መልካም ዕውቀት ሞገስን ይሰጣል
ለሰው ልጆች ከተሰጡ ጸጋዎች አንዱ ዕውቀት ነው፡፡ የሰው ልጅ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ አዲስ ነገርን የመልመድ፣ አካባቢውን የማጥናትና መገንዘብን እያዳበረ አካባቢውን ከመልመድ አልፎ በዕውቀት እየጎለመሰ፣ ጥሩውንና መጥፎውን እየለየ ያድጋል፡፡ መልካም የሆነውን መንገድ ለሚከተሉና እንደ እግዚአብሔር ቃል ለሚመላለሱት ዕውቀትና ጥበብን ያሳድርባቸዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “የምድር ገዢዎች ሆይ ጽድቅን ውደዷት፤ የእግዚአብሔርንም ኃይል በበጎ ዕውቅት አስቡት፣ በቅን ልቡናም ፈልጉት” ይለናል፡፡(ጥበ.፩፥፩)፡፡ መልካም ዕውቀትን በቅንነት መሻትና ፈልጎ ማግኘት ይገባል፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ከይሁዳ ነገድ ስለሆነው ባስልኤል ሲናገር እንዲህ ይላል፡- “በሥራ ሁሉ ብልሃት በጥበብም፣ በማስተዋልም፣ በዕውቀትም የእግዚአብሔር መንፈስ ሞላበት” ሲል ይነግረናል፡፡(ዘጸ.፴፭፥፴፩)፡፡ አባቶቻችን በዚህ መንገድ አልፈዋልና ከእነርሱ መማር ያስፈልጋል፡፡
ልጆችን በዕውቀትና በጥበብ ተንከባክቦ ለማሳደግ ደግሞ የወላጆች ሚና ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ልጆች ገና ከሕፃንነታቸው ጀምሮ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አንጾና ኮትኩቶ ማሳደግ ከተቻለ ፍሬው ያማረ ይሆናል፡፡ ዛፍ ተጣምሞ ቢያድግ በኋላ ማቃናት እንደማይቻል ሁሉ ልጆች ከልጅነታቸው ጀምሮ ቃለ እግዚአብሔርን እየሰሙ ቢያድጉ ለራሳቸው ለቤተሰብ፣ እንዲሁም ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር ጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
ይህንንም በመረዳት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን በሮችዋን ከፍታ ልጆችዋን ለመቀበል ተዘጋጅታ የምትጠብቀው፡፡ በሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመፍጠርም የቤተ ክርስቲያን ድርሻ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡ በዚህም መሠረት ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት በግቢ ጉባኤያት ላይ ላለፉት ሠላሳ ዓመታት ወጣቱ ትውልድን በማነጽ ላይ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ስንቶቻችን ተጠቅመንበታል?
ዓለም ለሥጋዊ ፍላጎታችን እንድንሮጥ ስታደርገን ቤተ ክርስቲያን ደግሞ “ጥበብና ዕውቀት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነውና ኑ ልጆቼ እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችኋለሁ” ትለናለች፡፡ ዕውቀትና ጥበብ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይሰጣሉና ለዚህም በማስተዋል መጓዝ በተለይ ለወጣቶች እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ “ጥበብ ፈጽማ የጎላች ናት፤ ውበቷም አይጠወልግም፡፡ የሚወዷትም ፈጥነው ያዩአታል፤ የሚፈልጓትም ያገኟታል፡፡ ለሚወዷትም ትደርስላቸዋለች፤ አስቀድማም ትገለጥላቸዋለች፡፡” (ጥበ.፮፥፲፪-፲፫) እንዲል፡፡
በግቢ ጉባኤ ውስጥ መሆን ሕይወታችንን ከክፉ ነገር እንድንታደግ፣ ውጤታማም ሆነን ለመውጣትና የወደፊት ሕይወታችን በእግዚአብሔር ቸርነት የተስተካከለ እንድንሆን ያደርገናል፡፡ ወደ እገዚአብሔር በቀረብን ቁጥር መልካም ሰዎች፣ ለቃሉም የምንታዘዝና እኔ ራሴ ብቻ ልኑር ሳይሆን ስለ ሌሎች መኖርን እንማራለን፡፡ ክርስቲያን እኔ ብቻ ይድላኝ አይልምና፡፡
ግቢ ጉባኤያት ውስጥ መሳተፍ እነዚህን በረከቶች ይዘን እንድንወጣ፣ በአገልግሎትም ጠንካሮች እንድንሆን መንገዱን ያመቻችልናል፡፡ እግዚአብሔርም መንገዱን እንድንከተል ዘወትር ይጠራናል፣ ዓይኖቹም ወደሚፈልጉት ነውና ሕይወታችን ከእግዚአብሔር እንዳይለይ ዕውቀትን፣ ጥበብንና ሞገስን አስተባብረን እንድንይዝ ያደርገናል፡፡ ሕይወታችንም በወንዝ ዳር እንደምትበቅል ዛፍ ለምልማ መልካም ፍሬ እንደምትሰጥ ሁሉ በሕይወታችን እንለመልማለን ለሌላውም አርአያ በመሆን ፍሬ እናፈራለን፡፡ ስለዚህ ለዓለሙ እና ለክፉ ተግባሩ ተባባሪዎች እንዳንሆን መንፈሳዊውን ዕውቀትና ጥበብን ገንዘብ እናደርግለን፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት እርሷንም እሻለሁ፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ” እንዳለው እኛም እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ሊኖረን፣ በቅጥሩም ልንጠለል ያስፈልጋል፡፡(መዝ.፳፮፥፬)፡፡ ይህንን ብናደርግ እግዚአብሔር ሞገስን ይሰጠናል፡፡
የግቢ ጉባኤ ጥቅሞች በርካታ ናቸውና እግዚአብሔር በዚህ ዘመን የሰጠን በረከታችን ነውና እግዚአብሔርን ለመፈለግ በምናደርገው ጥረት ውስጥ መንገዱን በመምራት ሠላሳ፣ ስልሣ፣ መቶም በማፍራት ለሌሎች አርአያ እንሆናለን፤ እግዚአብሔርም አገልግሎታችንን ይባርክልናል፡፡
እግዚአብሔር እንደቃሉ ተጉዘን በረከት እንድናገኝ ይርዳን፡፡ አሜን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!