መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

በሀገር ውስጥና በውጭ የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና ምእመናት፣ እንዲሁም ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ!

የይቅርታ ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታ በሰላም አደረሳችሁ!!

“ወሣህሉኒ ለትውልደ ትውልድ ለእለ ይፈርሕዎ፣ ይቅርታው ለሚፈሩት ለልጅ ልጅ ነው” (ሉቃ.፩፥፶)፡፡

ይህ ኃይለ ቃል የቅዱስ መጽሐፍ ቀዋሚ ምሰሶ ሆኖ በብዙ ቦታ የሚገኝ ነው፣ ቃሉ እግዚአብሔር ለሚፈሩት የሚያጎናጽፋቸውን የምሕረት ቃል ኪዳን በውስጡ ይዞአል፤ ማኅደረ መንፈስ ቅዱስ የሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያምም እግዚአብሔርን ባመሰገነችብት የምስጋና መዝሙር ይህንን ኃይለ ቃል ተናግራዋለች፡፡

በዚህ ኃይለ ቃል የእግዚአብሔር ይቅርታ ምን ጊዜም የከበረና እንደ ተስፋ ቃሉ የሚፈጸም መሆኑ፣ ያም ሊሆን የሚችለው ለሚፈሩት ሰዎች መሆኑ በሚገባ ተገልጿል፡፡ የእግዚአብሔር ይቅርታ አጭርና ቀጭን ሳይሆን ለልጅ ልጅ እንደሚሆንም ተብራርቷል፡፡

ይህ አባባል እውነት እንደሆነ ለመረዳት ከእኛ ከሰዎች የበለጠ ሌላ ምስክር ሊኖር አይችልም፡፡ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ሣህሉ ለእግዚአብሔር መልአ ምድረ፣ የእግዚአብሔር ይቅርታ ምድርን መላ” ብሎ እንዳስተማረን ይቅርታው በየጊዜው በዝቶ ባይደረግልን ኖሮ ውሎ ማደሩ የሚቻል አልነበረም፡፡ እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ኃጢአትን፣ ክፋትን፣ ርኵሰትንና ክህደትን የሚጠላ አምላክ ነው፡፡ እኛ ደግሞ ከእነኚህ ክስተቶች ለአንድ ደቂቃ ስንኳ ጸድተን አናውቅም፣ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር በቅጣት ፈንታ ምሕረትንና ይቅርታውን እያበዛልን በምሕረቱ ተጠልለን እንኖራለን፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያምን በመውደድ፣ አስተብቍዖቷን፣ ጸሎቷንና ልመናዋን በመሻት ይህንን ጾም በመጾም በመንፈስ ተሞልታ ያስተማረችንን ፈሪሐ እግዚአብሔር ገንዘብ በማድረግ መሆን አለበት፤ እንደ ተስፋ ቃሉም ለቃሉ በመታዘዝ መሆን አለበት፤ ቃሉ ይቅር እንድትባሉ ይቅር በሉ፣ ሰላምና አንድነትን አጽንታችሁ ያዙ ይለናል፡፡

ይህን ይቅርታ ለማግኘት የተጠየቅነው ዋናው ነገር እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ እግዚአብሔርን በእውነት የምንፈራ ከሆነ ይቅርታ ለመስጠትም ሆነ ለመቀበል ዳገት አያግደንም ነው፡፡ እግዚአብሔርን መፍራት ማለት በምሠራው ሥራ፣ በመንናገረው ቃል፣ በምናስበው ሐሳብና ምኞት ሁሉ እግዚአብሔር ያውቅብናል፣ ያየናል፣ ይፈርድብናል የሚል አስተሳሰብ በውስጣችን ኖሮ ክፉ ድርጊትን ከማድረግ እንድንቆጠብ መሆን ማለት ነው፡፡

ሰው ሁሉ እግዚአብሔርን ከእርሱ ውጪ እንዳለ ሳይሆን በአጠገቡና በመንፈሱ ውስጥ ሆኖ እንደሚያውቅበት ተገንዝቦ እግዚአብሔርን መፍራት አለበት፣ የሰላምና የአንድነት መሠረት ከፈሪሐ እግዚአብሐየር መነሣት ሲችል ዘላቂና ጠቃሚ ይሆናል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናትና ምእመናን!

ዘንድሮ የምጾመው ጾመ ማርያም ሀገራችንና ሕዝባችን በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋ ውስጥ ተከበው ባሉበት ወቅት ነው፤ የተጋረጡብን ፈተናዎች እግዚአብሔርን ይዘን ካልሆነ በቀር ብቻችንን ሆነን የምንወጣቸው አይደሉም፤ በእግዚአብሔር ከለላነት እነዚህን ፈተናዎች ልናልፋቸው ከሆነ እሱን በመፍራት ከክፋታችን መመለስና ንስሓ መግባት አለብን፤ በነገው ዐለት የምንጅመረው የጾመ ማርያም ሱባኤም ዋናው ዓላማው በንስሓ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስና እሱን በመፍራት ለእሱ ተገዢዎች ለመሆን ነው፡፡

ሁሉም እንደሚያውቀው ንስሓ በይቅርታና በዕርቅ መታጀብ ይገባዋል፤ ችግሮቻችን ምን ያህል ቢበዙም ለእግዚአብሔር ብለን ብንፈጽመው ይቅርታና ዕርቅ፣ በምናረጋግጠው ሰላምና አንድነት ተሸናፊዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ችግሮችን ለማሸነፍ ብሎም ለማስወገድ ከይቅርታና ዕርቅ፣ ከሰላምና አንድነት የተሻለ አማራጭ እንደሌለልሂቃኖቻችንም ሆኑ ሕዝቦቻችን በውል መገንዘብ አለባቸው፡፡

ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር የዚህ ትውልድ ሀገር ብቻ አይደለችም፤ ያለፉ አባቶች፣ የሚመጡ ትውልዶችም የኢትዮጵያ ባለቤቶች ናቸው፡፡ እኛ በክብ ጠረጴዛ ተገናኝተን ተወቃቅሰንና ተመካክረን ችግሮቻችንን በተሸንፎ ማሸነፍ ጥበብ ማረም ካቃተን ቢያንስ ኢትዮጵያን ባለችበት ሁናቴ ለባለመብቱ ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ እንዳለብን መዘንጋት የለብንም፤ ነገሮችን ሁሉ በትዕግሥት፣ በአርቆ አስተዋይነትና በሰላማዊ ሁኔታ ለማስተናገድ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይገባናል፤ በመሆኑም ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች ሁሉ ተቋቁማ በአሸናፊነት መሻገር የምትችለው እግዚአብሔርን በመፍራት ለይቅርታና ለዕርቅ ስንዘጋጅ ነው፤ ስለዚህ ይህ ግንዛቤ ተወስዶ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ቆመናል የሚሉ የፖለቲካ ተፎካካሪ ወገኖች ሁሉ አንድ ላይ ተገናኝተውና በክብ ጠረጴዛ ሆነው በመወያየት የሀገሪቱን አንድነት፣ ሰላምና ልማት እንዲያስቀጥሉ በዚህ አጋጣሚ በእግዚአብሔር ስም እንማፀናለን፡፡

በመጨረሻም፣

ሕዝበ ክርስቲያኑ የጾም ሱባኤ በኮረና ቫይረስ እንዳይጎዳ ጥንቃቄ በማድረግ የሱባኤውን ወቅት ስለ ሀገር ሰላምና አንድነት በኃዘን፣ በምህላ፣ በጸሎት፣ በንስሓና በፍቅር፣ የተቸገሩትንም በመርዳት እግዚአብሔርን በመፍራት እንዲያሳልፍ አባታዊና መንፈሳዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

                        እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ፣ ይቀድስ፤

                        ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም

ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ሐምሌ ፴ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *