ሕንጸተ ቤተ ክርስቲያን
በኬልቄዶን አውራጃ በቂሣርያ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ያለ እንጨት፣ ያለ ጭቃና ያለ ውኃ በሰኔ ፳ ቀን ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሦስት ድንጋዮች ቤተ ክርስቲያን ያነጸበት ዕለት የከበረ በዓል ነው፡፡
ይህም የሆነው ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ በርናባስ ወደ ፊልጵስዩስ ገብተው በክርስቶስ ስም አሳምነው ብዙ አሕዛብን ካጠመቁ በኋላ ቤተ ክርስቲያን ሊሠሩላቸው ፈልገው በተነሡበት ጊዜ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያኗንም ለመሥራትም ለርእሰ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ መልእክት ላኩበት፡፡ ከቅዱስ ጳውሎስ እና ቅዱስ በርናባስ ጋር በኢየሩሳሌም ተገናኙ፤ ቅዱስ ዮሐንስም ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር አብሮ መጥቶ ነበር፡፡
በዚያም በአንድነት ሱባዔ ይዘው በለመኑት ጊዜ ጌታችን የሞቱትን አስነሥቶ፣ ያሉትንም ጠርቶና ቅዱሳን ሐዋርያትን በፊልጵስዩስ ሀገር ሰብስቦ “በእናቴ በድንግል ማርያም ስም ከጽንፍ እስከ ጽንፍ የሚሠራውን የአብያተ ክርስቲያናት ሥራ ላሳያችሁ፤ ሥርዓቱንም ላስተምራችሁ ሰብስቢያችኋለሁ” ብሎ ወደ ምሥራቅ ይዟቸው ወጣ፡፡ (መጽሐፈ ሥንክሳር ሰኔ ፳ ቀን)
በዚያ ሥፍራ የነበሩትን ሦስት ድንጋዮችንም የተራራቁትን አቀራርቦ፣ ጥቃቅኑን ታላላቅ አድርጎ ቁመቱን በ፳፬ ወርዱን በ፲፪ ክንድ ለክቶ ለቅዱሳን ሐዋርያት ሰጣቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት ድንጋዩ በእጃቸው ላይ እየተሳለ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን ሠርተው ፈጽመውታል፡፡ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑም የተሠራው ጌታችን በዐረገ በ፲፱ኛው፣ እመቤታችን በዐረገች በ፬ኛው ዓመት ሰኔ ፳ ቀን ሲሆን በማግሥቱ በ፳፩ኛው ቀን ኅብስት ሰማያዊ፣ ጽዋዕ ሰማያዊ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ወረደ፡፡ ጌታችንም ከእመቤታችን ጋር ከሰማየ ሰማያት መጥቶ እመቤታችንን ታቦት፣ ሐዋርያትን ልዑካን አድርጎ፣ እርሱ ሠራዒ ካህን ሆኖ ቀድሶ አቆረባቸው፡፡
ከዚያም በኋላ “ከዛሬ ጀምሮ እናንተም እንደዚህ አድርጉ” ብሎ አዟቸው በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐርጓል፡፡ የሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ቁመት የ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይ አምሳል ነው፤ ወርዱ ደግሞ የ፲፪ቱ ሐዋርያት ምሳሌ ነው፡፡ አንድም ሦስቱ ድንጋዮች የሥላሴ አምሳል ምሳሌ ናቸው፤ ከታች አቀማመጣቸው ሦስት፣ ከላይ ሕንጻቸው አንድ መሆኑ የሥላሴን ሦስትነትና አንድነት ያስረዳል፡፡ የሠሩት ሦስት ክፍልም የመጀመሪያው ክፍል የታቦተ አዳም፣ ሁለተኛው የታቦተ ሙሴ፣ ሦስተኛው የታቦተ ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ አንድም የሦስቱ ዓለማት ማለትም የጽርሐ አርያም፣ የኢዮር፣ የጠፈር ምሳሌ ነው፡፡ አንድም አንደኛው የኤረር፣ ሁለተኛው የራማ፣ ሦስተኛው የኢዮር አምሳል ነው፡፡ በኤረር፡- መላእክት፣ መኳንንት፣ ሊቃናት፤ በራማ፡- ሥልጣናት፣ መናብርት፣ አርባብ፤ በኢዮር፡- ኃይላት፣ ኪሩቤል፣ ሱራፌል ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ዘጠኙ ነገደ መላእክት የዘጠኙ መዓርጋተ ቤተ ክርስቲያን (መዓርጋተ ክህነት) አምሳል ሲሆኑ ይኸውም መላእክት የመዘምራን፣ የመኳንንት የአናጕንስጢሳውያን፣ ሊቃናት የንፍቀ ዲያቆናት፣ ሥልጣናት የዲያቆናት፣ መናብርት የቀሳውስት፣ አርባብ፣ የቆሞሳት፣ ኃይላት፣ የኤጲስ ቆጶሳት፣ የሱራፌል፣ የጳጳሳት፣ የኪሩቤል እንዲሁም የሊቃነ ጳጳሳት ምሳሌዎች ናቸው፡፡
ይህም በምድር የሚኖሩ ደቂቀ አዳም ከቅዱሳን በቀር ወደ ሰማይ መውጣት እንደማይቻላቸውና ከመዘምራን እስከ ጳጳሳት ድረስ ያሉ ካህናትም ከእነርሱ በላይ ያሉትን መዓርግ መሥራት እንደማይቻላቸው ያስረዳል፡፡ እንደዚሁም መላእክት ወደ ምድር መውረድ እንደሚቻላቸውና ሊቃነ ጳጳሳትም ከእነርሱ በታች ያሉ ካህናትን ተልእኮ መፈጸም እንደሚቻላቸው ያስረዳል፡፡ በጽርሐ አርያም መንበረ ብርሃን፣ ታቦተ ብርሃን፣ መንጦላዕተ ብርሃን እንደዚሁም ፬ ፀወርተ መንበር፣ ፳፬ አጠንተ መንበር (መንበሩን የሚያጥኑ) መላእክት አሉ፡፡ ጽርሐ አርያም የመቅደስ፣ መንበረ ብርሃን የመንበር፣ መንጦላዕተ ብርሃን የቤተ መቅደሱ መጋረጃ፣ ፬ቱ ፀወርተ መንበር የ፬ቱ ሊቃነ ጳጳሳት ወይም የመንበሩ እግሮች፣ ፳፬ቱ አጠንተ መንበር የጳጳሳት (የኤጲስ ቆጶሳት) ምሳሌዎች ናቸው፡፡
ምንጭ፡-መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ ፳ ቀን እንዲሀም መጽሐፈ ታሪክ ወግስ፣ ገጽ ፫፻፵፱-፫፻፶፩
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!