“ጾም ትፌውስ ቊስለ ነፍስ፤ጾም የነፍስን ቁስል ታድናለች” (ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ)

በመ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ

ጾም:- ጾመ፤ ተወ፣ ታረመ፣ ታቀበ ከሚል የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን፣ ጾም ከመባልእት መከልከል ማለትም ለተወሰነ ሰዓት ከምግብ ተከልክሎ መቆየት እና ከጥሉላት ምግቦች ለአንድ ቀንም ሆነ ለሦስት ቀን፣ ለሳምንት፣ ለሁለት ሳምንት ለወርና ለሁለት ወር ወዘተ በመታቀብ  ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር  ከላመ ከጣመ ምግብ መከልከል ማለት ነው፡፡ በዚህም ሁሉ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት ነው፡፡ ጾም ሥጋን አድልበው ለፈቃደ ሥጋ ከሚገፋፋ ስሜት ተላቆ ፍትወተ ሥጋን አጥፍቶ ለፈቃደ ነፍስ ማደር እንዲቻል የመንፈስን ጥንካሬ ገንዘብ ማድረጊያ የጽድቅ መሣሪያ ነው፡፡

የጾም መሠረታዊው ዓላማም ሕዋሳትን ሁሉ ለእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲኖሩ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ያሬድ፡- “ይጹም ዐይን፣ ይጹም ልሳን፣ እዝንኒ ይጹም፣ እምሰሚዓ ኅሡም፤ ዐይን ይጹም፣ አንደበትም ይጹም፣ ጆሮም ክፉ ከመስማት ይጹም” በማለት የገለጸው (ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ)፡፡

ጾምን ፍጹም የሚያደርገው ከምግብ መከልከል በተጨማሪ ዐይን ክፉ ከማየት ተቆጥቦ የክርስቶስን መስቀል በመመልከት የእግዚአብሔርን ማዳን በመጠባበቅ ደጅ መጥናት ሲችል፣ ጆሮም ክፉ ከመስማት ርቆ መልካሙን የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ሲችል፣ እጅ ክፉ ከማድረግ ተቆጥቦ ለምጽዋት ሲዘረጋ፣ የደከመውን ሲደግፍ፣ የወደቀውን ማንሣት ሲችል፣ እግር ወደ አልባሌ ስፍራ ከመሄድ ይልቅ በቅድስና ስፍራው ተገኝቶ በእግዚአብሔር ፊት መንበርከክ ሲችል፣ ልብም ክፉ ከማሰብ ይልቅ በጎ በጎውን በማሰብ ለእግዚአብሔር የተከፈተ በር፣ ለኃጢአት ግን የተዘጋ በር ሆኖ ለእግዚአብሔር የሚመች ሲሆን ነው፡፡ እነዚህን ሕዋሳት ስም ጠቅሰን ዘረዘርናቸው እንጂ ሰው እነዚህን ከላይ የዘረዘርናቸውን ሁሉ መጠበቅ፣ ሕዋሳቱን መግዛት፣ ስሜቱን መቆጣጠር ሃይማኖታዊም፣ ተፈጥሮአዊም ግዴታው ወይም ሓላፊነቱ ነው፡፡

ጾም ከእግዚአብሔር ጋር ታስታርቃለች፡፡ “ወታጸምም ኩሉ ፍትወታተ ዘሥጋ፤ የሥጋ ፍላጎትን ሁሉ ታጠፋለች” እንዲል፡፡ የሥጋ ፍላጎት ደግሞ ኃጢአት ነው፡፡ እንዲሁም “ትሜህሮሙ ለወራዙት ጽሙና፤ በወጣትነት ዕድሜ ያሉትን እግዚአብሔርን መፍራት ታስተምራቸዋለች”  እንዲል ቅዱስ ያሬድ፡፡  ጾም በበደል ምክንያት ከእግዚአብሔር የራቀን ሰው ወደ እግዚአብሔር ታቀርባለች፡፡ ምክንያቱም ጾም እንዲሁ በልማድ ከእህልና ከውኃ ለተወሰነ ጊዜ ተከልክሎ መቆየት ብቻ ሳይሆን ልማድነቱ ቀርቶ ፍጹም መፀፀት ያለበት ኃጢአትን፣ በደልን እያሰቡ በጸሎት የእግዚአብሔርን ምሕረት በመጠባበቅ በፍቅሩ ተማርኮ የሚጾሙት መሆን ሲቻል በእውነትም ከእግዚአብሔር ጋር መታረቂያ መንገድ፣ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ የሚያስችል የንስሓ ጉዞ ነው፡፡

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበጎ ምግባር መጀመሪያ ጾም እንደሆነ በመግለጽ በአብዛኛው በዓላቶቿን ከማክበሯ አስቀድማ ጾምን ታውጃለች እነዚህንም ለአብነት ያህል ጠቅሰን እንመለከታለን፡-

የትንሣኤን በዓል(ፋሲካን) ከማክበራችን አስቀድመን ዐቢይ ጾምን፣ ብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስን በማሰብ በዓለ ዕረፍታቸውን ከማክበራችን አስቀድሞ ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላ አገልግሎታቸውን ከመጀመራቸው አስቀድሞ ሱባዔ እንደገቡና እንደ ጾሙ እኛም ጾመ ሐዋርያትን፣ የእመቤታችንን በዓለ ፍልሰት ከማክበራችን አስቀድሞ ቅዱሳን ሐዋርያት ዕረፍቷን ዓይተን ትንሣኤዋን እንደ ቅዱስ ዮሐንስ ሳናይ ብለው ሱባኤ እንደ ገቡና እንደ ጾሙ እኛም በዓሏን ከማክበራችን አስቀድመን እንጾማለን፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ከማክበራችን አስቀድመን ቅዱሳን ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው ትንቢት እየተናገሩ፣ ቅዱሳን አበው ሱባዔ እየቆጠሩ ሲጠብቁት እንደ ነበረ የተስፋው ፍጻሜ ሲደርስ በገባው ቃል መሠረት ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን እያሰብን ያን ያናገራቸውን የነቢያት ትንቢት እንደተፈጸመ እያሰብን ከበዓለ ልደት አስቀድመን እንጾማለን፡፡ በመሆኑም ጾምን የምግባራት ሁሉ መጀመሪያ ብላ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረው ለዚህ ነው፡፡

ጾም የሕግ መጀመሪያም ነው፡፡ ይህንንም ሊቀ ነቢያት ሙሴ የሥነ ፍጥረትን ነገር በአስተማረበት መጽሐፉ እንደ ጠቀሰው እግዚአብሔር አምላክ በኤዶም በስተ ምሥራቅ ገነትን እንደ ተከለ እና የፈጠረውን ሰው በዚያ እንዳኖረው ገልጾ አድርግ እና አታድርግ ወይም ብላ እና አትብላ የምትል የጾም ሕግን እንደሰጠው ይናገራል፡፡

“እግዚአብሔር አምላክም አዳምን እንዲህ ብሎ  አዘዘው በገነት ካለው ዛፍ ሁሉ ብላ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያሳየውና ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና”(ዘፍ.፪፥፲፮) እንዲል፡፡  በዚህም ቃል መሠረት ጾም ትእዛዘ እግዚአብሔር፣ ሕገ እግዚአብሔር፣ ፍቅረ እግዚአብሔር እንደሆነና በጾም ሕግ ሕይወትና ሞት እንዳለ ተረዳን፡፡ ማለትም ጾምን ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ብለን ደስ ብሎን ብንጾም ሕይወትን እንደምናገኝ ሁሉ ጾምን እንደ ግዳጅ ወይም ግዳጅን እንደመወጣት መጾም ስላለብን ብቻ እና ስለ ታዘዝን ብለን ትእዛዝ ለመፈጸማችን ማረጋገጫ አድርገን ለይስሙላ የምንጾም ከሆነ ዋጋ አናገኝበትም፡፡ በሌላም መንገድ ጭራሽ የጾምን ሕግ በመጣስ ለጾም ያለን አመለካከት ዝቅተኛ ሆኖ ብንገኝ ሞትን እንደምንሞት ከእግዚአብሔር እንደምንለይ ከላይ የተመለከትነው በሙሴ መጽሓፍ የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ያስረዳናል፡፡

በመጀመሪያ የጾምን አዋጅ ያወጀው የሁሉ ባለቤት የሆነው አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ነው፡፡ ይህም “መልካሙንና ክፉን ከሚያሳየውና ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ” ያለው ነው፡፡ ከዚህ ተነሥተው አበው ቅዱሳን ነቢያት፣ ካህናት፣ ሐዋርያት ሁሉ ጾምን ሰበኩ፡፡ በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር የተለየውን ሰው በጾም ወደ እግዚአብሔር አቀረቡት፡፡ እግዚአብሔርም በጾም፣ በጸሎት፣ በምጽዋት፣ በስግደት፣ በፍጹም ፍቅር እና ትኅትና ሆነው ለተመለሱት ቁጣውን በትዕግሥት፣ መዓቱን በምሕረት ይመልሳልና አባታችን አዳም በጾም በጸሎት ወደ እግዚአብሔር በመመለሱ ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው ቃል ገብቶለት ጊዜው ሲደርስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ አዳነው፡፡ “ነገር ግን ቀጠሮው በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ፣ ከሴትም ተወለደ የኦሪትንም ሕግ ፈጸመ” (ገላ.፬፥፬)እንዲል፡፡

የነነዌ ሕዝቦችም እንዲሁ በነቢዩ ዮናስ ስብከት በጾም በጸሎት ወደ እግዚአብሔር በመመለሳቸው ከተቃጣባቸው መዓት ዳኑ (ዮና.፫፥፩ )፡፡ ሌሎችም በዚህ ክፍል ያልጠቀስናቸው ብዙዎች በጾም በጸሎት የእግዚአብሔር ምሕረት ተደርጎላቸዋልና ጾም ሰውና እግዚአብሔር የሚታረቁባት ደገኛ ሕግ ናት፡፡ ለዚህም ነው ነቢዩ ኢዩኤል “በጽዮን መለከትን ንፉ ጾምንም ቀድሱ፣ ምሕላንም ዐውጁ”(ኢዩ.፪፥፲፭) በማለት ለጾም ልዩ ፍቅር እንዲኖረን እና ስንጾም በደስታ ሆነን የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ሞልቶ ምስጋናውን እያቀረብን መሆን እንዳለበት ያስረዳናል፡፡ ጾምን ከጸሎት፣ ከስግደት፣ ከምጽዋት፣ ከፍቅር፣ ከትኅትና ጋር አስተባብረን ብንጾም የኃጢአት ሥርየትን፣ የእግዚአብሔርም ጸጋ ይበዛልናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *