ከስደት የመመለሱ ምሥጢር
ኅዳር 5 ቀን 2006 ዓ.ም.
ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ
እግዚአብሔር በሐዲስ ኪዳን ሊያደርገው ያሰበውን ነገረ ድኅነት አስቀድሞ በብሉይ ኪዳንና ቅድመ ብሉይ ኪዳን ለሕዝቡ በተለያየ መንገድ መግለጹን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክሩልናል ዕብ 1÷1:: ምክንያቱም ፈታሒነቱና መሐሪነቱ የማይነጣጠሉ በመሆናቸው ነው ይሏል፡፡ የሰው ልጆች በዚያ ዘመን እግዚአብሔር ፈታሒነቱን በተከፈላቸው የኃጢአት ደመዎዝ የተረዱ ሲሆን መሐሪነቱን ደግሞ በተለያየ ኅብረ አምሳል መግለጹ አልቀረም:: ከእነዚያ ብዙ ከምንላቸው ኅብረ አምሳላት አንዱ እንዲህ የሚለው ነው “በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ፤ ሙሴ ጎበዝ መሆን በጀመረ ጊዜ ወንድሞቹን ሊጎበኛቸው ወደ ወንድሞቹ ወጣ የግብፅም ሰው የወንድሞቹን የዕብራውያንን ሰው ሲመታ ተመለከተ” ዘጸ.2÷11፡፡ በፈርዖን ቤተ መንግሥት ላደገው ለዚያ ሰው የተነገረለት ቃል በዕውነት አስደናቂ ነው፡፡ ዕድሜው በአባቶቻችን አነጋገር አርባ ዓመት ሆኖት የነበረው ይህ ሰው በጉብዝናው ወራት ወደ ወገኖቹ ሲመጣ ከተማው መከራ የበዛበት፤ ሕዝቡ ለቅሶና ዋይታ የጸናበት አስቸጋሪ ወቅት ሆኖ ነበር የጠበቀው፡፡ የሰው ልጆች ከአስገባሪዎቻቸው የተነሣ እስከ ጽርሐ አርያም ዘልቆ የሚሰማ ጩኸታቸውን አሰምተው የጮሁበት፤ እግዚአብሔርም የሰውን ጩኸት የሰማበት ጊዜ ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር የመከራው ማለቂያ፤ የመጎብኘቱ ዘመን መግቢያ ነበር ማለት ነው፤ በመከራ ዘመን የሚጎበኝ ወዳጅ ታማኝ ወዳጅ ነውና፡፡
ይህ የመጎብኘት ወራት ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚመጣበት ወራት አምሳል መርገፍ የሚሆን ወቅት ነበር፡፡ በዚያኛው ወራት የተነሣው ጎበዝ በመከራ ውስጥ ለነበረው ሕዝብ የደረሰለላቸው በአርባኛው ዓመቱ ነበር፡፡ በዚህኛው ወራት የተነሣው ኢየሱስ ክርስቶከስም ለሕዝቡ የደረሰለት በአራተኛው ክፍለ ዘመን ነው (ዘመነ አበው፣ ዘመነ መሳፍንት፣ ዘመነ ነገሥት፣ ዘመነ ካህናት) እነዚህ አራት ክፍላተ አዝማናት በእውነት የሙሴን አርባ ዓመታት ይመስላሉ፡፡ የሙሴ አርባ ዓመታት በፈርዖን ቤተ መንግሥት ውስጥ በዝምታ ያለፉ ዓመታት ናቸው፡፡
እስከ አርባ ዓመት ድረስ ሙሴ ወደ ወገኖቹ ሳይወጣ ለምን ዘገየ? በፈርዖን ቤተ መንግሥት ውስጥ ያደገ ሰው ቢሆንም ቅሉ ፈረዖናዊ እንዳልሆነ ከእናቱ የሰማው ገና በልጅነት ዘመኑ አልነበረምን? ቢሆንም ግን ዘገየ፡፡ የፈርዖናውያን ግፍ እስኪፈጸም፤ የእስራኤልም መከራ እስኪደመደም አልጎበኛቸውም ነበር፡፡ ዛሬ የእስራኤል የመጎብኘት ወራት ከመድረሱም ባሻገር ሙሴ ጎበዝ በመሆኑ ግብፃዊውን ገድሎ እስራኤላዊውን ማዳን የሚችልበት ደረጃ ላይ ነው ያለው፤ ስለዚህም ወደ ወገኖቹ ወጣ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በዝምታ ያሳለፋቸው አራቱ ክፍላተ አዝማናትም ከዚህ ጋር ተመሳሳዮች ናቸው፡፡ የሰው ልጅ የቀኖና ጊዜውን እስኪያጠቃልል መንጸፈ ደይን ወድቆ ለዘመን ዘመናት ያለቀሰ ቢሆንም በአራቱም ክፍላተ አዝማናት የነበረው የእግዚአብሔር ዝምታ አንዳንዶችን “ኢሀሎኑ በዝ ሰማይ አምላከ እስራኤል አዶናይ፤ በዚህ ሰማይ እስራኤልን የሚጠብቅ ጌታ እግዚአብሔር የለምን?” ብለው በሰለለ ድምፅ እንዲናገሩ አድርጓቸዋል፡፡
የመጎብኘት ጊዜው ሲደርስ የዲያብሎስ ምክሩ እንዲፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋ ወደ ወገኖቹ መጣ፡፡ ይህ ወራት የአዳም ሥጋ ጎበዝ እየሆነ የመጣበት ወራት በመሆኑ በወገኖቹ ላይ የነበረውን ፍዳና መርገምን እንቢ ብሎ ያለ ኃጢአትና ያለ በደል ሆኖ ተፀነሰ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የግብፃዊው ምሳሌ የሆነው ዲያብሎስ ጉድጓዱ ተማሰ፤ ወገኖቹን ሊጎበኛቸው በመጣው በዚያ ሰው በኩል የማይደፈረው ተደፈረ፤ ግብፃዊው ተቀበረ፡፡ ይህ ጎበዝ እየሆነ የመጣው የሙሴ ወገኖች የተስፋ ምልክት እንደነበረ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መዳን ለተደረገለት ቅዱስ ሕዝብም እግዚአብሔር ወደ ወገኖቹ የመጣባት የመጀመሪያዋ ዕለተ ፅንስ ከሲዖል እስከዚህ ዓለም ለነበሩ ነፍሳት የፀሐይ ብርሃን ብልጭ ያለባት ዕለት ናት፡፡ ከዚህም የተነሣ የዓመተ ምሕረት መጀመሪያ አድርገን እንቆጥራታለን፡፡
ምንም እንኳን ሙሴ ግብፃዊውን ገድሎ ሊታደጋቸው የሚችል መሆኑን ያስመሰከረ ቢሆንም ወገኖቹ ግን በእልልታ የተቀበሉት አይደሉም፡፡ እርሱ ግን በእጁ መዳንን እንዲሰጣቸው የሚያምኑ ይመስለው ነበር ሐዋ.ሥራ.7÷25፡፡ እስራኤልን የመታደግ ሥራውን ግብፃዊውን በመግደል የጀመረው ያ ታላቁ ታዳጊያቸው ከሁለት ቀን በኋላ ባደረገው ወገኖቹን የመጎብኘት ሥራ ከወገኖቹ በጎ ነገርን ሊያስገኝለት አልቻለም፤ ከሀገር ወጥቶ እንዲሰደድ የሚያደርግ ክፉ ሀሳባቸውን ሰማ እንጂ፡፡ ከወገኖቹ ከንቱ ሀሳብ የተነሣ አርባ ዓመታትን ያለ ኃጢአትና በደሉ በስደት አሳለፈ የምድያምን ካህን በጎች እየጠበቀ በባዕድ ምድር ለረጅም ዘመን ተቅበዘበዘ፡፡ ከንጉሡ ቤት ወጥቶ ሲሄድ የንጉሡ የልጅ ልጅ መባልን እንደ መቀማት አልቆጠረውም ራሱን ዝቅ አድርጎ በምድያማውያን ምድር ለሚገጥመው የመስቀል መከራ እንኳን የታዘዘ ሆነ እንጂ፤ የግብፅ ጌታዋ ሙሴ እንደ ባሪያ ዝቅ ብሎ የበግ እረኛ ሆነ፡፡ እግዚአብሔር ግን ከቀደሙት መሳፍንት ሁሉ በላይ የሆነ ስምን ሰጠው በግብፅ ካለው ተድላ ደስታ ይልቅ ከወገኖቹ ጋር መከራ መቀበልን መርጧልና መከራ በተቀበለላቸው ወገኖቹ ላይ ሹም አድርጎ ደስ አሰኘው፡፡
የአባቶቹን ዕዳ ሊከፍል የመጣው ዳግማዊው ሙሴ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ዓለም ነቢያትን እንዳሳደደች እርሱንም እንዲሁ አደረገችበት፡፡ ሙሴ ግብፃዊውን በገደለውና ለእስራኤልም የመዳን ተስፋን ባሳየ በሁለተኛው ቀን ከሀገር አስወጥታ እንዳሳደደች፤ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን በሰው ልጆች ታሪክ ጉልህ ስፍራ የነበረውን ቁራኝነትን በማጥፋት ይቅርታውን አሐዱ ብሎ በጀመረበት በሁለተኛ ልደቱ ሲገለጥ በገዛ ወገኖቹ በካህናትና በነገሥታት ምክር ከሀገር ወጥቶ ተሰደደ፡፡ ሙሴ ወደ ወገኖቹ የመጣባት ሁለተኛይቱ ቀን፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም በሥጋ የመጣባት ሁለተኛይቱ ልደቱ ሲነጻጸሩ እጅግ ይገርማሉ፡፡ ስለ ወገን እንጂ ስለ ራስ መኖርን የሚያስንቁ ዕለታት! እንደዚያኛው ወራት በዚህም ወራት ስለ ሕዝቡ የሚቆረቆር ሌላ ሙሴ ለምድር ተወልዶላታል፡፡ እግዚአብሔርነቱን እንደ መቀማት ሳይቆጥረው የባሪያውን መልክ ይዞ ከሰማይ ወደ ምድር መጣ፡፡ በብዙ ሠራዊት ዘንድ ጌታ የሆነው እርሱ ከአብ ጋር ተካክሎ ሲኖር ሳለ በፈቃዱ ከክፉ ወገኖቹ መካከል ተለይቶ ወደ ምድረ አፍሪቃ ተሰደደ፡፡ ሙሴን የሕዝቡ መከራ ውል ብሎ እየታየው በፈርዖን ቤት በደስታ መኖርን እንደከለከለው ከሕዝቡ ጋርም ስለሕዝቡ መከራ መቀበልን እንዲመርጥ እንዳደረገው ኢየሱስ ክርስቶስንም በሕዝቡ የደረሰው ግፍ ከሰማይ ወደ ምድር አመጣው፤ ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች እስኪል ድረስ አስጨነቀው ፡፡
ሙሴ ስለ ሕዝቡ ወደ ምድረ አፍሪቃ ወርዶ በግ ጠባቂነትን ሥራ አድርጎ ኖረ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም ራሱን የገለጠው በዚህ ስም እንደነበረ ቅዱስ ወንጌል ምስክርነትን ይሰጠናል “እኔ የበጎች እረኛ ነኝ” እንዲል ዮሐ10÷11፡፡ በእውነት እዚህ ላይ ያለውን የእግዚአብሔር ዐሳብ እስኪ በደንብ ተመልከቱት፡፡ ለአርባ ዓመታት ግብፃዊነትን ስሙ አድርጎ የፈርዖን የልጅ ልጅ መባልን ተቀብሎ ይኖር የነበረው ሰው ሙሴን አስነስቶ በጉብዝናው ወራት ወገኖቹን አስጎበኘው፡፡ ያንን ተከትሎ ግብፅን ለቆ እንዲወጣ አድርጎ ከሌሎች ዐርባ ዓመታት በኋላ ተመልሶ ወገኖቹን እንዲያድናቸው አደረገው፡፡ እግዚአብሔር ጥበበኛ አምላክ ነው፤ ያባቶቹን የያዕቆብንና የአስራ ሁለቱን አባቶች ስደት የሚመልስ ትውልድ አስነስቶ ከግብፅ በተገኘው ሰው ግብፅን በዘበዛት፡፡ ይህንንም በማድረጉ በዚህኛው ወራት ለኛ ሊያደርጋት ያሰባትን በጎ ነገር አስቀድሞ ነገረን፡፡ በዚያኛው ወራት ሕዝቡን የታደገው መሪ በግብፅ ምድር ተወልዶ በፈርዖን ቤት ያደገ ነው እንዳልን ሁሉ በዚህኛው ዘመን ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ሊያድናቸው የመጣው ኢየሱስ ክርስቶስም ከግብፃዊው ሰው ከአዳም የተገኘ ተገኝቶም ስለ ወገኖቹ የሚቆረቆር ሆነ፡፡ በአባ እንጦንስ አነጋገር ግብፃዊ ማለት ሥጋዊ ስሜቱን ብቻ የሚንከባከብ ሰው ስያሜ ነው፡፡ አባ እንጦንስ ወደ ገዳማቸው እንግዳ ሲመጣ ስለመጣው እንግዳ መረዳት ሲፈልጉ እንግዳውን ለሚቀበለው ደቀ መዝሙር የሚያቀርቡት ጥያቄ “ግብፃዊ ነው? ወይስ ኢየሩሳሌማዊ?” የሚል ነበር:: ሥጋዊው በግብፃዊ መንፈሳዊው በኢየሩሳሌም ይሰየማሉና፡፡
የሙሴ እናት በፈርዖናዊው የባርነት ወቅት ሳለች ሙሴን ወለደች ለሌላው ትውልድ መድኃኒት እንዲሆን ታስቦም ለሦስት ወራት ሸሸገችው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም የተወለደው ዓለም በዲያብሎስ ብርቱ የዐመጻ ውጊያ ውስጥ በነበረችበት ጊዜ ነበር፡፡ በተወለደበት ወቅት ብዙ ሕፃናት ለሞት የተዳረጉ ቢሆንም እርሱ ግን ለብዙዎቹ ለመዳናቸው፤ ለመነሣታቸው የተሾመ ነበርና እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ሶስት ዓመታትን ሸሸገችው፡፡ ከዚያም በኋላ በግብፃውያን መካከል አድጎ ለግብፃዊቷ ዓለም ይደርስ ዘንድ ስደትን ገንዘብ አደረገ የአባቱ ያዕቆብ እና የሌሎችም ቅዱሳን ስደት እንዲያበቃ ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰደደ፡፡ ሲሰደድ ከጥቂቶቹ በስተቀር ስደቱን ማን አወቀ? ሕዝቡን ሲያወጣ ግን በሁሉም ዘንድ የተገለጠ ነበር፡፡ ስደቱ ለዚህ ሁሉ ሕዝብ መዳን ምክንያት ይሆናል ብሎ ማን አሰበ? ግን ሆነ፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አፍሪቃ ምድር ተሰዶም እንደ ሙሴ በእግዚአብሔር መልአክ እስኪጠራ ድረስ በምድረ አፍሪቃ መቀመጥን መረጠ ዘጸ3÷4፤ማቴ2÷20፡፡ ለዚህም ነው በመነኮሳቱ መጽሐፍ “ንዑ ንርአዮ ለወልደ መንክራት” ተብሎ የተጻፈው፡፡ ሙሴ ከግብፅ አስማተኞች ጋር ባደረገው ክርክር አሸንፎ ሕዝቡን ይዞ በመኮብለል ከግብፅ ወጣ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በግብፅ ያሉትን ገዳመ ሲሐትን፤ ገዳመ አስቄጥስን ባርኮ፤ በግብፃውያን የሚመሰሉ አጋንንትን አባሮ እስክንድርያን መንበር አደረጋት፡፡ ከዚያ እስከ ዛሬ ግብፅ ያፈራቻቸው ቅዱሳን ሁሉ የዚያ ስደት ውጤቶች ናቸው፡፡ በሙሴ ወደ ግብፅ መመለስ የሞቱትም በሕይወት ያሉትም እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደ ተመለሱ፤ አማናዊው ሙሴ ኢየሱስ ክርስቶስም በስደቱ ለሞቱትም በሕይወት ላሉትም አባቶቻችን ተስፋ እያደረጓት ሳያገኟት ከሩቅ እየተሳለሟት ወደ አለፏት ቅድስት ምድር መንግሥተ ሰማያት ለመመለሳቸው ምልክት ሆነ፡፡ የክርስቶስ ከኢየሩሳሌም ወደ ግብፅ መሄድ ከገነት ወደ ሲኦል ያለውን የሰው ልጆች ስደት የሚያመለክት ሲሆን፤ ከግብፅ ወደ ኢየሩሳሌም ያደረገው መመለስ ደግሞ ከሲኦል ወደ መንግሥተ ሰማያት ያደረግነውን የይቅርታ ጉዞ ያሳያል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በሙሴ መታዘዝና ወደ ግብፅ መውረድ ሕገ ኦሪት በሙሴ ተመሠረተች፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ እስከ መስቀል የደረሰ መታዘዝ ወንጌል ተመሠረተች፡፡ ለሁሉም ግን መሠረቱ ስደት መሆኑን ልብ ይሏል ፡፡ በዚያኛው ወራት በሙሴ የተመሰረተችው ማኅበር በዚህኛው ወራት በኢየሱስ ክርስቶስ ለተመሰረተችው ማኅበር ምሳሌ ነበረች፡፡ አባቶቻችን ነቢያቱ የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን እንደ ስደተኛ ቆጥረው “ተመየጢ ተመየጢ ሱላማጢስ፤ ሱላማጢስ ሆይ ተመለሽ ተመለሽ” መኃ 7÷1 እያሉ ሊያዩአት ሲመኙ ነበሩ ጊዜው ሲደርስ የሄሮድስ ሞት የስደት ዘመኗን አሳለፈው፡፡ ሔሮድስ የዲያብሎስ ምሳሌ ሲሆን ዲያብሎስ በመስቀል ራስ ራሱን ተቀጥቅጦ ሲሞት ቤተ ክርስቲያን ግን መኖር ጀመረች፡፡ እስከ ዛሬም ድረስ በጠላቶቿ ላይ ድልን እየተቀዳጀች፤ ጠላቶቿን አሳልፋ ባለ ማለፍ ጸንታ ትኖራለች፡፡
እመቤታችን የሄሮድስን ሞት ከሰማች በኋላ ቁስቋም ከሚባል ተራራ ላይ ሆና ደስታዋን አብረዋት መከራን ከተቀበሉት ከዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር አከበረች፡፡ የቤተ ክርስቲያንም ደስታ የሚጀምረው በተራራ ላይ ነው፡፡ እመቤታችን ደብረ ቁስቋም ላይ ሆና ከአባቷ ዳዊት ጋር “ርኢክዎ ለኃጥእ አብየ ወተለዐለ ከመ አርዘ ሊባኖስ ወሶበ እገብዕ ኃጣዕክዎ፤ ኃጥእ ሔሮድስን ከፍ ከፍ ብሎ ተመለከትኩት ስመለስ ግን አጣሁት” መዝ 36÷35 ብላ ዘመረች፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ቀራንዮ ላይ ለዘመን ዘመናት ያስጨነቃት ዲያብሎስ ተወግዶላት የሞቱትንም በሕይወት ያሉትንም አንድ አድርጋ በደስታ ዘመረች፡፡ የዚያኛው ወራት ስደት ለቀደመው የእግዚአብሔር ሕዝብ ከግብፅ መውጣት፤ የዚህኛው ወራት ስደት ለአሁኑ የእግዚአብሔር ሕዝብ ከሲኦል መውጣት ፊታውራሪ ነው፡፡ ያኛው ሕዝብ በዚያኛው ስደት እንደተዋጀ ይሄኛው ሕዝብ ደግሞ በዚህኛው ስደት ተዋጀ፡፡ ምክንያቱም ስደቱ ስደታችንን ሲያመለክት መመለሱ መመለሳችንን ያሳያልና፡፡



ድሚያ ከዘመን ወደ ዘመን ያሸጋገረን ለብርሃነ መስቀሉ ያደረሰን በሀብቱ የሳበን በረድኤቱም ያቀረበን አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፡፡
አቡነ አኖሬዎስ በ13ኛው መ.ክ.ዘ የነበሩ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ ናቸው፡፡ ትልቁ አኖሬዎስ ይሏቸዋል፡፡ የአቡነ ዜና ማርቆስ የእኅት ልጅ ናቸው፡፡ አባታቸው ቄስ ሰላማ እናታቸው ክርስቶስ ዘመዳ ሲባሉ የትውልድ ቦታቸው ምዕራብ ሸዋ ሙገር አካባቢ ልዩ ስሙ ማትጌ በሚባል ቦታ ነው፡፡ ገድለ ዜና ማርቆስ አባቱ ዘርዐ አብርሃም የተባለ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት አባት ዘመድ ነበረ ይላል፡፡
በ1317ዓ.ም ንጉሥ ዓምደ ጽዮን በዘመነ መንግሥቱ የስብከተ ወንጌልን መስፋፋት ሥራ አጠናከረ፡፡ ይኸውም ግብፃዊው ጳጳስ አቡነ ዮሐንስ ሲያርፉ ወደ ግብፅ ልዑካንን ልኮ አቡነ ያዕቆብን አስመጣ፡፡ በዚህ ወቅት አቡነ ያዕቆብ ከአቡነ ፊልጶስ ጋር በመነጋገር “ኢትዮጵያ በአንድ ጳጳስ መወሰን የለባትም፡፡” በማለት እጨጌ አቡነ ፊልጶስን ኤጲስ ቆጶስነት ሰይመው ሐዋርያዊ አገልግሎት እንዲፈጽሙ ዐሥራ ሁለቱን ንቡራነ ዕድ ለስብከተ ወንጌል በመላዋ አገሪቱ ክርስትና እንዲስፋፋ አቡነ ያዕቆብ ባቀረበው ሀሳብ መሠረት ተሰማሩ፡፡ እነሱም አቡነ ፊልጶስ ዘደብረ ሊባኖስ /ኤጲስ ቆጶስ/፣ አቡነ አኖሬዎስ ዘሞረት፣ አቡነ ማትያስ ዘፈጠጋር፣ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ፣አቡነ አኖሬዎስ ዘወረብ፣አቡነ ታዴዎስ ዘጽላልሽ፣አቡነ ገብረ ክርስቶስ ዘግድም፣ አቡነ መርቆሬዎስ ዘመርሐ ቤቴ፣ አቡነ አድኃኒ ዘዳሞት፣ አቡነ ቀውስጦስ ዘመሐግል፣ አቡነ ኢዮስያስ ዘወጅ፣ አቡነ ዮሴፍ ዘእናርያ ነበሩ፡፡
የአምላክ ሰው መሆን አንዱ ምክንያት ምሥጢረ መለኮት ለተሰወረበት ዓለም ምሥጢረ መለኮትን መግለጥ ነው፡፡ ክፉውንና ደጉን ለይቶ ከሚያስታውቀው ዛፍ የተነሳ ከ8ኛ መዐርግ ላይ ሆኖ በመፈጠሩ የተሰጠውን ከፍተኛ የዕውቀት ፀጋ ክፉ ዕውቀት ስለተጨመረበት ለነፍሱ ምሥጢረ መለኮትን ማወቅ የሰው ልጅ ተስኖት ነበር ፡፡ ጌታችን ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ዓለም ምንም ምሥጢር የላትም ነበር፡፡ ምሥጢራት ሁሉ በልበ መለኮት ተሰውረው ይኖሩ ነበር እንጂ፡፡ በሌላ አነጋገር የተፀነሰ ምሥጢር እንጂ የተወለደ ምሥጢር አልነበረም ማለት ነው፡፡ ለዚህ አይደል መድኀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ከሕዝብ ለይቶ ምሥጢራትን ይነግራቸዉ የነበረው ማቴ.13 ፥11፡፡ በቀዳማዊው ሰው በአዳም በኩል ለሰው ልጀች ሁሉ የተሰጠው የመንግሥቱ ምሥጢር ዳግም በሁለተኛው ሰው በክርስቶስ በኩል ካልተገለጠ በሌላ በምን ይገለጣል!! ለዚህም በአብ ልብነት ተሰውሮ ይኖር የነበረው ብቸኛ ምሥጢር እርሱ ሆኖ ሳለ ከልደቱ ጀምሮ የመንግሥቱን ምሥጢር በብዙ መንገድ ገለጠ፡፡



የቀድሞው አባ ኅሩይ ወልደ ሰንበት የአሁኑ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ በ1930 ዓ.ም ተወለዱ
ቆሞስ አባ ኀይለጊዮርጊስ ኀይለ ሚካኤል ይባላል፡፡ ፊደል የቆጠሩት፣ ዜማን የተማሩት፣ ቅኔን የተቀኙት በሀፋፍ ማርያም በኢቲሳ ደብረ ጽላልሽ ገዳም ነው፡፡ ቅዳሴን በዳግማዊ ምኒሊክ መታሰቢያ የቀሳውስት ማሠልጠኛ ት/ቤት ተምረዋል፡፡ በሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ት/ቤት ለ4 ዓመታት ተምረው በዲፕሎማ ተመርቀው ዘመናዊ ትምህርታቸውን እስከ 12ኛ ክፍል በማጠናቀቅ በምዕራብ ጀርመን እሸት ኬርከሌ መንፈሳዊ ት/ቤት ስለ ገዳማት አስተዳዳር አጥንተዋል፡፡
የቀድሞ ስማቸው መልአከ ምሕረት አባ ሀብተ ማርያም ይባላል፡፡ ግንቦት 7 ቀን 1946 ዓ.ም በደቡብ ወሎ አማራ ሳይንት ልዩ ስሙ ደብረ ብርሃን ለንጓጥ ሥላሴ ተወለዱ፡፡ አባታቸው ግራ ጌታ መኮንን ኀይሉ እናታቸው ወ/ሮ አታላይ ደርሰህ ይባላል፡፡ ዜማ፣ አቋቋም፣ ቅኔ፣ ፍትሐ ነገሥት ትርጓሜ ተምረዋል፤ የቅኔ መንገድ ከነአገባቡ ተምረው በመምህርነት ተመርቀዋል በ1956 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ ገብርኤል ዲቁና ተቀብለዋል፡፡
አቋቋም፣ ቅኔ ከነአገባቡ ቅዳሴ ኪዳን አንድምታ፣ ዜማ፣ ሠለስት፣ አርያም፣ ጾመ ድጓ፣ ቁም ዜማ ተምረዋል፡፡ በ1969 ዓ.ም ከብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ዲቁና ተቀብለው ቅስና ከብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ተቀብለዋል፡፡ በ1975 ዓ.ም በደብረ ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ሥርዓተ ምንኩስና ፈጽመዋል፡፡ በሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ለ4 ዓመታት ያህል ተምረው በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ በሆላንድ ሆህ እስኩል የነገረ መለኮት ትምህርት ቤት ገብተው ለ4 ዓመታት ተምረው የመጀመሪያ ዲግሪ ተቀብለዋል፡፡