“ለግቢ ጉባኤ ትምህርቴ የመደበኛው ትምህርቴን ያህል ትኩረት ስሰጠው ነበር፡፡” (ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ አበበ)
ክፍል ሁለት
በእንዳለ ደምስስ
ጉባኤ ቃና፡- በርካታ ተማሪዎች መደበኛ ትምህርቱንና የግቢ ጉባኤ ትምህርትን አጣጥሞ ለመቀጠል የጊዜ እጥረት ሊገጥመን ይችላል የሚል ስጋት ያድርባቸዋል፡፡ የእርስዎን ተሞክሮ ቢያካፍሉን?
ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡- አንድ ሰው ሊያደርገው የሚገባውን ነገር አስቦና አምኖበት የሚያደርግ ከሆነ በምንም ነገር ሊቸገር አይችልም፡፡ ችግር እንኳን ቢገጥመው ተቋቁሞት ያልፈዋል እንጂ ላመነበት ነገር ወደ ኋላ ማለት የለበትም፡፡ መደበኛውም ሆነ የግቢ ጉባኤ ትምህርቱ በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው ለእኔ፡፡ የመደበኛው የትምህርት ሰዓቴን በአግባቡ ነው የምጠቀመው፡፡ በዚህ ጊዜ ወደ አገልግሎት አልሄድም፡፡ ሁለቱንም የየራሳቸው ሰዓት መድቤ ነው የማከናውነው፡፡ ለመንፈሳዊው ትምህርት እንዲሁም ለአገልግሎት በመደብኩት ሰዓት በምንም ምክንያት ወደ መደበኛው ትምህርቴ አላተኩርም፡፡ ሁለቱ ተጋጭተውብኝ አያውቁም፡፡ ተማሪዎች ስሕተት ውስጥ የሚገቡት ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ ለማከናወን መሞከራቸው ነው፡፡ በተለይ የዚህ ዘመን ትውልድ ሁሉም ነገር ያምረዋል፡፡ ፊልም ማየቱ፣ መንፈሳዊ ትምህርቱ፣ ኳስ ጨዋታው፣ ከጓደኖች ጋር በሳቅ በጨዋታ ማሳለፍ፣ በመደበኛ ትምህርቱ ውጤታማ መሆንን … ያምታቱታል፡፡ ለእያንዳንዱ ነገር ጊዜ አይመድቡለትም፡፡ ይህ ደግሞ የሚሆነው ጥርት ያለ ግብ ስለሌላቸው ነው፡፡
በእርግጥ መጀመሪያ ሰው መሆን ይቀድማል፡፡ እኔ እውነተኛ ሰው መሆን እፈልጋለሁ፡፡ የትምህርቴ ግብ ደግሞ ጥሩ ተማሪ፣ ጥሩ ሐኪም መሆን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ማንነቴን የሚያንጽልኝ የግቢ ጉባኤ አገልግሎትና መደበኛው ትምህርቴ ናቸው የሚል እምነት በውስጤ አሳድሬያለሁ፡፡ የግቢ ጉባኤ ትምህርቴን የመደበኛው ትምህርቴን ያህል ትኩረት የምሰጠው ጉዳይ ነው ምናልባትም ሳላስበልጠው አልቀርም፡፡ ያ ማለት ሁለቱን አምታታለሁ ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ሄዶ መማርን፣ መጸለይን፣ ማገልገልን እንደ መደበኛ ትምህርቴ ዋጋ ሰጥቼዋለሁ፡፡ በትምህርቴ ደግሞ ድርድር አላውቅም፡፡ የዕረፍት ጊዜ የሚባል ነገር ኖሮኝ አያውቅም፡፡ ለእኔ መደበኛ ትምህርቴ ላይ ካልሆንኩ ቤተ ክርስቲያን ነኝ ማለት ነው፡፡ አለበለዚያ ከቤተሰቦቼ ጋር ነው የምሆነው፡፡ ስለዚህ ተማሪዎች የወደፊት ግባቸውን ማሰብና ለዚያም የሚገባቸውን መሥዋዕትነት መክፈል ይገባቸዋል፡፡
ጉባኤ ቃና፡- በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ በእናንተ ዘመንና አሁን ያለውን ትውልድ የአገልግሎት ትጋት በማነጻጸር ቢገልጹልን?
ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡- ድሮ በነበረው ሁኔታ ዛሬ ላይ ያሉት የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች እንዲያልፉ አይጠበቅባቸውም፤ በትናንት መለካት የለባቸውም፡፡ ቀድሞ የነበረውና አሁን ያለው የአገልግሎት መንፈስ የተለያየ ነው፡፡ እኛ ግቢ ጉባኤ ስንገባ የጅማ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን በደሳሳ መቃኞ ውስጥ ነበረች፤ አዳራሽ አልነበረንም፡፡ ከእኛ በፊት ገብተው የነበሩ ታላላቅ ወንድሞቻችን እኛን ለማስተማርና የተቀናጀ አገልግሎት ለመስጠት ይሰበሰቡባት የነበረችው ቤት አነስተኛ ስትሆን የከብቶች እዳሪ እየለቀለቁና እያጸዱ ይጠቀሙበት ነበር፡፡ እኛ ደግሞ መማሪያ አዳራሽ ያስፈልገናል አልን፡፡ ስለዚህ ቅድሚያ ሰጥተን አዳራሽ መሥራት ወደሚለው ስላዘነበልን አዳራሹን ለመሥራት ቻልን፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ የአጥቢያው ምእመናንን ጨምረን በማስተባበር ቤተ ክርስቲያኑን ለምን አንሠራም ብለን ተነሣሣን፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የእናታችን ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያንን ለማሠራት በቃን፡፡ አሁን ያሉት ተማሪዎች ግን ይህ ሁሉ አይጠበቅባቸውም፡፡ ሊገጥማቸው የሚችለው ችግር ከእነርሱ በፊት በነበሩ ወንድሞች ተፈትቶ ስለሚያገኙት በቀላሉ አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የቀድሞው አገልግሎት በርካታ ውጣ ውረድ ይበዛበት ነበር፡፡
በዚህ ዘመን የሚጠበቅባቸው ነገር ቢኖር መንፈሳዊ ሕይወታቸው ላይ መሥራትና ዓለሙን አሸንፈው በትምህርታቸውም በመንፈሳዊ ሕይወታቸውም ውጤታማ ሆነው እንዲወጡና ሙሉ ሰው እንዲሆኑ ነው፡፡ ሁሉም ነገር የተሟላላቸው ስለሆነ የተዘጋጀ ምግብን አንስቶ የመጉረስ ያህል ነው፡፡ አዳራሽ፣ ወይም ቤተ ክርሰቲያን እንሥራ አይሉም የተዘጋጀውን መንፈሳዊ ማዕድ ላይ መሳተፍ ብቻ ነው የሚጠበቅባቸው፡፡
በእኛ ዘመን ከነበርንበት ግቢ ቢያንስ እስከ ፻፶ ኪሎ ሜትር ድረስ በእግራችን እየተጓዝን በዙሪያው ያሉትን አብያተ ክርስቲያናት እናገለግል ነበር፡፡ ከእኛ በፊት የነበሩት ወንድሞቻችን እኛንም እያስከተሉ ቅዳሜና እሑድ ጋምቤላ፣ መቱ፣ ወልቂጤ ድረስ እየሄድን ነበር የምናገለግለው፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን በማቋቋምና ቃለ እግዚአብሔርን በማስተማር እንተጋ ነበር፡፡ ከሰንበት ትምህርት ቤቶች ጋር የቀረበ ግንኙነት በመፍጠር ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ጥረት እናደርግ ነበር፡፡
የሰንበት ትምህርት ቤት አገልግሎትን በተመለከተም በጅማ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ሰንበት ትምህርት ቤት ሥር በሌሎች ሰንበት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያልተሞከረ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ክፍል በሚል ተጠሪነቱ ለሰንበት ትምህርት ቤቱ የሆነ ራሱን የቻለ ዋና ክፍል እንዲቋቋም አደረግን፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ከሌሎች ወንድሞችና እኅቶች ጋር በመሆን አገልግሎት ውስጥ በስፋት በመሳተፍ ሰንበት ትምህርት ቤቱንና ግቢ ጉባኤውን የማስተሳሰርና የተቀናጀ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ችለናል፡፡
በዚህ ዘመን በተለይ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ስማርት ስልኮች፣ ላፕ ቶፕ ኮምፒዩተሮች በቀላሉ በእያንዳንዱ ተማሪ እጅ ስለሚገኙ ተማሪዎች በስልኮቻቸው ላይ እየተጠመዱ ረጅም ሰዓት ቢጠቅማቸውም ባይጠቅማቸውም ያሳልፋሉ፡፡ ይህ ደግሞ ከዓላማቸው ወደ ኋላ እንዲሉና ለትምህርታቸውና ለአገልግሎት የሚሰጡትን ጊዜ እንዲያጡ ያደርጋቸዋል፡፡ ሐሳባቸውን ከሚከፋፍል ድርጊት መቆጠብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በግቢ ጉባኤ ውስጥ ተሳተፉም አልተሳተፉም ለመጡበት ዓላማ ታማኞች መሆን አለባቸው፡፡ ጠንክሮ መማር ያስፈልጋል፡፡
ጉባኤ ቃና፡- በግቢ ጉባኤያት አማካይነት ከእናንተ በፊት አዳራሽና ቤተ ክርስቲያን የመሥራት እንቅስቃሴ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ ሐሳቡ እንዴት መነጨ?
ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡- ሐሳቡ እኛ ያሰብነው ሐሳብ አይደለም፡፡ ከእኛ በፊት ገብተው የነበሩ ታላላቅ ወንድሞቻችን ሐሳብ ነው፡፡ ለአገልግሎት ምቹ አልነበረም፡፡ ቅድም እንደገለጽኩት ቤተ ክርስቲያኑ በመቃኞ ነው የነበረው ያለው፣ በዚህ ላይ በጣም ትንሽ ነበር፡፡ በወቅቱ እናድሰው የሚል ሐሳብ ቢኖርም እንደ አዲስ መሥራት የተሻለ እንደሆነ ታምኖበት እኔ ሁለተኛ ዓመት ሆኜ ገንዘብ ማሰባሰብ ተጀመረ፡፡ በወቅቱ የነበሩ አንድ ኢንጂነር ቤተ ንጉሥ የሚባለው ቤተ ክርስቲያን ዲዛይን ሠርተውልን ነበር፡፡ የተሠራው ዲዛይን አነስተኛ ቢሆንም ተማሪው ብቻ ሳይሆን የአጥቢያው ምእመናንም ቁጭት ስለነበር ሁሉም የተቻለውን ጥረት ማድረግ ቀጠለ፡፡ ነገር ግን ለተወሰኑ ዓመታት ሥራው ሳይጀመር ቀረ፣ እኔም ተመረቅሁ፡፡ እኔ ዕድለኛ ሆኜም በነበረኝ ከፍተኛ ውጤት ምክንያት እዚያው ለሁለት ዓመታት እንድሠራ ስለተመደብኩ ከምረቃ በኋላ ግንባታው ተጀመረ፡፡ የሕንጻ አሠሪው ኮሚቴም አባል ነበርኩ፡፡ የደብሩ አስተዳደርና ሰበካ ጉባኤው በጣም ያከብሩንና የምናቀርበውን ሐሳብ የማድመጥ፣ ተግባራዊም ለማድረግ ወደ ኋላ የማይሉ ነበሩ፡፡ እኛም እንታዘዛቸው ነበር፡፡ ዲዛይኑን የማሠራት ኃላፊነት ተሰጥቶን ስለነበር ወደ አዲስ አበባ ከአስተዳዳሪው ጋር መጥተን ማኅበረ ቅዱሳን ሠርቶ እንዲያቀርብ አደረግን፡፡
የሚያግዙን ከአምስት ኪሎ ኢንጂነሪንግ የተመረቁ ወንድሞችም ወደ ጅማ መጡ፤ ተጨማሪም ኃይል ሆኑን፡፡ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያኗን የሚሠራላትን ሰው አሰባሰበች ማለት እንችላለን፡፡ በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ቤተ ክርሰቲያኑ ተሠራ፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለሆነ እንጂ የእኛ መሰባሰብ ብቻ እንዲሠራ አላደረገውም፡፡ በጣም ጥሩ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለማነጽ ቻልን፡፡
ይቆየን
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!