‘‘እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት’’(ማቴ. ፲፭፥፲፪)

በመ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ የወይን ሐረግ ስለመሆኑና አምነው የተከተሉት ሁሉ ደግሞ ቅርንጫፎች እንደሆኑ በብዙ ምሳሌ ካስረዳ በኋላ ከላይ በርዕስ የተነሣንበትን ቃል ተናግሯል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ቃል በቃል ስንመለከተው “እኔ እንደወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ የእኔ ትእዛዜ ይህች ናት፣ ስለ ወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ሰው ያለ እንደሆነ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የለም፤ እናንተስ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ካደረጋችሁ ወዳጆቼ ናችሁ” (ዮሐ.፲፭፥፲፪-፲፭) ይላል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛ እርስ በእርሳችን እንዋደድ ዘንድ እንደሚገባ ከማዘዙ አስቀድሞ እርሱ እኛን የወደደበትን ፍጹም ፍቅሩ አብነት እንዲሆነን ጠቅሶልናል፡፡ እሱም ፍጹም አምላክ  ሲሆን ፍጹም ሰው ሆኖ በሥጋ የተመላለሰው እኛ የሰው ልጆች በግብራችን (በሥራችን) ደካሞች (ሰነፎች) ብንሆንም በነገር ሁሉ ብርቱ የሆነውን እርሱን ተመልክተን ከድካማችን እንድንበረታ ነው፡፡

ለዚህም ነው ጌታችን በወንጌሉ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ፣ ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ የዋህ ነኝና በልቤም ትሑት ነኝና ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀላል ነውና” (ማቴ. ፲፩፥፳፰) በማለት ያስተማረን፡፡

እኛ ምንም ሳይኖረን ማለትም በበደላችን ምክንያት ከጸጋው ተራቁተን፣ በኃጢአት ተጎሳቁለን፣ ደስታ ርቆን በኀዘን ተውጠን ሳለ እንዲሁ የወደደን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ከእኛ ምንም አገኛለሁ ወይም እጠቀማለሁ ሳይል ሕመማችንን የታመመ፣ ስለ እኛ የቆሰለ፣ ሞታችንን ሞቶ ሕይወቱን ያደለን እርሱ ፍቅር ስለሆነ ነው፡፡ እንግዲህ እንዲህ ያለ ዋጋ እንደ ወደደንና መተኪያ የሌለውን የደም(የሕይወት) ዋጋ ከፍሎልን ፍጹም ፍቅሩን እንዳሳየን ሁሉ እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ አዝዞናል፡፡

እርሱ እንደወደደን እርስ በርሳችን መዋደድ ማለትም፡ ጥቅምን፣ ዋጋን፣ ክፍያን፣ ውለታን ምክንያት ሳናደርግ እንዲሁ ያለ ዋጋ፣ ያለ ውለታ፣ ያለ ጥቅም መዋደድ ነው፡፡ ይህም ያለው ለሌለው፣ ያገኘው ላላገኘው፣ የተማረው ላልተማረው፣ የበረታው ለደከመው ነገ ይከፍለኛል ወይም ውለታዬን ይመልስልኛል ብሎ ሳያስብ እንዲሁ ያለ ዋጋ በነፃ የሚደረግ ስጦታ ከእውነተኛ ፍቅር የተገኘ ነው፡፡

እርስ በእርስ መዋደድ፡- ዘርን፣ ብሔርን፣ ቋንቋን ምክንያት ሳያደርግ ድሃ፣ ባለጠጋ ሳይል ሁሉን በእኩል ዓይን መመልከትና መውደድ ነው፡፡ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ለሙሴ ከሰጠው ከዐሥሩ ትእዛዛት መካከልም አንዱ “ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ” (ዘሌ. ፲፱፥፲፰) የሚል ነው፡፡

ስለዚህ ክርስትና ስለራስ ብቻ የሚኖሩበት፣ ስለራስ ብቻ የሚያስቡበት፣ ስለራስ ብቻ የሚጨነቁበት ሕይወት ሳይሆን ስለ ሌላውም የሚኖሩት፣ የሚያስቡበት፣ የሚጨነቁበት፣ የመረዳዳትና የመተሳሰብ ሕይወት ነው፡፡ ለዚህም ነው ጌታችን ኢሱስ ክርስቶስ በወንጌሉ “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ኦሪትም ነቢያትም የሚያዝዙት ይህ ነውና” (ማቴ. ፯፥፲፪) በማለት ያሰተማረን፡፡

የክርስትና ሃይማኖት እርስ በእርስ የሚፋቀሩበት፣ የሚረዳዱበትና የሚተሳሰቡበት ሕይወት  ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እንቅፋት የሚሆኑብንን ክፉ ምግባራት ከሕይወታችን ልናስወግዳቸው ይገባል፡፡ እነዚህ ክፉ ምግባራት ራስን ከመጉዳታቸው በተጨማሪ በማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ ክርስቲያናዊ የሆነ መልካም ግንኙነት እንዳይኖረንና እውነተኛ ፍቅር እንዳናሳይ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ በመሆኑም እነዚህን የመልካምነት እንቅፋቶች የሆኑትን፣ ከክርስቲያናዊ ሕይወት ሊወገዱ የሚገባቸውን ክፉ ተግባራት ከብዙው በጥቂቱ ስንመለከት፡-

፩ኛ. ራስ ወዳድነት

ራስ ወዳድነት ሲባል ስለ ራስ ምቾትና ጥቅም ሲባል ብቻ በጣም ከማሰብ የተነሣ ስለ ሌሎች ሰዎች ወይም ስለ ማኅበረሰቡ ግዴለሽ መሆንና እንዲያውም ስለ ግል ጥቅም ሲባል የሌላውን ሰው መብት መጋፋት ማለት ነው፡፡ ስለ ሌላው ሰው ማሰብ ሲባል ደግሞ ሰው ለራሱ እንዲሆንለት ወይም እንዲደረግለት የሚፈልገውን ጉዳይ ለሌላም ሰው እንዲደረግለት መመኘት ወይም ለማድረግ ፈቃደኛ መሆን ማለት ነው፡፡ እንዲሁም በራስ ሊደርስ የማይፈለግ ድርጊት በሌላ ሰው ላይ እንዲደርስ አለመመኘት ነው፡፡

ይህንን በጎ ተግባርም የእምነት አባት አብርሃም በመፈጸሙ እንደ ምሳሌ ተጠቃሽ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነገረን አብርሃምና ሎጥ በቤቴል ሰፍረው ሳለ እግዚአብሔር በብዙ ባረካቸው እጅግ የብዙ መንጎች ባለቤትም ሆኑ ነገር ግን መንጎቻቸው ከመብዛታቸው የተነሳ የማሰማሪያ ስፈራ ስለ ጠበባቸው እረኞቻቸው መጋጨት ጀመሩ፡፡ በዚህን ጊዜ አብርሃም ሎጥን እኛ ወንድማማቾች ነንና በእኔና በአንተ፤ በእረኞቼና በእረኞችህ መካከል ጠብ እንዳይሆን እለምንሃለሁ…አንተ ግራውን ብትወስድ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ አንተም ቀኙን ብትወስድ እኔ ወደ ግራ እሄዳለሁ በማለት የመረጠውን ይወስድ ዘንድ የወንድሙን ምርጫ አስቀደመ፡፡

ምንም እንኳ አብርሃም በታላቅነቱ ቅድሚያና መከበር የሚገባው ቢሆንም እርሱ ግን ምርጫን ለወንድሙ ልጅ ለሎጥ ትቶለት ከራስ ወዳድነት ሸሸ፡፡ ሎጥ ግን በወቅቱ የራሱን ምርጫ በማስቀደም የተሻለ መስሎ የታየውን  አቅጣጫ መረጠ፡፡ ከዚያ በኋላ ሎጥ የመረጠው ሀገር ሰዶምና ገሞራ እንዲጠፉ በተወሰነበት ጊዜ ከዚያች ተሰዶ ተንከራተተ፡፡ አብርሃምን ግን ባለበት ቦታ እግዚአብሔር ባረከው (ዘፍ. ፲፫፥፰)፡፡

ይህንን አስመልክቶ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በወንጌል “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተም ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው” በማለት አስተምሮናል (ሉቃ. ፮፥፴፩)፡፡

ብዙዎች መንፈሳውያን ሰዎችም ከራሳቸው ክብርና ጥቅም ይልቅ የሌላውን ሰው ክብርና ጥቅም ያስቀድማሉ፡፡ በዚህ በጎ ተግባራቸውም እንደ አብርሃም ተባርከውበታል፡፡ በመሆኑም ለኔ ብቻ ይመቸኝ እንጂ ስለ ሌላው ምን ገዶኝ ከሚለው ራስ ወዳድነት ይልቅ ጸጋና በረከት የሚገኝበትን ለሌላ ሰው የማሰብን ጠባይ ቅዱሳን አባቶቻችን አብነት አድርገን ፈለጋቸውን እንከተል ዘንድ ያስፈልጋል፡፡

በመሁኑም  ክርስትና ስለ ራስ ብቻ ሳይሆን ስለ ሌላውም የሚኖሩበት ሕይወት ነው፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው ስለ ራስ ብቻ በማሰብ፣ እኔን ከተመቸኝ፣ ለእኔ ከሆነልኝ፣ እኔን ከተስማማኝ፣ ለእኔ ከዘነበለልኝ በማለት ግላዊ ጥቅምንና የራስን ድሎት ብቻ በማስቀደም የሚኖሩት ሕይወት መንፈሳዊ ሳይሆን ሥጋዊ (ዓለማዊ) ኑሮ ነው፡፡ ለዚህም የሚጠቀስ አንድ አባባል አለ፡፡ እሱም፡- “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አለች አህያ” የሚል ነው፡፡ ይህንን ቃል አህያ አፍ አውጥታ ተናገረች ለማለት ሳይሆን ራሱን ብቻ የሚወድ ሰው ስለራሱ እንጂ ስለ ሌላው ምንም የማይገደው መሆኑንና ይህም ክፉ ጠባይ እንደሆነ ለማሳየት ነው፡፡

ራስ ወዳድ ሰው የራሱን ጥቅም ለማስከበር ሲል በወንድሙ ደም ይረማመዳል፡፡ ሌላውን ገፍትሮ ጥሎ ራሱ ብቻ ለመቆም ይጥራል፡፡ የሌላውን እድል ሰብሮ የራሱን ነገር ብቻ ያደላድላል፡፡ ይህ ደግሞ ከክርስቲያናዊ ሕይወት የማይጠበቅ እኩይ ተግባር ነው፡፡ ከቅዱሳን አባቶቻችን  ሕይወት እንደተማርነው ክርስትና ለራስ እየተራቡ ሌላውን ማብላት፣ ራስ እየሞቱ ሌላውን ማዳን፣ ለራስ እየተቸገሩ ሌላውን ከችግሩ ማውጣት፣ ለራስ ክብርን እያጡ ሌላውን ማክበር፣ ለራስ እየተጠሉ ሌላውን መውደድ፣ ለራስ እየተጨነቁ ሌላውን ከጭንቀት ማውጣት ወዘተ… እንደሆነ እናስተውላለን፡፡

፪ኛ. ስስታምነት

ስስታምነት ባለን ነገር አለመርካት፣ ተመስገን አለማለት፣ ያለንን ነገር ሳይሆን ሁልጊዜ የለኝም የምንለውን ነገር ማሰብ፣ ያለንን ብዙ ነገር ባለማስተዋል የሌለንን ጥቂት ነገር ባለማግኘታችን በእግዚአብሔር ላይ የሚደረግ ማጉረምረም ነው፡፡ አንድ ሰው በፊቱ ያለውን ሳያነሣ የጀርባውን የሚመኝ፣ የቆረሰውን ሳይጎርስ በሚመገበው ላይ ዓይኑን የሚጥል፣ የቀረበለትን ሳይበላ ነገ ስለሚቀርበለት የሚጨነቅ፣ የራሱ እያለው የሌላውን የሚመኝ ከሆነ ስስታም ይባላል፡፡

ስስት ለማኅበራዊ ኑሮም ሆነ ለመንፈሳዊ ሕይወት እንቅፋት ነው፡፡ ምክንያቱም ስስታም ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት የለውም፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “በዓይኑ ትዕቢተኛ የሆነውና ልቡ የሚሳሳው ከእኔ ጋር አይተባበርም”  (መዝ. ፩፻፩፥፭) ይላልና፡፡

ስስታምነት የሚመጣው ከሆዳምነት ወይም ከአልጠግብ ባይነት ነው፡፡ በመሆኑም መቀበል እንጂ መስጠት፣ መለመን እንጂ መለመን(እባክህ መባል) የማይወድ ሰው ስስታም ይባላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሰው ቢበላም አይጠግብም፣ ቢጠጣም አይረካም፣ ቢለብስም አይሞቀውም፡፡ ምክንያቱም ስስት አንቆ ይዞታልና በጥቂትም ሆነ በብዙው ነገር መርካት አይችልም፡፡

ክርስቲያናዊ ሕይወት ግን ከእንዲህ ዓይነት ነገር የራቀ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ልጁ ጢሞቴዎስን ሲመክር “በቃኝ ከማለት ጋር እግዚአብሔርን ማምለክ ታላቅ ረብ ነው፡፡ ወደ ዓለም ያመጣነው የለንምና ከእርሱም ልንወስደው የምንችል የለንም፡፡ ምግባችንን እና ልብሳችንን ካገኘን ይበቃናል፡፡ ባለጸጋ ሊሆኑ የሚወዱ ግን በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን  በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ” (፩ኛ ጢሞ. ፮፥፮) ብሏል፡፡

፫ኛ. ክፉ ቅንዓት

ክፉ ቅንዓት ለክርስቲያናዊ ሕይወት ጠንቅ ነው፡፡ ይህም በሌላው ማግኘት፣ መከበር፣ መበልጸግ፣ ማደግና ወደተሻለ ነገር መሸጋገር መናደድ ለምን እገሌ ተለወጠ? ለምን እገሊት ከፍ አለች? በሚል የክፋት አሳብ መያዝ ነው፡፡ ክፉ ቅንዓት በራስ ሳይሆን በሌላ ማግኘት መበሳጨት ነው፡፡ ምንም እንኳ ያ በክፉ ቅንዓት የተያዘ ሰው የማያገኘው ወይም የማይደርስበት ነገር ቢሆንም እንኳ ሌላው ሰው (አካል)እንዳያገኘው ወይም እንዳይደርስበት መፈለግ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ክፉ ጠባይ ለማኅበራዊ ኑሮም ሆነ ለመንፈሳዊ ሕይወት እንቅፋት ነው፡፡

ይህ ዓይነቱ ክፉ ቅንዓት ቃዔል በወንድሙ በአቤል ላይ እንደቀናበት ያለ ቅንዓት ነው፡፡ እንደምንመለከተው በዚህ ክፉ ቅንዓት ሰበብ ብዙ ወንድማማቾች ተለያይተዋል፣ ወዳጆች ወዳጅነታቸውን ሰርዘውበታልና ከክፉ ቅንዓት መራቅ ያስፈልጋል፡፡

፬ኛ ዘረኝነት

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕዝብና አሕዛብ የታረቁበት የሰላም ባለቤት ነው፡፡ ለሰው ልጅ ሕይወት እውነተኛ ሰላም ያደለው እርሱ ነው፡፡ ይህንን ያልተረዱ አንዳንድ ግለሰቦች ግን ዛሬም ድረስ የሀገሬ ልጅ፣ የወንዜ ልጅ እየተባባሉ ራሳቸውንም ሆነ ሌላውን የሚጎዱ ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ የክርስትና ሃይማኖት የፀብ ግድግዳ የፈረሰበት ሁሉን በእምነት አንድ ወገን ያደረገ ሃይማኖት መሆኑን ያልተረዱ በየስፍራው አይታጡም፡፡ ዘረኝነትን ከውስጣችን ካላጠፋን ክርስቲያናዊ  ሕይወታችን በማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ መገለጥ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ዘረኝነት አንዱ ለክርስቲያናዊ ሕይወት እንቅፋት ስለሆነ፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በአሁኑ ሰዓት እየተፈተነች ያለችበት አንዱ የዘረኝነት ጉዳይ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም የሥጋ ሥራ ብሎ ከዘረዘራቸው መካከል አንዱ ይኸው ዘረኝነት ነው፡፡ “ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና እርሱም ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ” የሚል ነው፡፡ ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱ ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ ነገር ግን እላለሁ በመንፈስ ተመላለሱ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ” (ገላ. ፭፥፲፬) እንዲል፡፡ በመሆኑም ዘረኝነትን ከመካከላችን አስወግደን እውነተኛ ፈቅርን ገንዘብ ማድረግ ለማኅበራዊ ኑሮአችን አስፈላጊ ነው፡፡     

፭ኛ. ሐሜት

ሐሜት፡- ስለ አንድ ሰው እርሱ በሌለበት የነቀፋ ወይም የስም ማጥፋት ወሬ መናገር ነው፡፡ ሐሜት በእውነት ወይም በሐሰት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል፡፡ በእውነት ላይ የተመሠረተ በሚሆንበት ጊዜ የሚታማው ሰው የፈጸመውን ክፉ ድርጊት በማንሣት ባለቤቱም ሆነ ሌላው ሰው እንዲማርበት ተብሎ ሳይሆን በድክመቱ ሌላው ሰው እንዲዘባበትበት በማሰብ ሆን ተብሎ ለሌላው ወገን በነቀፋ መልክ መናገር ነው፡፡

ሐሜት በሐሰት ላይ የተመሠረተ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ‘‘ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ’’  እንደሚባለው ሁሉ ሆን ተብሎ የሰው ስም ለማጥፋት ወይም ለመጉዳት ሲባል የሚወራ ክፉ ወሬ ግን እርስ በርስ በመዋደድ ፍቅርን የሚያደርግ ሰው ከሐሜት ይርቃል፡፡ በመሆኑም ክርስቲያናዊ ሕይወት ያለው ሰው ምንም እንኳ በዙሪያው ያሉ ሰዎች ኢ-ክርስቲያናዊ ተግባር የሆነውን የሐሜትን ቃል ቢናገሩም ሰምቶ እንዳልሰማ ዝም ይላል እንጂ ከእነሱ ጋር ለሐሜት አይተባበርም፡፡

ሐሜት በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ተግባር ከመሆኑ ባሻገር ለማኅበራዊ ኑሮ ጠንቅ ነው፡፡  በክርስቲያናዊ ሕይወትም አይፈቀድም፡፡ ለዚህ ነው ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “እግዚአብሔር ሆይ ወደ መኖሪያህ መግባት የሚችል ማነው? የሌሎች ሰዎችን ስም የማያጠፋ… ጎረቤቶቹን የማያማ… እነዚህን ነገሮች የሚያደርግ ሰው ከማናቸውም ክፉ ነገር ተጠብቆ ይኖራል እንጂ ከቶ አይናወጥም” (መዝ. ፲፭፥፩) በማለት ስለ ሐሜት ነውርነት አስገንዝቧል፡፡

ስለዚህ ከሐሜት መራቅ የክርስያናዊ ሕይወት መገለጫ ሲሆን መልካም ለሆነ ማኅበራዊ ግንኙትም ወሳኝ ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህንና መሰል በጎ ተግባራን በመፈጸም ሕይወታችንን ልንመራ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡

እነዚህንና መሰል የማይገቡ ክፉ ተግባራትን አርቀን መልካምነትን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የመልካምነት እንቅፋቶችም ከላይ የዘረዘርናቸው የሥጋ ሥራዎች ከላይ የጠቀስናቸውን እናንሳ እንጂ ፍቅርን ሊያቀዘቅዙ የሚችሉ በርካታ ናቸው፡፡ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ በማስገዛት የመንፈሳዊነታችን መገለጫ የሆነውን ፍቅርን ልናደርግ ይገባል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን እርስ በእርሳችን የምንግባባበትን እውነተኛ ፍቅር ለሁላችንም ያድለን አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *