“ሁሉን መርምሩ መልካሙን ያዙ” (፩ኛተሰ. ፭፥፳፩)

ይህ መልእክት የጥናትን ምርምርን አስፈላጊነት ከምንረዳባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ኃይለ ቃላት አንዱ ሲሆን በአካባቢያችን የምናገኛቸው በርካታ መልካም እና መልካም ያልሆኑ ነገሮችን መርምረን (ተመራምረን) ፈትነን መልካም የሆነውን ያውም የሚጠቅመንን ብቻ እንድንይዝ የተመከርንበት ኃይለ ቃል ነው፡፡

ምርምር ለእኛ በእግዚአብሔር ለምናምን ሰዎች አዲስና እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ቀደምት አባቶቻችን መርምረው (ተመራምረው) ችግሮቻቸውን ፈትተዋል፤ በርካታ ሥራዎችንም ሠርተዋል፡፡ ከኢአማኒነት ወደ አማኒነት የመጡ ብዙ ሲሆኑ ከእነዚህ ሰዎች መካከል አበ ብዙኃን አብርሃም ተጠቃሽ ነው፡፡ አብርሃም ፈጣሪውን ፍለጋ ተመራምሮ ከጣዖት አምላኪነት እና ሻጭነት እግዚአብሔርን ወደማመን በፍጹም ልቡ የተመለሰ ቅዱስ አባት ነው፡፡

የአባታችን የአብርሃም ምርምር ዛሬም መንገዱ ስለጠፋብን፣ ብዙ ነገር ድብቅ ሆኖብን ወዴት መሔድ፣ ምን መያዝና ወዴት ማምራት እንዳለብን ግራ ለገባን ሰዎች ምሳሌ ይሆነናል፡፡ እስቲ የአብርሃም የሕይወት ጉዞ ሒደት ምን ይመስል እንደነበር በጥቂቱ እንመልከት፡-

አብርሃም የጣዖት ጠራቢው የታራ ልጅ ሲሆን አባቱ ታራ የሠራቸውን ጣዖታት እንደ ገበያው ፍላጎት እያዋደደ ይሸጥ ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ግን አብርሃም እግዚአብሔር የሰጠውን አእምሮ ተጠቀመበት፡፡ የአባቱ ጣዖት ዐይን እያለው የማያይ፣ ጆሮ እያለው የማይሰማ፣ እግር እያለው የማይሔድ በመሆኑ “ይህ አምላክ ሊሆን አይችልም” ብሎ ዐሰበ፡፡ አባቱንም “ከዚህ ከጣዖት አምልኮ ምን ትጠቀማለህ?” ብሎ ጠየቀው፡፡ ታራም ወገኖቹ ጣዖት አምላኪ በመሆናቸው አብሮ ለመኖር እንጂ ጣዖቱ ምንም እንደማይረባው መለሰለት፡፡ (ኩፋ. ፲፥፵፪-፵፯) ከዚያም አብርሃም ወደ ገበያ ይዞት የወጣውን ጣዖት “ዐይን እያለው የማያይ፣ ጆሮ እያለው የማይሰማ፣ እግር እያለው የማይሔድን አምላክ የሚገዛ” እያለ ለገበያ ያስተዋውቅ ጀመር፡፡ ገዢዎችም “ባለቤቱ እንዲህ ያቀለለውን ጣዖት ማን ይገዛል?” እያሉ ሳይገዙት ቀሩ፡፡ ከዚያም አብርሃም ጣዖቱን በድንጋይ ቀጥቅጦና ሰባብሮ አማናዊውን አምላኩን ይፈልግ ጀመር፡፡

አብርሃም አምላኩን ለማግኘት ባደረገው ሒደት የተለያዩ ፍጥረታትን (ተራራን፣ ውኃን፣ ነፋስን፣ እሳትን፣ …) እየፈተነ አምላክ አለመሆናቸውን እያረጋገጠ ከፀሐይ ደረሰ፡፡ ፀሐይም በጨለማ ስትሸነፍ በማየቱ  አምላክ አለመሆኗን አረጋገጠ፡፡ አብርሃምም በዚህ ሁኔታ ባደረገው ምርምር መሠረት የእርሱ አምላክ በምርምር የማይደረስበት መሆኑን አረጋገጠ፡፡ ስለዚህም “አምላከ ፀሐይ ተናበበኒ፤ የፀሐይ አምላክ አነጋግረኝ” በማለት ወደ አምላኩ ተጣራ፡፡ (የኦሪት ዘፍጥረት አንድምታ ትርጓሜ ምዕራፍ ፲፰) እግዚአብሔርም አብርሃምን ሰማው፤ ተገለጠለትም፡፡ በማለት በታላቅ ቃል ኪዳን ተቀበለው፡፡ “እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፡- ከሀገርህ፣ ከዘመዶችም፣ ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ፡፡ ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ፤ እባርክሃለሁ፤ ስምህንም አከብረዋለሁ፤ ለበረከትም ሁን፡፡ የሚባርኩህንም እባርካለሁ፣ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፣ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ” (ዘፍ.፲፪፥፩)፡፡ በመሆኑም አብርሃም ብዙ ነገሮችን ፈትኖ አምላኩን ወደ ማግኘት ደረሰ፤ እግዚአብሔርም በታላቅ በረከት ጎበኘው፡፡

ሌላው በምርምር ሒደት ከሚጠቀሱት ሰዎች መካከል ነቢዩ ሳሙኤል ነው፡፡ ነቢዩ ሳሙኤልም እግዚአብሔር አምላክ “በቀንድህ ዘይቱን ሞልተህ ሒድ፤ በልጆቹ መካከል ንጉሥ አዘጋጅቻለሁና ወደ እሴይ ወደ ቤተልሔም እልክሃለሁ” ባለው ጊዜ ለእሥራኤል ንጉሥ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር የመረጠውን ዳዊትን እስኪያገኝ ድረስ የእሴይን ልጆች ተራ በተራ እየጠራ ተመልክቷል፡፡ ነቢዩ ሳሙኤል በስምንተኛው ሙከራው ትክክለኛውን የእግዚአብሔርን ምርጫ አግኝቶ ቀብቶ አንግሦታል፡፡ (፩ኛሳሙ. ፲፮፥፩-፲፫) ዳዊት የእግዚአብሔር ምርጫ ሲሆን የሳሙኤል ደግሞ የጥናቱ ግኝት ሆኖ እስራኤልን ለ፵ ዓመታት መርቷል፡፡

አንዳንድ ሰዎች ጥናትና ምርምር ከቤተ ክርስቲያን ጋር ሊገናኝ አይችልም ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ የጥናትና ምርምር ቦታም ሌላ ተቋም መሆን እንዳለበት ያስባሉ፡፡ መልሱ ግን እጅግ ቀላልና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው፡፡ “በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም፣ የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፣ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደሆነች ዕወቁ፤ በእርሷም ላይ ሂዱ፤ ለነፍሳችሁ ዕረፍትን ታገኛላቸሁ” (ኤር. ፮፥፲፮) ተብሎ እንደተጻፈው ምርምር በሃይማኖት የሚቻል ብቻ ሳይሆን ሊደረግ የሚገባ መሆኑንም ጭምር የሚያሳይ ነው፡፡

ከዚህ መልእክት ሁለት ዐበይት ጉዳዮችን እንረዳለን፡፡ አንደኛው በእምነት የዛሉ ወይም መንገድ የጠፋባቸው ሰዎች ቆም ብለው እንዲያስተውሉ፣ ዝም ብለው በደመ ነፍስ ከመመራት ይልቅ በማስተዋል፣ በመራመርና በመጠየቅ ወደ ቀደመችው ወደ አማናዊቷ ቤታቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን በመምጣት ሕይወት እንዲሆንላቸው የተሰጠ ምክር እና ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የጥናትና ምርምር (Research) ዋነኛ መሣሪያዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ መነገሩ ነው፡፡

የጥናትና ምርምር ዋነኛ መሣሪያዎችን ሰንመለከት በመንገድ ላይ ቁሙ ሲል የምርምር ጥያቄ (Research questions (hypothesis)፤ ተመልከቱ ሲል (Obserevation) እና ጠይቁ የሚለው ደግሞ መጠይቅ (Questioner, intereview) ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ እነዚህም ምርምር መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት እንዳለው የምንገነዘብባቸው መልእክቶች ናቸው፡፡

ከዚህ ሌላ የምንመለከተው መመርመር ያለብን የሚታየውን ግዙፉን ዓለም ብቻ ሳይሆን ረቂቅ የሆነውን የመናፍስትን ዓለም ጭምር መሆኑን ነው፡፡ ይህም “መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደሆነ መርምሩ” (፩ኛዮሐ. ፬፥፩) በሚል ተገልጾ እናገኘዋለን፡፡ ከእግዚአብሔር የሆነውን መልካሙን ለመቀበል መመርመር ተገቢ መሆኑን ያሳያል፡፡

ምርምር የሚለው ቃል ዘርፈ ብዙ ነው፡ የማይዳስሰው ነገር አለ ማለት አይቻልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “ሥራን እንዴት እንሥራ፣ እንዴትስ እናቀላጥፈው?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ምርምራችን ከየት ተነሥቶ የት መድረስ እንዳለበት ይነግረናል፡፡ እንዲሁም ወደ ፍጥረታት (ገብረ ጉንዳን) ሔደን በመመልከት መማር እንደምንችል የሚያሳየን ክፍል የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው፡፡ “አንተ ታካች ወደ ገብረ ጉንዳን ሒድ፤ መንገዱንም ተመልክተህ ቅና፡፡ ከእርሱም ይልቅ ብልህ ሁን” (ምሳ. ፮፥፮-፲፩)፡፡

ሌላው ቀርቶ የሕይወት መስመራችንን እንኳ ሳይቀር ለመወሰን በጥናት ላይ ተመሥርተን በፈቃደ እግዚአብሔር እንድንመራ ነጻ ፈቃድ ተሰጥቶናል፡፡ “እነሆ እሳትና ውኃን በፊትህ አኖርኩልህ፤ ወደፈቀድከው እጅህን ስደድ” (ዘዳ. ፴፥፲፱፤ ሲራ. ፲፮፥፲፮) አይተን መርምረን እንድንወስን፣ ግን ውኃን (ሕይወትን) ብንመርጥ እንደሚሻለን ተነግሮናል፡፡

ዓለም የምታቀርብልን ነገር ለሥጋችን የሚስማማና ጊዜያዊ ደስታን የሚፈጥርልን ስለሆነ በእርሱ ተጠቃሚ ለመሆን እንፈተናለን፤ እንጓጓለን፡፡ ሆኖም ግን የሚያጓጓ ነገር በመንፈሳዊ ሕይወታችን ላይ የሚፈጥረውን ተጽዕኖ ውጤቱን ከወዲሁ መርምረንና አገናዝበን ካላየነው ድንበሩን በማናውቀው ሁኔታ ልንጥስ ስለምንችል ሁል ጊዜ የሚገባንን ምላሽ ለመስጠት በቅድሚያ መመርመር ይገባናል፡፡

ምርምር አስፈላጊ፣ ዕውቀትን የምንገበይበትና የተሻለ ነገን ለማየት የምንጠቀምበት ነው፡፡ ይህንንም በረከት ሁል ጊዜ ለመልካም ነገር ማዋል ይገባል፡፡ “ሁሉን መርምሩ መልካም የሆነውን ያዙ” ተብለናልና፡፡ (፩ኛተሰ. ፭፥፳፩)

በአጠቃላይ የምርምር ዘርፍ ለቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ በመሆኑ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች በቤተ ክርስቲያን ሊሠሩ የሚችሉትን ጥናትና ምርምር ዓይነቶች በመለየት የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ጉዳያችን በማለት ዐቅማቸው የፈቀደውን ያህል ምርምር በማድረግ ችግር ፈቺ የጥናት ውጤቶችን ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለጥናትና ምርምር የሚሆኑ በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ መዘንጋት የለብንም፡፡ ለዚህም ዋናው ማሳያ በዘናችን የሚገኙ የሀገራችን የሥነ ጽሑፍ፣ የሥነ ጥበብ፣ የኪነ ሕንፃ፣ የሕግና አስተዳደር፣ የዘመን አቆጣጠር፣ የሥርዓተ ትምህርትና ማኅበራዊ ሕይወትን የመሳሰሉ ጉዳዮች በአብዛኛው በቀደሙት የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና መምህራን የተቃኙ የምርምር ውጤቶች ናቸው፡፡

ማኅበራችን ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በጥናትና ምርምር ሊደገፉ የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን ተገንዝቦ የጥናትና ምርምር ማእከል በማቋቋም የጥናትና ምርምር ሥራን በመሥራትና በማስተባበር ላይ ይገኛል፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል ዋና ዓላማ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር በተያያዘ በማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ባህላዊና የመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር እንዲካሔድ ማድረግና ቤተ ክርስቲያንም በውጤቱ ተጠቃሚ እንድትሆን ማስቻል ነው፡፡ በመሆኑም ‘ሁሉን መርምሩ መልካሙን ያዙ” በማለት ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረው የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ጥናትና ምርምር ያደርጉ ዘንድ ሊበረታቱ ይገባል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ፡- ጉባኤ ቃና፤ ፯ኛ ዓመት፣ ቁጥር ፪፤ ኅዳር ፳፻፯ ዓ.ም

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *