ክርስቲያናዊ ሕይወት ከግቢ ጉባኤያት በኋላ

በመ/ር ተመስገን ዘገዬ

የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ከብዙ ውጣ ውረድ ማለትም ዓለማዊና መንፈሳዊ ትምህርታቸውን በአግባቡ ከተማሩ በኋላ ተመርቀው ሲወጡ እንዴት መኖር እንደለባቸውና ምን ማድረግ እንደሚገባቸው በዚህ ጽሑፍ ለማሳየት እንሞክራለን፦

፩. ከወንድሞች ጋር በኅብረት መኖር 

የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ከምረቃ በኋላ በተሰማሩበት ሁሉ ከማኅበረሰቡ ጋር በኅብረት መኖሩ መልካም ነው፡፡ ክርስትና የኅብረት እንጂ የብቸኝነት ሩጫ አይደለችም፡፡ መጽሐፍም «ወንድሞች በሕብረት ቢቀመጡ እነሆ መልካም ነው፤ እነሆም ያማረ ነው» ሲል መናገሩም ይህንን ያስረዳል፡፡ (መዝ.፻፴፫፥፩)

ጠቢቡ ሰሎሞንም «ድካማቸው መልካም ዋጋ አለውና አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል፡፡ አንዱ ቢወድቅ ሁለተኛው ያነሣዋልና፤ አንድ ብቻውን ሆኖ በወደቀ ጊዜ ግን የሚያነሣው ሁለተኛ የለውምና ወዮለት፡፡» ብሎ እንደተናገረው የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ከምረቃ በኋላ በዚህ ዓለም ሲኖሩ በብዙ መንገድ መደጋገፍ ያሻቸዋል፡፡ (መክ.፬፦፱) አንዱ ለሌላው መሥዋዕት  እስከ መሆን ድረስ  አብሮ በፍቅር  መኖር ይገባል፤  የክርስትና ትርጉሙ ይህን  ነውና፡፡ የሞላለትና በሁሉ  ምሉዕ  የሆነ ሰው በዚህ ዓለም ማግኘቱ አስቸጋሪ ሊሆን ስለሚችል መደጋገፍ፣ መረጃ መለዋወጥ  ያስፈልጋል፡፡

በአንድነት መኖር በኢኮኖሚም ለመደጋገፍ፣ እንዲሁም ከተለያዩ የውስጥና የውጭ ፈተናዎች ለመከላከል፣ እንዲሁም ለመጠበቅ ይረዳል፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን «ብረት ብረትን ያስለዋል፤ ሰው ባልንጀራውን ይስለዋል፡፡» በማለት መልካም ጓደኛ ሌላውን ጥሩና የተስተካከለ ሰው እንዲሆን እንደሚረዳው ተናግሯል፡፡ (ምሳ.፳፯፥፲፮) መተራረም የሚቻለው በመከባበርና መልካሙን መንገድ በመከተል፤ አንተ ከእኔ ትሻላለህ በመባባል የተሰጠውን አስተያየት በመጠቀም የሕይወት ለውጥ ማምጣት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት «ከቸር ሰው ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ፤   ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፤ ከንጹሕ  ጋር ንጹሕ  ሆነህ ትገኛለህ» እንዲል፡፡ (መዝ.፲፯፥፳፭)

፪. በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ተካፋይ መሆን፡-

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ የምታድላቸው ሰባት ሀብታት (ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን) አሏት፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን «ጥበብ ቤትዋን ሠራች፥ ሰባቱንም ምሰሶችዋን አቆመች። ፍሪዳዋን አረደች፥ የወይን ጠጅዋን ደባለቀች፥ ማዕድዋን አዘጋጀች። ባሪያዎችዋን ልካ በከተማዪቱ ከፍተኛ ሥፍራ ላይ ጠራች። አላዋቂ የሆነ ወደዚህ ፈቀቅ ይበል፤ አእምሮ የጐደላቸውንም እንዲህ አለች። ኑ፥ እንጀራዬን ብሉ፥ የደባለቅሁትንም የወይን ጠጅ ጠጡ። አላዋቂነትን ትታችሁ በሕይወት ኑሩ፥ በማስተዋልም መንገድ ሂዱ።» በማለት ይገልጻል፡፡ (ምሳ.፱÷፩-፭) በዚህ ቃለ ትንቢት መሠረት ጥበብ የተባለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ቤት የተባለችውም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፣ እንዲሁም የክርስቲያኖች ሰውነት ናት፤ ሰባቱ ምሰሶዎች የሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናቸው። የታረደው ፍሪዳ ቅዱስ ሥጋው፣ የተደባለቀው ወይን የክቡር ደሙ ምሳሌ ነው።

በቅዱስ ወንጌል «ኢየሱስም፡- ‘ኑ፥ ምሳ ብሉ’ አላቸው። ከደቀ መዛሙርቱ አንተ ማን ነህ? ብሎ ሊጠይቀወ የደፈረ የለም፤ ጌታችን እንደሆነ አውቀዋልና፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መጣና ኅብስቱን   አንሥቶ ሰጣቸው፥ ከዓሣወም እንዲሁ።» ተብሎ እንደተጻፈ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ከምረቃ በኋላ በምንችውለውና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በሚፈቅድልን መሠረት በአገልግሎት መሳተፍ ይጠበቅብናል፡፡ ገና በሥራ ቦታ ተመድበን እንደሄድንም የንስሓ አባት መያዝ፣ በየጊዜው ንስሓ መግባትና እየተገናኘን ቀኖና ተቀብለን ሥጋ ወደሙን መቀበል ያስፈልገናል፡፡ (ዮሐ.፳፩፥፲፪)

በሕይወታችን «የበይ ተመልካች» መሆን አያስፈልግም፡፡ «እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅን ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም፤ … ሥጋዬን   የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ» እንደተባለ ክርስቲያን  የሆነ ሁሉ  ከዚህ ምሥጢር  በየጊዜው  መሳተፍ  እንዳለበት መረዳት ይገባል፡፡ (ዮሐ.፮፥፶፫-፶፮)

የምንሠራቸው ሥራዎች የሚባረኩት በመንፈሳዊ ሕይወታችን የምናድገው፣ መንግሥቱንም መውረስ የምንችለው ቅዱስ ሥጋውን ስንበላ፣ ክቡር ደሙንም ስንጠጣ ብቻ ነው፡፡ የምሥጢራት ተካፋይ በመሆን ሌሎችም እንዲካፈሉ ማድረግ ይኖርብናል፡፡

፫. ኑሮን በዕቅድ መምራት፡-

ዕቅድ የሌለው ሁሉ መንገዱ ውጣ ውረድ የበዛበት ነው፡፡ ኑሮዬ ይበቃኛል ብለን መኖር የምንችለው በዕቅድ ስንመራ ብቻ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ «ስለ ጉድለት አልልም የምኖርበት ኑሮዬ ይበቃኛል ማለትን ተምሬለሁ» ያለው ክርስቲያን ሕይወቱን እንደዚሁ በዘፈቀደ እንደመጣለት መምራት እንደማይገባው ሲያስገነዝበን ነው፡፡ (ፊል.፬፥፲) ዕድሜያችን በዕቅድ ላይ ተመሥርተን በመምራት ካልተጠቀምንበት ምንም ሳንሠራበት ያልቃል፡፡ እግዚአብሔር ፍጥረቱን ሲፈጥር በአንድ ጊዜ ማከናውን የሚችለውን ስድስት ቀናት የፈጀበት እያንዳንዱን ነገር በዕቅድና በሥርዓት ማከናወን እንደሚገባ ሲያስተምረን ነው፡፡ ሥራ የምንሠራበት፣የምንጸልይበት፣ ትምህርተ ሃይማኖት የምንማርበት፤ ንስሓ ገብተን ቅዱስ ቊርባኑን የምንቀበልበት የራሳችን  ዕቅድ ያስፈልገናል፡፡

የምናገኘው ገንዘብ ያለ ዕቅድና ዓላማ የምናወጣ ከሆነ ከወር ወር መድረስ አንችልም፡፡ ደመወዛችን የተቀበልን ሰሞን ሆቴል የምናማርጥ ከሆነ በወሩ አጋማሽ ጾማችንን ማደራችን የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ «ነገር ግን ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን» ይላል (፩ኛቆሮ.፲፬፥፵) የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር የቄሣርን ለቄሣር እንደተባለ በእግዚአብሔር ድርሻ ላይ ታማኞች መሆን አለብን፡፡ ስለሆነም በበረከት እንዲያትረፈርፈን ዐሥራት የማውጣት ልምድ  ከመጀመሪያው ደመወዛችን መጀመርና በየወሩ ዐሥራታችንን ማውጣት ይኖርብናል፡፡

፬. በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት መዋቅር ውስጥ በአገልግሎት መሳተፍ

ልዑል እግዚአብሔርን ማገልገል የምንችለው በቤተ ክርስቲያን ሲሆን በዕውቀታችን፤ በጉልበታችን፤ በገንዘባችንና በጊዜያችን ሁሉ እግዚአብሔርን ማገልገል ይጠበቅብናል፡፡አንዳንዶች ለምን አታገለግሉም ሲባሉ የማይረባ ምክንያት እየደረደሩ ከቤተ ክርስቲያን ይርቃሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ እንዲለመኑ፣ «እባካችሁ» እንዲባሉ ይፈልጋሉ፡፡ በማገልገላችን ከኃጢአት እንጠበቃለን፣ ሰላምና ተስፋ የተሞላበት ኑሮ እንኖራለን፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም «ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታፀኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ፤ እነዚህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉም» በማለት በአገልግሎት መትጋት እንደሚገባን ይመክረናል፡፡ (፩ኛጴጥ.፩፥፲)

ብዙዎች ከተመረቅን በኋላ አገልግሎት ያለ አይመሰለንም፡፡ አገልግሎታችንም ግቢ ጉባኤ ላይ ብቻ ይቀራል፡፡ ይህ ደግሞ የክርስትናውን ምሥጢር በአግባቡ አለማወቅ ነው፡፡ ጌታችንም ስለ ለቅዱሳን ሐዋርያት ስለ ነገረ ምጽአቱ ሲያስተምራቸው «እስከ መጨረሻው የሚጸና ግን እርሱ ይድናል» እንዳላቸው ግቢ ጉባኤ ብቻ በማገልገላችን የምንድን አይደለንም፤ እስከ መጨረሻው የሕይወት ፍጻሜ ድረስ ቃሉን በመጠበቅና በማገልገል መጓዝ እንጂ፡፡ (ማቴ.፳፬፥፲፫) የሕይወት አክሊልንም ለመቀበል እስከ መጨረሻው መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም  «ትቀበለው ዘንድ  ስላለህን መከራ ምንም አትፍራ፤ እነሆ እንድትፈተኑ ሰይጣን ከእናንተ አንዳንዶችን ወደ እሥር ቤት እንዲገቡ ያደርጋል፡፡  ዐሥር ቀንም መከራ ትቀበላላችሁ፤ እስከ ሞት ድረስም የታመንህ ሁን የሕይወት አክሊልንም እሰጥሃለሁ» ይላል፡፡ (ራዕ.፪፥፲)

የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ከምረቃ በኋላ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚገኙ መዋቅሮች ማለትም በሰ/ት/ቤት፣ በሰበካ ጉባኤ በመታቀፍ ማገልገል ይገባል፡፡ በተለይም ለአገልግሎት   የሚመች ሰበካ ጉባኤ እንዲመሠረትና በዚያም ውስጥ የራስን አሻራ በማሳረፍ ቤተ ክርስቲያንን መደገፍ፣ የተሻለና ቀልጣፋ አሠራርን መከተል የሚያስችሉ መንገዶችን በመቀየስ የድርሻን መወጣት ያስፈልጋል፡፡

የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ከምረቃ በኋላ በተመረቁበት የሙያ መስክ ገብተው አስፈላጊውን ሥራ መሥራት ብቻ በቂ አይደለም፡፡ በታማኝነትና በቅንነት መሥራትንም ይጠይቃል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ የልጆቿችን ሙያ እንደምትሻ ግልጥ ነው፡፡ በተለይም የልማት ተቋማትን በማደራጅት (ለምሳሌ ፕሮጀክት በመቅረጽ) በኩል ያለባትን የመዋዕለ ንዋይ  ችግር ለመቅረፍ የምትወስዳቸው ርምጃዎች ማንነቷን የሚያሳውቁ እንጂ የሚያደበዝዙ እንዳይሆኑ  በውስጧ ሆነው ምሥጢሯንና  ቋንቋዋን የሚያውቁ የራሷ ልጆች ቢያጠኑላት ዛሬ የሚታዩት አስተዳደራዊ ችግሮች ባልተከሠቱ  ነበር፡፡

ተመርቀን ከየግቢ ጉባኤያት ተለይተን ወደ ሥራ ዓለም ስንሠማራ እንደ የአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ በተለያዩ ደረጃዎች ላይ ያሉ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ያጋጥሙናል፡፡ ተጠናክረው በጥሩ አገልግሎት የሚገኙ፣ ተቋቁመው በአገልጋይ እጥረት ምክንያት አገልግሎት ያቆሙ፣ እንዲሁም ያልተቋቋሙባቸው አካባቢዎች ሊያጋጥሙን ይችላል፡፡ ከጠንካሮቹ ሰ/ት/ቤቶች ልምድ በመውሰድ የሚጠናከሩበትን መንገድ ማሰብ፣ መቀየስና ተግባራዊ እንዲሆን የተቻለውን ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በግቢ ጉባኤያት ካገኘናቸው ልምዶችም በመነሣት ስልት መቀየስ ከግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ከምረቃ በኋላ የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡

በየሄድንባቸው አካባቢዎች ሰ/ት/ ቤት ከማቋቋማችን በፊት አስቀድመን አካባቢውን ሕዝብ ጠባዩን ፍላጎቱን ባህሉንና የኗኗር ዘይቤውን ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ ማጥናት፣ ከዚያም በቃለ ዓዋዲው መሠረት ማደራጀት እንዳለብን ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ብዙ ከመናገር ብዙ መስማትና ከማገልገልም በፊት ብዙ መገልገልን መምረጥ አስፈላጊ ነው፡፡ ያለውን ሁኔታ ሳናጠና በድፍረት መግባት መውጫችንን ያከብደዋልና፡፡ «እንደ እባብ ብልህ እንደ ርግብ የዋህ» መሆን ያስፈልጋል፡፡(ማቴ.፲፥፲፮) በተቻለ መጠን እኛ እንደ ወንድምና እኅት ቀርበን የሥጋዊ ሕይወታችን አለመሟላት መንፈሳዊና ሕይወታችንን እንደሚያጎድለው ብዙዎችም ወደ መጥፎ ሕይወት እንዳይገቡ ማሰገንዘብ አለብን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *