ለቅዱሳን የተሰጠችን ሃይማኖት ትጋደሉላት ዘንድ እማልዳችኋለሁ” (ይሁ.፩፥፫)

“ለቅዱሳን የተሰጠችን ሃይማኖት ትጋደሉላት ዘንድ እማልዳችኋለሁ” (ይሁ.፩፥፫)

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮዋን በመስበክ፣ የሚደርስባቸውን መከራ ሁሉ ታግሰው እስከ መጨረሻው በመጋደል ያሉትን በማጽናት፣ በእግዚአብሔር ቃል መረብነት አሕዛብንና አረማውያንን ካለማመን ወደ ማመን ይመጡ ዘንድ በማጥመድ ወደ ክርስያኖች ኅብረት የሚያስገቡትን ቅዱሳንን ቀን ሰይማ በዓላቸውን ታከብራለች፡፡ ከእነዚህ ቁጥር ስፍር ከሌላቸው ቅዱሳን ሰማዕታት መካከል ደግሞ የሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስና የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዓለ እረፍት ሐምሌ ፭ ቀን በየዓመቱ በዓላቸውን በድምቀት ታከብራለች፡፡ የእነዚህ ቅዱሳን ሰማዕታት ሕይወት ምን ይመስል ነበር? እንዴትስ ተጠሩ? አገልግሎታቸውንና ተጋድሏቸው በተመለከተ ቀጥለን እናቀርባለን፡፡

ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በገሊላ ባሕር ከወንደሙ እንድርያስ ጋር እንደ ልማዳቸው ዓሣ በማጥመድ ሥራ ላይ ሳሉ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወልጌል መረብነት ሰዎችን ወደ ክርስትና በማምጣት ያጠምዱ ዘንድ በቅድሚያ ቅዱስ ጴጥሮስን ቀጥሎም እንድርያስን ጠርቷቸዋል፡፡ “በገሊላ ባሕር ዳር ሲመላለስም ሁለቱን ወንድማማቾች ጴጥሮስ የተባለ ስምዖንና ወንድሙን እንድርያስን መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፤ ዓሣ አጥማጆችም ነበሩና፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ‘ኑ ተከተሉኝ፤ ሰውን የምታጠምዱ እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ’ አላቸው፡፡ ወዲያውኑ መረባቸውን ትተው ተከተሉት” እንዲል (ማቴ. ፬፥፲፰-፳)

የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አመራረጥ ደግሞ በተአምራት ነው፡፡ ጳውሎስ የተባለው ሳውል ለአይሁድ እምነት ታማኝና ይህንንም የሚቃወሙትን በማሳደድ የሚታወቅ የክርስትና ጠላት የነበረ ሰው ነው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ከድቅድቅ የኃጢአት ባሕር ውስጥ ሰዎችን ማውጣት ይቻለዋልና ሳውል ክርስቲያኖችን ይገድል፣ ያሳድድ ዘንድ በተሰማራበት ጠራው፡፡ “ሳውል ግን ገና አብያተ ቤተ ክርስቲያናትን ይቃወም ነበር፡፡ የሰውንም ቤት ሁሉ ይበረብር ነበር፤ ወንዶችና ሴቶችንም እየጎተተ ወደ ወኅኒ ቤት ያስገባቸው ነበር” በማለት እንደተገለጸው (ሐዋ. ፰፥፫) በዚህ ብቻ ሳይበቃው ሐዋርያትንም ያሳድድና ይገድል ዘንድ ከሊቀ ካህናቱ ዘንድ የፈቃድ ደብዳቤ ይሰጠው ዘንድ እስከመጠየቅ የደረሰ አሳዳጅ ነበር፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ ይህንን ሲገልጽ “ሳውል ግን የጌታን ደቀ መዛሙርት ለመግደል ገና እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናቱ ሄደ፡፡ ምን አልባት በመንገድ የሚያገኘው ሰው ቢኖር ወንዶችንም ሴቶችንም እያሰረ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጣቸው ዘንድ በደማስቆ ላሉት ምኩራቦች የሥልጣን ደብዳቤ ከሊቀ ካህናቱ ለመነ፡፡” (ሐዋ. ፱፥፩-፪)

ሳውል ለሃይማኖቱ ቀናተኛ ነውና የሚሠራው ሁሉ ከእግዚአብሔር የሚለይ የኃጢአት ሥራ መሆኑን አልተረዳም፡፡ ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ በአይሁድ እጅ ሲወገር የገዳዮቹንም ልብስ ጠባቂ የነበረ አሳዳጅ ነበር፡፡ (የሐዋ. ፯፥፶፰-፷) ክርስቲያኖችን እያሳደደ መግደል፣ በወኅኒ ማጎር የዘወትር ሥራው አድርጓልና በዚህም ይደሰት ነበር፡፡ ነገር ግን ወደ ደማስቆ ሲሄድ ድንገት መብረቅ ከሰማይ ብልጭ አለበት፡፡ መቋቋም አልቻለምና በምድር ላይ ወደቀ፡፡ ወዲያውም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚለውን ቃል ሰማ፡፡ ሳውልም የሰማውን ድምጽ መቋቋም እየተሳነው በወደቀበት ሆኖ እየተንቀጠቀጠ “አንተ ማነህ?” ሲል ጠየቀ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ፤ በሾተል ብረት ላይ ብትቆም ለአንተ ይብስብሃል” አለው፡፡ ሳውልም ምን እንዲያደርግ እንደሚፈልግ ጌታችንን በጠየቀው ጊዜ ወደ ከተማ እንዲገባና ሊያደርገው የሚገባውን በከተማው እንደሚነግሩት አስረዳው፡፡ ነገር ግን ሳውል ከወደቀበት ሲነሣ ዓይኖቹ ታውረው ስለነበር ማየት አልቻለም፡፡ እየመሩም ወደ ደማስቆ ወሰዱት ሳይበላና ሳይጠጣ ለሦስት ቀናት ቆየ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐናንያ ለተባለው ደቀ መዝሙር ተገልጦም ሳውልን ይፈውሰው ዘንድ ላከው፡፡ ሐናንያ የሳውልን ኃጢአት አንድ በአንድ እየዘረዘረ ከጌታችን ጋር ተከራክሯል፤ ነገር ግን ጌታችን ”ተነሥና ሂድ በአሕዛብና በነገሥታት በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ አድርጌዋለሁና፡፡ እኔም ስለ ስሜ መከራን ይቀበል ዘንድ እንዳለው አሳየዋለሁ” በማለት ነገረው፡፡ ሐናንያም ወደ ሳውል ሄዶ እጁን ጫነበት፤ ፈጥኖም ከዓይኖቹ እንደ ቅርፊት ያለ ነገር ወደቀ፤ ዐይኖቹም አዩ፤ ወዲያውም ተጠመቀ፡፡ ለሳምንታት በዚያ ከቆየም በኋላ በምኩራቦች እየተገኘ የጌታችን መድኃኒታችንን አምላክነት እየሰበከ ዞረ፡፡ አይሁድም ሳውልን ይገድሉት ዘንድ ተማከሩ፡፡ (ሐዋ.፱፥፩-፴፩)

ቅዱስ ጳውሎስም “የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም” በማለት ራሱን በትኅትና ዝቅ በማድረግ ለወንጌል ታማኝ ሆኖ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ በተጋድሎ ኖሯል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ፲፬ መልእክታትን፣ ቅዱስ ጴጥሮስ ደግፖ ሁለት መልእክታትን በመጻፍም ብዙዎችን ከጣዖት አምልኮ፣ ከአሕዛብነትና ከአረማዊነት መልሶ ሐምሌ ፭ ቀን በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ የዮና ልጅ ስምዖን ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ (ዮሐ.፳፩፥፲፭) ነገር ግን ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን “እናንተስ ማን ትሉታላችሁ” ብሎ ሲጠይቃቸው ሐዋርያው ተነሣና፡- “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎ መለሰለት፡፡ ያን ጊዜም ጌታችን “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ፡፡ እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም አለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሏትም” በማለት ጴጥሮስ ብሎ ሰየመው፡፡ (ማቴ.፲፮፥፲፯—፲፰)
ጳውሎስን ደግሞ ጌታችን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጠራው በመጀመሪያ ስሙ ሳውል ብሎ ጠራው፤ በምስክርነቱ ጊዜ ደግሞ “ጳውሎስ ሆይ፥ በኢየሩሳሌም ስለ እኔ እንደ መሰከርህ እንዲሁ በሮሜም ትመሰክርልኝ ዘንድ ይገባሃልና፥ አይዞህ አለው፡፡” (የሐዋ.፳፫፥፲፩)
የቅዱስ ጴጥሮስ አገልግሎቱ በአብዛኛው ሕግ ለተጻፈላቸው፣ ነቢያት ለተላኩላቸው፣ መሥዋዕት ለሚያቀርቡ፣ ግርዛት ለተሰጣቸው ለአይሁድ ነበር፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የቅዱስ ጳውሎስ አገልግሎት የነበረው በአሕዛብ መካከል ነበር፡፡
በአገልግሎታቸውም ድንቅ ተአምራትን ፈጽመዋል፡፡ ለምሳሌ ስለ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፡፡ “እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር፤ ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር፥ ደዌያቸውም ይለቃቸው ነበር ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር፡፡” (የሐዋ.፲፱፥፲፩-፲፪) በኢዮጴም ጣቢታ የምትባል አገልጋይን ከሞተች፤ አጥበውም በሰገነት ከአኖሯት በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ ካለበት ተጠርቶ ከጸለየ በኋላ ጣቢታ ሆይ ተነሽ ሲላት ዐይኖቿን እንደከፈተች ተጽፏል፡፡ (የሐዋ.፱፥፴፮—፵፪) በተመሳሳይ ቅዱስ ጳውሎስ አውጤኪስ የሚባል ከሦስተኛ ደርብ ወደ ታች ወድቆ የሞተን ጎልማሳ እንዲነሣ አድርጓል፡፡ (የሐዋ.፳፥፯—፲፪)
ሁለቱም ቅዱሳን ሐዋርያት በሮማው ቄሳር ኔሮን ዘመን ፷፯ ዓ.ም. ሰማዕትነትን ተቀብለዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ቁልቁል ተሰቅሎ ሰማዕትነት የተቀበለ ሲሆን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ አንገቱን ተቀልቶ ሰማዕትነትን ተቀብሏል፡፡
በረከታቸው ይደርብን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *