ሆሣዕና በአርያም
ሆሣዕና የሚለው ቃል በዕብራይስጥ “ሆሼዕናህ” የሚል ሲሆን ትርጉሙም “እባክህ አሁን አድን” ማለት ነው፡፡ ይህ ቃል በዘመነ ብሉይ በቀደምት ነቢያት ዘንድ የተለመደ ቃል ነው፡፡ “አቤቱ እባክህ አሁን አድን፣ አቤቱ እባክህ አሁን አቅና፣ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩከ ነው፡፡” (፻፲፯፥፳፭-፳፮) እንዲል፡፡ የሆሣዕና በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የሚቀድሙትና የሚከተሉት ሕዝብ በተለይም አእሩግና ሕፃናት ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ፣ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፣ ሆሳዕና በአርያም በማለት ጌታችንን በክብር መቀበላቸው የሚታወስበት በዓል ነው፡፡ በዓሉም ሆሣዕና የሚለውን ስያሜ ያገኘው በዕለቱ ከተዘመረው መዝሙር ነው፡፡
ሆሣዕና በዐቢይ ጾም ስምንተኛ ሳምንት የሚከበር በዓል ሲሆን ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙ ዓበይት በዓላት አንዱ ነው። ከስምንቱ የዐቢይ ጾም እሑዶች አንዱና የመጨረሻው ሳምንት ከትንሣኤ ቀድሞ የሚገኝ የሕማማት መግቢያ ዋዜማ ነው።
“አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በዪ፤ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም በአህያይቱም ግልገል በውርንጫይቱ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል፡፡” (ዘካ. ፱÷፱) በማለት በነቢያት የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደብረ ዘይት ቤተ ፋጌ በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱን በማሰብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዓሉን በድምቀት ታከብረዋለች፡፡

ሰውን ከወደቀበት የበደል ጉድጓድ ያወጣው ዘንድ እግዚአብሔር ክንዱን ወደ ዓለም ላከ፡፡ ሰው ሆኖ የተገለጠው እግዚአብሔር ወልድ በጉድጓድ ተጥሎ የነበረውን በዚያም በሥጋ በነፍስ፤ በውስጥ በአፍአ ቆስሎ የነበረው አዳምን በትኅትና ሁለተኛ አዳም ሆኖ በሥጋ የቆሰለውን በለበሰው ሥጋ ቆስሎ፣ በነፍስ የታመመውን በትምህርቱ አዳነ፡፡ ከእርሱ አስቀድሞ ሰውን ከሞት ወደ ሕይወት፤ ከባርነት ወደ ነፃነት የሚያመጣ ባለመኖሩ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ለሰው መድኃኒት ሆነ፡፡ በሞቱም መድኃኒትነትን አደረገ፡፡ በነቢይ “እግዚአብሔር ለሕዝቡ መድኃኒትን ሰደደ፡፡” (መዝ. ፻፲፥፱) ተብሎ የተነገረው ተፈጸመ፡፡
ክርስቶስ ባለ መድኃኒት ሆኖ በኃጢአት ለታመሙ ደቂቀ አዳም ሁሉ ሕይወትን ይሰጥ ዘንድ ወደዚህኛው ዓለም መጣ፡፡ በምድራዊ ሥርዓት እንደምናየው መድኃኒትና ባለ መድኃኒት እንደሚለያዩ አይደለም፡፡ ሁለቱንም እርሱ በመምጣቱ (ሰው በመሆኑ) ፈጸመ እንጂ፡፡ መድኃኒት አድርጎ ሥጋውን ደሙን የሰጠ እርሱ ነው፡፡ በካህናት አድሮ ሰው በንስሓ ሲመለስ መድኃኒት ወደሆነው ወደ ራሱ የሚመራ እርሱ ነው፡፡
ክርስቶስ መድኃኒት መሆኑ በሕማሙ እና በሞቱ ነው፡፡ በእመቤታችን ማኅፀን የተጀመረው የእርሱ መድኃኒትነት እና ፍቅሩ ፍፃሜውን ያገኘው በሕማሙ እና በሞቱ ነው፡፡ መሐሪ ንጉሥ እርሱ መሆኑን ይገልጥ ዘንድ በፈቃዱ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፡፡ ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም ከመግባቱ አስቀድሞ ከኢየሩሳሌም ፲፮ ምዕራፍ ያህል በምትርቀው በቤተ ፋጌ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ነበር፡፡
ከኢየሩሳሌም ለመግባት በደብረ ዘይት አጠገብ ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በደረሱ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለቱን (ማለትም ጴጥሮስን እና ዮሐንስን) ላከ፡፡ እንዲህም አላቸው “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፣ ወደ መንደርም በገባችሁ ጊዜ ሰው በላዩ ያልተቀመጠበት የዘህ ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፍቱና አምጡልኝ፡፡” (ማር. ፲፩፥፪) በማለት አዘዛቸው፡፡ ሰው ወዳልገባባት የተዘጋች የምሥራቅ ደጅ ወደ ምትባል ወደ ድንግል መጥቶ ዘጠኝ ወር ማኅፀኗን ከተማ አድርጎ እንደኖረ፤ ማኅየዊት ከምትሆን ሕማሙ በኋላም ሰው ባልተቀበረበት መቃብር እንደተቀበረ፤ አሁንም ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም ለመግባት ማንም ሰው ያልተቀመጠባቸውን በሌላ መንደር የሚገኙ አህያንና ውርንጫን እንዲያመጡ ደቀ መዛሙርቱን አዘዘ፡፡
የፍጥረት ሁሉ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በልደቱ እስትንፋሷን የገበረችለትን አህያ አሁን ደግሞ በፈቃዱ ስለ ሰው ሁሉ ሊሞት ሲል ንጉሥነቱን ሊያስመሰክርባት ወደደ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ካለው ፲፮ ምዕራፍ አሥራ አራቱን በአህያ ላይ ሳይቀመጥ በእግሩ ሄደ፡፡ ከዚያም ሁለቱን ምዕራፍ በአህያ ላይ በመቀመጥ ከተጓዘ በኋላ የኢየሩሳሌምን መቅደስ ሦስት ጊዜ በውርጫዋ ላይ በመሆን ዞረ፡፡ በዚህም ለሰው ሁሉ ያለው ቸርነቱ፣ ሕግ የተሰጣቸው አይሁድ እና ሕግ ያልተሰጣቸው አሕዛብ ላይ እኩል ቀንበርን መጫን እንዳይገባ አጠየቀ፡፡
ደቀ መዛሙርቱም የሰው ንብረት ዘርፈን እንዴት እናመጣለን?” ብለው መፍራታቸውን የተረዳው ጌታችንም “ምን ታደርጋላችሁ? የሚላችሁ ቢኖር ጌታቸው ይሻቸዋል በሉ፤ ያን ጊዜ ይሰዱአችኋል” አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ጌታችን ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፡፡
ልብሳቸውንም በአህያውና በውርንጫይቱ ላይ አድርገው ጌታችንም በእነርሱ ላይ ተቀመጠ፡፡ ሕዝቡም ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉለት፤ ዘንባባ እና የዛፎችንም ጫፍ ጫፍ እየቆረጡ “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም” እያሉ ይጮሁ ነበር፡፡ (ማቴ. ፳፩÷፩-፲፩) ልብሳቸውን ማንጠፋቸውም ለክብሩ መግለጫ ነው፡፡ እንዲህ ባለ ክብርና ምስጋና ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ከተማዋ በዝማሬና በአመስጋኞች ጩኸት ተናወጠች፡፡
የሕዝቡ ጩኸትና ደስታ ያበሳጫቸው ፈሪሳዊያንና አይሁድ የሚያመሰግኑትን ዝም እንዲያሰኝ ጌታችንን ቢጠይቁትም “እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ያመሰግኑኛል” ብሎ መልሶላቸዋል፡፡ በነቢዩ ዳዊት “ከሚጠቡ ሕፃናትና ከልጆች ምሥጋናን አዘጋጀህ” (መዝ. ፰÷፪) ተብሎ የተነገረው ትንቢት እንዲፈጸም የአርባ የሰማንያ ቀን የዓመት የሁለት ዓመት ሕፃናትም አመስግነውታል፡፡ አዋቂዎችም ሕፃናትም “ሆሣዕና በአርያም” እያሉ ማመስገናቸው “መድኃኒት መባል ለአንተ ይገባሃል” ማለታቸው ነው።
በበዓለ ሆሣዕና ከሚነሣው ታሪክ ውስጥ የአህያዋና የውርንጫዋ ጉዳይ ነው፡፡ ጌታችን ኪሩቤል በሚሸከሙት ዙፋን የሚቀመጥ አምላክ ሲሆን ትሁት ሆኖ በአህያ ላይ ተቀመጠ፡፡ አህያዋን ከነውርንጫዋ “ፈታችሁ አምጡልኝ” ማለቱ የሰውን ልጅ ከኃጢአት እሥራት ለመፍታት የመጣ አምላክ መሆኑን ያመለክተናል፡፡ ደቀ መዛሙርቱም አህዮቹን ፈተው ማምጣታቸው ሥልጣነ ክህነታቸውን ያመለክታል፡፡ “በምድር የፈታችሁት በሰማይ የተፈታ ይሁን” እንዲል፡፡
በአህያ ላይ ልብሳቸውን ማንጠፋቸው የምትመች የማትቆረቁር የወንጌልን ሕግ ሰጠኸን ሲሉ ነው፡፡ በአህያ የተቀመጠ ሰው በፈረስ እንደተቀመጠ ሰው ፈጥኖ አያመልጥም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከፈለጉኝ አያጡኝም ሲል በአህያ ተቀምጧል፡፡
ከኢየሩሳሌም እስከ ቤተ መቅደስ ፲፮ ምዕራፍ ነው፡፡ ፲፬ቱን በእግሩ ሄዶ ሁለቱን በአህያዋ፣ በውርንጫይቱ ደግሞ ሦስት ጊዜ ቤተ መቅደሱን መዞሩ የሦስትነቱ ምሳሌ፣ አሥራ አራቱን በእግሩ መሄዱ አሥርቱ ትእዛዛትን፣ አራቱ ደግሞ የአራቱ ኪዳናት ማለትም ኪዳነ ኖኅ፣ ክህነተ መልከ ጼዴቅ፣ ግዝረተ አብርሃም እና ጥምቀተ ዮሐንስን ያመለክተናል፡፡
ከግለሰብ ደጅ የተፈታችን አህያ “ጌታዋ ይፈልጋታል” ብሎ ያስፈታት በፈጣሪነቱ ወይም ስለፈጠራት ገንዘቡ ስለሆነች ነው፡፡ አህያን ያልናቀ አምላክ እኛም ከኃጢአት ርቀን ብንፈልገው ማደሪያዎቹ ሊያደርገን ፈቃዱ ነው፡፡ የአህያዋን መፈታት የፈለገ ጌታ እኛም ወደ ካህናት ቀርበን ኃጢአታችንን ተናዘን ከበደል እሥራት እንድንፈታ ይፈልጋልና፡፡
ሆሣዕና ከረቡዕ ጀምሮ የሚታሰብ ታላቅ የቤተ ክርስቲያን የበዓል ቀን እንደሆነ ይታወቃል። በዋዜማዎቹ ዕለታት ከቅዱስ ያሬድ ድርሰት ከሆነው ከጾመ ድጓ “ሆሣዕና በአርያም፣ ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት …’’ በማለት ይዘመራል፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገባ ሕዝቡ ዘንባባ ይዘው “ቡርክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር፤ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረክ ነው።’’ (መዝ. ፻፲፯፥፣፳፮) በማለት ስለተቀበሉት ይህን በማሰብ ቤተ ክርስቲያናችን ዘንባባ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ታድላለች፤ በቤተ ክርስቲያን በአራቱም ማዕዘናት ከአራቱም ወንጌል ዕለቱን የሚመለከቱ ምንባባት ይነበባሉ፡፡ ከቅዱስ ማቴዎስ (ማቴ. ፳፩፥፩-፲፯)፤ ከቅዱስ ማርቆስ (ማር. ፲፩፥፩-፲)፤ ከቅዱስ ሉቃስ (ሉቃ.፲፱፥፳፱-፴፰)፤ ከቅዱስ ዮሐንስ (ዮሐ. ፲፪፥፲፪-፳)።
በሰሙነ ሕማማት ጸሎተ ፍትሐት ስለማይፈጸም ጸሎተ ፍትሐት የሚደረገው በዚሁ ዕለት ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!