዊ ሕይወታቸው ምስክር ነው፡፡

ከፊታቸው የዐቢይ ጾም፣ ከዚያም በዓለ ሃምሳ፣ ቀጥሎም የአገልግሎታቸው መጀመሪያ የሆነው የሐዋርያት ጾም ስለሚከተል ከሰው ተለይተው ሱባዔ ገብተው ጾም ጸሎት የጀመሩት ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምሮ ነው፡፡ ለሁለት ሱባኤ በጾም ጸሎት ከቆዩ በኋላ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ሰምቶ ነሐሴ ፲፬ ቀን የእመቤታችንን ሥጋ ሰጥቷቸው በክብር ገንዘው በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል፡፡ እሷም እንደ ልጇ እንደ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታለች፡፡ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ እንደ ልጇ ትንሣኤ” ያሰኘውም ይህ ታሪክ ነው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ሲሰብክ ቆይቶ ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ወደ ሰማይ ስታርግ አገኛት፡፡ በዚህ ጊዜ “ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ፤ ዛሬ ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁን?” ብሎ ትንሣኤዋን ባለማየቱ ኀዘን ስለ ተሰማው ከደመናው ወደ መሬት ይወድቅ ዘንድ ወደደ፡፡ እመቤታችንም “አይዞህ አትዘን፤ ባልንጀሮችህ ሐዋርያት ያላዩትን ትንሣኤዬን አንተ አይተሃል” ብላ ከሙታን ተለይታ መነሣቷንና ማረጓን እንዲነግራቸው ካዘዘችው በኋላ የተገነዘችበትን ሰበን ሰጠችው፡፡

ሐዋርያው ቶማስም ትእዛዟን ተቀብሎ ወደ ሐዋርያት በመሄድ ምንም እንዳልሰማ እንዳላየ መስሎ “የእመቤታችን ነገር እንደምን ሆነ?” ሲል ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም “ሥጋዋን አግኝተን ቀበርናት” አሉት፡፡ እርሱም “ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንዴት ይሆናል?” አላቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ከዚህ በፊት የክርስቶስን ትንሣኤ መጠራጠሩን ጠቅሶ እየገሠፀ ስለ እመቤታችን መቀበር እነርሱ የሚነግሩትን ሁሉ መቀበል እንደሚገባው ለቅዱስ ቶማስ አስረዳው፡፡ በዚህ ብቻ ሳያበቃም ሐዋርያት የቅዱስ ቶማስን ጥርጣሬ ለማስወገድ ሲሉ የእመቤታችንን ክቡር ሥጋ ለቅዱስ ቶማስ ለማሳየት ወደ መቃብሯ ጌቴሴማኒ ሄደው መቃብሯን ቢከፍቱት የእመቤታችንን ሥጋ ማግኘት አልቻሉም፡፡

ቅዱስ ቶማስም “አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ እንደ ልጇ ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ስታርግ አግኝቻታለሁ” ብሎ የሰጠችውን ሰበን ለሐዋርያት ሰጥቷቸዋል፡፡ እነርሱም በእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት እየተደሰቱ ሰበኑን ለበረከት ተካፍለውታል፡፡ በቅዳሴ ጊዜ ሠራዒ ዲያቆኑ በሚይዘው መስቀል ላይ የሚታሠረው መቀነት መሰል ልብስ፤ እንዲሁም አባቶች ካህናት በእጅ መስቀላቸው ላይ የሚያስሩት ቀጭን ልብስና በራሳቸው የሚጠመጥሙት ነጭ ሻሽ የእመቤታችን ሰበን ምሳሌ ነው፡፡

በዓመቱ ቅዱሳን ሐዋርያት “ቶማስ የእመቤታችን ትንሣኤዋንና ዕርገቷን አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን?” ብለው ከየሀገረ ስብከታቸው ተሰባስበው ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ በመያዝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሥጋ እንዲሰጣቸው እግዚአብሔርን ተማጸኑ፡፡ ጌታችንም ልመናቸውን ተቀብሎ ነሐሴ ፲፮ ቀን እመቤታችንን መንበር፤ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፤ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ እመቤታችንንም ሐዋርያትንም አቍርቧቸዋል፡፡ እነርሱም እመቤታችንን በዓይናቸው ከማየት ባሻገር አብረው ሥጋውን ደሙን ተቀብለዋል (ትርጓሜ ውዳሴ ማርያም)፡፡

ይህንን ትምህርት መሠረት በማድረግ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ከነሐሴ ፩-፲፬ ያለውን ሁለት ሱባዔ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ሆኖ በምእመናን ዘንድ መጾም እንደሚገባው ሥርዓት ሠርተውልናል (ፍት.ነገ.አን. ፲፭)፡፡ ይህ ጾምም “ጾመ ማርያም”  ወይም “ጾመ ፍልሰታ ለማርያም” እየተባለ ይጠራል፡፡ “ፍልሰት” የሚለው ቃልም “ፈለሰ ሔደ፤ ተሰደደ” ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጕሙም ከአንድ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር መሔድን ያመለክታል፡፡ “ፍልሰታ ለማርያም” ሲልም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካረፈች በኋላ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መወሰዷን የሚያስረዳ ነው፡፡

በጾመ ፍልሰታ በቤተ ክርስቲያናችን በየቀኑ በማሕሌቱ፣ በሰዓታቱና በቅዳሴው በሚደርሰው ቃለ እግዚአብሔር ነገረ ማርያም ማለትም የእመቤታችን ከመፀነሷ ጀምሮ እስከ ዕርገቷ ድረስ ያለው ታሪኳ፣ ለአምላክ ማደሪያነት መመረጧ፣ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ክብሯ፣ ርኅርራኄዋ፣ ደግነቷ፣ አማላጅነቷ፣ ሰውን ወዳድነቷ በስፋት ይነገራል፡፡ እመቤታችንን ከሚያወድሱ ድርሳናት መካከልም በተለይ ምሥጢረ ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌንና ነገረ ድኅነትን ከነገረ ማርያም ጋር በማዛመድ የሚያትተው ቅዳሴ ማርያም፤ እንደዚሁም ነገረ ድኅነትን ከምሥጢረ ሥጋዌ (ከነገረ ክርስቶስ) እና ከነገረ ማርያም ጋር በማመሥጠር የሚያትተው ውዳሴ ማርያምም በስፋት ይጸለያል፤ ይቀደሳል፤ ይተረጐማል፡፡ በሰንበታት የሚዘመሩ መዝሙራት፤ በየዕለቱ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለእናትነት  በእግዚአብሔር መመረጧን፣ ዘለዓለማዊ ድንግልናዋን፣ ክብሯን፣ ቅድስናዋን፣ ንጽሕናዋን የሚያወሱ ናቸው፡፡

የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት ጸጋና በረከት አይለየን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *