መናፍቃን የሚስቱባቸውና የሚያስቱባቸው መንገዶች (ክፍል ሁለት)
በዳዊት አብርሃም
- ጥቅሱን ከዓውዱ ነጥሎ መጥቀስ
አንድን ጥቅስ በተሟላ መልኩ በትክክል ጠቅሶ ድምዳሜ ላይ መድረስ ትክክል ባይሆን እንኳ የተሻለ ነገር አያጣውም፡፡ ስሕተቱን የከፋ፣ የስሕተት ስሕተት የሚያደርገው አንዲቷን ጥቅስ ቆንጽለው ሲጠቅሷት ነው፡፡ ብዙዎች መናፍቃን አንድን ጥቅስ አሟልተው ለመረዳት ጥቂት መስመሮችን ከፍ ብለው እንዲሁም ከጠቀሱት ጥቅስ ቀጥሎ ያሉትን ጥቂት ዐረፍተ ነገሮች ጨምረው ለመመልከት ቢሞክሩ ድምዳሜያቸውን ርግፍ አድርገው መተው ወይም የሚያሰሙትን ተቃውሞ ባልደገሙት ነበር፡፡
ይህንም በሚቀጥሉት ስለ ነገረ ድኅነት ከተጻፉት ጥቅሶች አንጻር እንመልከት፡፡ “ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፡፡” (ኤፌ2፡8-9) የዚህ ጥቅስ መልእክት በጣም ግልጽ ይመስላል፤ ጥቅሱ ‹ሥራ አያስፈልግም፣ እምነትና ጸጋ ብቻቸውን ለመዳን በቂ ናቸው› የሚል መልእክት የያዘ መስሎ ይታያል፡፡ ግን ሳንቸኩል አንድ ቁጥር ወረድ ብለን ንባባችንን ብንቀጥል እንዲህ የሚል እገኛለን፡፡ “እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን።” (ኤፌ2፡10)
ሌላ ምሳሌ ደግሞ እንመልከት፡፡ “እንግዲህ የተሰናከሉ እስኪወድቁ ድረስ ነውን? እላለሁ አይደለም ነገር ግን እነርሱን ያስቀናቸው ዘንድ በእነርሱ በደል መዳን ለአሕዛብ ሆነ፡፡” (ሮሜ.11፡11) “በጸጋ ከሆነ ግን ከሥራ መሆኑ ቀርቶአል፤ ጸጋ ያለዚያ ጸጋ መሆኑ ቀርቶአል።” (ሮሜ11፡6) ነገር ግን አሁንም በዚህ ጥቅስ ሳንወሰን በዚያው ምዕራፍ ወረድ ብለን ንባባችንን እንቀጥል፡፡ “መልካም፤ እነርሱ ከአለማመን የተነሣ ተሰበሩ፤ አንተም ከእምነት የተነሣ ቆመሃል። ፍራ እንጂ የትዕቢትን ነገር አታስብ። እግዚአብሔር እንደ ተፈጠሩት ለነበሩት ቅርንጫፎች የራራላቸው ካልሆነ ለአንተ ደግሞ አይራራልህምና። እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ጭከና ተመልከት፤ ጭከናው በወደቁት ላይ ነው፤ በቸርነቱ ግን ጸንተህ ብትኖር የእግዚአብሔር ቸርነት በአንተ ላይ ነው፤ ያለዚያ አንተ ደግሞ ትቈረጣለህ።” (ሮሜ.11፡20-22)
ይህ ማለት ምን ማለት ነው? በክርስቶስ ደም ሁላችንም መዳንን አግኝተናል፡፡ ሆኖም ከርሱ ጋር ካልተጣበቅን ማለትም እስከ ፍጻሜ ድረስ ከርሱ ጋር እንድንኖር የሚያደርገንን የጽድቅ ሥራ መሥራት ካልቻልን የመቈረጥ ቅጣት ይደርስብናል፡፡ ከግንዱ ተቈርጦ ዕጣው መድረቅና መጠውለግ እንደሆነበት ቅርንጫፍ እንሆናለን ማለት ነው፡፡ ይህንን ለመረዳት ግን ጥቅሱን በምልዓት ማንበብ ይጠበቅብናል፡፡
አሁንም ሦስተኛ ምሳሌ እንጨምር “ትምክሕት እንግዲህ ወዴት ነው? እርሱ ቀርቶአል። በየትኛው ሕግ ነው? በሥራ ሕግ ነውን? አይደለም በእምነት ሕግ ነው እንጂ። ሰው ያለ ሕግ ሥራ በእምነት እንዲጸድቅ እንቆጥራለንና” (ሮሜ.3:27-28) ይህንን ጥቅስ ስናነብ ለመዳን ሥራ አያስፈልግም የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ እንዳንቸኩል ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ወደ ሌላ ቦታ መሔድ ሳያስፈልገን ጥቂት ብቻ ዝቅ ብለን እናንብበው፡፡ “እንግዲህ ሕግን በእምነት እንሽራለንን? አይደለም፤ ሕግን እናጸናለን እንጂ።” (ሮሜ.3:31)
አራተኛ ምሳሌ፡- “ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም” (ቲቶ.3:4-6) ይህ ጥቅስ መዳን የሚገኘው በጥምቀትና በመንፈስ ቅዱስ ሥራ እንደሆነ የሚገልጥ መሆኑን አስቀድመን ልብ ልንል ይገባናል፡፡ ይህም መዳን “በእምነት ብቻ” የሚለውን ኑፋቄ የሚቃወም ሐሳብ ነው፡፡ ከዚያ ቀጥለን ስናነብ ደግሞ ከጥምቀትና ከጸጋ መንፈስ ቅዱስ በተጨማሪ ሐዋርያው የሥራን አስፈላጊነት እንዲህ በማለት ይገልጥልናል፡፡ “ቃሉ የታመነ ነው፤ እግዚአብሔርንም የሚያምኑት በመልካም ሥራ በጥንቃቄ እንዲጸኑ እነዚህን አስረግጠህ እንድትናገር እፈቅዳለሁ። ይህ መልካምና ለሰዎች የሚጠቅም ነው፡፡” (ቲቶ.3፡8)
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!