“ለፍጥረትም ሁሉ ወንጌልን ስበኩ” (ማር. ፲፮፥፲፭)
በእንዳለ ደምስስ
ይህንን ቃል ለደቀ መዛሙርቱ የተናገረው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን በሞቱ ድል አድርጎ ከተነሣ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጠው በሌሊት ፈጥነው ወደ መቃብሩ ላመሩት ለመግደላዊት ማርያም እና እርሷን ተከትለው ለመጡት ሴቶች ነበር፡፡ ወደ መቃብሩም በደረሱ ጊዜ ሁለት መላእክት ተገልጠውላቸው መግደላዊት ማርያምን “አንቺ ሴት ምን ያስለቅስሻል?” አሏት፡፡ እርስዋም “ጌታዬን ከመቃብር ውስጥ ወስደውታል፤ ወዴትም እንደወሰዱት አላውቅም” አለቻቸው፡፡
ይህን ተናግራ ወደ ኋላዋ መለስ ስትል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ቆሞ አየችው፡፡ ጌታችን ኢየሱስም እንደሆነ አላወቀችም፡፡ … “አትንኪኝ፤ ወደ አባቴ አላረግሁምና ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሂጂና ወደ አባቴ ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬ ወደ አምላካችሁም አርጋለሁ አለ ብለሽ ንገሪያቸው” አላት፡፡
ማርያም መግደላዊት እና ሴቶቹም ፈጥነው ሄደው ሐዋርያት ተስፋ ቆርጠው በአንድነት ተሰብስበው እያዘኑና እያለቀሱ ሳሉ መግደላዊት ማርያም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መነሣት የምሥራች ነገረቻቸው፡፡ ነገር ግን አላመኗትም፤ ተረትም መሰላቸው፡፡ ሉቃስ እና ቀለዮጳም ተስፋ ቆርጠው ወደ ኤማሁስ ሲሄዱ እንደተገለጠላቸው ለሐዋርያቱ ምሥክርነት ቢሰጡም ሊያምኑ አልቻሉም፡፡ ከዚህ በኋላ ዐሥራ አንዱ ሐዋርያት በሐዘንና በትካዜ ውስጥ ሆነው ሳሉ ጌታችም መድኃኒታችን ኢሱስ ክርስቶስ በመካከላቸው ተገኝቶ ራሱን ገለጠላቸው፡፡
በመጨረሻም “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፣ ለፍጥረትም ሁሉ ወንጌልን ስበኩ” በማለት ከተናገራቸው በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ (ማር. ፲፮፥፲፭፤ ማቴ. ፳፰፥፩-፲፤ ሉቃ. ፳፬፥፩-፳፯)፡፡
ይህ ትእዛዝ ለሐዋርያት ብቻ ሳይሆን ከእነርሱ በኋላ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ለሚነሡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ መምህራንና ቃሉን ሰምተው አምነው ለሚያስተምሩ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዋስ ጠበቃ ለሆኑ ሁሉ ነው፡፡ “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን ያመሰግኑ ዘንድ እንዲሁ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ” ተብሎ እንደተጻፈ ጨለማውን ዓለም በወንጌል ብርሃንነት ተመርተው እንቅፋቱን ሁሉ ማስወገድ፣ እንደሚገባ ያስገነዝበናል፡፡ (ማቴ. ፭፥፲፬-፲፮)
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ያሳድድ፣ ይገርፍና ያሠቃይ እንደነበር፤ ከዚያም አልፎ ሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስን አይሁድ በድንጋይ ሲወግሩት የገራፊዎችን ልብስ እስከ መጠበቅ የደረሰ እንደ ነበር ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡ ነገር ግን ያ ሁሉ አልፎ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ምርጥ ዕቃ” እስከ መሆን ደርሷል፡፡ “ተነሥና ሂድ፤ በአሕዛብና በነገሥታት በእስራኤል ልጆችም ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ አድርጌዋለሁና” እንዲል፡፡ ሳውል የተባለው ቅዱስ ጳውሎስም ወንጌል በዓለም ሁሉ ይዳረስ ዘንድ ሳይታክት እያስተማረና እየገሠጸ በአገልግሎቱ ጸንቶ ሰማዕትነትን እስኪቀበል ድረስ ለአምላኩ ታምኗል፡፡ (ሐዋ. ፯፥፶፬-፷፤ ፱፥፲፭)
የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ሆነን የእግዚአብሔር ማዕድ ከመደበኛው ትምህርት በተጨማሪ ተዘርግቶ ይጠብቀናል፡፡ በተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ጊዜአችንን ብቻ መሥዋዕት በማድረግ የእግዚአብሔርን ቃል ለመማር የሚያቅተን ብዙዎች ነን፡፡ ለመማር ፈቃደኞች ሆነን ብንመጣም ከግቢ ተመርቀን ስንወጣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በክብር እንደተቀበለችን በክብር በአባቶች ቡራኬና መስቀል ባርካ ወደ ዓለም ስትልከን ስንቶቻችን እንሆን የተሰጠንን አደራ የምንወጣው?
ከግቢ ወጥተን ወደ ማኅበረሰቡ ስንቀላል ዓለም የራሷን ዝግጅት አድርጋ ትጠብቀናለች፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም “ልጆቼ ኑ፣ የሰጠኋችሁን አደራ ትወጡ ዘንድ ጊዜው ደርሷልና በደረሳችሁበት ሁሉ መልካም የሆነውን አድርጉ” ትለናለች፡፡ የትኛውን ነው የምንመርጠው? እንደ ዴማስ መኮብለለን ወይስ እንደ ጢሞቴዎስ ታምኖ ማገልገል? ጢሞቴዎስ ወንጌሉን ከማን እንደተማረ ያውቃልና ለአምላኩም፣ ለመምህሩም ታምኖ ተገኘ፡፡ “አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፤ ከማን እንደተማርኸው ታወቃለህና፡፡” ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ (፪ኛጢሞ.፫፥፲፬)
መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ፡- ዘሪ ዘሩን ሊዘራ ወጣ፤ አንዱም ዘር በመንገድ ላይ ወደቀና ተረገጠ፣ ሌላውም በጭንጫ መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ ወዲያው ደረቀ፤ ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፣ በአደገም ጊዜ እሾሁ አነቀውና ደረቀ፡፡ “በመልካም መሬት ላይ የወደቀ ዘርም ነበረ፡፡ በበቀለም ጊዜ መቶ እጥፍ አፈራ” ይለናል፡፡ በተሰማራንበት ሁሉ መሬት የተባለውን የሰዎችን ልብ አለምልመን ዘር የተባለውን የእግዚአብሔርን ቃል የምንዘራ የወንጌል ገበሬዎች ሆነን መገኘት ይጠበቅብናል፡፡ (ሉቃ. ፰፥፬-፰)፡፡
በግቢ ጉባኤያት ሳለን መንፈሳዊውን ዕውቀት ለመገብየት እንሮጥ እንደነበረው ሁሉ ዕውቀትን ከእምነት ጋር አዋሕደን ወደ ዓለም ስንሰማራ ከቀደመው ይልቅ መትጋት፣ ለገባነውም ቃል ታማኞች ሆነን መገኘት ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም ኦርቶዶክሳውያን ተመራቂዎች ሕይወታችንን በቃለ እግዚአብሔር በማነጽ በተሰማራንበት ሁሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ባሏት መዋቅሮች ውስጥ ገብተን ቃለ እግዚአብሔርን መማርና ማስተማርን የሥራችን አንድ አካል ልናደርግ ይገባል፡፡
ጌታችን በወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ወንጌል “ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ያጠፋታል፤ ሰውነቱን ስለ እኔና ስለ ወንጌል የሚያጠፋትም ያገኛታል፡፡ ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ለሰው ምን ይጠቅመዋል?” በማለት እንደገለጸው በተሰማራንበት ሁሉ ከፊታችን የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ሁሉ በመቋቋም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለሰጠችን አደራ ታምነን ነፍሳችንን ማዳን፤ ለሌሎችም ብርሃን ሆነን የእግዚአብሔር መንግሥት ወራሾች እንሆን ዘንድ ዘወትር መትጋት ይጠበቅብናል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!