“ለንስሓ የሚገባ ፍሬ አድርጉ።” (ማቴ. ፫፥፰)
በደሳለኝ ብርሃኑ
ክፍል አንድ
ንስሓ “ነስሐ” ከሚለው የግዕዝ ግሥ የወጣ ሲሆን ትርጉሙም ማዘን፣ መጸጸት፣ የኖርኩበት የኃጢአት ሕይወት ይበቃኛል ማለት፣ በደለኛነትን አምኖ ኃጢአትን ለካህን መናዘዝ ማለት ነው። ንስሓ እግዚአብሔርን መፈለግ ነው። ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ለይትፌሣሕ ልብ ዘየኀሦ ለእግዚአብሔር፤ እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው” (መዝ. ፻፭፥፫) በማለት እንደተናገረው።
ቅዱስ ዳዊት በዚህ ብቻ አያበቃም የአምላኩን ገጸ ምሕረት በመፈለግ “ስምዓኒ እግዚኦ ጸሎትየ ዘሰአልኩ ኀቤከ እምትሕዝብተ ጸላኢ አድኅና ለነፍስየ፤ አምላኪየ አምላኪየ እገይሥ ኀቤከ ጽምአት ነፍስየ ለከ። እፎ እስፋሕ ለከ ሥጋየ በምድረ በድው ኀበ አልቦ ዕፅ ወማይ ከመዝ በመቅደስከ አስተርአይኩከ፤ አቤቱ ጌታየ ሆይ ወደ አንተ የለመንኩትን ጸሎቴን ስማኝ፣ ነፍሴንም ከሚከታተሏት ከክፉ ጠላት አድናት፤ አምላኬ አምላኬ ወደ አንተ እገሠግሳለሁ፤ ነፍሴ አንተን ተጠማች፤ እንጨትና ውኃ በሌለበት ምድረ በዳ ሥጋዬን ለአንተ እንዴት ልዘርጋልህ? ኃይልህና ክብርህን ዐውቅ ዘንድ እንዲሁ በመቅደስ ውሰጥ ተመለከትሁህ” በማለት በፍጹም ንስሓ እና በተሰበረ ልብ አምላኩን ይማጸናል። (መዝ. ፷፫፥፩)።
ንስሓ ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበት መንገድ ነው። እግዚአብሔር የጠፋውንና ከእርሱ የኮበለለውን አዳምን ፈልጎ ባገኘው ጊዜ በፍቅር በትከሻው እንደ ተሸከመው። ለዚህ ነው በተአምረ ማርያም መቅድም ላይ “ዘወፅአ እምኔኪ ኖላዊ ኄር ዘበአማን ዘኀሠሦ ለበግዕ ግዱፍ ወሶበ ረከቦ ጾሮ ዲበ መትከፍቱ፤ የጠፋ በግ አዳምን የፈለገው ባገኘውም ጊዜ የተሸከመው” የሚለው። አምላካችን ቸር ሰው ወዳጅ ስለሆነ የጠፋውን የሰው ልጅ ባገኘው ጊዜ አልተቆጣም ይልቁንም የእሱን በደል በትከሻው በመስቀል ላይ በመሸከም ፍቅሩን ገለጠለት እንጂ። ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያ በሥርዓተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ “ነአኩቶ ለገባሬ ሠናያት ላዕሌነ እግዚአብሔር መሐሪ፤ ለእኛ በጎ ነገርን ያደረገ ይቅርባይ እግዚአብሔር አምላካችንን እናመሰግናለን” እንዳለው ንስሓ የእግዚአብሔር የቸርነቱ በር ናት። ቅዱስ ጎርጎርዮስ “የንስሓ በር ከፈተልን” እንዳለው (ሃይማኖተ አበው ፲፬፥፴)።
ንስሓ ነበር፡፡ ነገር ግን የሚገቡት ንስሓ ወደ ገነት ማስገባት አይችልም ነበር፡፡ ከአዳም ጀምሮ ሌሎቹም እግዚአብሔርን በማምለክ የነበሩ ሁሉ በእግዚአብሔር እጅ ይከለሉ /ይጠበቁ/ ስለነበር የሲዖል እሳት አይበላቸውም ነበር፡፡ ይህቺ የእግዚአብሔር የቸርነቱ በር ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከሚወለድ ድረስ ተዘግታ ነበር። ለዚህ ነው ጌታችንም “መዝጊያን አንኳኩ ይከፈትላችኋል” በማለት የቸርነቱን በር በንስሓ ያለማቋረጥ እና ያለ መሰልቸት እንድናንኳኳ ያዘዘን። (ማቴ. ፯፥፯)። ንስሓ በኃጢአት ትንሣኤ ፈውስ ናት። ኃጢአትን መሥራት እግዚአብሔርን ማጣት፣ ከእሱም መለየት፣ የዲያብሎስም ባሪያ መሆን ነው፣ በግብርም እሱን መምሰል ነው።
ኃጢአት መሥራት ከእግዚአብሔር መራቅ እንደሆነው ሁሉ፤ ንስሓ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው (ሚል. ፫፥፯)። ቅዱስ ዳዊት በተመለሰ ጊዜ “አቤቱ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ፤ ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ ከኃጢአቴም አንጻኝ፤ እኔ መተላለፌን አውቃለሁና ኃጢአቴም ሁል ጊዜ በፊቴ ነውና። አንተን ብቻ በደልኩ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ” በማለት በቁርጥ ኅሊና የአምላኩን ምሕረት ተማጽኖአል (መዝ. ፶፥፩-፫)።
ንስሓ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ነው። ከእግዚአብሔር በነቢዩ ኢዩኤል ላይ አድሮ “አሁንስ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ።
ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር ቸርና መሓሪ፥ ቁጣው የዘገየ፥ ምሕረቱም የበዛ፥ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ።” (ኢዩ. ፪፥፲፪-፲፫) በማለት ከኃጢአታቸው ቢመለሱ እግዚአብሔር ቸር፣ ይቅር ባይ፣ መሓሪም መሆኑን ይገልጻል፡፡
ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ንስሓ እንደ እሳት ሆና ስለምታቃጥለው ንስሓን ይጠላል። ምክንያቱም ንስሓ ዲያብሎስ በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ የገነባውን ግንብ የምታፈርስ መዶሻ ናትና። ለዚህም ነው ዲያብሎስ ሰው ኃጢአት ሲሠራ በእግዚአብሔር ቸርነት እንዲያመካኝ ያደርግና በኃጢአቱ ተጸጽቶ ንስሓ ሊገባ ሲል ደግሞ “ይህን ሁሉ በድለህ እግዚአብሔር አይምርህም” በማለት የንስሓ ዕድል እንዳያገኝ የንስሓን በር ይዘጋበታል። በዚህም ተስፋ በማስቆረጥ የራሱን ምርኮ ያበዛል። ስለዚህ “በሰይጣን እንዳንታለል፤ የእርሱን ሐሳብ አንስተውምና” እንዳለው ቅዱስ ጳውሎስ ተንኮሉን ዐውቀን ልንነቃበት ይገባል (፪ኛቆሮ. ፪፥፲፩)።
ኃጢአትን የምንናዘዘው ደግሞ ለካህን ነው። ካህን ስንልም ቤተ ክርስቲያን የምታውቀው፣ በአገልግሎት ያሰማራችውና አድራሻው የሚታወቅ መሆን አለበት። አገልግሎቱን በአግባቡ ለማግኘትና በቅርበት ለመከታተልም የንስሓ አባት መያዝ የሚገባው ከሚገለገሉበት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ነው።
ንስሓ ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንዱ ስለሆነ የሚፈጸመውም በቤተ ክርስቲያን ነው። አንድ ተነሳሒ ለካህኑ የሚናዘዘው ካህኑን እንደ እግዚአብሔር መልእክተኛ አድርጎ እግዚአብሔርን ደግሞ ዳኛ አድርጎ ነው። “ካህኑ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ነውና” እንዲል (ሚል. ፪፥፯)። ኑዛዜውንም በዝርዝር ሳይደብቅና ሳያድበሰብስ መናዘዝ አለበት። ለምሳሌ ሕዝበ እሥራኤል በኢያሱ ዘመን ዮርዳኖስን ተሻግረው መጀመሪያ ከወረሷት ከኢያሪኮ ምድር ምንም ነገር እንዳይወስዱ እርም ነውና አትንኩ ተብለው ታዘው ነበር። ነገር ግን አካን የተባለው ሰው ከተከለከለው ሰርቆ በመውሰዱ ተጣርቶ እሱ መሆኑ ተደረሰበት። በዚያን ጊዜ ኢያሱ አካንን እንዲህ አለው:- “ልጄ ሆይ፥ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ክብር ስጥ፥ ለእርሱም ተናዘዝ፤ ያደረግኸውንም ንገረኝ፤ አትሸሽገኝ” አለው። አካንም መልሶ ኢያሱን፡- “በእውነት የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በድያለሁ፤ እንዲህና እንዲህም አድርጌአለሁ። በዘረፋ መካከል አንድ ያማረ የሰናዖር ካባ፥ ሁለት መቶም ሰቅል ብር፥ ሚዛኑም አምሳ ሰቅል የሆነ ወርቅ አይቼ ተመኘኋቸው፥ ወሰድኋቸውም፤ እነሆም፥ በድንኳኔ ውስጥ በመሬት ተሸሽገዋል፥ ብሩም ከሁሉ በታች ነው አለው።”(ኢያ. ፯፥፲፱-፳፩) በማለት ያደረገውን በዝርዝር ለኢያሱ ተናዘዘ። ይህም የሠሩትን ኃጢአት በዝርዝር ለንስሓ አባት መናገር ተገቢ መሆኑን እንረዳለን።
በሐዲስ ኪዳንም ስንመለከት ዮሐንስ ሕዝቡን ሲያጠምቅ “ያን ጊዜ ኢየሩሳሌም ይሁዳም ሁሉ በዮርዳኖስም ዙሪያ ያለ ሀገር ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር። ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር።” በማለት የኑዛዜን ተገቢነት ያስረዳናል (ማቴ. ፫፥፭-፮)። በዘመነ ሐዋርያትም ኑዛዜ እንደ ነበረ ሲገልጽ “አምነውም ከነበሩት እጅግ ብዙ ሰዎች ያደረጉትን እየተናዘዙና እየተናገሩ ይመጡ ነበር” በማለት ይመሰክራል (ሐዋ. ፲፱፥፲፰)። ጌታችንም አንድ ለምጽ የነበረበትን ሰው ቀርቦ “ጌታ ሆይ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” እያለ እየሰገደ በጠየቀው ጊዜ እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና “እወዳለሁ ንጻ” አለው። ወዲያውም ከለምጹ ዳነ። ጌታችንም “ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ! ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ” አለው። (ማቴ. ፰፥፪-፬)።
ዳግመኛም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተአምረ ኢየሱስ ላይ ስሟ ብርስፌንያ የተባለችውን ሳምራዊቷን ሴት ለብቻዋ አነጋግሯት ኃጢአቷን እንድትናዘዝ አደረጋት (ዮሐ. (፬፥፩-፵፪)። በዚህም ንስሓ አባት ቀስ አድርጎ ለብቻ በጥበብና በጥንቃቄ ተነሳሒን ማናገርና ማስተናገድ እንደሚገባ ለማጠየቅ ነው።
የንስሓ መንገዶችና አፈጻጸሙ
አንድ ሰው ንስሓ ከመግባቱ በፊት በደላኛነቱን ወይም ኃጢአተኛነቱን ማመን አለበት። የራሱን ኃጢአትና የእግዚአብሔርን ቸርነት ማሰብ አለበት። ምንም እንኳ ኃጢአተኛ ቢሆን እግዚአብሔር ይምረኛል ይቅር ይለኛል ማለት ይገባዋል እንጂ ተስፋ መቁረጥ የለበትም። ምክንያቱም እግዚአብሔር ተስፋ የሚቆረጥበት ሳይሆን የተቆረጠው ተስፋ የሚቀጠልበት አምላክ ነው እንጂ። ለዚህ ነው ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ወይእዜኒ መኑ ተስፋየ አኮኑ እግዚአብሔ፤ አሁንስ ተስፋዬ ማነው እግዚአብሔር አይደለምን? (መዝ. ፴፰፥፯) ያለው። ስለዚህ ኃጢአት መጀመሪያ የሚናዘዘው ለራስ ነው፤ የንስሓ የመጀመሪያ ደረጃም ትንሣኤ ልቡና ወይም ንስሓ ለመግባት መፈለግ ነው። “በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም” (ራእ. ፳፥፮) እንዲል። የመጀመሪያው ትንሣኤ (ትንሣኤ ልቡና) ከኋለኛው ሞት ያድናል። ።
በሉቃስ ወንጌል ፲፭ ላይ የጠፋው ልጅ ታሪክ የሚያስተምረን ይህንኑ ነው። “ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ” የሚለው ዐረፍተ ነገር በኃጢአት ውስጥ መሆኑን ተረዳ፣ ልብ አደረገ የሚለው ሲሆን፣ “ተነሥቼ ወደ አባቴ ልሂድ። አባቴ ሆይ በሰማይና በፊትህ በደልኩ፤ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከአገልጋዮችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ” ብሎ ለራሱ መናገሩ ደግሞ ለማድረግ መወሰኑን ያመለክታል። ወስኖም አልቀረ “ተነስቶም ወደ አባቱ መጣ” እንዳለው የወሰነውን በተግባር አደረገ። ስለዚህ የንስሓ መንገድ ኃጢአት ውስጥ መሆናችንን መንቃት፣ ንስሓ ለመግባት መወሰንና ንስሓ አባት መያዝ፣ ቀጥሎም ንስሓ መግባት ነው፡፡
ሦስተኛ ኃጢአትን መናዘዝ ነው። በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት ተነሳሒው ከካህኑ ጋር ፊት ለፊት እየተያዩ መናዘዝ አለበት። ስለ ኃጢአቱም እንዲሰቀቅና በዚህም የሚገኘውን መንፈሳዊ ጸጋ እንዲያገኝ ያደርጋል። ስንናዘዝም ኃጢአትን እንደ ጀብድ በመቁጠር ወይም በትዕቢት ሳይሆን ራስን በእግዚአብሔር ፊት በማዋረድ “ቀና ብዬ የሰማዩን ርዝመት አይ ዘንድ አገባቤ አይደለም” (ጸሎተ ምናሴ) በማለት መሆን አለበት። ካህናት “አዕይንተ እግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔር ዓይኖች” ናቸው። በካህኑም አድሮ የኃጢአትን ይቅርታ የሚሰጠን እግዚአብሔር ነው። ለዚህ ነው ካህናትም ኑዛዜ ከሰጡ በኋላ “እግዚአብሔር ይፍታ” የሚሉት።
የሰይጣን ተንኮል የሰው ልጅ ያለ መሰቀቅ እና ያለ ፍርሃት ኃጢአትን እንዲሠራ ያደርግና ኃጢአትን አምኖ ንስሓ እንዲገባ ደግሞ ዕድል አይሰጠውም፤ እግዚአብሔርን ጨካኝ ያስመስለዋል። ስለዚህ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ እንዳለው “ካህኑን እንደ መንፈሳዊ አባትነቱ እየው። ልክ በሽተኛ የተሸፈኑ ቁስሎችን ገልጦ ለሐኪም እንደሚያሳይና እንደሚፈወስ ምሥጢሮችህን በግልጽ ንገረው” ኑዛዜን በካህኑ ፊት በአግባቡ መፈጸም ይገባል። እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ ነውና ሰው ኃጢአቱን ከእግዚአብሔር ፊት መደበቅ አይችልም። በእግዚአብሔር ፊት ሁሉ ነገር እንደ አሁን የተገለጠ ነው፤ ከእርሱ የተሰወረ ነገር የለምና።
ስለዚህ ኃጢአትን ለመናዘዝ ማፈር ሁል ጊዜ ሰይጣን እየከሰሰው ኃጢአቱም እየወቀሰችው ለመኖር መፍቀድ ነው። ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ አርጋኖን ዘረቡዕ ላይ “ኃጢአቴን ለመናገር ለምን አፍራለሁ? አለመናዘዜስ ለምንድነው? የሚከሱኝ ጠላቶቼ የሚመሰክሩብኝ ኃጢአቶቼ ሳሉ እንግዲህ ኃጢአቴን እናገራለሁ የተሰወረውን በሚያይ አፍ የተናገረውን ልቡና የመከረውን መርምሮ በሚያውቅ በልዑል እግዚአብሔር በዓይኖቹ ፊት የተገለጸ ሲሆን እኔ ለምን እሰውረዋለሁ” ይላል። “እኛ ኃጢአታችንን ስንደብቅ እግዚአብሔር ይገልጥብናል፤ እኛ ስንናዘዝ ደግሞ እግዚአብሔር ይሸፍንልናል” እንዳለው አባ መቃርዮስ ኃጢአትን ለመሰወር መሞከር ሌላ ኃጢአትን ይጨምራል።
ከዚህ ላይ የቅዱስ ዳዊትን ታሪክ መመልከት ጉዳዩን በደንብ ግልጽ ያደርግልናል። ዳዊት ሥራ ፈትቶ በሰገነቱ ላይ ሲመላለስ የኦርዮ ሚስት ገላዋን ስትታጠብ ተመለከታት፤ በልቡም ተመኛት፤ አስነወራትም። የራሱ ካልሆነች ሴት ጋር ተኛ ዝሙትን ፈጸመ። ይህንን ኃጢአቱን ለመሰወር ሲል ኦርዮን ከጦር ሜዳ አስጠርቶ በልቶ ጠጥቶ ታጥቦ ከሚስቱ ጋር እንዲተኛ ቢያባብለውም ኦርዮ ግን እምቢ አለ። “የእግዚአብሔር ታቦት በጠላት ተማርካ ሕዝበ እግዚአብሔር በጦርነቱ እየተማገዱ እኔ ገብቼ ከሚስቴ ጋር እንዴት እተኛለሁ?” አለው። ኦርዮ ንጉሡ ዳዊትን አሳፈረው። ዳዊትም መልእክተኞቹን ልኮ ኦርዮ በጦር ሜዳ እንዲሞት አደረገው። አንዱን ኃጢአቱን ለመደበቅ ሌላ የከፋ ኃጢአትን ጨመረ።
ነገር ግን የሰውን ጥፋት የማይወድ እግዚአብሔር ለነቢዩ ዳዊት ነቢዩ ናታንን ላከለት። ናታንም ንጉሥ ዳዊትን በፈሊጥ ተናገረው። “ንጉሥ ሆይ አንድ ሰው መቶ በጎች ነበሩት፣ አንዲት በግ የነበረችው ሰው ደግሞ ወደ ሩቅ መንገድ ለመሄድ አንዲቱን በጉን ለባለ መቶ በጎች ሰው አደራ አስጠበቀው። መቶ በጎች ያሉትም ሰው እንግዳ መጣበት፣ ያቺን የአደራ በግ አደራውን በልቶ ለእንግዳው አረደለት። ነቢዩ ናታንም ንጉሥ ዳዊትን አለው፣ ንጉሥ ሆይ ይህ ሰው ፍርድ ይገባዋል ወይስ አይገባውም?” አለው። ንጉሥ ዳዊትም “ይህ ሰው ምናምንቴ ነው አራት እጥፍ ፍርድ ይገባዋል” አለ። ነቢዩ ናታንም መልሶ “ንጉሥ ሆይ በራስህ ላይ ፈረድህ” አለው። ባለ መቶ በግ የተባለው ዳዊት ነው፤ ዳዊት ብዙ ሚስቶች ነበሩትና። ባለ አንድ በግ የተባለው ኦርዮ ነው። እንግዳ መጣበት የተባለው የሥጋ ፍላጎቱ ነው። አርዶ እንግዳውን አስተናገደበት የተባለው የኦርዮን ሚስት ማስነወሩ ነው። ዳዊት ይህ ሰው ምናምንቴ ነው አራት እጥፍ ይክፈል ያለውም ራሱ ከአራት በላይ ቅጣት ተቀጣ።
በዝሙት ከኦርዮ ሚስት ከቤርሳቤህ የተወለደው ልጁ ሞተ፤ አምኖን የተባለው ልጁ የገዛ እኅቱን በመድፈር ከክብር አሳነሳት፣ በቁሟ ገደላት፤ ንጉሡንም በተከበረበትና በነገሠበት ሀገር አዋረደው፤ የተደፈረችው ልጅ የትዕማን ወንድም አቤሴሎም እንዴት በእኅቴ ላይ እንዲህ ያለውን ነውር ተግባር ታደርግባታለህ ብሎ አምኖንን ገደለው። በመጨረሻም የዳዊት የገዛ ልጁ ከመንበሩ አባረረው። ዳዊት ኃጢአቱን ለመሰወር ብሎ እጥፍ ቅጣት ተቀጣ። (፪ኛሳሙ. ፲፩ እና ፲፪).
“ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም። የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል”(ምሳ. ፳፰፥፲፫) እንዳለው እግዚአብሔር እንዳያስብብን አስቀድመን በደላችንን ማሰብ ተገቢ ነው። “የተገለጠውን ትሸፍነዋለህ፣ የተሸፈነውን ትገልጠዋለህ” እንዳለው ቅዱስ ኤፍሬም ሰው ኃጢአቱን ሲያስብ እግዚአብሔር ይረሳለታል፤ ሰው ኃጢአቱን ሲዘነጋ ግን እግዚአብሔር ያስታውስበታል። ጻፎችና ፈሪሳውያን ስታመነዝር አገኘናት ብለው ወደ ጌታ ያመጧትን ሴት ጌታ አልፈርድብሽም ሂጂ አላት (ዮሐ. ፰)። እግዚአብሔር በሾመው ካህን ፊት ኃጢአትን ለመሸሸግ መሞከር ከእግዚአብሔር ዓይኖች ለመደበቅ መሞከር ነው። ምክንያቱም ካህናት የእግዚአብሔር ዓይኖች ናቸውና። ሰው ንስሓ ሲገባ በማሰብ፣ በመናገር፣ በተግባር የሠራውን ኃጢአት መናዘዝ አለበት። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በተግሳጹ “በበደሉ ላይ ድፍረትንና ሽንገላን ቢጨምር ከዚያች ኃጢአት መጠበቅ አልችልም። እርስዋን በሚመስል ኃጢአት ከመውደቅም አይድንም” እንዳለው ኃጢአትን በአፍ ብቻ እየረገሙ በተግባር ደግሞ መፈጸም ራስን ማታለል ስለሆነ ኃጢአትን የጠላት ንስሓ ገብቶ ከእርሱ ያርቃታል። ስንሠራው ያላፈርነውን ኃጢአት ለካህን ስንናዘዝ ማፈር የለብንም። በነውር መሰቀቅ የሥራ ዋጋ ነውና።
“በኋላ በፍርድ ቀን በሰማይና በምድር ንጉሥ ፊት ከምናፍር በአንድ ካህን ፊት ማፈር ይሻላል” እንዳለው ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ። እግዚአብሔር በፍርድ ቀን በአደባባይ ይጠይቀናል። ስለዚያች ስለ ፍርድ ቀን ቅዱስ ባስልዮስ በውዳሴ አምላክ ዘሠሉስ ጸሎት ላይ “ፍጥረትም ሁሉ የኃጢአት ሸክም ተሸክሞ በሚያስፈራ ዙፋንህ ፊት በሚቆሙበት ጊዜ የሠሩትን ክፉውንም በጎውንም ሁሉ ያን ጊዜ ሥራችን ይታወቃል። ምሥጢራችንም ይወጣል። መጋረጃችንም ይገለጣል። አቤቱ የኃሣራችንና የኃፍረታችን ደብዳቤ በመላእክት ፊት ይዘረጋል። ሥራችን ሁሉ በፍጥረት ሁሉ መካከል ይነበባል። አቤቱ ጌታዬ ሆይ የዚያች ሰዓት ግርማዋ ምን ያህል ይሆን!” ይላል።
በኑዛዜ ወቅት ለኃጢአት ምክንያት መደርደር፣ ያለ ጸጸት መናዘዝና በሰው ማሳበብን ማስወገድ ይገባል። አዳም አባታችን ኃጢአቱን ብቻ ከመናገር ይልቅ ለኃጢአቱ ምክንያት መደርደርና ክስ ጨመረበት። ንስሓ ደግሞ የራስን ኃጢአት መናገር እንጂ የሰውን በደል መዘርዘር አይደለም።
ዐራተኛው ኃጢአትን መተውና ኃጢአትን ከሚቀሰቅሱ ነገሮች መራቅ ነው። እሳት ዳር ተቀምጦ እሳቱ አይንካኝ እንደማይባል ሁሉ ከኃጢአት መንገድም መራቅ ይገባል። “ንስሓ በጥምቀት ከእግዚአብሔር ከምትገኝ ልጅነት ሁለተኛ መዓርግ ናት። በሃይማኖት ገንዘብ ያደረግነው የመንግሥተ ሰማይ መያዣ ናት፤ ለሚሿት ሰዎች የተከፈተች የይቅርታ በር ናት። በንስሓ በርነት ከፈጣሪ ወደሚገኝ ቸርነት እንቀርባለን።
መከላከያ ከሚሆን ከንስሓ ርቀን ይቅርታን አናገኝም። ንስሓ እግዚአብሔርን በመፍራትና በሃይማኖት በልቡና የምትገኝ ሁለተኛ ጸጋ ናት። ቀዛፊዋ እግዚአብሔርን መፍራት በሚሆን በንስሓ መርከብ ካልተሳፈርን ኅሊና ጸንቶበት በእኛና በፍቅረ እግዚአብሔር መካከል ያለ ሽታው የከፋ ይህን ዓለም ሰንጥቀን ማለፍ አይቻለንም።” (ማር ይስሐቅ አንቀጽ ፳፮)
አምስተኛው፡- ቅዱስ ዳዊት እንዳለው “በእንተዝ ኵሎ ፍኖተ ዐመፃ ጸላእኩ፤ የሐሰትን መንገድ ጠላሁ” (መዝ. ፻፲፰፥፻፬) እንዳለው ኃጢአትን መጥላት ነው። ኃጣውእን የጠላ ሰው ኃጢአት መሥራት ያቆማል። በኃጢአቶቹም የተናዘዘ ሰው ሥርየትን ያገኛል። መጀመሪያ ከኃጢአት ጋር ጠላትነትን ማድረግ ያልቻለ ሰው ኃጢአት የመሥራት ልማዱን መተው አይችልም። ያለ ኑዛዜም ሥርየተ ኃጢአትን ሊያገኝ አይችልም። ምክንያቱም ኃጢአትን ሳያፍሩ መናዘዝ የእውነተኛ ትሕትና ምክንያት ነውና” ይላል አብርሃም ሶርያዊው፡፡
ስድስተኛው፡- የንስሓ ፍሬ ማፍራት ነው። “እንግዲህ ለንስሓ የሚገባ ፍሬ አድርጉ” (ማቴ. ፫፥፰) እንዳለው በሰረቀበት እጁ መመጽወት፣ ዝሙትን ትቶ መጸለይ፣ በጎነትን መጨመር ይገባል። ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ “በጎ ለማድረግ ዐውቆ ለማይሠራው ኃጢአት ነው”(ያዕ. ፬፥፲፯) እንዳለው የመንፈስ ፍሬዎች የተባሉትን ማፍራት ይገባል። (ገላ. ፭፥፳፪)።
ሰባተኛው፡- መቁረብ ነው። ሁሉም ክርስቲያን መቁረብ አለበት። ስንቆርብ ደግሞ ተዘጋጅተን ነው እንጂ በቅተን አይደለም። ቅድስና እንኳ ቢኖረን የክርስቶስን ሥጋና ደም ለመቀበል ብቁ የሚሆን የለም። “ነገር ግን ንስሓ ገብቶ መዘጋጀት ይገባል። ስለዚህ ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት። ሰው ግን ራሱን ይፈትን፥ እንዲሁም ከእንጀራው ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ፤ ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና፥ ይጠጣልምና።” እንዳለው ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ (፩ቆሮ. ፯፥፳፯-፳፱)
ይቆየን
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!