ሰሙነ ሕማማት

ክፍል ሦስት

. ዕለተ ረቡዕ

በሰሙነ ሕማማት ዕለተ ረቡዕ የሚከተሉት ሦስት ነገሮች ተፈጽመዋል፡-

  • የካህናት አለቆች፣ የሕዝብ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ፈሪሳውያን በጌታችን ላይ ተማክረዋል፤
  • ጌታችን በስምዖን ዘለምጽ ቤት ሳለ ማርያም እንተ ዕፍረት ስለ ኃጢአቷ ተጸጽታ ዕንባዋን እያፈሰሰች ውድ ሽቱ ቀብታዋለች፤
  • ከዳተኛው ይሁዳ ጌታችንን አሳልፎ ለመስጠት ከጸሐፍት ፈሪሳውያንና ከካህናት አለቆች ዘንድ ሠላሳ ብር ለመቀበል ተማክሯል (ተስማምቷል)፡፡

 . ምክረ አይሁድ፡ 

የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሹማምንት በጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስን ለመያዝና ለመግደል በቀያፋ የሚመራው ሸንጐ በአጠቃላይ ሰባ ሁለት አባላት ነበሩት፡፡ በዕለቱ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት ይዘው እንደሚገድሉት አይሁድ በዚህ ሸንጎ መክረዋል፡፡

ከዳተኛው ይሁዳም ጸሐፍት ፈሪሳውያንና የካህናት አለቆች በጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ላይ የነበራቸውን ጥላቻ ያውቅ ስለነበር “ምን ትሰጡኛላችሁ? እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ” በማለት ጌታችንን አሳልፎ ሊሰጣቸው እንደሚችል ተስማምቷል (ማቴ. ፳፮፥፲፭)፡፡

በዚህም  መሠረት ይህቺ ዕለት የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ፈሪሳውያን ጌታ ኢየሱስን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው ምክር የመከሩበት ምክራቸውንም ያጸኑበትና ሰቅለው ይገድሉት ዘንድ የወሰኑባት ቀን በመሆኗ የአይሁድ የምክር ቀን ተብላ ትጠራለች፡፡ ይሁን እንጂ በዚሁ ምክራቸው ወቅት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስን እንዴት አድርገው እንደሚይዙት በጣም ይጨነቁ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ወቅቱ የፋሲካ በዓላቸውን የሚያከብሩበት ወቅት በመሆኑ በጌታችን ትምህርት የተማረኩ ብዙ ሕዝብ ትምህርቱን ያደንቁ ስለነበር ሁከት እንዳይፈጠር ከመፍራታቸው የተነሣ ነው፡፡ በዚህ ጭንቀትም ሳሉ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ በመካከላቸው ተገኝቶ ጌታ ኢየሱስን እርሱ በመሳም አሳልፎ እንደሚሰጣቸው፤ ለዚህ ተግባሩም ሠላሳ ብር ወረታውን እንዲከፍሉት ከእነርሱ ጋር በመስማማቱና የምክራቸው ተባባሪ በመሆኑ ጭንቀታቸውን አስወግዶላቸዋል፡፡ (ማር. ፳፮፥፩-፭ ፤ ፳፮፥፲፬-፲፮ ፤ ማር. ፲፬፥፩-፲፩ ፤ ሉቃ. ፳፪፥፩)

. የመልካም መዓዛ ቀን፡

ዕለተ ረቡዕ ጌታችን በስምዖን ዘለምጽ ቤት ተቀምጦ ሳለ በመላ ዘመንዋ ራስዋን ለኃጢአት በማስገዛት በዝሙት ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ ዕፍረት ኃጢአትን ይቅር የሚል መልካም መዓዛ ያለው አምላክ መጣ ስትል ውድ የሆነ ዋጋ ያለው ወይም የሦስት መቶ ዲናር ሽቱን ገዝታ ወደ እርሱ በመምጣትና በራሱ ላይ በማርከፍከፍ ስለቀባችው የመልካም መዓዛ ቀንም ትባላለች፡፡ በዚህም ምክንያት ከኃጢአትዋ የተነሣ መልካም መዓዛ ያልነበራት ማርያም እንተ ዕፍረት በዚህ በጎ ተግባርዋ መልካም መዓዛ ያላት ሆና ወደ ቤትዋ ተመልሳለች፡፡ (ማቴ. ፳፮፥፮ ፤ ዮሐ. ፲፪፥፩-፰)

. የዕንባ ቀን፡

ማርያም እንተ ዕፍረት በጌታችን እግር ላይ ተደፍታ መላ ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት በዕንባዋ እግሩን እያጠበች፣ በፀጉሯም እግሩን እያበሰች ስለ ኃጢአቷ ሥርየት ተማጽናዋለችና የዕንባ ቀን ትባላለች፡፡ (ማቴ. ፳፮፥፮-፲፫ ፤ ማር. ፲፬፥፫-፱ ፤ ዮሐ. ፲፪፥፩-፰)

የአስቆሮቱ ይሁዳ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተምር በነበረበት ወቅት ከምእመናን ለሚገባው ገንዘብ ሰብሳቢ (ዐቃቤ ንዋይ) ነበር፡፡ ከሚሰበሰበው ሙዳየ ምጽዋት ለግል ጥቅሙ እየቀረጠ የማስቀረት የእጅ አመል ነበረበት፡፡ ይሁዳ ፍቅረ ንዋይ እንደሚያጠቃው ድብቅ አመሉ ጎልቶ የወጣው ጌታችን በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ አንዲት ሴት ዋጋው ውድ የነ ሽቱ በቀባችው ጊዜ ነው፡፡ በዚያች ዕለት ይሁዳ የተቃውሞ ድምፅ አሰምቶ ነበር፡፡

“ይህ ሽቱ ተሽጦ ለድሆች ቢሰጥ መልካም ነበር” አለ፡፡ ሽቱ ሲሸጥ የሚያገኘው ጥቅም አለ፤ ሽቶው በጌታችን እግር ሥር ከፈሰሰ ለእርሱ የሚተርፈው የለም፡፡ ይሁዳ ተቆርቋሪ መስሎ ያቀረበው አሳብ ተቀባይነት በማጣቱም ማኩረፊያ ያገኘ መስሎት በቀጥታ ከካህናት አለቆች ዘንድ ሔዶ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በሠላሳ ብር ለመሸጥ ተዋዋለ፡፡ (ማቴ. ፳፮፥፫-፲፮፤ ማር. ፲፬፥፩-፲፩፤ ሉቃ. ፳፪፥፩፮)፡፡

ክርስቲያን ነን በማለት የክርስትናውን ስም ብቻ በመያዝ እምነታቸውን፣ በገንዘብ የሚለውጡ ሰዎች ዛሬም እንደ ይሁዳ ጌታችንን እየሸጡት እንደ ሆነ ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ ለድሆች መመጽወት ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡ ዳሩ ግን በድሆች ስም የሰውን ገንዘብ ለግል ጥቅም ማዋል እጅግ የከፋ ኃጢአት ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ለገንዘብ ብለው ድሆችን ለረኃብ ለችግር ባልንጀራቸውን ለመከራ እና ለሞት አሳልፈው ሲሰጡ ምንም አይጸጽታቸውም፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን ሕይወታችንን ለገንዘብ ፍቅር ሳይሆን ለእምነታችንና ለባልንጀራችን አሳልፈን መስጠት ይኖርብናል፡፡ በፍቅረ ንዋይ ተጠምደን ሰዎችን አሳልፎ በመስጠት ለአይሁዳውያን ሸንጐ ምቹ ሆነን መገኘት እንደማይገባ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *