ጥቂት ስለ ነጻነት
በዲያቆን በረከት አዝመራው
ከጥቂት ወራት በፊት ነው፤ በተሳፈርኩበት ታክሲ ውስጥ በአለባበሳቸውም ሆነ በአነጋገራቸው ወጣ ያሉ ሦስት ወጣቶች አብረው ተሳፍረዋል። እነዚህ ወጣቶች ድምጻቸውን ለቀቅ አድርገው አብዛኛውን ተሳፋሪ የሚረብሽና አንገት የሚያስደፋ ንግግር ይነጋገራሉ።ድምጻቸው ከፍ ከማለቱ የተነሳ በታክሲው ውስጥ ያለው ሰው ሳይፈልግም ቢሆን እነርሱን ከመስማት ውጭ ሌላ ምንም አማራጭ አልነበረውም።
ይባስ ብሎ ከእነርሱ መካከል አንዱ ፉጨቱን ለቀቀው ፤አብዛኛው የታክሲው ተሳፋሪ በድርጊቱ ቢከፋም በጣም የተናደደ አንድ በአርባዎቹ የእድሜ ክልል ያለ ጎልማሳ “ከብት አደርግኸን እንዴ? ለምን ታፏጭብናለህ?” አለው፤ “ምን አገባህ ማፏጨት መብቴ ነው፤” በማለት መለሰ።
በተለያዩ ጊዜያት ይህንን የመሰሉ ክስተቶች ያጋጥሙናል። በተለይ በወጣቶች ዘንድ እንደፈለጉ መናገር፤መጮህ ፤የሰውን ክብር መንካት አንዳንዴ እንደ ነጻነት ይታያል። እንዲያውም “ፈታ ማለት”፣ “አለመጨናነቅ”፣ “ጣጣ የለሽ መሆን” የሚሉ ቃላት ተደጋግመው የሚባሉና በብዙዎች ዘንድ የሚወደዱ ናቸው። ይህን የሚያደርጉ ሰዎች ምክንያታቸው ልዩ ልዩ ሊሆን ይችላል። ከእነዚህ ምክንያቶች አንዱ ግን “ነጻ ሆኖ ለመኖር መፈለግ ” ነው። በዚች አጭር ጽሑፍ ስለ ነጻነት ጥቂት ነገሮችን እንነጋገራለን።
ለመሆኑ ነጻነት ምንድን ነው?
ነጻነት ማለት ማንም ውጫዊ አካል ሳያስገድደን ማሰብና መወሰን መቻል፤ያሰብነውንና የወሰነውን ነገር ለማድረግ አለመከልከል ነው። ነጻነት ለሰው ልጆች ከተሰጡት ታላላቅ ስጦታዎች አንዱና ሰው በእግዚአብሔር አርኣያና አምሳል ሲፈጠር ያገኘው ተፈጥሮአዊ ስጦታ ነው። እግዚአብሔር በባሕርዩ ነጻ ነው። የወደደውን ያደርጋል፤ ያሰበው እንደ ፈቃዱ ይከናወንለታል። በእግዚአብሔር ዘንድ ወሰን፣ ገደብ፣ ለማድረግ አለመቻል የለም፤ እግዚአብሔር ፍጹም ነጻ ነው።
ሰውም በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል ነጻ ሆኖ ተፈጥሯል። (ዘፍ 1፥26) በዚህም ምክንያት አውቆትም ይሁን ሳያውቅ ለሰው ነጻነቱ ውድ ሀብቱ ነው። ስለ ነጻነት ሲባል ብዙ ጦርነቶችና ደም መፋሰሶች ተደርገዋል፤ ብዙዎችም ሞተዋል ፤ብዙዎችም ተጋድለዋል።
በውስጣችን ከፍተኛ ነጻ የመሆን ፍላጎትና ግፊት አለ፤ በተለይ በወጣትነት ዘመናችን! ይህም ነጻ ሆነን የመፈጠራችን ውጤት ነው። በእውቀት ማጣት እና በኃጢአት ምክንያት ቢደበዝዝም ነጻ መሆንን መፈለግ እግዚአብሔር በነፍሳችን ውስጥ ያተመው ማሕተም ነው።
ነጻነት (ነጻ ፈቃድ) በሰው ልጆች ታሪክ መሠረታዊ ነገር ነው። የሰው ልጅ አሁን ያለበት ሁኔታ የነጻ ፈቃድ ውጤት ነው። ሰው ከተፈጠረበት ጀምሮ ነጻነቱን ተጠቅሞ አሁን ከደረሰበት ደረጃ ደርሷል።
የአዳም ከገነት መባረር፤ በምድር ላይ ሰው ያሳለፈው ረጅም የመከራ ዘመናት፤ የእግዚአብሔር ወልድ ሰው መሆንና ክርስትና …. እነዚህ ሁሉ የሰው በነጻነቱ ተጠቅሞ ያመጣው ችግርና የፈጠረው እግዚአብሔር ሰውን ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር ያደረገው የድኅነት ሥራ ውጤቶች ናቸው።
የሰው ነጻ ሆኖ መፈጠር ዓላማው ሰው ተገዶ ሳይሆን ወዶ ፈቅዶ ከክብር ወደ ክብር ከጸጋ ወደ ጸጋ እየተሸጋገረ እንዲኖር ነበር
ነጻ ሆኖ በተፈጠረ የሰው ልጅ ውስጥ ምንጊዜም ነጻ የመሆን ፍላጎት አለ፤ይህ ፍላጎቱ ነጻ ሆኖ ሳለ ያለአግባብና ያለመረዳት ሲፈልግና ሲጠቀም በራሱም በሌሎችም ላይ ችግር ይፈጥራል። ከነጻነት ጋር ሁልጊዜም አብረው መታሰብ ያለባቸው ጉዳዮችን መዘንጋት ታላቅ ጥፋት ነው። ስለ ነጻነት ስንነጋገርም የሚከተሉትን ነገሮች የግድ መታሰብ አለባቸው።
- እውነተኛ ነጻነት ከውስጥ ይጀምራል
እውነተኛ ነጻነት ከኃጢአትና ከምኞቶቹ ነጻ መሆን ነው፤“ኢየሱስም ያመኑትን አይሁድ እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀመዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣቸኋል አላቸው፤ እነርሱም መልሰው የአብርሃም ዘር ነን ለአንድም እንኳ ከቶ ባሪያዎች አልሆንም። አንተ አርነት ትወጣላችሁ እንዴት ትላለህ አሉት። ኢየሱስም መለሰ እንዲህም ሲል፡ እውነት እላችኋለሁ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባሪያ ነው ፡- እንግዲህ ልጁ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትውጣላችሁ።” (ዮሐ 8፥3) ከጌታ ትምህርት እንደምንረዳው እውነተኛ ነጻነት ራስን ከኃጢአት ነጻ ከማድረግ ይጀምራል። አንድ ሰው ከዚያ ውጭ መንቀሳቀስ እንዳይችል ተደርጎ በኃጢአት ማሰሪያ ጥፍር ተደርጎ ታስሮ እንዴት ነጻ ነኝ ሊል ይችላል?
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሰዎች በቅድስና እና በንጽህና ስለሚኖሩት ስለሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም ሲያወራ “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት የምትኖር ናት፤ እርሷም አናታችን ናት።” ይላል። ዝቅ ብሎም “በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እንደገናም በባርነት አትያዙ።”(ገላ 4፥26 ገላ 5 ፥1) ራሱን ከዚህ ዓለም የኃጢአት ፍቅርና ምኞት ያላቀቀ ሰው በጥልቅ ሰብእናው (በነፍሱ ) ውስጥ እውነተኛ ነጻነት ይሰማዋል። በዙሪያው ያለው ነገር አይረብሸውም፤ ነጻነቱን አያሳጣውም። በዚህ ውስጣዊ ነጻነት ውስጣዊ ጥልቅ ደስታ እና ሠላም ይፈልቃል። የውስጥ ሰውነታችን በዚህ ዓለም የኃጢአት ምኞት ታስሮ እውነተኛ ነጻነትን መፈለግ ግን ነፋስን እንደ መጎሰም ነው።
- እውነተኛ ነጻነት የሌሎችን ነጻነት የሚያከብር ነው
እርሱ ነጻ መሆን የሚፈልግ ሰው እንዴት የሰዎችን ነጻነት ይጋፋል? እንደዚህ ያለ ሰው እኮ የእርሱ ነጻነት በሰዎች ሲነካበት ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት አይችልም። እርሱ ለነጻነቱ ትልቅ ቦታ የሚሠጥ ከሆነ የሰዎችን ነጻነት ማክበር አለበት። መጽሐፍ “ ለአንተ ሊያደርጉልህ የምትፈልገውን ነገር አንተ ደግሞ ለሰዎች አድርግ” ይላልና።
አንድ ሰው ተደባድቦ “ማንም እንዳይነካኝ ነጻ ነኝ” ማለት ይቻላልን? ሰውነታችን እኮ የእኛ ገንዘብ ብቻ አይደለም፤ የፈጠረው የእግዚአብሔር ነው እንጅ። ከዚህም በተጨማሪ በብዙ ዋጋ ከፍለው ያሳደጉን ወላጆቻችንና ማኅበረሰባችን አሉ። እነርሱ የእኛን መኖርና እንዳሰቡን ዓይነት መልካም ሰዎች መሆን ይመኛሉ፤ይፈልጋሉም። ስለዚህ እኛ የእኛ ብቻ አይደለንም፤ ታዲያ እንዴት የእኛ የግላችን ባልሆነ ሰብእናችን ላይ በደል እንፈጽማለን?
- ነጻነት ኃላፊነት መውሰድን ያስከትላል
እግዚአብሔር ነጻ አድርጎ ሲፈጥረን በነጻነታችን ለምናምነው ነገር ሁሉ ኃላፊነት እንድንወስድ በማስጠንቀቅ ነው። “ተመልከት ዛሬ በፊትህ ሕይዎትንና ሞትን በረከትንና መርገምን እንዳስቀመጥኩ እኔ ዛሬ ሰማይና ምድርን በአንተ ላይ አስመሰክራለሁ። እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ።” (ዘዳ 30፥15-20)
በነጻነታችን ምክንያት ወደን ፈቅደን ላመጣነው ነገር ኃላፊነት እንወስዳለን።
ሕይወትና ሞት፣ ደስታና መከራ፣ መንግስተ ሰማያትና ገሃነመ-እሳት ሁሉ በነጻ ፈቃዳችን የምንቀበላቸው ናቸው። ሰው በነጻነቱ ተጠቅሞ ለሕይዎትም ለሞትም፣ ለዘላለም ደስታም ለዘላለም ስቃይም የሚሆን ሥራ መሥራት፤ ሆኖም መኖር ይችላል። የሠራው ሥራ ግን ወደ ዘላለም ስቃይ ከከተተው እግዚአብሔርንም ሰውንም ጥፋተኛ ሊያደርግ አይገባም፤የነጻነቱ ውጤት ነውና።
ሰው በነጻነቱ ተጠቅሞ ሰዎችንም እግዚአብሔርንም ሊያስቀይም ይችላል። የሚመጣውን ውጤት ለመቀበል ግን ነጻ አይደለም። ወደድንም ጠላንም በነጻነት የተደገረ ነገር በግዳችን የምንቀበለውን ነገር ያስከትላል።
አንድ ሰው ሰውነቱን በተሰጠው ነጻነት ተጠቅሞ በዝሙት፣ በሱስና በተለያዩ ኃጢአቶች ማጎሳቆል ከባሰም ማጥፋት ይችላል። ነገር ግን ይህንን ሰውነት የፈጠረው እግዚአብሔር የእጁ ሥራ በእርሱ ላይ ሲያምጽ እና ቤተመቅደሱ እንዲሆን የፈጠረውን አካሉን ሲያረክስ ዝም አይልም። እግዚአብሔር ከእኛ የበለጠ በባሕርዩ ነጻ ነውና። “የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ እንደሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን፤ ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል። የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ ቅዱስ ነውና ያውም እናንተ ናችሁ።” (1ኛቆሮ 3፥16-17)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፡- ጉባኤ ቃና 4 ዓመት