“ሆሣዕና በአርያም ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት…” (ቅዱስ ያሬድ)
በቀሲስ ኃይለሚካኤል ብርሃኑ
ሆሣዕና በዕብራይስጥ ሆሼዕናህ የሚል ሲሆን ትርጒሙም “አቤቱ አሁን አድን” ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና መሠረት ዐቢይ ጾም ስምንት ሳምንታ አሉት፡፡ ሳምንታቱም የየራሳቸው ስያሜ አላቸው፡፡ ለማስታወስ ይረዳን ዘንድ ስንቃኛቸውም የመጀመሪያው ሳምንት ዘወረደ፣ ሁለተኛው ሳምንት ቅድስት፣ ሦስተኛው ሳምንት ምኲራብ፣ አራተኛው ሳምንት መጻጉዕ፣ አምስተኛው ሳምንት ደብረ ዘይት፣ ስድስተኛው ሳምንት ገብር ኄር፣ ሰባተኛው ሳምንት ኒቆዲሞስ ሲሆን ስምንተኛውና የመጨረሻው ሳምንት ከትንሣኤ ቀድሞ የሚገኝ የሕማማት መግቢያ ዋዜማ ላይ የሚከበረው ከዘጠኙ አበይት በዓላት መካከል አንዱ የሆነው በዓለ ሆሣዕና ነው፡፡
ይህ የሆሣዕና በዓል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የሚቀድሙት እና የሚከተሉት ህዝብ በተለይም አእሩግ እና ሕጻናት “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም ሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም” በማለት ጌታችንን መቀበላቸው የሚታወስበት በዓል ነው።
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮ የሆሣዕና በዓል ከረቡዕ ጀምሮ የሚታሰብ ታላቅ የቤተ ክርስቲያን በዓል እንደ ሆነና በዕለተ እሑድ ከቅዳሜ ምሽት ጀምሮ በደማቅ ሥነ ሥርዓት እንደሚከበር ይታወቃል። በዚሁ በዓለ ሰንበትና ከዋዜማው በፊት በነበሩት ዕለታት/ጥቂት ቀናት/ የሚዘመረው ጾመ ድጓ ‘ሆሣዕና በአርያም፣ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት፣ዕለተ ሆሣዕናሁ አርአየ፣… ወዘተ. የሚለው የቅዱስ ያሬድ ቀለም ይባላል፡፡
በዚህ ዕለት ሆሣዕና የሚለውን ቃል ቅዱስ ያሬድና ሌሎችም አባቶች በቅዱሳት መጻሕፍት የጠቀሱት እየተወሳ እየተዘመረለት በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ኢየሩሳሌም የገባበትን ሁኔታ እየተተረከ ስለሚዘመር ልዩ የምስጋና ቀን ነው፡፡
ይህ የሆሣዕና ሰንበት በጌትነትና በክብር በውዳሴና በዝማሬ ሆሣዕና በአርአያም እየተባለ በሽማግሌዎችና በሕፃናት አንደበት በድንጋዮችም ልሳን ሳይቀር እየተመሰገነ ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በከብር ሲገባ በምስጋና ለተባበሩት ሁሉ ለሰጣቸው ለተቀደሰ ሰላሙና ፍቅሩ መታሰቢያ ሆኖ የሚከበር ቀን ነው።
አስቀድሞ በነቢየ እግዚአብሔር ዘካርያስ እንደተነገረው ‘አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበለሽ ፣አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በይ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ትሑትም ሆኖ በአህያም በአህያያቱም ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል’’ ይላልና ይህንን የትንቢት ቃል ፈጸመው ፡፡ (ዘካ.፱፥፱)
ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይድረሰውና አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ነቢያትን ትንቢት ሳያናግር፣ለአበው በምሳሌ እና በራእይ ሳይገለጥ የፈጸመው የማዳን ሥራ እንደሌለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ብሉይን ከሐዲስ አስማምታ በሊቃውንቱ ትርጓሜ አመሥጥራ ታስተምራለች፡፡ በዕለተ ሆሣዕናም የሆነው ሁሉ ከላይ እንዳየነው ቀድሞ በትንቢተ ነቢያት የተነገረ፣በቅዱሳን አበው በምሳሌ የተገለጠ ሲሆን ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡ ይህም አራቱም ወንጌላውያን ተባብረው የጻፉት ሲሆን እስኪ ወንጌላዊው ማቴዎስ የጻፈውን እንመልከት፡-
“ጌታችን ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ቀርቦ ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ በደረሰ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከ እንዲህም አላቸው በፊታችሁ ወደ አለችው መንደር ሂዱ ያንጊዜም የታሰረች አህያ ከውርንጫዋ ጋር ታገኛላችሁ ፍቱና አምጡልኝ “ምን ታደርጋላችሁ የሚላችሁ ቢኖር ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ ያን ጊዜ ይሰዱአችኋል” ይህም ሁሉ የሆነው በነቢይ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው… ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ጌታችን ኢየሱስ እንደ አዘዛቸው አደረጉ አህያይቱንና ውርንጫዋንም አመጡለት ልብሳቸውንም በላያቸው ጫኑ ጌታችን ኢየሱስም በእነርሱ ላይ ተቀመጠ ብዙ ሕዝብም ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ ሌሎችም ከዛፎች ጫፍ ጫፉን እየቆረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር”(ማቴ.፳፩፥፩ ) ፡፡
በዚህ ገጸ ንባብ እንደተመለከትነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ ፋጌ መንደር ውስጥ ታስረው የነበሩ አህያቱንና ውርንጫዋን ፈትታችሁ አምጡልኝ በማለት በሞት ጥላ፣ በዲያብሎስ ቁራኝነት፣ በሲኦል በርነት ታሥሮ ይሠቃይ የነበረውን የሰውን ልጅ ከባርነት ነፃ ለማውጣትና ከኃጢአት ማሠሪያ ለመፍታት የመጣ መሆኑን ሲያስረዳ “ፈታችሁ አምጡልኝ” አለ፡፡ ይኸውም ሰው ሁሉ ከኃጢአት ማሠሪያ የሚፈታበት ጊዜ እንደደረሰ ለማጠየቅ ሲሆን በደላችንን ሁሉ ይቅር ብሎ በምሕረቱ ጎብኝቶን በእኛ አድሮ ይኖር ዘንድ ሊቀድሰን በደሙ ፈሳሽነት ከኃጢአታችን ሊያነጻን መዋረዳችንን አይቶ ስለ እኛ እሱ ተገብቶ መከራ መስቀልን በመቀበል ወደ ቀድሞ ክብራችን ሊመልሰን እንደ መጣ ለማሳየት ነው፡፡
“ማንም ምንም ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ” ማለቱም የጠፋናውን እኛን ሁላችንን ሊፈልግ የመጣ በመሆኑ በኃጢአት ማሠሪያ ለተያዝን ሁሉ ነጻነትን ሰጥቶ ልጆቹ ሊያደርገን መምጣቱን ሲነግራቸው የታሠረችውን አህያ ከነ ውርንጭላዋ ፈታችሁ አምጡልኝ አለ፡፡
በዚያችም ዕለት ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሳነው ነገር የለምና በአህያዋና በውርንጭላዋ ላይ በተአምራት በአንድ ጊዜ ተቀምጦባቸዋል፡፡ ብዙዎችም ልብሳቸውን በአህያዋና በውርንጫዋ ላይ አነጠፉ በመንገዱም ላይ እየተሸቀዳደሙ የለበሱትን ልብስ ሳይቀር አነጠፉላቸው ይህንንም ያደረጉት መንፈስ ቅዱስ ምሥጢር እያስተረጎማቸው መሆኑን እንረዳለን፡፡ ይኸውም በአህያዋ ጀርባ ኮርቻ ከማድረግ ይልቅ ልብሳቸውን ማንጠፋቸው ኮርቻ ይቆረቁራል ልብስ አይቆረቁርም የማትቆረቁር ሕግ ሠራህልን ሲሉ፤ አንድም ልብስ በአካል ያለውን ነውር ይሸፍናል አንተም ከባቴ አበሳ /በደልን የምትሸፍን/ ነህ ሲሉ ነው፡፡
በአህያ የተቀመጠበት ምክንያት ደግሞ ቀድሞ ነቢያት የጦርነት፣የበሽታ፣የረኃብ ዘመን የሚመጣ እንደሆነ በፈረስ ተቀምጠው ይታያሉ፡፡ ዘመነ ሰላም የሆነ እንደሆነ በአህያ ተቀምጠው መነሳንስ ይዘው ይታያሉና ዘመነ ሰላም ደረሰ ሲል ትንቢቱን ባወቀ አናግሯል፡፡ ምስጢሩም በአህያ የተቀመጠ ሸሽቶ አያመልጥም አሳዶም አይዝም እሱም ካልፈለጉኝ አልገኝም ከፈለጉኝም አልታጣም ሲል ነው፡፡ ሲሄዱም ሕዝቡ ልብሳቸውን በመንገድ ማንጠፋቸው አንተ የተቀመጥክባት አህያ መሬት መርገጥ አይገባትም ሲሉ ነው፡፡
እንዲሁም ሕዝቡ፣ ሕፃናቱ ሳይቀሩ ዘንባባ ይዘው የሚቀድሙትም የሚከተሉትም “ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት፣ ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር፤ለዳዊት ልጅ መድኃኒትን መባል ይገባዋል፣ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፡፡ ሆሣዕና በአርያም” እያሉ ያመሰግኑ ነበር፡፡ ታላላቆችም ሆኑ ታናናሾች የሰላም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ላይ ተቀምጦ ሲሄድ ዘንባባ ይዘው አመስግነውታል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ሲያመሰግኑ ከሕዝቡ መካከል ከፈሪሳውያንም “መምህር ሆይ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው አሉት፡፡ መልሶም እላችኋለሁ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ያመሰግናሉ አላቸው” ይህም እንደሚቻል በግልጽ ድንጋዮች ሳይቀሩ አመስግነውታል፡፡ (ሉቃ. ፲፱፥፵)
በመሆኑም የሆሣዕና በዓል በቤተክርስቲያን ጌታ ወደ ቤተመቅደስ ሲገባ ሕዝቡ ፀበርት ወይም ዘንባባ በመያዝ “ቡርክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር፤በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረክ ነው” በማለት ስለተቀበሉት ይህን በማሰብና በማድረግ ቤተክርስቲያናችን ዘንባባ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ታድላለች።(መዝ.፻፲፯፥፳፮) በቤተክርስቲያን በአራቱም ማዕዘናት ይህን በዓል የሚመለከቱ ምንባባት ይነበባሉ፡፡ ሥርዓቱም ከሌሎች ቀናት ለየት በሚል መልኩ ይከናወናል፡፡ እነዚህም (ማቴ.፳፩፥፩-፲፯፣ ማር.፲፩፥፩-፲፣ሉቃ.፲፱፥፳፱፣ ዮሐ.፲፪፥፲፪) በየማዕዘኑ የሚነበቡ ምንባባት ናቸው፡፡
በዚህ መሠረት ዕለቱ የምስጋና ቀን እንደመሆኑ ከሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ጀምሮ ልዩ ድባብ ባለው ሥርዓት ዘንባባ በመያዝ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ ምእመናን ሁሉ ያሉበት የጸሎትና የምስጋና ሥርዓት ይከናወናል፡፡ ከላይ እንደ ተመለከትነው ሕፃናትና አረጋውያን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ፣ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተመሰገነ ነው” እያሉ ሲዘምሩ አይሁድ በቅንዓት ስለተናደዱ የምስጋና ማዕበል ያቀርቡ የነበሩትን ሕፃናትን መከልከልና ዝም እንዲሉ መገሠጽ ሞከሩ፡፡
እነሱ ግን ከአይሁድ ቁጣ ይልቅ ለኢየሱስ ክርስቶስ በሚያቀርቡት ምስጋና ደስ ተሰኝተው ይበልጥ ድምጻቸውን ከፍ እያደረጉ “ሆሣዕና በአርያም ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት” እያሉ አመሰገኑት፡፡ አይሁድም ኢየሱስ ክርስቶስን “ዝም እንዲሉ ገሥጻቸው” አሉት፡፡ እሱ ግን ሕፃናቱ እንዲዘምሩ በሚያበረታታ ቃል እንዲህ ሲል መለሰላቸው “አስቀድሞ በነቢይ ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ” እንደተባለ አታውቁምን እናንተ እንዳሰባችሁት ሕፃናቱ ዝም ቢሉ እንኳን እነዚህ ድንጋዮች ያመሰግኑኛል” አላቸው፡፡(መዝ.፰፥፪) ያን ጊዜም የቢታንያ ድንጋዮች በሰው አንደበት በተአምር አመስግነውታል፡፡
ፍጥረት ሁሉ እንዲያመሰግነው ማድረግ ይቻለዋልና በቢታንያ ድንጋዮች ተመሰገነ፡፡ ስለ ሁሉ ነገር በየትኛውም ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ብንሆን ፈጣሪያችንን ማመስገን አለብን፡፡ የተፈጠርነውም ስሙን ለመቀደስ ክብሩን ለመውረስ ነውና፡፡ ስሙን ለመቀደስ ማለት ስሙን ለማመስገን ማለት ሲሆን ክብሩን ለመውረስ ማለት ደግሞ መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ማለት ነው፡፡ የተፈጠርነው ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ ስለሆነ ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን ማመስገን ይገባል፡፡ ምስጋናውም በፍጽም እምነት፣ በቅንነትና በንጹሕ ልብ መሆን አለበት፡፡
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት “እባርኮ ለእግዚአብሔር በኵሎ ጊዜ ወዘልፈ ስብሐቲሁ ውስተ አፉየ፤ እግዚአብሔርን ሁልጊዜ አመሰግነዋለሁ ምስጋነውም ዘወትር በአፌ ነው” በማለት እንደተቀኘ እኛም ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን ማመስገን የዘወትር ተግባራችን ሊሆን ይገባል፡፡(መዝ.፴፫፥፩)
የቅዱሳን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ለምስጋና የነቃን የተጋን ያድርገን አሜን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!