ሕንጸተ ቤተ ክርስቲያን

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው የእመቤታችን ፴፫ በዓላት አንዱ ሰኔ ፳ ቀን በኬልቄዶን አውራጃ በቂሣርያ አገር የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ያለ እንጨት፣ ያለ ጭቃና ያለ ውኃ በሦስት ድንጋዮች በተወደደ ልጇ በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የታነጸበት ዕለት ነው፡፡  

ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ በርናባስ ጌታችን በዐረገ በስምንተኛው ዓመት ለፊልጵስዩስ ሰዎች የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ካስተማሩ በኋላ በክርስቶስ ስም አሳምነው በርካታ አሕዛብን በማጥመቅ ቤተ ክርስቲያን ይሠራላቸው ዘንድ ፈለጉ፡፡ ነገር ግን ጌታችን በሊቀ ሐዋርያነት የሾመው ቅዱስ ጴጥሮስ እያለ እንዴት እኛ ይህንን እናደርጋለን? በማለት ቅዱስ ጴጥሮስ ወደ ፊልጵስዩስ ይመጣ ዘንድ መልእክት ላኩበት፡፡ እርሱም ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር መጥቶ ከቅዱስ ጳውሎስ እና ቅዱስ በርናባስ ጋር በኢየሩሳሌም ተገናኙ፡፡

በዚያም በአንድነት ሱባኤ ይዘው ከቆዩ በኋላ ጌታችን የሞቱትን አስነሥቶ፣ ያሉትንም ከያሉበት ቅዱሳን ሐዋርያትን ጠርቶ በፊልጵስዩስ አገር ሰብስቦ “በእናቴ በድንግል ማርያም ስም ከጽንፍ እስከ ጽንፍ የሚሠሩትን የአብያተ ክርስቲያናት ሥራ

ላሳያችሁ፤ ሥርዓቱንም ላስተምራችሁ”ብሎ ወደ ምሥራቅ ይዟቸው ወጣ፡፡ በዚያም ሥፍራ ተራርቀው የነበሩ ሦስት ደንጊያዎች ነበሩ፡፡ ጌታችንም ሦስቱን የተራራቁ ድንጋዮችን በተአምራት አቀራርቦ አንሥቶ ጎተታቸው፡፡ ድንጋዮቹም እንደ ሰም ተለጠጡ፣ እንደ ግድግዳም ሆኑ፡፡

ቁመቱን በ፳፬፤ ወርዱን በ፲፪ ክንድ ለክቶ ለቅዱሳን ሐዋርያት ሰጣቸው፡፡ የብርሃን ምሰሶ ከሰማይ ወረደ፣ በሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም አምሳያ አድርጎ አነጻት ሁለንተናዋም ተጠናቀቀ፡፡ ዛሬም በዕለተ ዐርብ በዕፀ መስቀል ላይ ጌታችን የተቆረሰውን ቅዱስ ሥጋ፣ ያፈሰሰውን ቅዱስ ደም ቅዱሳን መላእክት በብርሃን ፅዋ ቀድተው በዓለም ሁሉ ረጭተውታል፡፡ ስለሆነም የጌታችን ደም በነጠበባቸው ቦታዎች ሁሉ ላይ ዛሬም ድረስ ቤተ ክርስቲያን ይሠራባቸዋል፡፡  

ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ የተሠራውም ጌታችን በዐረገ በ፲፱ኛው፤ እመቤታችን በዐረገች በ፬ኛው ዓመት ሰኔ ፳ ቀን ሲሆን፣ በ፳፩ኛው ቀን (በማግሥቱ) ኅብስት ሰማያዊ፣ ጽዋዕ ሰማያዊ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ወረደ፡፡ ጌታችንም ከእመቤታችን ጋር በቅዱሳን መላእክት ታጅበው ከሰማየ ሰማያት መጥቶ እመቤታችንን ታቦት፤ እርሱ ሠራዒ ካህን፣ ሐዋርያትን ልዑካን አድርጎ ቀድሶ ካቈረባቸው በኋላ “እምይእዜሰ አንትሙኒ ከመዝ ግበሩ፤ ከዛሬ ጀምሮ እናንተም እንደዚህ አድርጉ”ብሎ አዟቸው በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐርጓል፡፡

የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ቁመት በነገሥታት ዘመን የነበሩ የ፳፬ቱ ነቢያት፣ ወይም የ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይ፤ ወርዱ ደግሞ የ፲፪ቱ ሐዋርያት ምሳሌ ነው፡፡ ሦስቱ ድንጋዮች የሥላሴ አምሳል ሲሆኑ፣ ከታች አቀማመጣቸው ሦስት፤ ከላይ ሕንፃቸው አንድ መሆኑ የሥላሴን ሦስትነትና አንድነት ያመለክታል፡፡ ሐዋርያት የሠሩትም ሦስት ክፍል አድርገው ሲሆን፡- የመጀመሪያው የታቦተ አዳም፤ ሁለተኛው የታቦተ ሙሴ፤ ሦስተኛው የታቦተ ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ዳግመኛም የሦስቱ ዓለማት ማለትም የመጀመሪያው የጽርሐ አርያም፣ ሁለተኛው የኢዮር፣ ሦስተኛው የጠፈር ምሳሌ ነው፡፡

በሌላም በኩል የመጀመሪያው የኤረር፣ ሁለተኛው የራማ፣ ሦስተኛው የኢዮር አምሳል ነው፡፡ በኤረር፡- መላእክት፣ መኳንንት፣ ሊቃናት፤ በራማ፡- ሥልጣናት፣ መናብርት፣ አርባብ፤ በኢዮር፡- ኃይላት፣ ኪሩቤል፣ ሱራፌል ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ዘጠኙ ነገደ መላእክት የዘጠኙ መዓርጋተ ቤተ ክርስቲያን (መዓርጋተ ክህነት) አምሳል ሲሆኑ፣ ይኸውም መላእክት – የመዘምራን፤ መኳንንት – የአናጕንስጢሳውያን፤ ሊቃናት – የንፍቀ ዲያቆናት፤ ሥልጣናት – የዲያቆናት፤ መናብርት – የቀሳውስት፤ አርባብ – የቆሞሳት፤ ኃይላት – የኤጲስ ቆጶሳት፤ ሱራፌል – የጳጳሳት፤ ኪሩቤል – የሊቃነ ጳጳሳት አምሳሎች ናቸው፡፡

በዚህችም ዕለት በቂሣርያው በቅዱስ ባስልዮስ ዘመን እንዲህ ሆነ፡- ቅዱስ ባስልዮስ የእመቤታችንን ቤተ ክርስቲያን ከሠራ በኋላ በውስጧ የሚያኖረውን የእመቤታችንን ሥዕል ሊያሠራ መሳያ ሠሌዳ ፈለገ፡፡ ሰዎችም በአንድ ባለጸጋ ቤት ጥሩ ሠሌዳ እንዳለ ነገሩትና ሄዶ ለባለጸጋው ሠሌዳውን እንዲሰጠው ለመነው፡፡ ባለጸጋውም “የልጆቼ ነው አልሰጥም” አለው፡፡ በትዕቢትም ሆኖ በታነጸቸው ቤተ ክርስቲያን ላይ የስድብን ነገር ተናገረ፡፡ ወዲያውም ወድቆ ክፉ አሟሟት ሞተና ልጆቹ ፈርተው ሠሌዳውን አምጥተው ለባስልዮስ ሰጡት፡፡ እርሱም ያንን ሠሌዳ የእመቤታችንን ሥዕል አሳምሮ ይስልበት ዘንድ ለሠዓሊ ወስዶ ሰጠው፡፡

በዚህም ጊዜ እመቤታችን በራእይ ለቅዱስ ባስልዮስ ተገለጠችለትና ከአመፀኛ ሰው የተገኘ ነውና በዚያ ሰው ሠሌዳ ሥዕሏን እንዳያስል ከለከለችው፡፡ የእመቤታችን ሥዕሏ የተሳለበትን ሠሌዳም የት እንደሚገኝ ነገረችውና ባስልዮስ ሄዶ በታላቅ ክብር አምጥቶ በቤተ ክርስቲያኑ አስቀመጠው፡፡ ከሥዕሏም ሥር ድውያንን ሁሉ የሚፈውስ የዘይት ቅባት መፍሰስ ጀመረ፡፡ በዚህም ብዙዎች ድንቅ የሆነ ፈውስን አገኙ፡፡ የከበረች ሥዕሏ ከተቀመጠበት ምሰሶ ሥር ጸበል ፈለቀና ብዙዎች ተፈወሱ፡፡ ይህም የተፈጸመው የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን በከበረችበት ዕለት በሰኔ ፳፩ ቀን ነው፡፡

ምንጭ፡

  • መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ ፳ ቀን፡፡
  • መጽሐፈ ታሪክ ወግስ፣ መ/ር አፈወርቅ ተክሌ፤ አዲስ አበባ፣ ፳፻፭ ዓ.ም፤ ገጽ ፫፻፵፱ – ፫፻፶፩፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *