“እግዚአብሔርን ፈልጉት፥ ትጸናላችሁም፤ ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ።”

፩ኛ ዜና መዋዕል ፲፮፥፲፩ 

በዲያቆን በረከት አዝመራው

እግዚአብሔርን መፈለግ እና ወደ እርሱ ሰው ሁሉ መቅረብ ይገባዋል? ወይስ ጥቂቶች ብቻ የሚጣጣሩበት ሕይወት ነው ብለን እንደፈለግን መሆን ይቻለናል? በውኑ አእምሮ ያለው ፍጡር ያስገኘውን ፈጣሪውን ከመፈለግ፣ ከፈጣሪው ጋር ኅብረት ከመፍጠር እና የተፈጠረበትን ዓላማ ከመፈጸም የበለጠ ምን ታላቅ ተግባር አለው?

መልካም አባት ሁልጊዜ ለልጁ ጥሩ ነገርን እንደሚያስብ እና እንደሚያደርግ የታወቀ ነው። በዚህም ምክንያት “ጤነኛ” ልጅ ሁሉ አባቱን ይወዳል:: ካለማወቅ እና ከድካም የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ቢሳሳትም በአብዛኛው ግን የአባቱን ትእዛዝ ይጠብቃል:: ታዲያ እግዚአብሔር “ከልብ ለሚፈልጉኝ ሁሉ እገኛለሁ፤ ከምድራውያን ወላጆች ጋር የማልነጻጸር መልካም አባት ነኝ፤ ለሚወዱኝ ዓይን ያላየው፣ ጆሮ ያልሰማው፣ በሰው ልብ ያልታሰበ ታላቅ ሥጦታን እሰጣለሁ” (፪ኛ ዜና መዋዕል ፲፭፥፪፣ ማቴ. ፯፥፲፩፣ ፩ኛ ቆሮ. ፪፥፱) እያለ ዘወትር እየተጣራ፤ ሰዎች ወደ እርሱ በሙሉ ልብ ለመቅረብ ፈቃዳችን የሚደክመው እና ዳተኛ የምንሆነው ለምንድን  ነው?

እግዚአብሔር ሰዎች ሁሉ የዳኑ እንዲሆኑ ፈቃዱን አስታውቋል:: በሙሉ ፈቃድ ወደ እርሱ ለመቅረብ እየጣሩ ከድካምና ከዲያብሎስ ጥቃት የተነሳ የሚሰነካከሉትን በረድኤት እንደሚስባቸው በጸጋ እንደሚያቀርባቸውም ተናግሯል። (ዮሐ. ፮፥፴፯፣ ዕብ. ፬፥፲፬‐፲፮፣ ፊልጵ. ፬፥፲፫) ታዲያ እኛ ሰዎች፣ የልቡናችን ብርሃን የሆነ አምላካችንን ዘወትር መፈለግ እና ወደ እርሱ መቅረብን ትተን ጨለማን ያስመረጠን ነገር ምንድን ነው?

አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሕመምተኞች እንጂ ባለ ጤናዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም፤ ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም፤” ብሏል። (ሉቃ. ፭፥፴፩) ከእግዚአብሔር ርቀን ሕመምተኞች አይደለንም ብንል ሐሰተኞች ነን። ከእግዚአብሔር ርቆ በኃጢአት የሚኖር ሰው መጨረሻው አስከፊ በሆነ ታላቅ ሕመም የተጠቃ ነው።

መድኃኒታችን “ጤነኞች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም” ያለው ከሰው ልጅ መካከል እርሱ የማያስፈልጋቸው ጤነኞች ስላሉ አይደለም። ሰው እንዴት በሽተኛ ሆኖ መድኃኒት ሳይፈልግ ራሱን እንደ ጤነኛ ቆጥሮ ይኖራል? እስከ ነፍሱ ዘልቆ የሚሰማውን ጽኑዕ በሽታውን የሚያስረሳው እና በከንቱነት የሚያባዝነውን ነገር እንዴትስ ዝም ብሎ ይመለከተዋል? ክርስትና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ቤዛ አድርጎ ለሰው ልጅ የሠጠበት የማዳን ጉዞ ነው። በአምላካችን ሰው መሆን በመስቀል ላይ የተገለጠው ፍቅር ድኅነትን ለሚፈልጉ ሁሉ ዘመን የማይገድበው ወደ እርሱ የመመለስ የመዳን ጥሪ ነው።

በአጠቃላይ የሰው ልጅ፡- በለመለመ መስክ የሚያሰማራውን መልካሙን እረኛውን እግዚአብሔርን መፈለግ እና ወደ እርሱ መቅረብን ረስቶ እንዲኖር የሚያደርጉት ነገሮችን በጥልቀት መመርመር ይገባዋል። ሕይወቱን ከነዚህ ቁራኛዎች ለማላቀቅ መጋደልም ይኖርበታል፤ ያመንበት እና ክርስቲያን የሆንበት ቅዱስ ወንጌል ይህን ያዝዛልና። ሰውን አምላኩን ከመፈለግ የሚያወጡት እና ያለ መድኃኒት በኃጢአት ተይዞ ከነ ሕመሙ እንዲኖር የሚተበትቡት ነገሮች ከተለያየ አቅጣጫ የሚመጡ ናቸው። ከነዚህ መካከል የመጀመሪያው እና ዋነኛው ልቡናውን እና ስሜቶቹን ተቆጣጥሮ የሚያቅበዘብዘው የዚህ ዓለም ክፉ ምኞት ነው። የዚህ ዓለም ክፉ ምኞት የሰውን ልብ የመቆጣጠር እና እውነተኛ ፍቅርን የማጥፋት ኃይል ስላለው ሰውን ወደ ሞት የሚወስድ መርዛማ ሕመም ነው።

የተለያዩ ዓለማውያን ፍልስፍናዎች እና በየዘመኑ የሚቀያየሩ “ዕውቀቶች” በእምነት ባልጸና ሰው አእምሮ  ላይ የሚፈጥሩት ጥርጥር እና በዚህ ምክንያት የሚፈጠር ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ተስፋ ማጣት ሁለተኛው እና ሌላው እግዚአብሔርን ለመፈለግ እና ወደ እርሱ ለመቅረብ የሚያደክም የዘመኑ ፈተና ነው። አንዳንድ ጥንታውያን ግሪኮችን ፍልስፍናቸው የወንጌልን ጥሪ እንደሞኝነት እንዲቆጥሩ አድርጓቸው ነበር:: ብዙዎቹ ግን እነርሱ ከፈጠሩት የዚህ ዓለም ጥበብ ይልቅ እግዚአብሔር ዓለምን ያዳነበት ሰማያዊ ጥበብ እንደሚበልጥ አውቀው የወንጌልን ጉዞ በድል ፈጽመዋል። ይህንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና። የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና። ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን? በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፥ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና። መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ፤ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፥ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፥ ለተጠሩት ግን፥ አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎችም ቢሆኑ፥ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው።” በማለት ገልጦታል። (፩ኛ ቆሮ. ፩፥፲፱‐፳፬)

ሌላው ብዙዎቻችን እግዚአብሔርን መፈለግ እንዳንችል ምክንያት የሚሆንብን ደግሞ የእግዚአብሔርን መልካምነት በኑሮ የሚተረጉም እና ሰዎች እግዚአብሔርን ከልብ ይፈልጉ ዘንድ ሕይወቱ ብርሃን የሚሆን አርዓያነት ያለው ሰው በቀላሉ ለማግኘት መቸገር ነው። የጥንት ሰዎችን ወደ እውነተኛ ክርስትና የሳባቸው እና እስከ ሞት ያጸናቸው በዘመናቸው የነበሩ ሰማዕታት እና መነኮሳት እንዲሁም ሌሎች ምዕመናን እውነተኛ ሕይወት ነው። እውነተኛ ፍቅር እንደ መልካም ሽቱ ነው፤ ሌሎችንም ይጣራል። በዘመናችንም እግዚአብሔር የሚያውቃቸው እውነተኛ ሰዎች ቢኖሩትም አርዓያ የሚሆን ሰው በቀላሉ ማግኘት ግን እየከበደ መጥቷል።

እግዚአብሔርን ከመፈለግ እና ወደ እርሱ ከመቅረብ ከሚያሰናክሉ ምክንያቶች በዋነኝነት ስለጠቀስነው ስለከንቱ የዓለም ክፉ ምኞት የሚከተለውን ማስተዋል ይገባናል::

ክፉ የዓለም ምኞት

በመጀመሪያ “እግዚአብሔር የሚወደዱ ነገሮችን ፈጥሮ እንዴት አትውደዷቸው ይለናል?” ብለን እናጉረመርም ይሆናል። በርግጥም እግዚአብሔር የፈጠራቸው ፍጥረታት እና እነርሱን የሚፈልጉ ውስጣዊ ሕዋሶቻችን ሁሉ የፈጣሪ ሥራዎች ናቸው። በመሆኑም የሰውን ልቡና በፍቅር እና በተደሞ የሚሞሉ እና ፈጣሪያችንን እንድናደንቅ የሚረዱ ናቸው። እግዚአብሔርም በአግባቡ እና በሥርዓቱ እየተጠቀምንባቸው ወደ እርሱ እንቀርብባቸው ዘንድ ለእኛ የፈጠራቸው በመሆኑ፤ እግዚአብሔር በፈቀደው እና ባዘዘው መንገድ እንጠቀምባቸው ዘንድ ይገባናል።

የሰው ልጅ፡- የተፈጠረበትን ክብር ሣይዘነጋ፣ ሥነ ፍጥረትን ለኑሮው እየተጠቀመ እና እያደነቀ አምላኩን ያመሰግን ዘንድ በአስተዋይ አእምሮ  እና በመንፈሳዊ ጸጋ አስጊጦ፣ ከሁሉም በላይ ዘወትር ወደ እርሱ ይበልጥ እየቀረበ ይኖር ዘንድ እግዚአብሔር በአርዓያው እና በአምሳሉ የፈጠረው ከፍጥረታት ሁሉ ድንቅ ፍጥረት ነው። (ዘፍ. ፩፥፳፮‐፴፩)

ክፉ የዓለም ምኞትም፡- ሁሉን አሟልቶ የፈጠረንን ሰማያዊውን አባታችንን ረስተን የፈጠራቸውን ፍጥረታት በትዕዛዙ ከተፈቀደልን በተቃራኒው ለማይሞላ ምኞታችን እና ለማይረካ ስሜታችን በማግበስበስ ተጠምደን ራሳችንን ለጊዜያዊ ደስታ አሳልፈን መስጠት ነው። ይህ ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት እና ለዘላለሙ የሚለይ ታላቅ ኃጢአት ነው።

በክብር እና በፍቅር ቃል ኪዳን የተጣመሩበትን ጋብቻቸውን ትተው ከሌላ ጋር የሚማግጡ እና ከልቡናቸው የትዳር አጋራቸውን ያጠፉ ሴት እና ወንዶች አመንዝራ እንደሚባሉ ክብሩን ወርሶ በምስጋና ይኖር ዘንድ የፈጠረውን እግዚአብሔርን ረስቶ ራሱን ለክፉ የዓለም ምኞት አሳልፎ የሰጠ ሰውም በሚወደው የአምላኩ ፍቅር ላይ ያመነዘረ ነው። ይህም ሐዋርያው “አመንዝሮች ሆይ፥ ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል፤” በማለት የገለጠው ነው። (ያዕ. ፬፥፬)

የእግዚአብሔር ትእዛዛት ሁሉ የፍቅሩ መግለጫዎች ናቸው፤ “እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፥ ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ” እንዳለ ጌታችን። (ዮሐ. ፲፭፥፲) በተቃራኒው ደግሞ ሰው ዓለምን በተሳሳተ መልኩ ሲወድ እና በክፉ የዓለም ምኞት ሲሞላ እግዚአብሔርን ይረሳል፤ ነፍሱን በከንቱ የኃጢአት ምኞት ያሳምማል፤ መጨረሻውም የዘላለም ሞት ይሆናል።

ይህ ራስን ለሥጋ ክፉ ምኞት አሳልፎ መስጠት ከአዳም እና ከሔዋን ጀምሮ ሰውን ከእግዚአብሔር ፍቅር እየለየ እና የሰውን ልብ በኃጢአት ፍላጻ እየወጋ የሚኖር ነው። የሰው ልጅ እንዴት ለከንቱነት እንደሚገዛ እንመልከት፤ ራሳችንንም እንመርምር! በሥጋ ምኞት፣ በዓይን አምሮት እና በከንቱ ክብር ፍለጋ ልቡናውን ያጣ እና ሕይወቱ በቅድስና እና በዘላለማዊ ደስታ ይሞላ ዘንድ ማደሪያ ሊያደርገው በልቡናው በር ቆሞ የሚጠራውን አምላኩን ረስቶ የሚኖር ስንት ሰው አለ?

ይህ ማለት ግን የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር የተሰጡትን ፍላጎቶቹን እና ስሜቶቹን መካድ አለበት ለማለት አይደለም። የእግዚአብሔር ትዕዛዛት የሕይወታችን ሚዛን እንድንጠብቅ እና በሥጋዊ ምኞት ታውረን ፍቅሩን እንዳንረሳ የተሰጡ እንጂ እግዚአብሔር መከልከል ስለሚወድ የተሰጡ አይደሉም። ስለዚህ ባህርያችንን የፈጠረ እና ውስጣችንን የሚያውቅ እግዚአብሔር የሚያስፈልገንን እና ለእኛ መልካም የሆነውን ሁሉ በሥርዓት እና በትእዛዙ መሠረት እንድንጠቀም ፈቅዶልናል። በዚህ መልኩ የእግዚአብሔርን ፍቅር ጠብቀን ብንኖር በሕይወታችን ሁሉ እውነተኛ ደስታ እና ማንም የማይወስደው ሠላም እናገኛለን።

ከዚህ ርቆ እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ መኖር የሚገባው የሰው ልጅ በቁስ አካል ማግበስበስ (Material Consumption) እና በዚህ ዓለም ብልጭልጭ ነገር ሊሞላ የሚባዝን ከሆነ፤ ሰውነቱ በጠና ታማለች እና ከነሕመሙ ወደ ዘላለማዊ ሞት ሳይወርድ መድኃኒት የሆነውን እግዚአብሔርን መፈለግ ይገባዋል። ታላቁ ንጉሥ ዳዊት በዝሙት ኃጢአት በታመመ ጊዜ “ድውይ ነኝና አቤቱ፥ ማረኝ፤ አጥንቶቼ ታውከዋልና ፈውሰኝ፤” በማለት ወደ አምላኩ ጮኾ ነበር። አምላኩን ረስቶ በዓለም ከንቱ ምኞት የተያዘ እና መቅደስ ሰውነቱን በኃጢአት ምኞት እና በከንቱ ክብር ፍለጋ ያጎሰቆለ እና ያሳመመ ሰውም በንስሃ ይቅር ሊለው የሚችለውን እግዚአብሔርን ሊፈልግ ይገባል። (መዝ. ፮፥፪)

ክፉ ምኞት ጤናማ የሰው ተፈጥሮን ከማበላሸት ጋር የተያያዘ ስለሆነ በሁሉም ዘመናት የኃጢአት ምንጭ ሆኖ ኖሯል። በሁሉም ዘመናት በዚህ ተይዘው የነፍሳቸውን ጩኸት ባለመስማት እና በልቡናቸው ያለውን ቦታ ሁሉ በዚህ ዓለም ፍቅር ቅድስናቸውን ያጡ፣ የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነች ሰውነታቸውንም በሥጋ ምኞት እና ከንቱ ክብር ፍለጋ አጎስቁለው፣ በቅድስት ተዋህዶ እምነታቸው መፅናት ሲያቅታቸው፣ አዲስ እምነት እየፈጠሩና እየፈለጉ ወደማይቀረው መቃብር የወረዱ፤ አሁንም የሚባዝኑ ብዙዎች ናቸው።

በተቃራኒው በዓለም ከንቱ ምኞት ሳይያዙ የአምላካቸውን ፍቅር ጠብቀው የኖሩ፣ በድካም በቆሰሉ ጊዜም መድኃኒታቸው እግዚአብሔርን በንስሐ የፈለጉ፣ በቅድስናና በንፅሕና እንዲሁም በፅናት የኖሩ ፃድቃን ሰማዕታት ቤተ ክርስቲያን አሏት:: እነርሱ ለዘላለማዊው የእግዚአብሔር መንግሥት ተዘጋጅተው በሥጋቸው አሸልበዋል፤ በነፍሳቸው ወደ ጌታቸው ደስታ ገብተዋል፤ ነጻ የምታወጣ ኢየሩሳሌም ሰማያዊትን በደስታ ይጠብቃሉ፤ “ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ በእነርሱ አያፍርም፥ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና።” (ዕብ. ፲፩፥፮)

በዘመናችን ከንቱ የዓለም ክፉ ምኞት በዝቶ እናያለን። የሰው ልጅ ፍጥረታትን የሚመረምርበት ዕውቀቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመሩ ቁሳዊ ሥልጣኔው (Material Civilization) ቢያድግም ፍጥረታትን ከፈጣሪያቸው የሚያገናኛቸውን የሃይማኖት መንገድ እየተው እና ፈጣሪያቸውን እየረሱ መጥተዋል። ይህ ቁሳዊ አስተሳሰብ (Materialism) ዓለማቀፋዊ ይዘት ስላለው ሁሉን የሚፈታተን እየሆነ ነው።

በዚያው ልክ ደግሞ የኃጢአት ምኞት በተለያየ አቅጣጫ እያየለብን ይገኛል። እግዚአብሔር ለቅድስና እና ለፍቅር የፈጠረው እና በተቀደሰ ጋብቻ ዘር እንድንተካበት የተሰጠን ሩካቤ ዓላማውን እና ቅድስናውን እያጣ ሰውነትን ማቃጠያ ሆኗል። በተለይ ከዘመናዊነት እና ከኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ ቤታችን እና ስልኮቻችን ድረስ የሚደርሰው ልዩ ልዩ ኃጢአት የሰውን ነፍስ ክፉኛ እያቆሰለ ይገኛል።

እኛ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ፍቅር እና የቅድስና ትእዛዛቱ ማደሪያ ሆነን፣ እግዚአብሔር በፈቀደው መልኩ ራሳችንንም ሰውንም ሳንጎዳ እንደ ቅዱስ ፈቃዱ ለመኖር የተጠራን ስለሆን፤ ሰውን ወደ አውሬነት ከሚቀይር ሰዶማዊ የሥጋ ምኞት ራሳችንን መጠበቅ አለብን።

ወጣቶች በምኞት ቀስት ቆስለን ብንወድቅ እንኳ ምኞት ሥር ሰድዶ ባሪያ ሳያደርገን እና ሳይገድለን ወደ ይቅርታውና ምህረቱ የበዛ አምላካችን ሳንዘገይ ወደ ካህናት አባቶቻችን በመቅረብ በንስሐ መመለስ አለብን። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳለው ክርስቲያን እንደመሆናችን ከዚህ ዓለም የክፉ ምኞት ጥፋት አምልጠን በተስፋ የመለኮታዊ ባህርይ (ክብር) ተካፋይ ስለሆንን ለዚህ መጠራታችን እንደሚገባ መኖር ይጠበቅብናል። (፪ኛ ጴጥ. ፩፥፬)

ወጣትነት ምኞት የሚበዛበት እና ብዙ ፍላጎቶች የሚሰለጥኑበት ወቅት በመሆኑ፤ ፍላጎታችን ወደ ከንቱ ምኞት እና ቁሳዊ ባርነት እንዳያስገባን ራሳችንን በቅድስና መጠበቅ ይገባናል። በምናገኛቸው “ዘመናዊ ዕውቀቶች” ውስጥ ሰውን በቁሳዊ ባህርዩ ብቻ የሚመለከቱ እና የቁሳዊ ፍላጎቶች ጥርቅም አድርገው የሚያሳዩ አስተሳሰቦች ስናገኝ በእግዚአብሔር የማያምኑ አንዳንድ ኢ-አማንያን ሳይንቲስቶች ዝግመተ-ለውጣዊ እምነታቸውን የጫኑባቸው የዘላለማዊ እውነትን ቀርቶ ሳይንሳዊ መስፈርቶችን እንኳ የማያሟሉ ምድራዊ ዕውቀቶች (Pseudo-knowledge) መሆናቸውን መረዳት ይገባል።

የሰው ልጅ ከቁስ ያለፈ መሆኑን ለመረዳት፣ ጠለቅ ብለን ወደ ራሳችን ውስጥ በጥሞና መመልከት በቂ ነው። በጥሞና ከመረመርነው ፍላጎታችን፣ ደስታችን፣ ኃዘናችን፣ የሕሊና ሕጋችን በአጠቃላይ ሕይወታችን የሚመሩት ውስጣዊ ስሜቶቻችን እና አስተሳሰቦቻችን ሁሉ በዚህ ዓለም ብቻ የማይሞሉ እና ዘላለማዊ ይዘት ያላቸው እንደሆኑ የራሳችን ውስጥ ይነግረናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ባህርያችንን የፈጠረ አምላክ በነባቢት ነፍስ በአርዓያው እና በአምሳሉ ለዘላለማዊ ሕይወት እንደፈጠረን ራሱ ሰው ሆኖ ክብራችንን ነግሮናል፤ አሳይቶናል።

በዓለም ክፉ ምኞት ተይዞ መኖር የሞት መንገድ ስለሆነ፤ ታላቅ ኃጢአት ነው። የዓለም ክፉ ምኞት ታላቅ ኃጢአት ከሚሆንባቸው ምክንያቶች አንዱ በቅድስና መኖርን ስለሚያስረሳን እና ፍቅሩን ስለሚያጠፋብን ነው።

ልቡናችን በተፈጥሮ እግዚአብሔርን ወደ መፈለግ ያዘነበለ እና ለፍቅሩ የተዘጋጀ ነው። ከልቡናችን ውስጥ እግዚአብሔርን መፈለግ እና ደረጃው ቢለያይም የእግዚአብሔር ፍቅር ከጠፋብን በተለያየ መንገድ የሚገለጥ ዓለምን እና ምኞቱን የማሳደድ ሕመም ልቡናችንን አቁስሎታል ማለት ነው። ልቡናችንን በዓለም ከንቱ ምኞት ሞልተን ለውዱ የእግዚአብሔር ፍቅር ማደሪያ አሳጥተናል ማለት ነው።

ፍላጎታችንን ሁሉ በአላፊው እና በጠፊው ምኞት አስይዘን ብርሃናውያን መላእክት አመስግነው የማይጠግቡትን፣ ለዘላለም በምንኖርባት የሕያዋን ምድር ዘወትር ሊያበራልን ወደ መንግሥቱ የጠራንን የአማልክት አምላክ ትዕዛዛቱን ባለመጠበቅ ወደ እርሱ መቅረብን ከዘነጋን ዓለም በክፉ ምኞቶቿ ወደ ጉስቁልና ሞት እየጎተተችን ነው።

እንዲህ ከሆነ በእሪያ ምግብ በተመሠለው የዓለም ምኞት ተይዘናልና እንደትዕዛዙ መኖር ሲያቅተን ከቅድስት ቤተክርስቲያን ርቀናልና ጊዜ ሳንቀጥር እንደጠፋው ልጅ ወደ ልቡናችን እንመለስ ዘንድ ይገባናል። እርሱ “እህል የሚተርፋቸው የአባቴ ሠራተኞች ምን ያህል ናቸው? እኔ ግን በዚህ በረሃብ ልሞት ነው። ተነሥቼ ወደ አባቴ ልሂድ።” እንዳለው እኛም ወደ እግዚአብሔር ልንመለስ እና በቅድስና ልንኖር ይገባናል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ፡- ጉባኤ ቃና ፱ኛ ዓመት ቁጥር ፩