መንፈሳዊ ተጋድሎ
መንፈሳዊ ተጋድሎ አንድ ሰው የሚያምንበትን እምነት፣ የሚመራበትን ሕግ፣ የሚያልመውን ተስፋ እና የሚወደውን ነገር ተከትሎ ከግቡ ለመድረስ ማድረግ ያለበትን በማድረግ፣ ማድረግ የሌለበትን በመተው በነጻ ፈቃዱ ወስኖ ሙሉ ኃይሉን አስተባብሮ የሚያከናውነው የመንፈሳዊ አገልግሎት፤ ጥረትና ትግል ነው።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ ሩጫዬንም ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖቴንም ጠብቄአለሁ፡፡ እንግዲህስ የጽድቅ አክሊል ይቆየኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው እግዚአብሔር በዚያ ቀን ለእኔ ያስረክባል፤ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም፡፡” (፪ኛ ጢሞ. ፬፥፯-፰) እንዲል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ በአገልግሎቱ መጨረሻ ላይ በአገልግሎት ለተከተለው ለመንፈስ ልጁ ጢሞቴዎስ ይህንን ቃል ሲጽፍ በተጋድሎው ይመስለው ዘንድ፣ በኋላም ለክብር አክሊል እንዲበቃ መንገዱን ለማሳየት ነው፡፡ “የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን መምህሮቻችሁን ዐስቡ፤ መልካም ጠባያቸውን አይታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው” (ዕብ. ፲፫፥፯) በማለት፡፡
ሐዋርያው የክርስቶስን መስቀል በመሸከም፣ መከራ በመቀበል ሕይወቱን በመንፈሳዊ ተጋድሎ ፈጽሞታል። ረጅም ሐዋርያዊ ጉዞ በማድረግ በታናሿ እስያና በምድረ አውሮፓ፣ በባሕርና በየብስ በመዘዋወር የክርስቶስን የምሥራች ዜና ለብዙዎች እንዲዳረስና በጨለማም ለሚኖሩት አሕዛብ ብርሃን የሆነውን የክርስቶስን ወንጌል ሰብኳል፣ አሳምኗል፤ ብዙዎችንም ከኃጢአት ወደ ጽድቅ መንገድ መልሷል፡፡ የእርሱን ፈለግ ለሚከተሉ ሁሉም የጽድቅ ዋጋ እንደሚያገኙ አስረድቷል።
መንፈሳዊ ተጋድሎ ከፈቃደ ሥጋ ጋር የሚደረግ ውጊያ ነው። ሰው በዚህ ዓለም በተሰጠው ዘመኑ ራሱን ለፈጣሪው ለማስገዛት ከራሱ ጋር ብርቱ ተጋድሎ ማድረግ ግድ ይለዋል። ቅዱስ ጳውሎስ “ሥጋ በመንፈስ ላይ፣ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛል፤ ስለዚህም እርስ በእርሳቸው ይቀዋወማሉ፡፡ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም“ ብሎ የገለጸው ይህንን በሰው ሕይወት ውስጥ ያለውን የማይቋረጥ ጦርነት ነው። (ገላ. ፭፥፲፪)
ታላቁ አባት ኢዮብም “ጥንቱን በምድር ላይ የሰው ሕይወት ጥላ አይደለምን? ኑሮውስ እንደ ቀን ምንደኛ አይደለምን?” (ኢዮ. ፯፥፩) በማለት ሰው ጽኑ ጦርነት የሚያካሄድበት የጦር ሜዳ መሆኑን ገልጿል። ይህም ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ የሥጋ ፈቃዳችንን ብቻ ተከትለን እንድንጓዝ በማድረግ ከነፍስ ጋር የሚደረገው ጦርነት በተወሰነ ጊዜ ተነሥቶ የሚጠፋ ሳይሆን በሰው ዘመን ሁሉ የሚኖርና የዕድሜ ልክ ትግል ነው። ይህን የሥጋና የነፍስ ጦርነት በነፍስ አሸናፊነት ማጠናቀቅና ፈቃደ ሥጋን ድል አድርጎ ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት ይገባል ።ይህም ሲባል ሥጋ ርኵስ ነው፤ ሥጋ መጥፋትና መወገድ አለበት ማለት አይደለም፤ ሥጋ በራሱ የረከሰ አይደለምና። ምክንያቱም ሥጋ የተፈጠረው በራሱ በእግዚአብሔር ነውና፡፡ አምላካችን ደግሞ ርኵስ ነገር አይፈጥርም፡፡ ሰው የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ ውጤት በመሆኑም ፍጥረታትን ፈጥሮ ከጨረሰ በኋላ “እግዚአብሔርም የፈጠረውን ሁሉ እጅግ መልካም እንደሆነ አየ” እንዲል፡፡ (ዘፍ. ፩፥፴፩)
ስለዚህ ፈቃደ ሥጋን መዋጋት ማለት ተፈጥሮአዊና ንጹሕ የሆነውን ሥጋን ማጥፋት ወይም ደግሞ የሥጋን ፈቃድ ማስወገድ ማለት ሳይሆን፣ ኃጢአትን በማየት፣ በመስማት፣ በመለማመድ ያደገውን÷ ወደ ኃጢአት ያዘነበለውን ፈቃዳችንን መጐሰም /መግራት/ ማለት ነው፡፡ ይህ ፈቃድ (ኃጢአት) ሥጋን ከነፍስ ቁጥጥር ውጭ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡የሰው ሥጋዊ ባሕርዩ ምግብ ሲያጣ ይራባል፣ ይደክማል፣ ሥራ መሥራት ይሳነዋል፡፡ ሲሰጡት ደግሞ ኃጢአትን ተለማምዷልና ሌላ ፈቃድ በማምጣት ጠላት ሆኖ ይፈትነዋል፡፡ “ያዕቆብ በላ፣ ጠገበ፣ ወፈረ፣ ደነደነ፣ ሰባ፣ የፈጠረውንም እግዚአብሔርን ተወ፣ የመድኃኒቱንም አምላክ ናቀ” ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ (ዘዳ. ፴፪፥፲፭)
ሰውነት የሚፈልገውን ሁሉ እንደ ልቡ ካገኘና ያለ ገደብ የሚቀለብ ከሆነ ወደ ኃጢአት ለመገስገስ የተዘጋጀ መርከብ ነው፡፡ ሰውነት በተመቸውና ፈቃዱን ለመፈጸም ኃይል ባገኘ ጊዜ ነፍስ እየደከመች ትሄዳለች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሰውነት ፈጽሞ ከደከመና ከዛለ ሥራ መሥራት ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ ሐዋርያው “ሰውነቴን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ” እንዳለ፡፡ (፩ኛ ቆሮ. ፱፥፳፯) በአግባቡ ሊያዝና ሊገራ ይገባዋል፡፡ በአጠቃላይ ቅዱስ ጳውሎስ “ወንድሞቻችን አሁንም በሥጋችን ሳለን በሥጋ ፈቃድ እንኖር ዘንድ አይገባም፡፡ እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞታላችሁ፤ ነገር ግን በመንፈሳዊ ሥራችሁ የሥጋችሁን ፈቃድ ብትገድሉ ለዘለዓለም በሕይወት ትኖራላችሁ፡፡” (ሮሜ ፰፥፲፫) እንዳለ ከፈቃደ ሥጋ ጋር በመጋደል ፈቃደ ሥጋችንን ለፈቃደ ነፍሳችን ማስገዛት ይገባናል፡፡
ስለዚህ እያንዳንዳችን በተሰጠን ጸጋ መሠረት የሐዋርያውን ትምህርትና አርአያ ተከትለን እንደ ስጦታችን እና እንደ ችሎታችን መንፈሳዊ ሩጫችንን ልንሮጥ ይገባናል፡፡ ቅዱሳን ሥጋቸውን ለነፍሳቸው በማስገዛት እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ በተጋድሎ ዲያብሎስን ድል ነሥተውታልና እነርሱን አርአያ አድርገን መከራውን ሳንሰቀቅ በትዕግሥት መንግሥተ እግዚአብሔር የሚያስገባንን መንፈሳዊ ተጋድሎ እየፈጸምን እንሩጥ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ሲጽፍ እንዲህ ይላል፡- “እንግዲህ እነዚህ የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ የኃጢአትንም ጭንቀት ከእኛ አስወግደን ከፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፡፡” (ዕብ. ፲፪፥፩-፪) ይህ ሩጫ ወደ ክብር አክሊል ያደርሰናል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!