መናፍቃን የሚስቱባቸውና የሚያስቱባቸው መንገዶች (ሦስተኛ ክፍል)
…በዳዊት አብርሃም…
ጥቅሱን ከዳራው መነጠል
መጽሐፍ ቅዱስ ምንም በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት የተጻፈ ቢሆንም የተጻፈው ግን በሰዎች ነው፡፡ የተጻፈውም ለሰዎች ነው፤ የተጻፈበት ቋንቋ፣ ቦታና የተወሰነ ጊዜ አለ፡፡ ስለዚህ የአጻጻፉን ባህል፣ በዘመኑ የነበረውን ኹኔታ፣ መጽሐፉ የተጻፈበትን ዓላማ በማወቅና በዚያም ውስጥ የጥቅሱን ትክክለኛ መልእክት በመረዳት መጥቀስ እንጂ እንደመሰለ አንሥቶ መጥቀስ ስሕተት ላይ ይጥላል፡፡
ለምሳሌ “እነርሱም፦ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ አሉት” የሚለውን ጥቅስ እንመልከት፡፡ (ሐዋ.16፡31) አንዳንዶች ይህን ጥቅስ በመምዘዝ ‹ለመዳን ማመን ብቻ በቂ ነው› ይላሉ፡፡ ይህን ንግግር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ የእስር ቤት ጠባቂ ለነበረው ሰው የተናገሩት ኀይለ ቃል ነው፡፡ ጥቅሱ የተነገረው ለማን ነው? ለምን ተነገረ? ከዚያስ ወረድ ብሎ ምን ይላል? ከሌሎች ጥቅሶች ጋር ያለው ተዛምዶ ምን ይመስላል? ብለው ሳይጠይቁ ለውሳኔ መቸኮል ትክክል አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ልናስታውስ የሚገባን ቁም ነገር ቃሉ የተነገረው እምነት ላልነበረው ሰው መሆኑን ሲሆን ሰውየው ካመነ በኋላ ደግሞ መጠመቅንና ሌሎች ለመዳኑ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ሁሉ ያስፈልጉታል እንጂ በእምነት ብቻ የሚቋረጥ እናዳልሆነ ነው፡፡ (የዚህ ጥቅስ ትርጕም ጥቅሱ ከተነገረበት ዳራ አንጻር ተተንትኖ በእምነት ስለመዳን በምንነጋገርበት ክፍል ውስጥ ይገኛል)
ጥቅሱን ከዓላማው ውጪ አውጥቶ መጥቀስ
አንዳንድ ጥቅሶች ደግሞ ከተጻፉበት የመጀመሪያ ዓላማ ፍጹም ባፈነገጠ መልኩ ተጠቅሰው ሰውን ለማሳሳት ሲውሉ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ ለሥጋዊ ፈውስ የተነገሩትን “እመን ትድናለህ” “እምነትህ አዳነችህ” የሚሉ ቃላትን በመምዘዝ ለነፍስ መዳን ወይም የዘላለም ሕይወትን ስለመውረስ እንደተነገሩ አድርጎ የመጥቀስ ስሕተት በክርክሮች ጊዜ ይስተዋላል፡፡
እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የተጻፈበት ልዩ ዓላማ አለው፡፡ ይህንንም ዓላማ አጠቃላዩን አውደ ንባብ በማንበብ፣ የተጻፈበትን ታሪካዊ ኹኔታ በማጥናት እንዲሁም የጥንታውያኑን አበው ትርጓሜ በመመልከት ሊታወቅ ይችላል፡፡ ሆኖም ይህን ሁሉ ሒደት መጠንቀቅ ቢቸግራቸው እንኳ ቢያንስ ንባቡን አሟልቶ በማንበብ እውነተኛውን መልእክት ማወቅ የሚቸግራቸው ወገኖች አንድን ጥቅስ ቆንጽለው በማስረጃነት ሲያቀርቡ የገጸ ንባቡን ዓላማ ይስታሉ፡፡ ለምሳሌ “ስለዚህም ማንም በሰው አይመካ” (1ኛቆሮ.3፡21) በሚለው ጥቅስ መነሻነት የቅዱሳንን ምልጃ ለመቃወም መሞከር ጥቅሱን ከዓለማው ውጪ ለግል ፍላጎት ማዋል ይሆናል፡፡
ከሌሎች ጥቅሶች አንጻር ለማየት አለመቻል
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ትክክለኛ ትርጕሙ ከሚታወቅባቸው መንገዶች መካከል አንዱ በሌሎች ጥቅሶች ሚዛንነት መመዘን፣ የተጠቀሰውን በሌሎች ጥቅሶች መነጽርነት ገምግሞ መረዳት ዓይነተኛ ዘዴ ነው፡፡ ሆኖም በተግባር እንደዚያ ማድረግ ባለመቻል የተነሣ ብዙ ስሕተቶች ይፈጠራሉ፡፡ ለአንዳንድ ስሕተቶች ምርኩዝ ሆነው የቀረቡ ጥቅሶች በዚያው ምዕራፍ ውስጥ፣ ወይም ጥቅሱ በሚገኝበት የመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያም ካልሆነ በሌሎች ክፍሎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ለምሳሌ ፕሮቴስታንቶችና “ተሐድሶዎች” ስለመዳን ሲከራከሩ የሚያነሡት ጥቅስ “እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ” (ሮሜ5፡1) የሚለውን ነው፡፡ አንዳንዶች ይህን ጥቅስ እያሳዩ “ከዚህ በላይ ማስረጃ ምን ትፈልጋለህ? በእምነት ብቻ እንደሚጸደቅ በግልጥ ተጽፏል፤ ይህን ጥቅስ ምን ታደርገዋለህ? ወይስ እንዴት ልትክደው ትችላለህ?” በሚል ክርክር ይገጥማሉ፡፡
የእኛ ምላሽም እንዲህ ነው፡፡ ይህንን ጥቅስ አንክድም፤ አናስተባብልምም፡፡ ነገር ግን ለብቻው ነጥለን አንመለከተውም፡፡ ጥቅሱን ቆንጽሎ መጥቀስ ምን ያህል እንደሚጎዳ ማወቅ እንድንችል በዚያው ምዕራፍ ያለ ሌላ ጥቅስ እንመልከት፡፡ “በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚያደርጉ ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙ አይደለም” (ሮሜ 2፡13) ይህን የሐዋርያውን ሐሳብ ነጥለን ከወሰድን መዳን ሕጉን በመተግበር ብቻ የሚገኝ ነው ልንል እንችላለን፡፡ ስለዚህ ይህን መሰል ስሕተት ውስጥ እንዳንወድቅ ጥቅሶችን በተሟላ መልኩ አንብቦ መረዳትን ልንለምድ ይገባናል፡፡
ሐዋርያው በሁለቱም ቦታዎች (ሮሜ.2፡13 እና ሮሜ 5፡1) ላይ የጻፈልንን ለድኅነታችን አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች እንማራለን፡፡ በዚህም ለመዳናችን ማመናችን የሚኖረውን ዋጋ መልካም ሥራ አይተካውም፤ እንዲሁም መልካም ሥራ ለመዳናችን አስፈላጊ መሆኑ የእምነትን አስፈላጊነት አይሽረውም፡፡ “ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ። እንደዚሁም ጋለሞታይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን?” (ያዕ2፡24-25) እንደሚለው ለመዳን ሁለቱንም እምነትንና ሥራን አዋሕደን መያዝ እንዳለብን መጽሐፍ ቅዱስን እርስ በራሱ አነጻጽረን በማንበብ እነገነዘባለን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!