“ለንስሓ የሚገባ ፍሬ አድርጉ።” (ማቴ. ፫፥፰)

በደሳለኝ ብርሃኑ

ክፍል ሁለት

የንስሓ እንቅፋቶች

፩. ኃጢአትንና ጽድቅን ለይቶ አለማወቅ:- ድንቁርና ጨለማ ነው። ኃጢአት በውኃ ይመሰላል፣ ውኃ የተኛበት መሬት ከስር ምን እንዳለ እንደማይታወቅ የኃጢአት ውኃ የተኛበትም ሰው ኃጢአቱ ከእርሱ እስኪወገድ ድረስ ምንም አያውቅም። ኃጢአት ልብን ይደፍናል። “ሕዝቤ ዕውቀት ከማጣት የተነሣ ጠፋ” (ሆሴ. ፬) እንዳለው ነቢዩ ኃጢአትና ጽድቅን ለይቶ አለማወቅ የንስሓን በር ይዘጋብናል። ቅዱስ ጳውሎስ ከመመለሱ በፊት መልካም የሠራ እየመሰለው ከአይሁድ ጋር ክርስቲያኖችን ያሳድድ ነበር፣ በኋላ ግን ይህንን የልጅነትን(የአላዋቂነትን) ጠባይ ሽሯል። እግዚአብሔር አንድ የመዳኛ መንገድ ይፈልጋል፣ ምክንያት ፈልጎ ያድናል። ሰው ስለተማረ ብቻ ጽድቅን መሥራት አይችልም፤ በተጨማሪም ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ያስፈልጋል። ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደተናገረው “ክርስቲያን ክርስቲያን ካልሆኑት ሰዎች የሚለየው የሚጠቅመውን እና የማይጠቅመውን ለይቶ ማወቁ ነው፡፡” በኃጢአት ውስጥ ያለ ሰው እንደታመመ፣ ኃጢአት እየሠራ መሆኑን ሊያውቀው ይገባል።

፪. ለራስ ይቅርታ ማድረግ:- ሰው ራሱን መካድ አለበት እንጂ ለራሱ ይቅርታ ማድረግ የለበትም። “እኔን ሊከተል የሚወድ ራሱን ይካድ” (ማቴ. ፲፮፥፳፬። ከእኛ በላይ ለራሳችን የሚያዝነው እግዚአብሔር ነው እንጂ እኛ ለራሳችን ልናዝን አይገባም። ለራስ ይቅርታ ማድረግ ከቀድሞ አሁን ተሻሽያለሁ ማለትና ራስን ማጽደቅ ነው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ጥቂት እንደበደልክ አትንገረኝ። የኃጢአት ጠባዩ አንድ ነው፣ ልዩነት የለበትም” ይላል። ሰይጣን በዕድሜ፣ በኑሮ ሁኔታ፣ በጓደኛ እና በመሳሰሉት እያሳበበ ኃጢአት ያሠራናል። በኋላ ተመልሰን ንስሓ ልንገባ ስንል ደግሞ ዕድል አይሰጠንም። “ደክሞህ ነው፣ ሰክረህ ነው፣ አጥተህ ነው? መቼም ሰው ነህ ምን ታደርግ? አንተ ከማን ትበልጣለህ? ልጅነት ይዞህ ነው፣ ዕድሜህ ነው ወጣትነት ገፋፍቶህ ነው…” እና የመሳሰሉትን ማደንዘዣዎች እያመለከተው ለኃጢአቱ ጠበቃ እንዲያቆም ያደርገዋል። “ዓይንህ ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሁለት ዓይን ኖሮህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትጣል ይልቅ አንዲት ዓይን ኖራህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል።” (ማቴ. ፲፰፥፱) እንደተባለው ጠቃሚ የሰውነታችን ክፍል እንኳ ሳይቀር እንዲሁም አካላችን የሆነው/ቺው ባል ወይም ሚስት እንኳ የድኅነት መንገዳችን ላይ እንዲቆሙብን አንፈቅድላቸውም። ስለዚህ ለሰይጣን በር ባለመክፈት የሰይጣንን ማታለያዎች ዐውቆ በእምነት መቃወም ይገባል እንጂ ለራስ ይቅርታ እያደረጉ ራስን ማታለል አይገባም።

፫. ራስን ማነጻጸር:- በኑዛዜ ወቅት የራስን ኃጢአት ከሌሎች ሰዎች ኃጢአት ጋር፣ ከዘመኑ ሁኔታ ጋር፣ ቀድሞ ከነበረበት ክፉ ግብር ጋር ማነጻጸር ተገቢ አይደለም። እኔ ገንዘብ ነው የሰረቅኩት አሉ አይደል እንዴ ሰውን የሚገድሉት! እኔ በጠላ ነው የሰከርኩት፤ አሉ አይደል እንዴ በጫት የሚሰክሩት! እኔ ከአንድ ሴት ጋር ነው የወደቅኩት፣ አሉ አይደል ሴቶችን የሚያተራምሱት! ቄሱና መነኩሴው እንደዚህ ይሠሩ የለ! ታዲያ ምእመኑ ይህንን ሁሉ ኃጢአት ሲሠራ እኔ ላይ ሲሆን ለምን እንደ ኃጢአት ይቆጠርብኛል? በማለት ራስን ከንስሓ ማራቅ ለኃጢአት መገዛትን ነው የሚያሳየው፡፡

ሰው የሚፈረድበት በግሉ ነው፣ ሰው ሁሉ የራሱን ሸክም ይሸከማል።  “እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ።” እንዳለው። (ራእ. ዮሐ. ፳፪፥፲፪)። ሰው ከማንም ጋር በኃጢአት ራሱን ማነጻጸር የለበትም። እንደ ቅዱስ ዳዊት ” እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፥ ኃጢአቴም ሁል ጊዜ በፊቴ ነውና።ነውና” ማለት አለበት እንጂ።(መዝ. ፶፥፫)።

፬. በእግዚአብሔርን ቸርነት ማመካኘት:- እግዚአብሔር ንስሓ እንድንገባና ከኃጢአት እንድንላቀቅ ይታገሳል። “እግዚአብሔር ዓለምን ሁሉ በስድስት ቀን ፈጥሮ ጨርሶ ለንስሓ ግን መቶ ሃያ ዓመት ሰጠ” እንዳለ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ። ጠባቂ መልአክም “በዚህች ዓመት ደግሞ ተዋት” (ሉቃ. ፰፥፫) እያለ ይማልድልናል። ነገር ግን “የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሓ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን? (ሮሜ. ፪፥፬) እንደተባለው በቸርነቱ አመካኝቶ በኃጢአት ላይ ኃጢአት መጨመር እግዚአብሔርን መገዳደር ነው። “እግዚአብሔር ቸር ነው እያልክ በኃጢአት ላይ ኃጢአት አትጨምር” (ሲራክ ፭፥፭) እንዳለው ጠቢቡ ሲራክ የተጨመረልንን ጊዜ ለንስሓ ልናውለው ይገባል።

፭. ማፈር:- ሰው ማፈር ያለበት ኃጢአት ሲሠራ እንጂ ንስሓ ሲገባ ማፈር የለበትም። በእግዚአብሔር ፊት ከማፈር በአንድ ሰው (በንስሓ አባት) ፊት ማፈር ይሻላል። ይኸውም ከንስሓ አባት ጋር ተገቢ ባልሆነ መቀራረብ እና ከመጠን ባለፈ መደፋፈር ሊመጣ ይችላል። ከዚህም የተነሣ ‘ንስሓ አባቴ እኔን የሚያውቁኝ ቤተ ክርስቲያንን እንደምረዳ ነው፣ ደግ እንደሆንኩ ነው እንዴት ብዬ ኃጢአተኛ ነኝ እላቸዋለሁ?” በማለት በኑዛዜ ወቅት ታላላቅ ኃጢአቶችን ትተን ጥቃቅኑን ብቻ ለመናገርም ልንገደድ እንችላለን። በንስሓ ወቅት በካህን ፊት በስሜት ተገፋፍቶ ‘ደግሜ ኃጢአት ብሠራ’ ብለው መማል እና መገዘት ሌላ ጊዜ በተመሳሳይ ከወደቁ ተመልሶ በንስሓ አባት ፊት ሊያሳፍር ይችላልና መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “ከኃጢአት ጋር እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም” (ዕብ. ፲፪፥፬) እንዳለው የጽድቅን መንገድ በጽኑ መከተል ይገባል።

፮. የጊዜ ቀጠሮ መስጠት:- በመጽሐፍ “ለነገ አትበሉ ነገ ለራሱ ያስባልና” (ማቴ. ፮፥) ይላል። ነገ ንስሓ እገባለሁ ፣ ዕድሜዬ ገና ነው ብለን የጊዜ ቀጠሮ መስጠት የሰይጣንን ዓላማ ለማሳካት መጣር ነው ምክንያቱም የሰይጣን ዓላማ የጊዜ ቀጠሮ እየሰጠ ንስሓ ሳንገባ (ኃጢአታችንን ሳንናዘዝ) እንድንሞትለት ነውና። ሰው ከኃጢአት ንጹሕ ሆኖ ስለማይገኝ ንስሓ ሁል ጊዜ የሚፈጸም እንጂ የጊዜ ቀጠሮ የሚሰጠው አይደለም። ቤተ ክርስቲያን የሁል ጊዜ ጥሪዋ  “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ” የሚለው ነው።

፰. ተስፋ መቁረጥ:- ደግመን ኃጢአት ብንሠራ ተስፋ መቁረጥ አይገባም ደግመን በንስሓ ሳሙና መታጠብና ኃጢአትን ማስወገድ እንጂ። ኃጢአት እንደ እሾህ ነው፤ እሾህ የወጋው ሰው ወዲያው ይነቅላል እንጂ ትንሽ ይቆይ ብሎ እንደማያቆየው ሁሉ ኃጢአትንም ያለ ቀጠሮ ወዲያው መናዘዝ ይገባል። ተስፋ መቁረጥና መሰላቸት ብዙዎችን ከንስሓ ሕይወት ያርቃቸዋል። እግዚአብሔር እኛን ይቅር ማለት ሳይሰለች እኛ ግን ማረን ይቅር በለን ማለት ይሰለቸናል። የሰይጣን ትልቁ ዓላማ ሰውን ተስፋ ማስቆረጥ ነው። ነገር ግን “እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ አያፍሩም” (መዝ. ፳፭፥፫) በእግዚአብሔር ተስፋ መቁረጥ ተገቢ አይደለም። “ተስፋ አያሳፍርም” እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ (ሮሜ. ፭፥፭) በነቢዩ ቃል “የወደቀ አይነሣምን? የሳተስ አይመለስምን?” ብለን ልናሳፍረው ይገባል። (ኤር.፰፥፬)። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “መውደቅ አዳማዊ ነው ወድቆ አለመነሳት ግን ዲያብሎሳዊ ነው” እንዳለው ወድቆ ሳይነሣ ምውት ሆኖ የቀረው ዲያብሎስ ብቻ ነው። “ንስሓ በገባህበት ሥራህ የምትጸጸት አትሁን” እንዳለው ቅዱስ ቀሌምንጦስ ዘሮም ንስሓ በገባንበትና ቀኖና በተቀበልንበት ኃጢአት መጨነቅ፣ እግዚአብሔር ይቅር ይለኝ ይሆን? ማለት አይገባም። የእኛ ኃጢአት የእግዚአብሔርን ምሕረት አይሸፍነውምና።

የንስሓ በረከቶች

፩. የኃጢአት ስርየት ይገኛል

ትልቁ ስጦታ የኃጢአት ስርየት ማግኘት ነው።  “እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ አስቀድሞም ለእናንተ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲልክላችሁ፥ ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሓ ግቡ ተመለሱም።” (ሐዋ. ፫፥፲፱-፳)። ንስሓ በኃጢአት የዛገውን እንደ ወርቅ ታጠራዋለች። ቅዱስ ጴጥሮስን ከወደቀበት አንሥታ ሊቀ ሐዋርያት እንዳደረገችው ማለት ነው።

፪. ሕይወት ይገኛል

ንስሓ ሕይወትን ታሰጣለች። “ወደ ሕይወት ልትገባ ብትወድስ ትእዛዛትን ጠብቅ” እንዲል፡፡ (ማቴ.፲፱፥፲፯)

፫. መንፈሳዊ አባት(እረኛ) ይገኛል

ሰው ደካማ ስለሆነ በመንፈሳዊ ሕይወቱ እንዲበረታ፣ ቢበድል ኃጢአቱን በመናዘዝ ስርየትን ያገኝ ዘንድ፣ ከእግዚአብሔርም ጋር ይታረቅ ዘንድ መንገዱንም የሚመራ መንፈሳዊ አባት ያስፈልገዋል፡፡ ምእመናን ካህንን ስለ ሁሉም ነገር ማማከር ይገባቸዋል፣ የማሰርና የመፍታት ሥልጣን ተሰጥቷቸዋልና፡፡ (ማቴ. ፲፰፥፲፰) ጌታችን በወንጌል “በቀን የሚመላለስ ቢኖር የዚህን ዓለም ብርሃን ያያልና አይሰናከልም በሌሊት የሚመላለስ ቢኖር ግን ብርሃን በእርሱ ስለሌለ ይሰናከላል።”(ዮሐ. ፲፩፥፱-፲) ብሏል። ‘የዚህ ዓለም ብርሃን’ የተባሉት “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ” የተባሉት ካህናት ሲሆኑ በቀን የሚሄድ የተባለው በምክረ ካህን የሚኖር ማለት ነው። በምክረ ካህን መኖር በትዳርና በማኅበራዊ ኑሮ ችግሮችን ለመፍታት ይረዳል። ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው “የትዳር ጉዳይ ይቅርና በመላእክት እንኳ እንድንፈርድ አታውቁምን?” (፩ቆሮ. ፮፥፫-፮) የካህናት ሥልጣን እስከምን ድረስ እንደሆነ ያስረዳል።

ንስሓ አለመግባት የሚያስከትለው ጉዳት

“የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና”(ሮሜ ፮፥፳፫) እንደሚል ሰው በኃጢአት ምክንያት አራት ዓይነት ሞቶች ያገኙታል:-

አንደኛ በበሽታ ጤናው ተቃውሶ የሥጋ ሞት ያገኘዋል። ሁለተኛው መልካም ምግባራት ይርቁትና የሥነ ምግባር ሞት ያገኘዋል።  ሦስተኛ የሥጋ ሞት ያገኘዋል። አራተኛ የዘለዓለም ሞት ያገኘዋል። ነቢዩ ሕዝቅኤል “ኃጢአትን የምትሠራ ነፍስ እሷ ትሞታለች”(ሕዝ. ፲፰፥፬) እንዳለው ማለት ነው። የዚህ ዓለም ሥቃይ ማብቂያ አለው። በዚህ ዓለም ለአምላኩ ብሎ የተሠቃየ ሰው በወዲያኛው ዓለም ያርፋል። በሞት የማያርፉት ሞት ግን የዘለዓለም ሞት ነው።

በአጠቃላይ ንስሓ ዲያብሎስን ከሚያስመስል ከጨለማ ሥራ ተላቆ እግዚአብሔርን የሚያስመስለውን የጽድቅን ሥራ መሥራት ነው። እግዚአብሔር ከጽድቅ እና ከጻድቃን ጋር ይተባበራል። ከኃጥኣንና ከኃጢአት ጋር ደግሞ ኅብረት የለውም። እኛም እግዚአብሔርን የሚያስመስለውን የጽድቅ ሥራ መሥራት ይገባናል? ንስሓ በምድር ላይ ሰላማዊ ሕይወት እንድንኖርና በሰማይም ዘለዓለማዊ ዕረፍትን የምታጎናጽፍ መንፈሳዊ ሕክምና ናት። የሕክምና ሂደቷም ዘርፈ ብዙ የጎንዮሽ ጥቅም እንጂ ፍጹም የጎንዮሽ ጉዳት የሌላት ሕክምና ናት። ስለዚህም ዕድሜያችን ኃጢአት ለመሥራት የደረስን ሁላችንም ለአቅመ ንስሓም ደርሰናልና ለነገ ሳንል ኃጢአታችንን ለንስሓ አባታችን ተናዝዘን ቀኖናችንን በአግባቡ ፈጽመን ቅዱስ ሥጋውን በልተን ክቡር ደሙን ጠጥተን የመንግሥቱ ወራሾች የክብሩ ቀዳሾች እንድንሆን የአምላካችን ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳን ሁሉ ጸሎት ያግዘን። አሜን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *