“ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ”(ኢዩ.፪፥፲፫)
በእንዳለ ደምስስ
ይህንን ቃል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በነቢዩ ኢዩኤል ላይ አድሮ ልባቸው ለደነደነና ኃጢአት በመሥራት ለሚተጉት አይሁድ የተናገረው ተግሣጽ ነው፡፡ እግዚአብሔር በባሕርይው ታጋሽ፣ ሁሉን ቻይ ሲሆን ስለ በደላቸው ብዛት ማጥፋት ሲችል ይመለሱ ዘንድ ከመካከላቸው ነቢያትን እያስነሣ ሲገስጻቸው እንመለከታለን፡፡ ስለ ኃጢአታቸው ተጸጸተው ወደ እርሱ ለሚጮኹ፣ ልብሳቸውን ሳይሆን ልባቸውን ለሚቀዱ ራሳቸውን ለአምላካቸው አሳልፈው ለሚሠጡ ደግሞ ምሕረቱ ቅርብ ነውና በዘመኑ ነቢየ እግዚአብሔር ኢዩኤልን አስነስቶ “አሁንስ ይላል አምላከችሁ እግዚአብሔር፣ በፍጹም ልባችሁ በጾም፣ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ፡፡ ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር በሓሪና ይቅር ባይ፣ ቁጣው የዘገየ ምሕረቱም የበዛ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ” እያለ ሰብኳቸዋል፡፡(ኢዩ.፪፥፲፪)፡፡
ሕዝቡም ልባቸው የደነደነ፣ ለጽድቅ የዘገዩ ቢሆኑም ነቢዩ ኢዩኤል ከእግዚአብሔር የታዘዘውን ከመናገር ወደ ኋላ አላለም፡፡ የእግዚአብሔርን ምሕረትና ቸርነትን ዘንግተው ራሳቸውን ለዓለም አሳልፈው በመስጠት ለኃጢአት በመንበርከካቸው ፈጣሪያቸውን አሳዘኑ፡፡ እግዚአብሔር ግን በየዘመናቱ ወደ እርሱ የቀረቡትንና የተመረጡትን ሰዎችን እያስነሳ ከሚመጣው መቅሰፍት ሕዝቡ ያመልጡ ዘንድ፣ ምድሪቱም ከበደላቸው ታርፍ ዘንድ ነቢዩን ልኮላቸዋል፡፡ “በጽዮን መለከትን ንፉ፣ ጾምንም ቀድሱ፣ ምሕላንም ዐውጁ፣ ሕዝቡንም ሰብስቡ፣ ማኅበሩንም ቀድሱ፣ ሽማግሌዎችንም ጥሩ፣ ጡት የሚጠቡትንና ሕፃናትን ሰብስቡ፣ ሙሽራው ከእልፍኙ ሙሽራይቱም ከጫጉላዋ ይውጡ” እያለ ወደ እግዚአብሔር እንዲጮኹ ነግሯቸዋል፡፡ (ኢዩ.፪፥፲፫)፡፡ እግዚአብሔርም ሕዝቡ በፍጹም ልባቸው መጸጸታቸውንና በነቢዩ ተግሣጽ ልባቸውን ወደ እርሱ እንደመለሱ በተመለከተ ጊዜ ስለ ሕዝቡ ራርቷል፤ ምሕረቱንም በምድሪቱ ላይ አፍስሷል፡፡
በሊቀ ነቢያት ሙሴ ዘመንም እግዚአብሔር ሕዝቤ ያላቸው እስራኤላውያን በግብፅ ምድር በባርነት ሲሰቃዩ ከኖሩበት ዐራት መቶ ሠላሳ ዘመን በኋላ በግብፃውያን ላይ ዐሥር ተአምራትን ከፈጸመ በኋላ፣ በዐሥራ አንደኛው ባሕረ ኤርትራን ከፍሎ አሻግሯቸዋል፡፡ እስራኤላውያን “ሕዝቤ” እያለ ይጠራቸው የነበሩት ፈጣሪያቸውን ረስተው በበደል ረክሰው በተመለከተ ጊዜ ሙሴን እያመለከተ ቁጣው በነደደ ጊዜ “ሕዝብህ” እያለ ጠርቷቸዋል፡፡ “እግዚአብሔር ሙሴን ተናገረው እንዲህም አለው፡- ‘ከግብፅ ምድር ያወጣኻቸው ሕዝብህ በድለዋልና ሂድ፣ ፈጥነህ ውረድ፡፡ ካዘዝኋቸው መንገድ ፈጥነው ፈቀቅ አሉ”(ዘጸ.፴፪፥፯) እንዲል፡፡
ከሥነ ፍጥረት ጀምሮ ብንመረምር የሰው ልጆች ያልበደሉበት ጊዜ የለም፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ቁጣውን በትዕግሥት፣ ሕዝቡን በንስሓ እየመለሰ የመጣውን መቅሰፍት አሳልፎ የምሕረት እጆቹን ዘርግቶ ተቀብሏቸዋል፡፡ “የእግዚአብሔርም አገልጋዮች ካህናት በወለሉና በምስዋዑ መካከል እያለቀሱ ‘አቤቱ ለሕዝብህ ራራ፤ አሕዛብም ይገዙአቸው ዘንድ ርስትህን ለማላገጫ አሳልፈህ አትስጥ፣ ከአሕዛብም መካከል አምላካቸው ወዴት ነው? ስለምን ይላሉ’ ይበሉ፡፡ እግዚአብሔርም ስለ ምድሩ ቀና፤ ለሕዝቡም ራራለት” በማለት እግዚአብሔር ፍጹም መሐሪና ቸር እንደሆነ ይነግረናል፡፡ (ኢዩ.፪፥፲፯-፲፰)፡፡ ሕዝቡንና ምድሪቱን በምሕረት ጎብኝቷልና፡፡
የነነዌ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ክፋትን አደረጉ፣ የእግዚአብሔርም ቁጣ ነደደ፣ ነገር ግን ለፈጠረውና የእጁ ሥራ ለሆነው ለሰው ልጅ እግዚአብሔር ይራራልና ነቢዩ ዮናስን አስነሳላቸው፡፡ ነቢዩ ዮናስ የነነዌ ሰዎችን ልበ ደንዳናነት፣ ጽድቅን ከመሥራት ራሳቸውን ያራቁና ለዓለም ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ መሆናቸውን ያውቃልና “የእግዚአብሔር ቃል ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ እንዲህ ሲል መጣ፡- “ተነሥተህ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፤ የክፋታቸውም ጩኸት ወደ ፊቴ ወጥቷልና ለእነርሱ ስበክ” የሚለውን ቃል ሲሰማ፡፡ ነገር ግን ዮናስ የታዘዘውን ማድረግ አልፈለገም፡፡(ዮና.፩፥፩-፪)፡፡ ለራሱ ክብር ተጨንቋልና፣ ዞሬ ብሰብክም አይሰሙኝም ይህን ከማይ ሐሰተኛ እንዳልባል በሚል ከእግዚአብሔር ፊት መኮብለልን ምርጫው አደረገ፡፡ ካለበት ተነሥቶም ወደ ተርሴስ በመርከብ ይጓዝ ዘንድ ወደደ፡፡ ቅዱስ ዳዊት “ወደ ሰማይ ብወጣ አንተ በዚያ አለህ፤ ወደ ጥልቁም ብወርድ አንተ በዚያ አለህ” እንዲል (መዝ.፻፴፱፥፰)፡፡ እግዚአብሔር በሁሉ የመላ መሆኑን ዘንግቶ መኮብለልን መረጠ፡፡ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ሸሽቶ ማመለጥ የሚችል የለምና በዓሣ አንበሪ ሆድ ውስጥ ለሦስት ቀንና መዓልት አሳርፎት ወደ ነነዌ እንደወሰደው መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ እግዚአብሔር ቃሉ አይታጠፍም፣ ላያደርገው አይናገርምና በነነዌ ምድር ስላሉት ንጹሐን ስለሆኑት ሕፃናትና እንስሳት እንዲሁም ምድሪቱ ይራራልና የታዘዘውን ይፈጽም ዘንድ “ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፣ የነገርኩህንም የመጀመሪያውን ስብከት ስበክላት” አለው፡፡ ነቢዩ ዮናስ በዚህ ወቅት ነው ከእግዚአብሔር ሸሽቶ ማምለጥ እንደማይቻል የተረዳው፡፡ ምርጫ አልነበረውምና ወደ ነነዌ ምድር ሄዶ የታዘዘውን ፈጸመ፡፡ ሕዝቡም በዮናስ ስብከት አማካይነት ለሦስት ቀናት ጾሙ፣ ጸለዩ፣ ንስሓም ገቡ፡፡ ቸር የሆነው እግዚአብሔር ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ሊመጣ ያለውን ጥፋት ወደ ምሕረት ለውጦታል፡፡
ዛሬ በሀገራችን ከነነዌ ሰዎች የባሰ ኃጢአት ነግሶ ወንድም በወንድሙ ተጨካክኖ ሲገዳደል ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ትላንት በታሪክ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ እንዳነበብነው በገሐድ ሞት፣ ስደትና መከራ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ሲፈጸም እያየን ነው፡፡ ኃጢአታችን ከሰዶምና ገሞራ ከፍቶ በአደባባይ ኃጢአትን መሥራት እንደ ነውር መቆጠር የቀረ እስኪመስል ድረስ ቆሽሸናል፡፡ የነነዌ ክርስቲያኖችን በአኒዩ ዮናስ አድሮ እንደገሰጻቸው እኛንም የሚገስጽ፣ ወደ ትክክለኛው መንገድ የሚመራን ያስፈልገናል፡፡ እኛም ወደ ጽድቅ ጎዳና ልናመራ፣ ክፍውንም ልንጠየፍ፣ ኃጢአትንም ከመሥራት ልንቆጠብ ያስፈልጋል፡፡
ነቢየ እግዚአብሔር ኢዩኤል “ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ” እንዲል በተሰበረ ልብ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፣ ጽድቅንም እንከተል፡፡ ለቅደስት ቤተ ክርስቲያናችን ሰላምን፣ ለሕዝቡም ፍቅር አንድነትን ያድልልን፡፡ አሜን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!