ሕይወት ከግቢ ጉባኤ በኋላ

በእንዳለ ደምስስ

ማኅበረ ቅዱሳን ላለፉት ሠላሳ ዓመታት በመላው ዓለም በሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የግቢ ጉባኤያትን በመመሥረት ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፣ ዶግማ እና ቀኖና እንዲሁም ሥርዓት እንዲያውቁ፣ ራሳቸውንም ከከፉ በመጠበቅ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን ማነጽ እንዲችሉ አገልገሎቱን በማጠናከር ከፍተኛ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡

በእነዚህም ዘመናት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን አስተምሮ በአባቶች ቡራኬ ማስመረቅ የቻለ ሲሆን፤ ተመርቀው ሲወጡም በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ጠንክረው በሚሄዱበት ሁሉ በተሰማሩበት የሥራ መስክ ሀገራቸውን፣ እንዲሁም በተማሩት የቤተ ክርስቲያን ትምህርት እንደ ጸጋቸው መልሰው ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ መመሪያ ይሰጣቸዋል፡፡ በተጣለባቸው ኃላፊነት መሠረት በርካቶች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚገኙ መዋቅሮች ማለትም በማኅበረ ቅዱሳን ማእከላትና ወረዳ ማእከላት፣ በሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ በሰበካ ጉባኤያት፣ በተለያዩ የጉዞና የጽዋ ማኅበራት በመሳተፍ አገልግሎት ሲሰጡ ማየት የተለመደ ነው፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በነበሩበት ወቅት ራሳቸውን ከኃጢአት ሥራና አልባሌ ሥፍራ በማራቅ በትምህርታቸው ውጤታማ ሆነው ሜዳልያና ዋንጫ በመሸለም ለሌሎች ምሳሌ በመሆንም ይታወቃሉ፡፡ ከመደበኛ ትምህርታቸው በተጨማሪም ማኅበረ ቅዱሳን የሚሰጠውን ተከታታይ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ከመማር አልፈው የአብነት ትምህርትን በመከታተል ዲያቆን፣ መሪጌታ እየሆኑ መውጣትም እንደሚቻል በተግባር ያሳዩ በርካቶች ናቸው፡፡

በግቢ ጉባኤ ቆይታቸው ከትምህርታቸው በተጨማሪ በመንፈሳዊ ሕይወታቸውም ለማደግ የሚያደርጉት ጥረት ከፍተኛ በመሆኑ ሲወጡም ቤተ ክርስቲያንና ሀገራቸውን በማገልግል ላይ የሚገኙ በሄዱበት ሁሉ በአገልግሎት በማሳተፍ በልዩ ልዩ ሙያዊ ዘርፎች ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዕድገት ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ያበረክታሉ፡፡

በተቃራኒው ደግሞ በግቢ ጉባኤ ውስጥ እያሉ በአገልግሎትም ሆነ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዳልበረቱ ሁሉ ትምህርታቸውን አጠናቀው ሲወጡ ግን ያንን ጥንካሬአቸውን ይዘው መቀጠል ይቸገራሉ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “በዓለም ግን መከራ ትቀበላላችሁ፤ ነገር ግን ጽኑ፤  እኔ ዓለምን ድል ነስቼዋለሁና” ብሎ እንዳስተማረው በጽናት ዲያብሎስ ያዘጋጀውን ወጥመድ ሁሉ ሰባብሮ ከማለፍ ይልቅ በቀላሉ ዓለም ባዘጋጀላቸው ወጥመድ ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ (ዮሐ.፲፮፥፴፫)፡፡

ነገር ግን ለተጠሩበት ዓላማ መታመን ከእያንዳንዳቸው ይጠበቃልና ለሚገጥሟቸው ፈተናዎች ሁሉ ከመንበርከክ በጽናት ማለፍ ይገባል፡፡ በተለያዩ ሰንካላ ምክንያቶችም በማመካኘት ከአገልግሎትና ከመንፈሳዊነት መራቅ አያድናቸውምና፡፡

ከምረቃ በኋላ የሚያጋጥሟቸውን የሕይወት ጉዞዎች በመንፈሳዊ ሕይወት መመዘን፡-

የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ከምረቃ በኋላ ወደ ማኅበረሰቡ የመቀላቀል ዕድል ስለሚያገኙ በትምህርት ላይ ካሳለፉት ሕይወት በተለየ መልኩ ዓለም በሯን ከፍታ ትቀበላቸዋለች፡፡ ራሳቸውን ችለው የሚቆሙበት ጊዜ ደርሷልና በበርካታ ጉዳዮች የመሳተፍ ዕድል ይገጥማቸዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ፡-

  • ሥራ
  • አገልግሎት
  • ማኅበራዊ ሕይወት
  • ጋብቻ

ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ሌሎችም ጉዳዮች ቢኖሩም እነዚህን አንድ በአንድ እንመለከታቸዋለን፡፡

፩. ሥራ፡-

የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ገና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንደወጡ ሥራ ማግኘት ትልቁና ከባዱ ፈተና ነው፡፡ ነገር ግን ብዙ ውጣ ውረድ ቢኖረውም ይህንን ተቋቁመው ሥራ የማግኘት ዕድል ይገጥማቸዋል፡፡ ከሥራ ጋር ተያይዞ ደግሞ የሥራውን ባሕርይ፣ የመሥሪያ ቤቱን ባህል ለመልመድ ጥረት ያደርጋሉ፤ ይህን ሲያደርጉ በተለይም ከአገልግሎት፣ ከጸሎት፣ በአጠቃላይ ከመንፈሳዊ ሕይወት የመዘናጋት ሁኔታ ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን በግቢ ጉባኤ ውስጥ እያሉ ያገኙት ዕውቀት፣ የቀሰሙት ልምድ፣ እንዲሁም የጸሎት ሕይወት ስለሚናፍቃቸው ከሥራቸው በተጨማሪ እግዚአብሔርን አጋዥ አድርጎ ለመጓዝ አይቸገሩም፡፡

ሥራ ለማንኛውም የሰው ልጅ መሠረታዊ ጉዳይ ስለሆነ ራስን በራስ የማስተዳደር፣ ቤተሰብን የመርዳት ዓላማ ተግባራዊ የሚያደርጉበት ወቅት ስለሆነ ይበልጥ ኃላፊነት እንዲሰማቸው ያደርጋቸዋል፡፡ ሥራ መያዛቸው በርካታ ጥያቄዎችን የሚፈታላቸው በመሆኑ ቀስ በቀስ ወደ አቋረጡት አገልግሎት በመመለስ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን መዋቅር ማለትም በማኅበረ ቅዱሳን፣ በሰንበት ትምህርት ቤት፣ በሰበካ ጉባኤ፣ በአገልልገሎትና በጽዋ ማኅበራት ውስጥ ሲሳተፉ መመልከትም የተለመደ ነው፡፡ በተለይም ለአገልግሎት የሚያበቃቸውን ሥልጠና ማኅበረ ቅዱሳን ባሉት መዋቅሮቹ አማካይነት በመስጠት መምህራን በሌሉባቸው ቦታዎች በመሸፈን፣ ክህነትም ካላቸው በጎደለው ቦታ ሁሉ ገብተው ያገልግላሉ፡፡ ይህም ባይቻል ግን ራሳቸውን አርአያ ያለው ክርስቲያን ይሆኑ ዘንድ በማብቃት መልካም ቤተሰብን ያፈራሉ፡፡

አንዳንዶቹም ገና ከከፍተኛ ትምህርት ተመርቀው ሲወጡ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ ወደ አገልግሎት መመለስ እንኳን ባይችሉ በአጥቢያቸው በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ኪዳን የማድረስ፣ ቅዳሴ የማስቀደስ፣ ራሳቸውንም ከመንፈሳዊ ሕይወት ጋር ማቆራኘቱ ላይ ይተጋሉ፡፡ ሥራ ቢያገኙም ባያገኙም በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ዙሪያ የሚመጣባቸውን ፈተና ሁሉ ይጋፈጣሉ፡፡ የንስሓ አባት የመያዝ፣ የምሥጢራት ተካፋይ የመሆን፣ በጸሎት የመበርታት ዕድላቸውም ከፍተኛ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ከሥራ ማግኘት ጋር ከሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች መካከል ዋነኛው የኢኮኖሚ ጉዳይ ከሞላ ጎደል በመመለሱ ለሌሎች ፍላጎቶች የመጋለጥ ዕድላቸውም ከፍተኛ መሆን ነው፡፡ መንፈሳዊ ፍሬን ከማፍራት ይልቅ አንቱ አንቱ እንዲባሉ ይተጋሉ፡፡ መንፈሳዊነትን እርግፍ አድርገው በመተዋቸውም የበላቸው ጅብ አልጮህ ይላል፤ ጠፍተውም ይቀራሉ፡፡ ይህ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግ ጉዳይ በመሆኑ በመንፈሳዊ ሕይወት አልፈዋልና መፍትሔውን ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር በመነጋገር በሰከነ መንፈስ ማየትና መፍታትን ይጠይቃል፡፡

ግባቸው ሥራ ማግኘት ላይ ብቻ ገድበው ዓላማቸው ሲሳካ የመጡበትንና ያለፉበትን ሕይወት በመርሳት ለአልባሌ ነገር ይጋለጣሉ፡፡ በተለይም ገንዘብ ማግኘታቸው ሁሉን ማድረግ እንደሚችሉ አድርጎ ዲያብሎስ ስለሚያተጋቸው ይህንን ተቋቁመው ማለፍ ባለመቻላቸው ወድቀውና ባክነው ይቀራሉ፡፡ ለቤተሰብ ያለመታዘዝ፣ ክፉንና ደጉን አለመለየት፣ ሁሉንም ነገር ሞክሬ ካላየሁ የሚል ስሜት ውስጥ በመግባት ሕይወታቸውን ያበላሻሉ፡፡ አንድ ጊዜ ከገቡ መውጣት ስለሚቸገሩም ከቤተ ክርስቲያንም ከአገልግሎትም ይርቃሉ፤ መንፈሳዊነታቸውንም እርግፍ አድርገው ይጥላሉ፡፡

እነዚህ ከላይ ያየናቸው ሁለት ገጽታዎች ጎልተው የሚታዩ ሲሆን ይህንን ችግር ለመፍታት ቤተሰብ ትልቁን ድርሻ ቢወስድም እንደ ተቋም ማኅበረ ቅዱሳን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሰጠችው ኃላፊነት መሠረት በግቢ ጉባኤ ውስጥ አልፈው የተመረቁ ተማሪዎችን ባለው መዋቅር የመከታተል ግዴት አለበት፡፡ በተለይም ከማእከላትና ወረዳ ማእከላት ብዙ ይጠበቃል፡፡

፪. አገልግሎት፡-

አገልግሎት በአንድ ወቅት ብቻ በሕይወት ተተግብሮ የሚጠናቀቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ የአባቶቻችንም ሕይወት እንዲሚያስተምረን እስከ ሕይወት ፍጻሜአቸው ድረስ የሚገጥማቸውን ፈተና ሁሉ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ  ማለፋቸውን ነው፤ ቅዱሳት መጻሕፍትም የሚያስተምሩን ይህንኑ ነው፡፡  “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” እንዲል፡፡(ማቴ. ፳፬፥፲፫)

አገልግሎት ከራስ ይጀምራል፤ ራስን በመንፈሳዊ ሕይወት በማነጽ ለሌሎች ብርሃን መሆንን የሚጠይቅ ነው፡፡ ራስን በመንፈሳዊ ሕይወት ከማነጽ ጀምሮ ቤተሰብን፣ ጎረቤትን፣ ማኅበረሰብን፣ ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል ከአንድ መንፈሳዊ ሰው የሚጠበቅ መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወት ባደግን ቁጥር ለአገልግሎት መፋጠናችንም እያደገ ይመጣል፡፡  ከዚህ አንጻር ከግቢ ጉባኤያት ተመርቀው ሲወጡ በሄዱበት ሁሉ ለአገልግሎት ራሳቸውን ማዘጋጀት፣ ከዚህ,ያም አልፎ በጎደለው በኩል በመቆም ክርስቲያናዊ ግዴታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይም ቤተ ክርስቲያን ብዙ ትጠብቅባቸዋለች፡፡

አንዳንዶች ግን በግቢ ጉባኤያት በቂ ዕውቀትን በመቅሰም የጀመሩትን የክርስትና ሕይወት ከምረቃ በኋላ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ ሥራ እስኪያገኙ ድረስ አገልግሎት ላይ ሲዘናጉ እንመለከታቸዋለን፡፡ ያለ መሰልቸት በሥራ አስፈጻሚነትና በተለያዩ የአገልግሎት ክፍሎች እንደ ፀጋቸው ሲያገለግሉ እንዳልነበር ከዚያ ሲወጡ ግን ዕረፍት እንደመውሰድ ወደ ኋላ የሚሉ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ብዙውን ጊዜ ከአገልግሎት ያራቃቸው ምን እንደሆነ ሲጠየቁ ሥራ ማጣት እንደ ምክንያት ሲያቀርቡ ቢደመጡም ሥራ ካገኙም በኋላ ከቤተ ክርስቲያን የሚርቁ ብዙዎች ናቸው፡፡

የአገልግሎት ዓላማና ግብ ምን እንደሆነ የገባቸው ግን ከፊት ይልቅ በመትጋት በማኅበረ ቅዱሳን፣ በሰንበት ትምህርት ቤት፣ በአገልግሎት ማኅበራት በመሳተፍ የተሰጣቸውን ፀጋ በተግባር ሲያውሉም እንመለከታለን፡፡ በአጠቃላይ ሕይወት ከምረቃ በኋላ በአገልግሎት ከፊት ይልቅ በመትጋት ለሌሎች ምሳሌ መሆን የሚችሉ አገልጋዮችም ለቤተ ክርስቲያን ማትረፍ ተችሏል፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን ተቀዳሚ ዓላማም ራሱን በክርስትና በማነጽ፣ ለአገልሎት በመትጋት ለቤተ ክርስቲያን ተስፋ የሚሆናትን ትውልድ ማፍራት ነውና፡፡

፫. ጋብቻ፡-

“መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር ነው” እንዲል (ዕብ. ፲፫፥፬) የሰው ልጆች በእግዚአብሔር ከተሰጣቸው ፀጋዎች አንዱ ጋብቻ ነው፡፡ ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉዋት እንደተባለ ከግቢ ጉባኤ በኋላ ይርዘምም ይጠር ወደ ጋብቻ የመግባት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ጊዜአቸውን በአግባቡ በመጠቀም ለትዳራቸው፣ ለቤተሰባቸው፣ ለማኅበራዊ ሕይወት፣ እንዲሁም ለአገልግሎት በመመደብ በሰንበት ትምህርት ቤት፣ በሰበካ ጉባኤና በመሳሰሉት በመሳተፍ የድርሻቸውን ለመወጣት ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ሁሉንም በአግባቡና በሥርዓቱ በመምራት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የጣለችባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ከበፊት ይልቅ ይተጋሉ፡፡ ለትውልድም አርአያ ይሆናሉ፡፡

በሌላው አቅጣጫ ደግሞ ትዳርን እንደ ምክንያት በማቅረብ ከአገልግሎት የሚርቁ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ይህ እንዳይሆን ትዳር የመጨረሻ ግባቸው ሆኖ እንዳይቀር፣ በአገልግሎት እንዲጸኑ፣ ራሳቸውንም በትምህርት እንዲያሳድጉ፣ በማኅበራዊ ሕይወትም መሳተፍ እንዲያስችላቸው መንገድ ማመቻቸት አስፈላጊ ነው፡፡

አገልግሎት ቢመችም ባይመችም የዘወትር የሕይወት አንድ አካል አድርጎ መመልከት ለዚህም በታማኝትና በቆራጥነት ማገልግል ተገቢ ነው፡፡ ግቢ ጉባኤን በትምህርት ላይ ሳሉ ከዓላማቸው እንዳይዘናጉ ማድረጊያ መንገድ እንደሆነ ብቻ በማሰብ ለመሳተፍ መወሰን እንደ ግብ አድርገው የሚያገለግሉ እንዳሉ የሚታወቅ ቢሆንም ተመርቀው ሲወጡ ቢያንስ ለራሳቸው ጥሩ ክርስቲያን ሆነው እንዲገኙ ማደረጉ አንዱ መልካም ነገር ነው፡፡

፬. ማኅበራዊ ሕወት፡-

ከትምህርት በኋላ በማኅበራዊ ሕይወት መሳተፍ የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሳሉ ትምህርትና አገልግሎት ብቻ ነበር ትኩረት የሚያደርጉት፡፡ ከግቢ ሲወጡ ግን  ከጠባቡ ዓለም ወደ ሰፊው ዓለም የሚሰማሩ በመሆኑ ዓለም በሯን ከፍታ ትጠብቃቸዋለች፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ በማኅበራዊ ሕይወት መሳተፍ ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በሠርግ፣ በለቅሶ፣ የተጣላ በማስታረቅ፣ ከወዳጆች ጋር የሕይወት ልምድ መለዋወጥ፣ በአጠቃላይ ያሉበት ማኅበረሰብ የሚኖረውን ኑሮ የመጋራት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

በዚህ ወቅት በተረጋጋና በሰከነ መንፈስ ለእያንዳንዱ ነገር ትኩረት በመስጠት ሕይወትን መምራት ያስፈልጋል፡፡ በእነዚህ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ምክንያት አገልግሎትን እርግፍ አድርጎ መተው ሳይሆን ቅድሚያ የሚሰጡትን በማስቀደም መትጋት ይገባል፡፡

ዓለም ሰፊ ናት፣ ቀዳዳዎቿም ብዙ ናቸው፡፡ በዚህ ውስጥ ቀልጦ መቅረት ሳይሆን በማስተዋል ሁሉንም በአግባቡና በሥርዓቱ መምራት ተገቢ ነው፡፡

ማጠቃለያ፡-

የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ከተመረቁ በኋላ ሕይወታቸውን እንዴት መምራት እንደሚገባቸው ቆም ብለው ማሰብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይም ለመንፈሳዊ ሕይወት ትልቁን ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ የሚሠሩት ሥራ፣ የሚመሠርቱት ጋብቻ፣ ማኅበራዊ ሕይወት እና የመሳሰሉ ገዳዮች ከመንፈሳዊነት እንዳያስወጣቸው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይገባል፡፡ አንድ ጊዜ ከአገልግሎት በተለይም ከቤተ ክርስቲያን ከራቁ በኋላ ለመመለስ ሲቸገሩ ማየት የተለመደ በመሆኑ ወደዚህ የሕይወት አቅጣጫ እንዳያመሩ ማእከላት፣ ወረዳ ማእከላት፣ ግንኙነት ጣቢያዎች ክትትል የመድረግ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብር በመፍጠር ማበርታት ይገባል፡፡

ዓለም ከመንፈሳዊ ሕይወት እንድንወጣ በሯ ወለል አድርጋ ስለምትቀበለን የሚያቀርብልንን   ሁሉ ወርቅ መስሎን ለመዝገን ከመሮጥ መቆጠብ፣ ክፉንና ደጉን የምንለይበት አእምሮ ተሰጥቶናልና ልናመዛዝን ይገባል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙሩ ዴማስ ዓለምን ናፍቆ ጥሎት እንደሄደ ሲገልጽ በሐዘን ነው፡፡ “ዴማስ ይህን የዛሬውን ዓለም ወድዶ እኔን ተወኝ ወደ ተሰሎንቄም ሄደ” እንዲል(፪ኛ ተሰ.፬፥፲)፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ዋስ ጠበቃ ይሆናሉ ተብለው ታስበው ነገር ግን ዓለም ጠልፋ የጣለቻቸው ብዙዎች እንዳሉ ተገቢ ነው፡፡ ስለዚህ ከግቢ ጉባኤ ተመርቀን ስንወጣ አንደ ክርስቲያን ማሰብ፣ መኖርን፣ በአገልግሎት መሳተፍን እንደ ዓላማ አድርገን ልንወጣ ያስፈልጋል፡፡ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ከልጆቿ ብዙ ትጠብቃለችና ድምጿን ለመስማት፣ የሰማነውንም ለመተግበር መፋጠን ከትውልዱ ይጠበቃል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *