“ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናቸሁ” (ገላ. ፫፥፳፯-፳፰)
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከእውነተኛ መምህራቸው እና አምላካቸው ክርስቶስ ይልቅ የእርሱን ቃል ባስተማሯቸው ሰዎች ማንነት መመካት እርስ በእርስ ሲከፋፈሉ ለነበሩት ለገላትያ ምእመናን “በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤ ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና፡፡ አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፣ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፣ ወንድም ሴትም የለም፣ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናቸሁ” ብሎ ነግሯቸዋል፡፡
ከዚህ መልእክት የምንረዳው እውነት አንድነታችን መሠረቱ በጥምቀት አማካይነት በእምነት በኩል የክርስቶስ አካል መሆናችን ነው፡፡ ይህም ሲባል ክርስቲያኖች ሁሉ አንድ ያደረጋቸው በክርስቶስ ማመናቸውንና በእምነት አንድ መሆናቸው እንጂ እንደማንኛውም ሰው በመልክ፣ በባሕል፣ ተወልደው ባደጉበት ቦታ እና በትምህርት ደረጃቸው አንድ ሊሆኑ እንደማይችሉ ይታወቃል፡፡ ይልቁንም ኦርቶዶክሳውያን የሆንን ሁላችን እንደማንኛውም ሰው አስቀድመው በተጠቀሱት በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ልንለያይ ብንችልም እንኳን አንድ አምላክ ብለን ስለምናምን ከአንዲት ማኅጸነ ዮርዳኖስ እና ከአንዱ አብራከ መንፈስ ቅዱስ በአንዲት ጥምቀት አማካይነት ተወልደን የአንዱ የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆንን፣ የክርስትና ሃይማኖትን በአንድነት ስለምንቀበል፣ በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለምኖር አንድ ነን፡፡
በአንዲት ጥምቀት አንዱ ክርስቶስን የለበሱ ክርስቲያኖቸ በሚለብሷቸው ባሕላዊ አልባሳት ምክንያት ሊለያዩ አይችሉም፤ ምድራዊው መገለጫ ከሰማያዊው ሊበልጥባቸው አይችልምና፡፡ በአንድ የፍቅር ገመድ የተሳሰሩ ምእመናን በቋንቋቸው መለያየት ምክንያት አንድነታቸው ሊፈተን አይገባውም፤ የክርስቲያኖች ዋነኛው መግባቢያ ፍቅር እንጂ ቋንቋ አይደለምና፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ በገላትያ ምእመናን አማካይነት “አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም” ብሎ ሲመክረን የትውልድ ዜግነታችንን ለማስካድ አይደለም፤ ከተወለድንበት ቦታ ይልቅ ክርስቲያን ሆነን የክርስትና ምግባራት ሁሉ ፈጽመን ከምንወርሳት ሰማያዊት ሀገር በእጅጉ እንደሚያንስ ለማጠይቅ እንጂ፡፡ በተመሳሳይ መልኩ “ባሪያ ወይም ጨዋ የለም” ሲልም በወቅቱ ሰዎች እርስ በእርሳቸው የተከፋፈሉባቸውን ኩነቶች ከመግለጡም ባሻገር “በክርስትና ሰው ሁሉ ሰው በመሆኑ ብቻ እኩል ነው እንጂ መበላለጥ አለመኖሩን” ለማስረዳት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በክርስትና የሚገኘው አንድነት “ወንድ” ወይም “ሴት” የሚባል የጾታ ልዩነትን እንኳን የሚያስረሳ ፍጹም አንድ አካል መሆንን እንደሚያረጋግጥ ሐዋርያው አስረግጦ የተናገረው ተፈጥሮን ለመካድ አይደለም፡፡ በክርስቶስ አንድ የሆነ ክርስቲያን እንኳንስ በሰው ሰራሽ ነገሮች መለያየት ቀርቶ የተፈጥሮ ድንበር እንኳን ረቂቁን መንፈሳዊ አንድነት ሊያፈርሰው እንደማይቻለው ለማሳየት እንጂ፡፡
በዚሁ መሠረት አንድ መንጋ የሆነው መንፈሳዊ ቤተሰብ ደግሞ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆኖ በፍጹም የአንድነት መንፈስ ጸንቶ ይኖራል እንጂ ዘመን በተቀየረ፣ ወሬ በተወራ ቁጥር በሆነው ባልሆነው ሁሉ አንድ አይደለም፡፡ ሐዋርያው በክርስቲያኖች መካከል አንድነት እንጂ መለያየት ፈጽሞ መኖር እንደሌለበት በተማጽኖ ቃል “ነገር ግን ወንድሞች ሆይ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ ሐሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋላሁ” ሲል የሚናገረውም ለዚሁ ነው፡፡ (፩ቆሮ. ፩፥፲)፡፡
ከምንም በላይ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ለክርስቲያኖች የሚሰጠው በአንድነት ሕይወት ውስጥ መሆኑ በሐዋርያት ኑሮ ተረጋግጧል፡፡ በጽርሐ ጽዮን “… ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ …” መንፈስ ቅዱስ እንደወረደላቸውም ቅዱስ መጽሐፋችን ይመሰክራልና(ሐዋ. ፪፥፩)፡፡ ደግሞም “በሰላም ተሳስራችሁ ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኘውን ለመጠበቅ ትጉ፡፡ በተጠራችሁ ጊዜ ለአንድ ተስፋ እንደተጠራችሁ ሁሉ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፡፡ እንዲሁም አንድ ጌታ አንድ እምነት እና አንድ ጥምቀት አለ፡፡ ደግሞም ከሁሉ በላይ የሆነ በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር የሁሉም አባት የሆነ አንድ አምላክ አለ” ተብለን እንደተመከርን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለብንም፡፡ (ኤፌ.፬፥፫-፯)፡፡
በጋራ በምንጸልየው ጸሎተ ሃይማኖታችንም ውስጥ “ሐዋርያት በሠሯት በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን” እንላለን፡ የቤተ ክርስቲያን ልዩ መገለጫዋ አንድነቷ ነውና፡፡ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በዋናነት በምድር ያሉት ምእመናንና ተጋድሏቸውን የፈጸሙ ቅዱሳን ኅብረት ወይም አንድነት ናት፡፡ “እንተ በምድር ሥረዊሃ ወበሰማይ አእጹቂሃ …፤ ሥሮቿ በምድር፣ ቅርንጫፎቿም በሰማይ ያሉ” የሚለው የቅዱስ ያሬድ ትምህርትም ለዚህ ትልቅ አስረጂ ነው፡፡
ከምንም በላይ ደግሞ አማናዊውን የክርስቶስን ሥጋና ደም የተቀበሉ ሁሉ የአንዱ ክርስቶስ አካል ብልቶች ሆነዋልና አንድ ናቸው፡፡ “… ይዌልጦሙ በቅጽበት አባላተ ክርስቶስ ይኩኑ፤ በኃይለ ጥበቡ መንክር ወዕጹብ ኪኑ፤ ድንቅና ዕፁብ በሆነ በጥበቡ ኃይል የክርስቶስ አካላት ይሆኑ ዘንድ በቅጽበት ይለውጣቸዋል” እንዲል መልክአ ቁርባን፡፡ በዚህ መልኩ አንድ የሆኑ ክርስቲያኖች የአንዱ ወይኑ ግንድ (የክርስቶስ) ልዩ ልዩ ቅርንጫፎች ናቸው እንጂ የተለያዩ ተክሎች አይደሉም፡፡ (ዮሐ. ፲፭፥፭)፡፡ እናም በክርስቶስ ክርስቲያኖች የተሰኙ ሁሉ በአንድ አማናዊ እረኛ የሚመሩ አንድ መንጋ ናቸው እንጂ የሚለያዩ አይደሉም(ዮሐ.፲፥፲፮)፡፡
እንዲህ ዓይነቱ የአንድነት መንፈስ ደግሞ የሚገኘው በሥጋዊና በደማዊ ዕውቀት አይደለም፤ ይልቁንም በእምነት እንጂ፡፡ ለዚሁም ነው “ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት ሙሉ ሰውም ወደ መሆን … እስክንደርስ ድረስ …” ተብሎ የተገለጸው፡፡ (ኤፌ. ፬፥፲፪-፲፫)፡፡ ምን ጊዜም ክርስቲያን ሆኖ ከምእመናን አንድነት በመነጠል “ሙሉ” ሊሆን የሚችል እንደማይኖር በዚህ ተገልጧል፡፡
እኛ ክርስቲያኖች “አንዲት ቤተ ክርስቲያን” ብለን የምናምነው በሰማይ ካሉት መላእክትና በአጸደ ነፍስ ካሉ ደቂቀ አዳም ጋር ጭምር አንድነት ያገኘንባትን መንፈሳዊ ኅብረት ነው፡፡ በምድር ካሉና ዕለት ዕለት ከምናያቸው ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን ጋር ያለንን ኅብረት በማቋረጥ ፈጽሞ ከማናያቸው ከእግዚአብሔር እና ቅዱሳኑ ጋር ኅብረት አለን ብንል ዘበት ይሆናል፡፡ “…ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል?” እንዲል (፩ዮሐ. ፬፥፳)፡፡
በምንም ሒሳብ አብረውን ከሚያገለግሉና መንግሥተ እግዚአብሔር ለመውረስ አብረውን ከሚደክሙ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን ኅብረት መነጠል ጤነኛነት ሊሆን አይችልም፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በአንድነት ውስጥ የሚሰጥ መሆኑን አስቀድመን ተመልክተናል፤ በተቃራኒው ደግሞ መለያየትን የሚዘራውና አንድነትን በመፈታተን ደስ የሚለው ቢኖር ጠላታችን ሰይጣን ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም አንዴ በቋንቋ፣ ሌላ ጊዜ በዘውግ፣ ከዚያም ሲያልፍም በትውልድ መንደር እየተከፋፈሉ መናቆሩ ማንን እንደሚያስደስት ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ከምንም በላይ ኦርቶዶክሳዊ ቤተሰብ መሆን መቼም ሊበጠስ በማይችል መንፈሳዊ የፍቅር ገመድ እርስ በእርስ ሊያስተሳስረን ይገባል፤ ከዚህ የወጣ ክርስትና የለምና፡፡
ምንጭ፡- ጉባኤ ቃና (መጋቢት ፳፻፲ ዓ.ም)
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!