መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ
መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፤
በሀገራችን በኢትዮጵያና በመላው ዓለም የምትገኙ ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ፡-
የክብር ባለቤት እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ ሰባት ዓ.ም የቅድስት ድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታ በሰላም አደረሳችሁ!
‹‹ታዓብዮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር፤ ነፍሴ እግዚአብሔርን እጅግ ታከብረዋለች›› (ሉቃ. ፩÷፵፮)፤
ይህንን ዐረፍተ ነገር የተናገረችው ማኅደረ መንፈስ ቅዱስ የሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፤ ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር ዓለምን ለማዳን በሠራው ስሥራ ሰውነታችንን ለመዋሐድ የመረጣት ምርጥ የፍጥረት ወገን ናት፤ ፍጥረት ሁሉ በእግዚአብሔር ለእግዚአብሔር ተፈጥሮአል፤ የእግዚአብሔርም ነው፤ የቅድስት ድንግል ማርያም መመረጥም በእግዚአብሔር ለሰው የተደረገ ምርጫ ነው፤
የሰው መዳን ከጥንቱ ከጠዋቱ በእግዚአብሔር ልዩ አሠራር እንደሚከናወን በነቢያት የተገለጸ ነበረ፣ ‹‹አኮ በተንባል ወአኮ በመልአክ አላ ለሊሁ እግዚእ ይመጽእ ወያድኅነነ፤ በአማላጅም አይደለም፤ በመልአክም አይደለም እሱ ራሱ ጌታ መጥቶ ያድነናል እንጂ›› የሚለው የነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ትንቢትም ይህንን ያስረዳል፤ ቃለ ትንቢቱ ድኅነታችን በጌታ ቤዛነት እንደሚከናወን ያረጋግጣል፤ ይህም ሊሆን የቻለው ከፍጡራን ወገን በደሙ ቤዛነት ፍጡራንን የሚያድን ስለሌለ ነው፤

ከዚህ አንጻር የሰው መዳን በእግዚአብሔር አሠራር በደም ቤዛነት ከሆነ፣ በደሙ ቤዛነትም ዓለምን ማዳን የሚችል ከፍጡር ወገን ከሌለ፣ መዳናችን በእግዚአብሔርና በእግዚአብሔር እጅ ብቻ የተንጠለጠለ ነበረ፤ እግዚአብሔር በደሙ ቤዛ ሆኖ ዓለምን ለማዳን ደግሞ ደም ሊኖረው ይገባ ነበር፤ በመሆኑም እግዚአብሔር በክዋኔው ደም የሌለው ስለሆነ ለቤዛ ዓለም የሚፈስ ደምን ገንዘብ ማድረግ ነበረበት፤ ይህንን ደም ለመዋሐድ ቅድስት ድንግል ማርያምን መረጠ፤ ለዚህ ብቁ እንድትሆንም በእስዋ ላይ ሥራውን ሥራ፤ በምርጫውም መሠረት ከቅድስት ድንግል ማርያም ደማዊ ሥጋንና ነፍስን ተዋሕዶ ለቤዛዊ መሥዋዕት መንገዱን አመቻቸ፤
ቅድስት ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት መሰላል ለመሆን በእግዚአብሔር የተመረጠች በመሆኗ አንቀጸ አድኅኖ ወይም የድኅነት በር ትባላለች፤ ቅድስት ድንግል ማርያም ለዚህ ታላቅ ነገረ ድኅነት መመረጥዋ እጅግ ታላቅ ዕድል መሆኑን ስለተገነዘበች ‹‹ታላላቅ ሥራዎችን ሠርቶልኛልና›› በማለት እግዚአብሔርን በመዝሙር አመስግናለች አክብራለችም፤
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
የቅድስት ድንግል ማርያም የምስጋና እና የአምልኮ መዝሙር የኛም መዝሙር ነው፤ እግዚአብሔር ለቅድስት ድንግል ማርያም ታላላቅ ሥራዎችን እንደሠራ ለኛም ብዙ ታላላቅ ሥራዎችን ሠርቶልናል፤ እየሠራልንም ነው፤ ለሠራልን አምላክም እንደ ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቅ ክብርን መስጠት ይገባናል፤ ለእግዚአብሔር የምንሰጠው ክብርም በቃል ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን በተግባር የሚታይ ሊሆን ይገባል፤ የድንግል ማርያም መንፈሳዊ ሕይወት በማስተዋል በትሕትና፣ በትዕግሥት በርኅራኄ በመታዘዝ በንጽሕና በቅድስና በክብርና በበረከት የተሞላ እንደሆነ በቅዱስ መጽሐፍ ከተጻፈው ሥነ ሕይወቷ መረዳት እንችላለን፤ ታድያ በእርሷ ክብርና ተማሕፅኖ የምንተማመን ልጆቿም የእሷን ያህል እንኳ ባንችል ወደ እርስዋ የሚጠጋጋ መንፈሳዊ ሕይወት ሊኖረን ይገባል፤ ይህም የምናደርገው ለእግዚአብሔር ክብርና ለእኛ መዳን ሲባል ነው፤ እኛ እግዚአብሔርን ስናከብር እንከብራለን እንድንማለን፤ ለእግዚአብሔር ክብር የማንሰጥ ከሆነ ግን ውጤቱ መክበር ሳይሆን ሌላ ነው የሚሆነው፤
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
እኛ በየጊዜው ጾምን እንድንጾም ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ፈቃደ ሥጋችንን በመግራት ለእግዚአብሔር ታዛዦች እንድንሆን ነው፤ ጾም የኃጢኣት መግቻ መሣሪያ በመሆኑ ‹‹ልጓመ ኃጢኣት›› ተብሎ ይታወቃል፤ በዚህም ሰውነታችንን ለግብረ ኃጢአት ከሚያጋግሉ ምግቦች አርቀን በሰከነ መንፈስ እግዚአብሔርን እያሰብን ኃጢአታችንንም እያስታወስን በንስሓ ወደ እርሱ ለመቅረብና ለሱ ለመታዘዝ እንጾማለን፤
የጾም ጥቅም ከጥንት ጀምሮ የታወቀ በእግዚአብሔርና በሰውም ተቀባይነት ያለው ነው፤ እግዚአብሔር ከመሥዋዕት ይልቅ መታዘዝን ይወዳልና በጾምና በጸሎት ለሱ ልንታዘዝ ይገባል፤ እግዚአብሔር በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ሊያድር የቻለው ‹‹እንዳልኸኝ ይሁንልኝ›› ብላ ታዛዥነትዋን በገለጸች ጊዜ ነው፤ እኛም እንዳልከን ይሁንልን እያልን እንደ እስዋ ታዛዥ መሆን አለብን፤
ዛሬ በዓለማችን ያለው መተረማመስ ለእግዚአብሔር ያለመታዘዝ ያመጣው ጣጣ እንደሆነ ማንም አይስተውም፤ መታዘዙ ቢኖር ኖሮ የሰው ልጅ ሰውን የሚያድን ብቻ እንጂ ሰውን የሚገድል መሣሪያ አያመርትም ነበር፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ወንድምህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ አለ እንጂ ግደል ብሎ አላዘዘምና ነው፤ አሁንም በዚህ ባለንበት ዓለም በጣም ተባብሶ የሚገኘው የመጠፋፋት ዝንባሌ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ በሰላምና በሰጥቶ መቀበል ካልተቋጨ ዳፋው አስከፊ መሆኑ አይቀርም፤
ከዚህ አንጻር ዛሬም ለሰው ልጆች ሁሉ የምናስተላልፈው መልእክት ‹‹በፍቅር ከሆነ ትንሹም ለሁሉ ይበቃልና ያለውን በጋራ በመጠቀም በፍቅርና በሰላም እንኑር›› የሚል ነው፤ ‹‹ፍትሕና ርትዕም ለሰው ልጅ መነፈግ የበለትም፤ ሰው በምድር ላይ ሠርቶ የመኖር መብቱ ሊከበርለት ይገባል፤ ይህንን ማድረግ ማለት ለእግዚአብሔር መታዘዝ ማለት ነው፤ ስለሆነም ለእግዚአብሔር ክብርና ለራሳችን መዳን ስንል ለእርሱ በመታዘዝ በሕይወትና በሰላም እንኑር፡፡
በመጨረሻም፡–
በጾመ ማርያም ሱባኤ ስለ ሀገር ሰላምና ስለ ሕዝብ ደኅንነት በመጸለይ፣ በልዩ ልዩ ምክንያት በመከራ ላይ ወድቀው የሚገኙ ወገኖቻችንን በሚያስፈልጋቸው ሁሉ በመርዳት ሱባኤውን እንድናሳልፍ አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን እናስተላልፋለን፤
መልካም የሱባኤ ወቅት ያድርግልን፤ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣
ነሐሴ 1 ቀን 2017 ዓ.ም
ዋሽንግተን ዲሲ
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!