ስንክሳር፡- መስከረም አምስት

መስከረም 5 ቀን 2008 ዓ.ም

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መስከረም አምስት በዚች ቀን የከበረች ሶፊያ ከሁለት ልጆቿ አክሶስና በርናባ ከሚባሉት ጋር በሰማዕትንት ሞተች፡፡

ይችም ቅደስት አስቀድማ አረማዊ ነበረች፣ ወላጆቿም ጣዖታትን የሚያመልኩ ናቸው፡፡ እርሷም በልቧ አስተዋለች፣ መረመረችም፣ የወላጆቿ ሃይማኖት ከንቱ እንደሆነ ተረዳች፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ መኖፌ ኤጲስ ቆጶስ ሔዳ ክብር ይግባውና በክርስቶስ ታመነች፡፡ እንዲህም አለችው፤ በሕያው አምላክህ አምኛለሁና አጥምቀኝ እርሱም ሃይማኖትን፣ የቤተ ክርስቲያንም ሕግ አስተማራት፡፡ ከዚህም በኋላ ከልጆቿ ጋር በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃት፡፡

ከዚህም በኋላ የሀገር ሰዎች ለአማልእክት መስገድን ትታ ክርስቲያን እንደሆነች በገዢው በክላድያኖስ ዘንድ ወነጀሏት፡፡ ገዢውም ወደ እርሱ አስቀርቦ መረመራት፡፡ እርሷም ክብር ይግባውና በክርስቶስ አመነች እንጂ አልካደችም፣ ከልጆቿም ጋር ብዙ ሥቃይን አሠቃያት፡፡

በሥቃይም ውስጥ ላሉ ልጆቿ ታስታግሳቸውና ታጽናናቸው ነበር፣ እንዲህም ትላቸው ነበር፡፡ ልጆቼ ጠንክሩ፣ ጨክኑ የአንጌቤንዋን እመቤት ሶፍያን እመስላታለሁ፤ እናንተም ጲስጢስ፤ አላጲስ አጋጲስ የተባሉ ልጆቿን ምሰሉ፣ እነርሱም እንዲህ ብለው መለሱላት፣ እናት ሆይ እኛ ፍለጋሽን እንከተላለንና ስለእኛ አትፈሪ ይህንንም በሚባባሉ ጊዜ ከእናታቸው ጋር ተሳሳሙ፡፡

ገዢውም ሲሳሳሙ አይቶ ደናግል ልጆቿ እንዲፈሩ እናታቸውን በጅራፍ ይገርፏት ዘንድ አዘዘ፡፡ ያን ጊዜም የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ ወርዶ እናታቸውን ከግርፋት ሲሠውራት አዩ፡፡

ዝንጉዎችም ይገርፏት ዘንድ ባራቆቷት ጊዜ በዚያን ሰዓት እንዲህ በማለት ትጮህ ነበር፡፡ ዓለሙን ሁሉ በፈጠረ በእውነተኛ አምላክ በእግዚአብሔር የማምን ክርስቲያናዊት ነኝ፣ ያን ጊዜም ገዢው ምላሷን ከሥሩ እንዲቆርጡ አዘዘ፡፡ እርሷ ግን መጮህንና መናገርን አላቋረጠችም፡፡

ከዚህም በኋላ ገዢው ወደ እሥር ቤት እንዲወስዷት አዘዘ፤ ትሸነግላትም ዘንድ ሚስቱን ወደእርሰዋ ላከ፡፡ እርሰዋ ግን ምንም አልመለሰችላትም፡፡ ራሷንም በሰይፍ ይቆርጧት ዘንድ አዘዘ፤ የድል አክሊልም ተቀበለች፡፡ አንዲት ሴትም መጥታ ሥጋዋን በጭልታ ወሰደች፣ ወደ ቤቷም አስገብታ በፊቷ መብራትን አኖረች፡፡

ከዚህም በኋላ ልጆቿን ጠርቶ እሺ ይሉት ዘንድ አስፈራራቸው፣ እምቢ ባሉትም ጊዜ እያከታተለ ራሳቸውን አስቆረጠ፣ ምሥክርነታቸውንና ተጋድሏቸውንም ፈጸሙ፡፡ ከመቃብራቸውም በሽታውንና ደዌውን ሁሉ የሚፈውሱ ብዙ የሆኑ ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ፡፡

ደግ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስም ዜናቸውን በሰማ ጊዜ የቅዱሳት ሰማዕታትን ሥጋቸውን ወደ ቁስጥንጥንያ አፍልሶ ወሰደ፡፡

የሶፍያንና የልጆቿን ዜና ከመስማቱ በፊት ታላላቅና ሰፊ የሆኑ ቤቶች እንዲሠሩ በላይዋም ይቺ ቤት የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ናት ብለው ጽሑፍ እንዲቀርጹበት አዘዘ፡፡ እነርሱም ንጉሡ እንዳዘዘ ወደ ማታ ሲሆን ይጽፋሉ፣ የእግዚአብሔርም መልአክ ወርዶ ያንን ደምስሶ ይቺ ቤት የሶፍያ ናት ብሎ ይጽፋል፡፡ የሕንፃውም ባለሙያዎች የሚያደርጉትን አጡ፣ መጻፋቸውንም ተዉ፡፡

በአንዲት ቀንም የንጉሥ ልጅ ብቻውን ሲጫወት መልአክ ተገለጸለትና የዚች ቤት ስሟ ማነው አለው፡፡ ሕፃኑም አላወቅሁም አለው፣ መልአኩም ሁለተኛ እንዲህ አለው አባትህን የሶፍያ ቤት ብለህ ሰይማት ብለህ ንገረው ሕፃኑም ተመልሼ እስክመጣ ትጠብቀኛለህን አለው፣ መልአኩ አዎን እጠብቅሃለሁ አለው፡፡

አባቱም ይህን ሰምቶ መልአክ እንደሆነ ዐወቀ፡፡ ሕፃኑንም በመጠበቅ ምክንያት ያ መልአክ ከዚያች ቦታ እንዳይሄድ ብሎ ንጉሡ ልጁን ገደለው፡፡ መልአኩም ሕፃኑን እየጠበቀ እስከዛሬ ድረስ አለ፡፡

የዚያች ቤተ ክርስቲያም ርዝመቷ ሰባት መቶ ዘጠኝ ክንድ ሆነ፣ አግድመቷም ሦስት መቶ ሰባት ክንድ፣ ምሰሶዎቿም ዐራት መቶ፣ ጠረጴዛዎቿም ስምንት፣ የሚያበሩ ዕንቁቿ ዐራት ናቸው፣ ከአጎበሩ በላይ የተቀረጹ ኪሩቤልም በየሁለት ክንፎቻቸው የእግዚአብሔር ሕግ የተጻፈበትን ታቦት ይጋርዳሉ፡፡

ሥጋቸው በውስጡ ያለበትን የቅድስት ሶፍያንና የልጆቿን ሳጥን በታላቅ ምስጋናና ክብር ወደዚያ አስገብተው አኖሩ፡፡

በድኖቻቸውን የሰበሰበች ያቺንም ሴት ከእርሳቸው ጋር ቀበሯት፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር፣ ከመስከረም እስከ የካቲት፣ አዲስ አበባ፤ ትንሣኤ ማሳተሚያ ደርጅት፣ 1994 ዓ.ም፣ ገጽ 20-21፡፡

የእመቤታችን ዕርገት

ነሐሴ 15 ቀን 2007 ዓ.ም

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ነሐሴ ዐሥራ ስድስት በዚች ቀን አምላክን የወለደች እመቤታችን ድንግል ማርያም ሥጋዋ ወደ ሰማይ ያረገበት መታሰቢያዋ ሆነ፡፡

ከዕረፍቷም በኋላ ከእርሳቸው ስለመለየቷ ሐዋርያት ፈጽሞ እያዘኑ ነበር፡፡

ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ተገለጠላቸው እርሷን በሥጋ ያዩ ዘንድ እንዳላቸውም ተስፋ ሰጣቸው፡፡

ወንጌላዊ ዮሐንስም እስያ በሚባል አገር እያስተማረ ሳለ በነሐሴ ወር ዐሥራ ስድተኛ ቀን ተድላ ደስታ ወደአለባት ገነት በመንፈስ ቅዱስ ተነጠቀ፡፡ የክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ካለበት ከዕፀ ሕይወት ዘንድ ተቀምጦ አየው፡፡ የንጽሕት እናቱንም ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው እነርሱም የንጽሕት እናቱን ሥጋ ታወጪ ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል አሏት፡፡

ያን ጊዜም ከዕፀ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ወጣ፡፡

የክብር ባለቤት ጌታችንም እንዲህ እያለ አረጋጋት፤ የተወደድሽ የወለድሽኝ እናቴ ሆይ ዘላለማዊ ወደ ሆነ መንግሥተ ሰማያት አሳርግሽ ዘንድ ነዪ፡፡

ያን ጊዜም በገነት ያሉ ዕፅዋት ሁሉም አዘነበሉ፤ መላእክት፤ የመላእክት አለቆች ጻድቃን ሰማዕታትም እየሰገዱላትና ፈጽሞ እያመሰገኗት አሳረጓት፡፡

አባቷ ዳዊትም ንግሥት እመቤታችን ወረቀ ዘቦ ለብሳ ደርባ ደራርባ በቀኝህ ትቀመጣለች እያለ በበገና አመሰገናት፡፡

በኪሩቤል ሠረገላ ተቀምጣ ከዐረገች በኃላ በልጆችዋና በፈጣሪዋ ቀኝ በታላቅ ክብር ተቀመጠች፡፡

ወንጌላዊ ዮሐንስም ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ ሰግዶላት ተመልሶ ከሰማይ ወረደ፤ ሐዋርያትን ተሰብስበው ስለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋ ፈጽሞ ሲያዝኑና ሲተክዙ አገኛቸው፡፡ እርሱም እንዳየ እንደሰማ ሥጋዋንም በታላቅ ክብር በምስጋና እንዳሳረጓት ነገራቸው፡፡

ሐዋርያትም በሰሙ ጊዜ ዮሐንስ እንዳየና እንደሰማ ባለማየታቸውና ባለመስማታቸው እጅግ አዘኑ፡፡

ከዚህም በኋላ እያዘኑ ሳሉ እነሆ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠላቸውና የፍቅር የአንድነት ልጆች ሰላም ይሁንላችሁ ስለ እናቴ ማርያም ሥጋ ለምን ታዝናላችሁ፡፡ እነሆ እኔ እርስዋን በሥጋ ላሳያችሁ ልባችሁም ደስ ሊለው ይገባዋል አላቸው፡፡ ይህንንም ብሎ ከእርሳቸው ዘንድ ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡

ሐዋርያትም ዓመት ሙሉ ቆዩ የነሐሴም ወር በባተ ቀን ለሐዋርያት ዮሐንስ እንዲህ አላቸው፡፡ አምላክን የወለደች የእመቤታችንን ሥጋዋን ለማየት የተዘጋጀን አድርጎ ያሳየን ዘንድ ኑ ይህን ሁለት ሱባዔ በጾም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንለምነው በልጅዋ በወዳጅዋ ቀኝ ተቀምጣ አይተን በእርሷ ደስ እንዲለን፡፡

በዚያን ጊዜም ዮሐንስ እንዳላቸው በጾም በጸሎት ሱባዔ ያዙ፤ የነሐሴ ወር እንደዛሬ ዐሥራ ስድስተኛ ቀን በሆነ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉንም ሐዋርያት ወደ ሰማይ አወጣቸው፡፡ በታላቅ ክብር በተወደደ ልጅዋ ቀኝ ተቀምጣ ከሥጋዋ ተዋሕዳ ተነሥታ እመቤታችን ማርያምን አዩዋት፡፡ እጆቿንም ዘርግታ የከበሩ ሐዋርያትን እያንዳንዳቸውን ባረከቻቸው በልባቸውም እጅግ ደስ አላቸው፡፡

የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በከበረ ሥጋውና ደሙ ላይ ሠራዔ ካህን ሆነ፡፡ እስጢፋኖስም አዘጋጀ፤ ዮሐንስም በመፍራት ቁሙ አለ፡፡ ሁሉም ሐዋርያት በመሰዊያው ዙሪያ ቆሙ፤ በዚያን ጊዜ ከቶ እንደርሱ ሆኖ የማያውቅ ታላቅ ደስታ ሆነ፡፡

ጌታችንም የቅዳሴውን ሥርዓት በፈጸመ ጊዜ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው፡፡

ከዚያም በኪሩቤልና በሱራፌል ሠረገላ ተቀምጣ በምታርግ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱን  እመቤታችን ማርያምን እንዲህ ብሎ ተናገራት፡፡ በዚች ቀን የሆነ የዕርገትሽን መታሰቢያ በዓለም ውስጥ እንዲሰበኩ ልጆችሽ  ሐዋርያትን እዘዣቸው፡፡ መታሰቢያሽን የሚያደርገውን ሁሉ ተጠብቆም በዚች ቀን ቅዱስ ቁርባን የሚቀበለውን ኃጢአቱን እደመስስለታለሁ፡፡ የእሳትን ሥቃይ ከቶ አያያትም መታሰቢያሽን ለሚያደርግ ሁሉ በዚች ቀን ለድኆች በስምሽ ለሚመጸውት ቸርነቴ ትገናኘዋለች ይህም ሥጋሽ ወደ ሰማይ ያረገበት ነው፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ክብር ይግባውና ጌታችንን እንዲህ አለቸው ልጄ ሆይ እነሆ በዓይኖቻቸውም አዩ፤ በጆሮዎቻቸውም ሰሙ፤ በእጆቻቸው ያዙ ሌሎችም ታላላቅ ድንቆች ሥራዎችን አዩ፡፡

እመቤታችንም ይህን ስትናገር ጌታችን ሰላምታ ሰጥቷቸው በታላቅ ደስታ ወደ ደብረ ዘይት ተመለሱ፡፡

የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ በፍጹም ደስታ መታሰቢያዋን እናደርግ ዘንድ ይገባናል፡፡ እርሷ ስለ እኛ ወደተወደደ ልጅዋ ሁልጊዜ ትማልዳለች፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ይማረን፡፡ በረከቷም ሐዋርያት በሰበሰበዋት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ከሁላችን ጋር ይሁን ለዘላለሙ አሜን፡፡

ምንጭ፡-ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ

kedus kerkos eyeleta

ተራዳኢው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል

ሐምሌ 18 ቀን 2007 ዓ.ም.

kedus kerkos eyeleta አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሐምሌ ዐሥራ ዘጠኝ በዚችም ቀን ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ በሰማዕትነት መከራ ተቀበሉ፡፡

ይህም ሕፃን ዕድሜው ሦስት ዓመት ሲሆነው ከሮሜ አገር ወደ ሌላ ሀገር እናቱ ይዛው ሸሸች፤ በዚያም የሸሸችውን መኮንን እለ አስክንድሮስን አገኘችው፡፡

ሰዎችም ነገር ሠሩባት፤ ወደእርሱ አስቀረባትና ስለ አምልኮ ጠየቃት፡፡ እርሷም መኮንን ሆይ ዕድሜው ሦስት ዓመት የሆነው ሕፃን አለ፡፡ አማልክቶችህን ማምለክ መልካም እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ያስረዳን ዘንድ እርሱን ጠይቅ አለችው፡፡

ሕፃኑም ወደአለበት ጭፍራውን ልኮ ወደእርሱ አስመጣው፡፡ ሕፃኑንም ፊቱ ብሩህና ደስተኛ እንደሆነ አየውና አንተ ደስተኛ ሕፃን ሆይ እንዴት ነህ አለው፡፡ ሕፃኑም መልሶ አዎ ለእኔ ደስታ ተጠብቆልኛል፤ ላንተ ግን ኀዘንና ልቅሶ ጥርስ ማፋጨትም ነው፡፡ መጽሐፍ ለዝንጉዎች ተድላ ደስታ የላቸውም ብሏልና አለው፡፡ እግዚአብሔር ኃይልና ንግግርን ሰጥቶታልና ብዙ ተናገረ፡፡ በዚያም ያሉትን እስከ አስደነገጣቸው ድረስ ንጉሡን መኳንንቱንና ጣዖታቱን ረገማቸው፡፡ ከብርታቱም የተነሣ አደነቁ፡፡

መኮንኑም በአፈረ ጊዜ በውስጡ ሰም፤ ጨው፤ ባሩድ፤ሙጫ፤ የዶሮ ማር፤ እርሳስ፤ ብረት፤ ቅንጭብ፤ ቁልቋል፤ጨምራችሁ ታላቅ የብረት ጋን አምጡልኝ ብሎ ጭፍሮቹን አዘዛቸው፡፡

ጭፍሮቹም እንዳዘዛቸው ከአደረጉ በኋላ ያዘዝኸንን ሁሉ ፈጸምን እሳቱ ነዶ ፈልቷል፤ ድምፁ እንደነጎድጓድ ይጮሃል፤ ወላፈኑም እንደ ፀሐይ ነፀብራቅ በሩቅ ይጋረፋል፤ የፍላቱም ኃይል በዐሥራ ዐራት ክንድ ያህል ከፍታ ወደላይ ይዘላል፤ እንግዲህ በውስጡ የሚጣሉትን እዘዝ አሉት፡፡

በዚህ ጊዜ ሕፃኙ ቅርቆስና እናቱ እየሉጣ በክርስቶስ ስም ስለሚያምኑ አስረዋቸው ነበርና ከፍላቱ ይጨምሯቸው ዘንድ ከእሥር ቤት አወጧቸው፡፡ በዚያም ፍላቱ ወደላይ በሚዘል ብረት ጋን ውስጥ ለመጨመር ወሰዷቸው፡፡ የእነዚህን ቅዱሳን አሟሟት ያ ዘንድ በብዙ ሺሀሕ የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲሰበሰቡ አዘዘ፡፡

በዚህ ጊዜ ቅድስት ኢየሉጣ የፍላቱን ጩኸት በሰማችና ባየች ጊዜ ተሸበረች፤ ተዘጋጅቶላት ከነበረውም ክብር ልታፈገፍግሞከረች፡፡ ልጇ ቅዱስ ቂርቆስ ግን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ አደረበት፡፡ እናት ሆይ ከዚህ ከብረት ጋን ግርማ የተነሣ አትፍሪ፤ ድንጋፄም አይደርብሽ፤ አናንያንና አዛርያን ሚሳኤልንም እግዚአብሔር ከእቶነ እሳት እንዳወጣቸው ሁሉ እኛንም ከዚህ ከብረት ጋን ሊያወጣን ችሎታ ያለው መሆኑን አትጠራጠሪ፡፡ እናት ሆይ ከዚህ ከሚያልፈው ዓለም ጭንቅና መከራ ለመዳን ስትይ በማያልፈው በዘለዓለም እሳት ለመቀጣት ትመርጫለሽን፤ ይህስ አይሆንም ይቅርብሽ በአሁኑ ጊዜ እግዚአብሔር በመካከላችን አለና ይረዳናል፡፡ እናት ሆይ ሶስናን ከረበናት/ከመምህራነ አይሁድ/፤ ዳንኤልን ከአፈ አናብስት ያዳነ እሱ እኛንም ከዚህ የጋን ፍላት ያወጣናል፡፡

ይልቁንም በዚህ የብረት ጋን ውስጥ ግዳጃችንን ልንፈጽም ፈቅዶ ከሆነ ኢዮብ ንብረቱንና ገንዘቡን ልጆቹንና ሚስቱን በመጨረሻም የተፈጥሮ አካሉን ባሣጣው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ፤ እግዚአብሔር ሰጠ፤ እግዚአብሔር ነሣ/ወሰደ/፤ እግዚአብሔር እንደወደደ አደረገ ከማለት በስተቀር ምንም የተናገረው ነገር እንደሌለ ሁሉ እኛም የእሱን ዓለማ በመከተል ይህን መከራ ልንታገስ ይገባናል አላት፡፡

ነገር ግን እናቱ በዚህ ምክር ልትጽናና ባለመቻሏ ቅዱስ ቂርቆስ ዓይኑን ወደ ሰማይ አቅንቶ አቤቱ አምላኬ ሆይ ይህችን ባሪያህን ከርስትህ የምትለያት ከሆነ እኔን ከባለሟልነትህ መጽሐፍ ፋቀኝ፤ አቤቱ አዝመራውን አቃጥለህ ፍሬውን ልትባርክ ትወዳለህን፤ ይህን እንዳተደርግ ግን ቸርነትህ ትከለክልሃለች፡፡

አቤቱ እንጨቱን ቆርጣችሁ እንድዱት፤ ቅጠሉን ግን ጠብቁት ብለህ ልታዝዝ መለኮታዊ በሕርይህ አይደለም፤ ነገር ግን እንጨቱንም ቅጠሉንም ባንድ ጠብቁት ብለህ ታዝዛለህ እንጂ እንግዲህ በዚህ ምክንያት ይህን ያየ ሁሉ ማዳን የሚችል አምላክ ቢኖራቸውስ ኖሮ ከዚህ እሳት ባልሸሹም ነበር ብሎ አይጠራጠር፡፡

አቤቱ ዲያብሎስም ከባለሥልጣኑ ይልቅ እኔ በረታሁ፤ ቅዱሳኖቹንም ድል ነሳኋቸው ብሎ እንዳይመካ ከመንጋውም አንድ በግ ቀማሁ በማለት እንዳይደነፋ ለእናቴ ጽኑ የሆነ ኃይለ መንፈስ ቅዱስን ስጣት፤ ብሎ በጸለየ ጊዜ ዲያብሎስ ከኢየሉጣ አጠገብ ብን ብሎ ጠፋ፡፡

ከዚህ በኋላ ቅድስት እናቱ ለሰማያዊው መንግሥት አባት የሆንከኝ ልጄ ሆይ ከእንግዲህ አንተ አባቴ ነህ፡፡ እኔም ልጅህ ነኝ አለችው፡፡ ያቺ ከኔ የተወለድክባትም ቀን የተባረከች ናት አለች፡፡

ጌታህ ኃይልን ሰጥቶኛልና የሚጠብቀንን ገድላችንን ፈጽመን ድል እናድርግ እነሆ በብረት ጋኑ ውስጥ የሚነደውን እሳት በማይበት ጊዜ በለምለም ምንጭ ላይ እንደሚወርድ ጠል ሆኖ አይቼዋለሁና አለችው፡፡

እኒህም ቅዱሳን ሕህንን በሚነጋገሩበት ጊዜ በውስጡ አንገትን የሚቆለምም፤ ልብን የሚቀልጥ ሆድን የሚሰነጥቅ ሥርን የሚበጣጣስ መሣሪያ ካለበት የብረት ጋን ወስጥ ጨመሯቸው፡፡

ከዚህ በኋላ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወረደና የብረቱን ጋን እሳት አጠፋው፤ ከቅዱሳኑም አንዳቸውንም ሳያቃጥላቸው የብረቱን ጋን ማቃጠሉን መፍላቱም ፀጥ አለ፡፡

ወንድሞቻችን ሆይ እንግዲህ በጭንቃቸው ጊዜ ገድላቸውን እስኪፈጽሙ ድረስ ይህ መልአክ ከሰማዕታትና ከፃድቃን ጎን እንደማይለይ እወቁ፡፡

ለኃጥአንም ኃጢአታቸው ይቅር ይላቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሄር ይጸልይላቸዋል፡፡ እኛም የዚህ የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል በዓሉን በየወሩ እያከበርን አማላጅና ወዳጅ እናድርገዋ፤ በዚህም በሚበጣውም ዓለም ሊረዳን ይችላልና፡፡

ዳግመኛም እለ እስክንድሮስ ዐሳቡ ሳሳካለት ስለቀረ ዐሥራ ዐራ የሾሉና የጋሉ ብረት ችንካሮች አምጥተው ሰባቱን በእናቱ በኢየሉጣ አካል፤ ሰባቱን በራሱ በቂርቆስ አካል ማለትም ሁለቱን በጆሮዎቹ፤ ሁለቱን በዓይኖቹ፤ ሁለቱን በአፍንጫው፤ አንዱን በልቡ ይቸነክሯቸው ዘንድ ጭፍሮቹን አዘዘ፡፡

ዳግመኛም የሕፃኑን የእራስ ቆዳው ገፈው እሳት ውስጥ ይጨምሩት ዘንድ አዘዘ፡፡ አሁንም መልአኩ መጥቶ ይህንን መከራ ከእሱ አራቀለት፡፡ ቀጥሎም በመቃን ውስጥ ጨምረው በገመድ እንዲጎተቱ አዘዘ፤ ያን ጊዜም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሕፃኑ ቂርቆስ ወርዶ አጽናናው፤ አረጋጋውም፡፡

ስሙን ለሚጠራና መታሰቢያውን ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ሰጠው፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ እኛንም በቅዱስ ቂርቆስና በኢየሉጣ ጸሎት ይማረን፤ በረከታቸውም ትድረሰን፡፡ ለዘላለሙ አሜን፡፡

ምንጭ፡- ስንክሳር የሐምሌ 19፤ ድርሳነ ገብርኤል ሐምሌ 19

ስንክሳር በሰኔ አሥራ ሁለት ቀን የሚነበብ

ሰኔ 12ቀን 2007 ዓ.ም.

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሰኔ ዐሥራ ሁለት በዚች ዕለት የከበረ የመላእክት አለቃ የመልአኩ የሚካኤል የመታሰቢያውን በዓል ያከብራሉ፡፡

የሚያከብሩበትም ምክንያት እንዲህ ነው፡፡ እስክንድርያ በምትባል ከተማ አክላወ ባጥራ የተባለች ንግሥት የንጉሥ በጥሊሞስ ልጅ ዙሐል በሚባል ኮከብ ስም ያሠራችው ታላቅ ምኵራብ ነበረና በየዓመቱ ሰኔ በባተ በዐሥራ ሁለት ቀን በዚያ ምኵራብ ሕዝቡ ተሰብስቦ ታላቅ በዓል ያደርጉ ነበር፡፡ በዚያም ምኵራብ ውስጥ ዙሐል የሚሉት ታላቅ የነሐስ ጣት ነበረና በዓሉ በሚከበርበት ዕለት ብዙ ፍሪዳዎችን ያርዱለት ነበር፡፡

አባ እለእስክንድሮስም እስከተሾመበት ዘመን ድረስ ለዚያ ጣት እንዲህ ሲያደርጉ ኖሩ፡፡ ይኸውም ሦስት መቶ ዓመተ ምሕረት ተፈጽሞ በአራተኛው ምዕት ውስጥ ነበር፡፡

አባ እለእስክንድሮስ በእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ ጻድቅ ቆስጠንጢኖስም በነገሠ ጊዜ የክርስትና ሃይማኖት ስለ ተስፋፋች ያን ጣት ሊሠብረው ወድዶ ሳለ ጐስቋሎች ሰዎች ከለከሉት እንዲህም አሉት እኛ በዚህ ቦታ ይህን በዓል ማክበርን ለምደናል እነሆ ከአንተ በፊት ዐሥራ ስምነት ሊቃነ ጳጳሳት አልፈዋል ይህን ልማዳችንንም አልለወጡብንም፡፡

አባ እለእስክንድሮስ ግን ገሠጻቸው አስተማራቸውም ስሕተታቸውንም በመግለጥ እንዲህ ብሎ አስተማራቸው ይህ ጣት የማይጎዳና የማይጠቅም ነው እርሱንም የሚያመልክ ሰይጣናትን ያመልካቸዋል፤ ምክሬንስ ብትሰሙ ቀድሞ እንደ ነበረ አድርጌ ይህን በዓል እሠራላችኋለሁ ይኸውም ጣቱን እንድንሰብረው ምኵራቡንም እንድንባርከውና በከበረ መልአክ በመላእክት አለቃ በሚካኤል ስም ቤተ ክርስቲያን አድርገን እንድንሰይመው ነው እኛም ይህን ታላቅ በዓል እንሠራለን፡፡ የሚታረዱትም ላሞችና በጎች ለድኆችና ለጦም አዳራዎች ለችግረኞችም በከበረው መልአክ ስም ምግብ ይሁኑ፡፡ እርሱ በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነት ያለው ስለሆነ ስለእኛ ይማልዳልና፡፡ ይህንንም ብሎ በዚህ በጎ ምክር አስወደዳቸው እነርሱም ታዘዙለት፡፡

ከዚህም በኋላ ያንን ምኵራብ አድሰው በዚህ የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ስም ቤተ ክርስቲያን አደረጉት በዚችም ዕለት አከበሩዋት፡፡ እርሷም የታወቀች ናት፡፡ እስላሞችም እስከ ነጉሡበት ዘመን ኑራ ከዚያ በኋላ አፈረሱዋት፡፡

ይህም ባሕል ተሠራ እስከ ዛሬም ጸንቶ ይኖራል፡፡ ዳግመኛም በዚች ዕለት እግዚአብሔር የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን በነገዱ ውስጥ በመላእክት ሁሉ ላይ በብዙ ክብር ሾመው፡፡

ይህም የከበረ መልአክ ክብር ይገባውና በጌታችን ፊት ስለ ሰው ልጆችና ስለ ፍጥረትም ሁሉ ይለምናል ይማልዳልም፡፡

የዚህ የከበረ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ተአምራቱ ብዙዎች ናቸው፡፡ ከእነርሱም አንዱ ይህ ነው፡፡ እግዚአብሔርን የሚፈራ አንድ ሰው ነበረ እርሱም የከበረ የሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ በየወሩ በዐሥራ ሁለተኛው ቀን ይልቁንም በሰኔና በኅዳር ወር አብልጦ ያከብር ነበር፡፡

በጐረቤቱም ርኅራኄ የሌለው አንድ ባለጠጋ ሰው ነበረ፡፡ ይህን እግዚአብሔርን የሚፈራውን ሰው የከበረ መልአክ የሚካኤልን በዓል በሚያደርግበት ጊዜ ይጠላውና ያቃልለው ነበር ለድኆች ስለ መራራቱም ይዘባበትበት ነበረ፡፡

የሕይወቱ ዘመንም ተፈጽሞ የሚሞትበትና ከዚህ ከኃላፊው ዓለም ድካምም የሚያርፍበት ጊዜ ሲቀርብ የክቡር መልአክ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ታደርግ ዘንድ ምጽዋት ሰጭም ትሆን ዘንድ ሚስቱን አዘዛት፡፡

ከዚህም በኋላ አረፈና ገንዘው ቀበሩት ሚስቱም ፀንሳ ነበረች የመውለጃዋ ጊዜም ደርሶ ምጥ ያዛት በታላቅ ጭንቀት ውስጥ ሳለችም እንዲህ ብላ ጸለየች የእግዚአብሔር መልአኩ ሆይ ራራልኝ በእርሱ ዘንድ ባለሟልነት አለህና በእግዚአብሔር ዘንድ ስለ እኔ ለምንልኝ፡፡

ይህንንም በአለች ጊዜ በቤቷ ውስጥ ብርሃን በራ ከችግርም ዳነች መልአኩ ውብ የሆነ ወንድ ልጅንም ወለደች የእግዚአብሔርም መለአክተኛ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማይ ወረዶ ሕፃኑን እንዲህ ብሎ ባረከው ርኅራኄ የሌለውን የዚህን ባለጸጋ ገንዘብና ሀብት ጥሪቱንም ሁሉ ይህ ሕፃን እንዲወርስ እግዚአብሔር አዝዟል ባለጸጋውም በቤቱ በዐልጋው ላይ ሳለ ጌታ ጆሮውን ከፍቶለት ይህን ነገር ከመልአኩ ሰማ፡፡

ይህንን በሰማ ጊዜ ታላቅ ኀዘን ደረሰበት ሕፃኑንም የሚገድልበትን ምክንያት ይፈልግ ጀመረ ነገር ግን ክብር ይግባውና ጌታ ይጠብቀው ነበር፡፡

ከዚህ በኋላ ያ ባለጸጋ ምክንያት አዘጋጅቶ የሚያገለግለኝ ልጅ ይሆነኝ ዘንድ ልጅሽን ስጪኝ እኔም እየመገብኩና እያለበስኩ አሳድገዋለሁ ለአንቺም ሃያ ወቄት ወርቅ እሰጥሻለሁ አላት፡፡

ይህንንም ነገር ከባለጸጋው በሰማች ጊዜ ስለችግሯ እጅግ ደስ አላት ልጅዋንም ሰጠችው እርሱም ሃያውን ወቄት ወርቅ ሰጣት ልጅዋንም ወሰደው የምሻው ተፈጸመልኝ ብሎ ደስ አለው፡፡

ከዚህም በኋላ በልጁ ቁመት ልክ ሣጥን አሠርቶ ሕፃኑን በሣጥኑ ውስጥ አስገብቶ ዘጋበት እስከ ባሕርም ተሸክመው ወስደው በባሕር ጣሉት ክብር ይግባውና በጌታችን ፈቃድ ያ ሣጥን ሳይሠጥም ከዚያች አገር የሃያ ቀን መንገድ ያህል ርቃ ወደምትገኝ ወደ አንዲት አገር ወደብ እስከ ሚደርስ በባሕሩ ላይ ተንሳፈፈ፡፡

በባሕሩም አካባቢ በጎቹን አሰማርቶ የሚጠብቅ አንድ ሰው ነበርና ሣጥኑን በውኃ ላይ ተንሳፎ አየው እርሱም ከባሕሩ አውጥቶ ወደ ቤቱ ወሰደው ይህን ሣጥን እንዴት እንደሚከፍተው ያስብ ጀመረ ይህንም ሲያስብ ወደ ባሕሩ ይሄድ ዘንድ ጌታችን በልቡናው ኃሳብ አሳደረበት ወዲያውኑም ተነሥቶ ወደ ባሕሩ ሔደና አንድ ዓሣ የሚያጠምድ ሰው አገኘ፡፡

ዓሣ አጥማጁንም መረብህን በኔ ስም ጣል ለሚያዘውም ዓሣ ዋጋውን እሰጥሃለሁ አለው አጥማጁም እንዳለው አደረገ ያን ጊዜም ታላቅ ዓሣ ተያዘ ዋጋውንም ይዞ ወደቤቱ ሔደ ለራትም ይጠብሰው ዘንድ አረደው በሆዱም ውስጥ መክፈቻ አገኘ፡፡ በልቡም ይህ መክፍቻ ይህን ሣጥን ይከፍተው ይሆን አለ በሣጥኑ ቀዳዳም በአስገባው ጊዜ ፈጥኖ ተከፈተ በውስጡም ይህን ታናሽ ብላቴና አገኘ፡፡ ልጅ የለውም ነበርና ታላቅ ደስታ ደስ አለው ጌታችንንም አመሰገነው፡፡ ሕፃኑንም በመልካም አስተዳደግ አሳደገው ሕፃኑም አድጎ ጐልማሳ ሆነ፡፡

ከብዙ ዘመናትም በኋላ ያ ባለ ጸጋ ተነሥቶ ወደ ዚያ አገር ሔደ በመሸም ጊዜ ወደ በግ ጠባቂው ደጅ ደረሰ በግ ጠባቂውን እስከ ነገ የምናድርበት ማደሪያ በአንተ ዘንድ እናገኛለን ኪራዩንም እሰጥሃለሁ አለው በግ አርቢውም እንዳልክ ይሁንና እደር አለው ባለጸጋውም በዚያ አደረ፡፡

ራት በሚቀርብም ጊዜ ሕፃኑን ባሕራን ብሎ ጠራው ባለጸጋውም ሰምቶ ልጅህ ነውን ብሎ ጠየቀው በግ ጠባቂውም አዎን ታናሽ ሕፃን ሁኖ ሳለ ከባሕር አግኝቼዋለሁና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጄ ነው አለው፤ ባለጸጋውም በምን ዘመን አገኘኸው አለው እርሱም ከሃያ ዓመት በፊት ብሎ መለሰለት፡፡ ያን ጊዜም እርሱ ወደ ባሕር የጣለው መሆኑን አውቆ እጅግ አዘነ፡፡

በማግሥቱም ጎዳናውን ሊጓዝ በተነሣ ጊዜ ሰይጣናዊ ምክንያት አመካኝቶ በግ ጠባቂውን እንዲህ አለው ዕገሊት ወደምትባል አገር በቤቴ የረሳሁት ጉዳይ ስለአለ እንድልከው ልጅህን ትሰጠኝ ዘንድ እሻለሁ እኔም የድካም ዋጋውን ሃያ ወቄት ወርቅ እሰጥሃለሁ አለው፡፡ የብላቴናውም አባት ስለገንዘቡ ደስ ብሎት ልጁ ባሕራንን ሰጠው እንዲህም ብሎ አዘዘው ልጄ ባሕራን ይህ የከበረ ሰው ስለ ጉዳዩ ወደ ቤቱ ይልክህ ዘንድ ና ወደ ቤትህም በሰላም ትመለሳለህ፡፡

ያን ጊዜም ባለጸጋው ወደ መጋቢው እንዲህ ብሎ ደብዳቤ ጻፈ ይችን ደብዳቤ በምታነባት ጊዜ ደብዳቤዋን ይዞ የመጣውን ገድለህ በጉድጓድ ውስጥ ጣለው ማንም አይወቅ በመካከላቸውም የሚተዋወቁበትን ምልክት ጽፎ አሸጋት፡፡ ለባሕራንም ሰጠው ለመንገዱም የሚሆነውን ስንቅ ሰጠው ባሕራንም ተነሥቶ ጉዞውን ጀመረ ሲጓዝም ሰንብቶ የአንዲት ቀን ጉዞ ሲቀረው እነሆ የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ ሚካኤል በንጉሥ ጭፍራ አምሳል በነጭ ፈረስ ላይ ተቀምጦ አንተ ጐልማሳ የያዝኸው ምንድነው አለው ወደ ዕገሌ አገር ወደ ቤቱ ለማድረስ ከአንድ ባለጸጋ የተጻፈች መልእክት ናት አለው ያቺን ደብዳቤ አሳየኝ አለው እርሱም ስለ ፈራ ሰጠው፡፡

በዚያን ጊዜም የከበረው መልአክ ሚካኤል ያቺን የሞት መልእክት ደመሰሳት በእርሷ ፈንታም በንፍሐት ለውጦ እንደህ ብሎ ጻፈ ይቺን ደብዳቤ ይዞ ለመጣ ባሕራን ለሚባል ሰይቺ ደብዳቤ ደርሳ በምትነበብበት ጊዜ ልጄ ዕገሊትን አጋቡት በውስጥና በውጭ ያለ ንብረቴንና ጥሪቴን ወንዶችና ሴቶች ባሮቼን ጠቅላላ ንብረቴንም አውርሼዋለሁና የፈለገውንም ሊያደርግ ሥልጣን ሰጥቼዋለሁና እኔን አትጠብቁኝ፡፡ እኔ ብዙ እዘገያለሁ የኔ ሹም እገሌ ሆይ በእኔና በአንተ መካከል ይቺ ምልክት እነኋት ከዚህ በኋላ አሽጐ ለባሕራን ሰጠውና ወደ ባለጸጋው ቤት ሒደህ ይቺን ደብዳቤ ለሹሙ ስጠው በጎዳናም እኔ እንደ ተገናኘሁህ አትንገረው እንዳይገድልህም ይህን የሞት ደብዳቤ ለውጨልሃለሁ አለው፡፡ ባሕራንም እሺ ጌታዬ ያዘዝኸኝን ሁሉ አደርጋለሁ አለ፡፡  

ባሕራንም ወደ ባለጸጋው ቤት በደረሰ ጊዜ ያቺን ደብዳቤ ለሹሙ ሰጠው በአነበባት ጊዜ በመካከላቸው ያለውን ምልክት አገኘ አስተውሎም እርግጠኛ እንደሆነ አወቀ፡፡

ከዚህም በኋላ በባሕራን ሠርግ አዘጋጅቶ እንደሚገባ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓ በተክሊል የባለጸጋውን ልጅ አጋቡት፡፡ አርባ ቀን ያህልም ደስታና ሐሴት እያደረጉ ኖሩ፡፡

ከዚህ በኋላ ባለጸጋው ከሔደበት መመለሻው ጊዜ ሁኖ በደስታ የሆነውን የመሰንቆና የእንዚራ ድምፅ ሰምቶ ይህ የምሰማው ምንድነው ብሎ ጠየቀ፤ እነርሱም ስሙ ባሕራን ለተባለ የአንተን ደብዳቤ ላመጣ ጐልማሳ ሰው ልጅህ ዕገሊትን አጋቡት እነሆ ለአርባ ቀናት በሠርግ ላይ ነው፡፡ ገንዘብህንና ጥሪትህን ሁሉ ወንዶችና ሴቶች ባሮችህን አንተ እንዳዘዝክ ሰጥተውታል አሉት፡፡ ይህንንም በሰማ ጊዜ ደንግጦ ከፈረሱ ላይ ወደቀ በድንገትም ሞተ፡፡

ባሕራንም በጎ ሥራዎችን የሚሠራ ሆነ የተገለጸለትና ከመገደል ያዳነው የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ ሚካኤል እንደሆነ ሊገድለው የሚሻውን የባለጸጋውን ጥሪቱን ሁሉ ያወረሰውም እርሱ እንደሆነ ተረዳ የዚህንም የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ ሚካኤልን መታሰቢያ በየወሩ ያደርግ ጀመረ፤ ቤተክርስቲያንም ሠራለት የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕሉን አሥሎ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ አደረገው፤ ከእርሱም ብዙዎች ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ፤ ባሕራንም ቅስና ተሹሞ እስከ ዕለተ ሞቱ በዚያች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግል ሁኖ ኖረ በዚህ በከበረ የመልአክት አለቃ ሚካኤል አማላጅነት ከእናቱና ከአባቱ ከልጆቹም ጋራ የዘላለም ሕይወትን ወረሰ፡፡

መድኃኒታችን በተነሣባትም ቀን ይህ ክቡር መልአክ ሚካኤል ከውስጠኛው መጋረጃ ውስጥ ገብቶ በክብር ባለቤት ፊት እንዲህ እያለ ይለምናል እውነት ስለሆነ ቃል ኪዳንህ በምድር መታሰቢያዬን የሚያደርጉትን ትምርልኝ ዘንድ ፈጣሪዬ ሆይ እኔ አገልጋይህና መልእክተኛህ ከቸርነትህ እለምናለሁ አንተ መሐሪና ይቅር ባይ ነህና፡፡

የክብር ባለቤት ጌታችንም እንዲህ ብሎ ይመልስለታል፤ የመንፈሳውያን ሰማያውያን መላእክት አለቃቸው ሚካኤል ሆይ መታሰቢያህን የሚያደርገውን ሁሉ መሸከም እንደምትችል ከሲኦል ሦስት ጊዜ በክንፎችኛ ተሸክመህ እንድታወጣ እነሆ እኔ አዝዤሃለሁ፡፡

ይህንንም ቃል በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ ብሎት የበዓሉን መታሰቢያ ከሚያደርጉት በክንፎቹ ተሸክሞ የእሳቱን ባሕር አሳለፋቸው እነርሱንም ከብቻው ጌታ በቀር የሚቆጥራቸው የለም፡፡

ስለዚህም የዚህን ታላቅ የከበረ የመላእክት አለቃ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ለማድረግ መታገል ይገባናል እርሱ ከሰይጣን ወጥመድ ያድነን ዘንድ በዘመናችን ሁሉም ይጠብቀን ዘንድ ኃጢአታችንንም ያስተሠርይ ዘንድ መከራችንንም ያርቅ ዘንድ የምድራችንንም ፍሬ ይባርክ ዘንድ ፈቃዱንም ለመሥራት ይረዳን ዘንድ ከእኛ ወገን የሞቱትን ዕረፍተ ነፍስ ይሰጥ ዘንድ፤ ወደ መንገድ የሔዱ አባቶቻችንና ወንድሞቻተንን ወደ ቤቶቻቸው በሰላም በጤና ይመልሳቸው ዘንድ በመካከላችንም ፍቅር ያደርግልን ዘንድ እስከ መጨረሻዪቱም ሕቅታ ድረስ በቀናች ሃይማኖት ያጸናን ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ ይለምናልና፡፡

የክርስቶስ ወገኖች የሆኑ መኳንንቶቻችንንም ጠብቆ በወንበሮቻቸው ላይ ያጸናቸው ዘንድ የሳቱትንም ወደ ቀናች ሃይማኖቱ ይመልሳቸው ዘንድ፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ መልአክ አማላጅነት ይማረን ለዘላለሙ ዓሜን፡፡

ዳግመኛም በዚህች ቀን እግዚአብሔርን የሚፈራ አስተራኒቆስ የሚስቱ የቅድስት አፎምያ የዕረፍቷ መታሰቢያ ሆነ፡፡

ይህም ሰው በየወሩ ሦስት በዓላቶችን እያከበረ ኖረ እሊህም ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደቱ መታሰቢያ በየወሩ በሃያ ዘጠኝ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በዓል መታሰቢያ በየወሩ በሀያ አንድ የከበረ የመላእክት አለቃ የሆነ የቅዱስ ሚካኤል በዓል መታሰቢያም በየወሩ በዐሥራ ሁለት ናቸው፡፡

የሚሞትበትም ጊዜው ሲቀርብ እርሱ ሲሠራው የነበረውን ምጽዋት ይልቁንም እሊህን ሦስቱን በዓላት እንዳታስታጉል ሚስቱን ቅድስት አፎምያን አዘዛት፡፡

እርሷም የከበረ የመልአኩ የሚካኤልን ሥዕል ያሥልላት ዘንድ ባሏን ለመነችው እርሱም አሠርቶ ሰጣትና በቤቷ ውስጥ በክብር አኖረችው፡፡

ባሏም ከአረፈ በኋላ ባሏ ያዘዛትን መሥራት ጀመረች ሰይጣን ግን ቀናባት በመበለት ሴት መነኵሲት ተመስሎ ከእርሷ ጋር ተነጋገረ እንዲህም አላት እኔ አዝንልሻለሁም ገንዘብሽ ሳያልቅ የልጅነትሽም ወራት ሳያልፍ አግብተሽ ልጅ ትወልጂ ዘንድ እመክርሻለሁ ባልሽም መንግሥተ ሰማያትን ወርሷል ምጽዋትም አይሻም፡፡

አፎምያም እንዲህ ብላ መለሰችለት እኔ ከሌላ ሰው ጋራ ላልገናኝ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አድርጌያለሁ ርግቦችና መንጢጦች እንኳ ሌላ ባል አያውቁም በእግዚአብሔር አርአያ ከተፈጠሩ ሰዎች ይህ ሊሆን እንዴት ይገባል፡፡

ምክሩንም ባልሰማች ጊዜ አርአያውን ለውጦ በላይዋ ጮኸባት እንዲህም አላት እኔ በሌላ ጊዜ እመጣለሁ እርሷም የከበረ የመልአኩ የሚካኤልን ሥዕል ይዛ አሳደደችው፡፡

ከዚህም በኋላ ሰኔ ዐሥራ ሁለት የከበረ የመልአኩ የሚካኤል በዓል በሚከብርበት ዕለት እርሷም የበዓሉን ዝግጅት ስታዘጋጅ ሳለች ብርሃናዊ መልአክ መስሎ መጣ አፎምያ ሆይ ሰላም ላንቺ ይሁን እኔ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ነኝ፤ ጌታ ወደ አንቺ ልኮኛልና እርሱም ይህን መመጽወትሽን ትተሽ ለአንድ ምእመን ሚስት ትሆኚ ዘንድ ጌታ አዞሻል ባል የሌላት ሴት መልሕቅ የሌለውን መርከብ እንደምትመስል ዕወቂ፤ እንደ አበርሃምና ያዕቆብ እንደዳዊትም እንደእነርሱ ያሉ ብዙ ሴቶችን እንዳገባ እግዚአብሔርንም ደስ እንዳሰኙት ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጥቅሶችን ያመጣላት ጀመረ፡፡

ቅድስት አፎምያም መልሳ አንተ የእግዚአብሔር መልአክ ከሆንክ የመስቀል ምልክት ከአንተ ጋር ወዴት አለ የንጉሥ ጭፍራ የሆነ ሁሉ የንጉሡን ማሕተም ሳይዝ ወደ ሌላ ቦታ አይሔድምና አለችው፡፡

ሰይጣኑም ይህንን በሰማ ጊዜ መልአኩ ተለወጠና አነቃት እርሷም ወደከበረው መልአክ ወደ ሚካኤል ጮኸች ወዲያውኑም ደርሶ አዳናት፡፡ ያንንም ሰይጣን ይዞ ይቀጣው ጀመረ ሰይጣኑም ጮኸ ማረኝ ያለ ጊዜዬ አታጥፋኝ እግዚአብሔር እስከ ዓለም ፍጻሜ ታግሦናልና እያለ ለመነው ከዚያም ተወውና አበረረው፡፡

የከበረ መልአክ ሚካኤልም እንዲህ አላት ብፅዕት አፎምያ ሆይ ሒደሽ የቤትሽን ሥራ አዘጋጂ አንቺ ዛሬ ከዚህ ዓለም በሞት ትለዪአለሸና እነሆ እግዚአብሔርም ዐይን ያላየውን ጆሮም ያልሰማውን በሰው ልብም ያልታሰበውን አዘጋጅቶልሻል፡፡ ይህንንም ብሎ ሰላምታ ሰጣት ወደ ሰማያትም ዐረገ፡፡

የበዓሉንም ዝግጅት እንደሚገባ ከፈጸመች በኋለ ወደ ኤጲስቆጶሱና ወደ ካህናቱ ሁሉ ላከች ወደርሷም በመጡ ጊዜ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ይሰጧቸው ዘንድ ገንዘቧን ሁሉ አስረከበቻቸው፡፡

ከዚህም በኋላ ተነሥታ ጸለየች የከበረ የመልአኩ የቅዱስ ሚካኤልንም ሥዕል አንስታ ታቅፋ ሳመችው ያን ጊዜም በሰላም አረፈች፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቷ ይማረን የዚህም የከበረ መልአክ ሚካኤል የረድኤቱ ኃይል ሁላችን የክርስቲያን ወገኖችን ይጠብቀን ለዘላለሙ አሜን፡፡

ምንጭ፡-ስንክሳር

“ወበ እንተዝ ኢየኃፍር እግዚአብሔር ከመ ይትበሃል አምላኮሙ”

(ክፍል 2)

ሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም.

በቀሲስ ይግዛው መኰንን

4. ሰማያዊውን ሕይወት ናፋቂዎች ስለሆኑ

ክቡር ዳዊት “በቤትህ የሚኖሩ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው፤ ለዓለምና ለዘለዓለምም ያመሰግኑሃል፡፡ አቤቱ እርዳታው ከአንተ ዘንድ የሆነለት በልቡም የላይኛውን መንገድ የሚያስብ ሰው ምስጉን ነው፡፡” በማለት ሰማያዊውን መናፈቅ እንደሚያስመሰግን በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ተናገረ፡፡ መዝ. 83፥4

ቅዱስ ጳውሎስም የሚጠበቅበትን አገልግሎት ካከናወነ በኋላ “ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፤ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤” በማለት ምድራዊ ያይደለ ሰማያዊ ሕይወት ምን ያህል እንደሚናፈቅ ገልጿል፡፡ ፊል.1፥23 ለዚህ ነው ቅዱሳን በሥጋ የምኞት ፈረስ እንዲጋልቡ፥ በኃጢአት ባሕር እንዲዋኙ፥ በክፉ አሳብ ጀልባ እንዲቀዝፉ የሚፈታተናቸውን ርኩስ መንፈስ በመልካም ሥራቸው በመቃወም ድል የሚያደርጉት፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ፡፡” በማለት የአሁኑን ችግርና ፈተና ከሚመጣው ጋር በማመዛዘን የተናገረው፡፡ ሮሜ.8፥18

ቅዱስ ኤፍሬምም በውዳሴ ማርያም ጸሎቱ “ሰማዕታት በእውነት የዚህን ዓለም ጣዕም ናቁ፤ ስለ እግዚአብሔርም ሲሉ ደማቸውን አፈሰሱ፤ ስለመንግሥተ ሰማያትም ሲሉ መራራ ሞትን ታገሡ፡፡” በማለት የዚህን ዓለም መከራ መታገሥ ሰማያዊውን ክብር በማስታወስና የሚገኘውን ዋጋ በማመን እንደሆነ ገልጿል፡፡ /የሐሙስ ውዳሴ ማርያም/ ለዚህም ነው ሰማእታት እሳቱን ስለቱን፣ ጻድቃን ግርማ ሌሊቱን፥ ጽምፀ አራዊቱን፣ ጸብአ አጋንንቱን ታግሰው ሥጋቸውን ለነፍሳቸው አስገዝተው የኖሩበት ዐቢይ ምሥጢር፡፡

ሰማዕታት የሚታሰሩበትን ገመድ፣ የሚሰቀሉበትን ግንድ ይዘው ወደ ሞት ሲነዱ ጻድቃንም አስኬማቸውን ደፍተው፣ ደበሎአቸውን ለብሰው፣ ከምግበ ሥጋ ተለይተው ርሃቡን ጥሙን ችለው ሲኖሩ ደስ ይላቸዋል፡፡ ምክንያቱም ከፈጣሪያቸው እንደሚያገኙ ያውቃሉና ነው፡፡ መሬት ፊቷን ወደ ፀሐይ ስታዞር ብርሃን እንደምታገኝ፣ ፊቷን ስትመልስ ደግሞ ጨለማ እንደሚሆን ሳይንሱ ይነግረናል፡፡ የሰው ልጅም ፊቱን ወደ እግዚአብሔር ካዞረ ብርሃን ይሆንለታል፤ ፊቱን ከፈጣሪው ካዞረ ግን ይጨልምበታል፡፡ ኑሮው፣ ትዳሩ፣ መንገዱ ሁሉ የተሳካ እንዲሆን፣ የውስጥ ሰላምን እንዲያገኝ፣ በሚያገኘው ተደስቶ እንዲኖር፣ ሰላም፣ ጤና በረከት ከቤቱ እንዳይርቁ፣ አሸሼ ገዳሜ በሉ፣ አይዟአችሁ ጨፍሩ የሚለውን የጥንት ጠላት የአጋንንት ስብከት በመልካም ሥራ በዝማሬ በማኅሌት በሰዓታት በቅዳሴ፣ በኪዳን ተጠምዶመቃወም ያስፈልጋል፡፡

የዘወትር ስብከት “ሥጋችሁ በነፍሳችሁ ላይ ትንገሥ” የሚል ስለሆነ እኛ ግን ነፍሳችንን በሥጋችን ላይ ልናነግሣት እንደ አባቶቻችን ቅዱስን ሰማያዊውን ናፋቂዎች ልንሆን ያስፈልጋል፡፡ “ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘለዓለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንፃ እንዳለን እናውቃለንና፡፡ በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና፣ ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም፡፡” እንዲል፡፡ 2ቆሮ.5፥1

5. ለሌላው አሳቢዎች በመሆናቸው

ለሌላው ማሰብ፥ ለሌላው መጨነቅ፥ ከሚደሰቱ ጋር መደሰት፥ ከሚያዝኑ ጋር ማዘን፥ ችግር የወደቀባቸውን ሰዎች የችግራቸው ተካፋይ መሆን ፈጣሪን መምሰል ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “በአንድ አሳብ ተስማሙ፣ አንድ ፍቅር፣ አንድም ልብ፣ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤ ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቁጠር፤ እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፡፡ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ፡፡

በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን፡፡” በማለት ከራስ ይልቅ ለሌላው ማሰብን እንድናስቀድም ያስተምረናል፡፡ ፊልጰ.2፥1 ታላቁ ሊቅም በሰቆቃወ ድንግል ላይ “ኢየሱስ ስዱድ ተስፋሆሙ ለስዱዳን፡፡ ኢየሱስ ግፉዕ ምስካዮሙ ለግፉዓን፡፡ እግዚአብሔር ማኅደር ዘአልቦ ከመ ነዳያን..” በማለት የጌታችን መሰደድ የተሰደደውን የሰውን ልጅ ለመመለስ እንደሆነ፤ ጌታችን ያለ በደሉ የተገፋው የተገፋ የሰውን ልጅ ሊያድን እንደሆነ፤ እግዚአብሔር ተስፋ፣ ላጡ ተስፋ ማረፊያ ቤት ለሌላቸው ማረፊያ እንደሆነ ይነግረናል፡፡ ይህንን ስለሚያውቁ ቅዱሳን ከራሳቸው በላይ ለሌላው ያስባሉ፡፡

“ይህንን ኀጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍ እባክህ ደምስሰኝ አለ፡፡” የሚለውን የታላቁን ሰው የሙሴን ልመና ስንመለከት ምን ያህል ለሌላው ማሰብ እንደሚገባ እንማራለን ዘፀ.32፥32 ዛሬ ቢሆን ምናልባት ሌላውን ደምስሰህ እኔን ጻፍ ሳይባል ይቀራል ትላላችሁ፡፡ ቅዱሳን ግን እንደፈጣሪያቸው ለሌላው አሳቢወች በመሆናቸው “እግዚአብሔር አያፍርባቸውም” ተባለ፡፡

ዛሬም ሰው ለድሃ እጁን ሲዘረጋ እግዚአብሔር ደግሞ የምሕረት እጁን ይዘረጋለታል፡፡ የወደቀ ባልንጀራውን ሲያነሣ እግዚአብሔር እርሱን ከወደቀበት ያነሣዋል፡፡ የተጨነቀውን ሲያጽናና፥ የተጨቆነውን ነጻ ሲያወጣ ተስፋ ለቆረጠው ሲደርስለት በእውነት ዋጋው አይጠፋበትም፡፡ ለዚህ ነው ክቡር ዳዊት “ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው፤ እግዚአብሔር ይጠብቀዋል፤ ሕያውም ያደርገዋል፡፡” በማለት ያስተማረን፡፡ መዝ. 40፥1 ስለዚህ በዘመናችን ያለውን የወገንተኝነት፥ የትዕቢትና የሥጋዊነትን አስተሳሰብና አመለካከት በወንጌል መሣሪያነት አፈራርሶና ንዶ ለራስ ነጻ በመውጣት ለሌላውም መትረፍ ያስፈልጋል፡፡ ከነዚህ ክፉ ተግባራት ካልተለየን ገና ዛሬም በጨለማ ውስጥ ስላለን እንጠንቀቅ፡፡

“ልጄ ድሃውን ምጽዋቱን አትከልክለው ከሚለምንህ ከድሃውም ዓይኖችህን አትመልስ፡፡ የተራበች ሰውነትን አታሳዝን ያዘነ ሰውንም አታበሳጭ፡፡ ያዘነ ልቡናን አታስደንግጥ፣ የሚለምንህን ሰው አልፈኸው አትሂድ፡፡ የሚገዛልህ ቤተ ሰብህን አትቆጣ፤ ከድሃም ፊትህን አትመልስ፡፡” ካለ በኋላ ቀጥሎ “ከሚለምንህ ሰው ፊትህን አትመልስ፤ በልቡናው አዝኖ ቢረግምህ ፈጣሪው ልመናውን ይሰማዋልና፡፡”

በማለት ምስካየ ኅዙናን፣ ረዳኤ ምንዱባን የሆነ እግዚአብሔር የድሃውን ኀዘን ሰምቶ እንደሚበቀል ይነግረናል፡፡ ሲራ.4፥2 ስለዚህ የነዚህ ቅዱሳን ልጆች የሆን እኛ ፍትሕ ተጓድሎባቸው የሚሰማቸው አጥተው የሚገባቸውን፣ ተነፍገው፣ መከበር ሲገባቸው ተዋርደው ከሰው በታች ሆነው ለሚቆዝሙ ወገኖች ፈጥነን ልንደርስላቸው ይገባል፡፡ “ሳትሞት ለባልንጀራህ በጎ ነገርን አድርግ፡፡” ተብለን ተመክረናልና፡፡ ሲራ.14፥13

6. ለመከራ ራሳቸውን ያዘጋጁ በመሆናቸው

ከላይ እንዳየነው እምነታቸው በማዕበል ቢመታ የማይፈርስ እውነተኛ እምነት ስለሆነ ለመከራ አይበገሩም፡፡ ከእሳቱ ከሰይፉ ከመከራው በስተጀርባ የሚወርድላቸው አክሊለ ሕይወት ስለሚታያቸው ወደሞት ሲነዱ ደስ እያላቸው ይሄዳሉ፡፡ ራሳቸውን ለሞት ራሳቸውን ለስቅላት፣ ራሳቸውን ለእንግልት አዘጋጅተው በሃይማኖት ስለሚኖሩ፣ ፈጣሪ ያዝንላቸዋል፡፡ ደስ ይሰኝባቸዋልም፡፡ ያለ መከራ ዋጋ እንደማይገኝም ስለሚያውቁ “አቤቱ ቅጣኝ ነገር ግን እንዳታዋርደኝ በመጠን ይሁን እንጂ በቁጣ አይሁን፡፡” እያሉ ድሎትን ሳይሆን መከራ ሥጋን ይለምናሉ፡፡ ኤር.1፥24 ሥጋ ሲጎሰም ለነፍስ እንደሚገዛ ይረዳሉ፡፡

“ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል መከራ ወይስ ጭንቀት ወይስ ስደት፣ ወይስ ረሃብ ወይስ ራቁትነት፣ ወይስ ፍርሃት፣ ወይስ ሰይፍ ነውን “ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፣ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጥረን” ተብሎ እንደተጻፈ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ግን በወደድን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን፡፡ ሞት ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ ግዛትም ፍጥረትም ቢሆን፣ በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ፡፡” የሚለው የቅዱስ ጳውሎስም ትምህርት የሚያስተምረው ራስን ለመከራ ማዘጋጀትን ነው፡፡ ሮሜ.8፥35

ገበሬ ብርዱን፣ ዝናቡን፣ ፀሐዩን ታግሦ እሾሁን ነቅሎ መሬቱን አለምልሞ ተክል የሚተክለውና ከበቀለም በኋላ የሚኮተኩተው የሚያርመው ፍግ እያስታቀፈ የሚንከባከበው ውኃ እያጠጣ፣ ፀረ ተባይ መድኀኒት እየረጨ ከተባይ የሚጠብቀው፣ ቅጥር ምሶለት፣ አጥር አጥሮለት ከእንስሳት የሚያስጠብቀው በአጠቃላይ ብዙ የሚደክምለት መልካም ፍሬን ለማግኘት ነው፡፡ እንዲህ ከለፋ በኋላ አመርቂ ውጤት ቢያገኝ በልፋቱ ይደሰታል፡፡ በሚቀጥለውም ከመጀመሪያው የበለጠ እንክብካቤ ያደርግለታል፡፡ ካልሆነ ግን ያዝናል፡፡ ተክሉ ፍሬ አልባ ቢሆን ወይም ደግሞ ጣፋጭ ፍሬን እየጠበቀ መራራ ፍሬን ቢያፈራ ከማዘንም አልፎ እንዲቆረጥ ያደርገዋል፡፡ ዮሐ.15፥5፣ ማቴ.21፥18

ሰውም የእግዚአብሔር ተክል ነው፡፡ በቃለ እግዚአብሔር በምክረ ካህን ተኮትኩቶ በረድኤተ እግዚአብሔር አጥርነት ተጠብቆ የሚኖር የእግዚአብሔር የእጁ ሥራ ነው፡፡ ታዲያ ይህንን ስለሚያውቁ ቅዱሳን መልካም ፍሬን አፍርተው በመገኘታቸው እግዚአብሔር ተደስቶባቸዋል፡፡

ፍሬአቸው መራራ የሆኑ ተክሎች /ሰዎች/ ጨለማን ተገን አድርገው ሰው አየን አላየን ብለው ኀጢአትን የሚፈጽሙትን ያህል በእግዚአብሔር ቤት የተተከሉ፣ ፍሬአቸው ያማረ ቅዱሳን ጨለማው ሳይከለክላቸው ጽድቅን ሲሠሩበት ያድራሉ፡፡ በዓለም ላይ ለ5 ሺሕ 5 መቶ ዘመናት ኀጢአት በዓለም ላይ ነግሦ ይኑርም እንጂ በዚህ ኀጢአት በነገሠበት ዘመን ጽድቅን ሲሠሩ የኖሩ አባቶችና እናቶች ነበሩ፡፡ ዛሬም ኀጢአት በዓለማችን ላይ ጠፍንጎ ይዞ እያስጨነቀን እንዳለ ብንረዳም የነዚህ የቅዱሳን አበው በረከት ያደረባቸው በየገዳማቱ ወድቀው ለጽድቅ ራሳቸውን ሲያስገዙ እንመለከታለን፡፡

ማጠቃለያ

አንድን መንፈሳዊ ሥራ መጀመር ብቻውን የጽድቅ ምልክት አይደለም፡፡ ከላይ ያየናቸው የቅዱሳን ሕይወት ጽድቃቸው ከሰውም አልፎ በእግዚአብሔር የተመሰከረላቸው ከመጀመሪያው ይልቅ መጨረሻቸው በማማሩ ነው፡፡ ጀምረው ያቋረጡማ የሚነገርላቸው ማቋረጣቸው እንጂ ጽድቃቸው አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው ሳጥናኤል የመላእክት አለቃ ነበር፡፡ አርዮስ ካህን፣ ይሁዳ ከሐዋርያቱ ጋር ተቆጥሮ የነበረ፣ ዴማስ ከአርድዕተ ክርስቶስ ከነ ሉቃስ ጋር ተደምሮ የነበረ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ታዲያ እነዚህ ሰዎች የጀመሩትን መንፈሳዊ አገልግሎት ችላ ማለታቸው ከሰማይ ወደ ምድር፣ ከክብር ወደ ውርደት፣ ከሹመት ወደ ሽረት፣ ከማግኘት ወደ ማጣት ተወረወሩ እንጂ ምን ጠቀማቸው? በትናንት ማንነት ብቻ ድኅነት አይገኝም፡፡ ዛሬ የማያሳፍር ሥራን መሥራት እንጂ፡፡

ትናንት ዘመነኞች፣ ቅንጦተኞች፣ ኩሩዎች፣ የነበሩ ነገሥታት ወመኳንንት ዛሬ የት አሉ? በሀብታቸው የሚኩራሩ፣ በሥልጣናቸው የሚንጠራሩ፣ ፊታቸውን ከፈጣሪ ያዞሩ ሁሉ ጊዜ አልፎባቸው ገንዘባቸው፣ ሥልጣናቸው፣ ወገናቸው አላድናቸው ብሎ በጸጸት አለንጋ ከመገረፍ ውጪ ምንም አላገኙም፡፡ ስለዚህ ከዚህ መማር የዘመኑ ትውልድ ድርሻ ነው፡፡ በሃይማኖት ቁመው ከተጠቀሙት በሃይማኖት የመቆምን ጥቅም፣ ወድቀው ከተጎዱት የመውደቅን አስከፊነትና ጉዳት መማር እንችላለን፡፡

ስለዚህ ቆም ብለን ራሳችንን እንመርምር፡፡ በየመሥሪያ ቤታችን የምንሠራው ሥራ ሰውንና እግዚአብሔርን የሚያስደስት ነው ወይስ የሚያሳዝን፣ በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ በተለይ በሐዲስ ኪዳን “ከአሁን በኋላ ባሮች አልላችሁም፣ ልጆች ብያችኋለሁ፡፡” በማለት ያቀረበውን ፍጹምም የወደደውን የሰው ልጅ እንዴት እያየነው ነው? እውነት የምንሠራው ሥራ አሳፋሪ ነው ወይስ የሚያስደስትና የሚያስከብር? የሚለውን ጠይቀን ለራሳችን ምላሽ ልንሰጥ ያስፈልጋል፡፡ ያለ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ መልካምን ማድረግም አይቻልምና ለመልካም ሥራ እንዲያነሣሣን ኃይሉን ብርታቱንም እንዲሰጠን መልካም ፈቃዱ ይሁንልን፡፡

የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፡፡ (ዮሐ.16፡13)

ግንቦት 23ቀን 2007ዓ.ም

ዲ/ን ሚክያስ አስረስ

ይህች ዓለም ከእውነትን የራቀች መኖሪያዋን ሐሰት ያደረገች መሆኗ ይታወቃል፡፡ ሰው ማንነቱን አጥቶ በበደል ምክንያት በሐሰት ሰጥሞ ኖሯል፡፡ ሰው በፈቃዱ ጥመት ምክንያት ከሚፈጽማቸው በደሎች ትልቁ በደል ውሸት ነው፡፡ ውሸት ተሸንፎ ይወድቃል፤ ከሕይወት ይርቃል፡፡ የኀጣውእ ሁሉ ራስ ሐሰት ናት፡፡ ለዚህ ነው ክፋትን ከራሱ አንቅቶ የበደለ ዲያብሎስ አቡሃ ለሐሰት፤ የሐሰት አባት(ዮሐ.8፡44) የተባለው፡፡

አዳም እና ሔዋንን ለሞት ያደረሰ ያልሆኑትን፤ ሊሆኑ የማይችሉትን እንሆናለን ብሎ ከሐሰት ጋር መተባበራቸው ነው፡፡ ሐሰት የሆኑትንና የተሰጣቸውን እንደዘነጉ አድርጎ ማግኘት የማይችሉትን የባሕርይ አምላክነትን አስመኛቸው፡፡ እነርሡ በበደል ወድቀው፤ ከገነት ርቀው ልጆችን በመውለድ ሲባዙ ሐሰት ግዛቷን አስፍታ በኃይል በርትታ እውነት እስኪገለጥ ድረስ ቆየች፡፡ እውነት እግዚአብሔር በሰው ባሕርይ ሲገለጥ የእውነት መንገድን (ሃይማኖትን) ዳግመኛ ሰጠ፡፡ የዓለም መድኃኒት ክርስቶስ ከፈጸመው ድኅነት ለመሳተፍ ሰው ሐሰት ከተባሉ አምልኮ ጣዖት፣ ራስ ወዳድነት እና ሴሰኝነት ርቆ በእውነት ሊኖር የግድ ነው፡፡ እርሡ ሁሉ እንዲድኑ እውነትንም እንዲያውቁት ይወዳልና፡፡(1.ጢሞ 2፡4) እንደተባለ ሰውም ቢሆን በእውነት ጸንቶ ለመኖር በመፍቀድ ከእግዚአብሔር ጋር በፈቃድ አንድ መሆን አለበት፡፡

የአንድነት ሦስትነት ምሥጢር የተገለጠው አምላክ ሰው በመሆኑ ነው፡፡ ይልቁንም ሰው ወደዚህ እውነት እንዲመጣ የሚያደርገው መንፈስ ቅዱስ ወደ ደቀመዛሙርት የወረደው ሰው የሆነ አምላክ ክብሩን በመስቀል ሞት ሲገልጽ ነው፡፡ ክርስቶስ ስለእኛ ብሎ በመስቀል ላይ ባይሞት መንፈስ ቅዱስ አይወርድም ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ እንደሚመጣ አካሉ ለሆነች ለቤተ ክርስቲያንም ሕይወት እንደሚሆናት የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል(ዮሐ 16፡13) በማለት አስቀድሞ ተናገረ፡፡ መንፈስ ቅዱስ መምጣቱ አምላክ ሰው ሆኖ የፈጸመውን ለመረዳት እና ለማመን ለማስቻል ነው፡፡ ክርስቶስን በመድኃኒትነቱ ለመግለጽ ነው፡፡ ለዚህ ነው የተወደደ ሐዋርያ ዮሐንስ መነሻ ያደረግነውን ኃይለ ቃል ከተናገረ በኋላ ወውእቱ ኪያየ ይሴብሕ፤ እርሱ እኔን ይገልጻል፡፡(ዮሐ.16፡14) ያለው፡፡ እንዲሁ በበደል ከወደቀ በኋላም በሥላሴ ፈቃድ በወልድ ሰው መሆን በመንፈስ ቅዱስ መሠጠት ከወደቀበት ተነሥቶ ድኅነት (ሁለተኛ ተፈጥሮ) ተፈጸመለት፡፡ አዳም ሲፈጠር መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ እንደከበረ (ዘፍ.2፡1) እንዲሁ ይኸው መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል ለክርስቶስ ደቀመዛሙርት ወረደ፡፡ ጸጋ ሆኖ ተሠጣቸው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት የአብን ተስፋ መንፈስ ቅዱስን ደጅ እንዲጸኑ ይኸንንም በኢየሩሳሌም በአንድነት በመቆየት እንዲያደርጉ አዘዛቸው፡፡ (ሉቃ 24፡49) ደቀ መዛሙርቱም መቶ ሃያ ሆነው በኢየሩሳሌም በማርቆስ እናት ቤት አስቀድሞ ምሥጢረ ቁርባን በተመሠረተበት ቦታ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እናት እመቤታችንን በመሐል አድርገው በጸሎት በአንድነት በኢየሩሳሌም ቆዩ፡፡ (ሐዋ.1፡14)፡፡ እመቤታችን ባለችበት መንፈስ ቅዱስ ይወርዳልና፤ አስቀድሞ በወንጌል ቅድስት ኤልሳቤጥ እመቤታችን ወደ እርሷ ስትሄድ “መንፈስ ቅዱስ ሞላባት” (ሉቃ.1፤41 ) ተብሎ እንደተነገረላት፡፡ ከዚያም ረቂቅነቱን እና ኃያልነቱን ሲያጠይቅ መንፈስ ቅዱስ ከወደ ሰማይ እንደ ዐውሎ ነፋስ ባለ ድምፅ መጣ፡፡ ደቀመዛሙርት ባሉበት ቤት ገብቶ ሲመላው የተከፋፈሉ የእሳት ልሳኖች ሆኖ ታያቸው፤ በሁሉም አደረባቸው (ሐዋ.2፡3) ሁሉም ኃይልን ዕውቀትን አገኙ፤ በአገራትም ሁሉ ቋንቋዎች ተናገሩ፡፡ ስለ እውነት ደፋሮች ሆኑ፡፡ በነቢይ እሰውጥ እምነ መንፈስየ ዲበ ኩሉ ዘሥጋ፤ በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ(አዩ 3፡1) ተብሎ የተነገረው ዛሬ ተፈጸመ፡፡

አንዲት ቤተክርስቲያንን በአንድነቷ ለዘለዓለም የሚያኖራት እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ እንዲህ ስንል አብን እና ወልድን በመተው አይደለም፡፡ የሦስቱም ማደርያ ትሆናለች እንጂ፡፡ ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ምሥጢራትን ይገልጥልን ዘንድ አለ፡፡ â€Ãƒ‚¹ÃƒÃ‚¢€Ãƒ‚¹እኛስ የክርስቶስ ልብ አለን፡፡â€Ãƒ‚ºÃƒÃ‚¢€Ãƒ‚º (1ቆሮ.2፡16) እንዳለ ብርሃን ቅ/ጳውሎስ፡፡ የክርስቶስ ልብ የሆነ እግዚአብሔር አብ â€Ãƒ‚¹ÃƒÃ‚¢€Ãƒ‚¹እኛâ€Ãƒ‚ºÃƒÃ‚¢€Ãƒ‚º በተባልን በቤተ ክርስቲያን አለ ማለቱ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተለየ አካሉ ሰው ሆኖ በሕማሙ እና በሞቱ፤ በትንሣኤውና በዕርገቱ ድኅነትን ፈጸመ፡፡ አሁንም በቤተ ክርስቲያን እርሱ ሊቀ ካህናት ኢየሱሰ ክርስቶስ በአባቶች ካህናት ላይ በረድኤት አድሮ ምሥጢራትን ይፈጽማል፡፡ â€Ãƒ‚¹ÃƒÃ‚¢€Ãƒ‚¹ኦ እግዚኦ በከመ አሜሃ ዘንተ ኅብሰተ ባርክ ወቀድስ ወወሃብ፤ አቤቱ እንደዚያን ጊዜ ይህን ኅብስት ባርከው ሥጋህን አድርገው ቁረሰው እንዲሁ ስጥâ€Ãƒ‚ºÃƒÃ‚¢€Ãƒ‚º (ቅዳሴ ማርያም) የተባለውን ማስተዋል በቂ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ የአንድነት መንፈስ ነውና፡፡

ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የሚያደርጉንን ምሥጢራት ራሱ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ያከናውናቸዋል፡፡ ካህኑ ውኃውን ሲባርኩት በዕለት ዓርብ ከጌታ ጎን የፈሰሰውን ውሃ ያደርግላቸዋል በዚያ ማየገቦ (የጎን ውሃ) አዲስ አማኝ ተጠምቆ የእግዚአብሔርን ልጅነት አግኝቶ ከእርሱ ጋር አንድ ይሆናል፡፡ ካህናቱ የከበረውን የቅዳሴ ጸሎት ሲጀምሩ ያቀረቡትን ኅብስት እና ወይን እንዲህ ነው በማይባል አኳኋን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ እና ደም የሚያደርገው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ከእርሱ ጋር አንድነትን እናገኛለን፡፡ ሰው ንስሐ እንዲገባ በበደሉ እንዲጸጸት በሰው ውስጥ ሆኖ የንስሐን ደወል የሚያሰማው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ይህን የንስሐ ጥሪ በእሽታ ቢቀበል ዳግመኛ ከቤተ ክርስቲያን ተደምሮ ከእግዚአብሔር ጋር በአንድነት ይኖራል፡፡ ጥሪውን በእንቢታ አልፎ እስከ ሞት ድረስ በዚህ ቢጸና መንፈስ ቅዱስን ተሳድቧልና ኃጢአቱ አይሠረይለትም፤ ከሞት በኋላ ንስሐ የለምና፡፡ (ማቴ. 12፡32) ለተቀበሉት ግን አሁንም መንፈስ ቅዱስ አንድነትን የሚያድል መሆኑን እናስተውል፡፡ እኛ እርስ በእርስ በአንዲት ሃይማኖት ተባብረን ከአንድ መሥዋዕት ተካፍለን አንድ ርስትን ተስፋ በማድረግ አንድ የሚያደርገን እርሱ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡

በቅዳሴያችን ሀበነ ንኅበር በዘዚአከ መንፈስ ቅዱስ፤ ባንተ ህልውና ባለ መንፈስ ቅዱስ አንድ አድራጊነት አንድ እንሆን ዘንድ አንድ መሆንን ሰጠን፡፡ በማለት አንድ አድራጊያችን እርሱ እንደሆነ እንመሠክራለን፡፡ አንድ ሆነን በአንድነት ከጸናን እንደ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል የበቃን የተዘጋጀን ስለምንሆን ቀጥለን ፈኑ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ላዕሌነ፤ በእኛ ላይ ጸጋ የሚባል መንፈስ ቅዱስን ላክበማለት እንለምናለን፡፡ በዚህ በግዙፉ ዓለም ባለች ሰማያዊ መንግሥት በቤተ ክርስቲያን እንደተባበርን በዚያች ለምድራውያን ሰዎች ዓለም ሳይፈጠር በተዘጋጀችው መንግሥት አንድ እንሆናለን፡፡ ሐዋርያው መንግሥተ ሰማያትን የእግዚአብሔር መንግሥት በመንፈስ ቅዱስ የሆነ ደስታ እንጂ መብል መጠጥ አይደለምና(ሮሜ.14፡17) በማት ይናገርላታል፡፡

መንፈስ ቅዱስ በወረደላቸው ዕለት ደቀ መዛሙርት ምሥክርነታቸውን ማሠማት ጀመሩ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ህዝቡ በተሰበሰቡበት በዚያን ዕለት መንፈስ ቅዱስ መውረዱና እነርሱ በቋንቋዎች መናገራቸው እንዲሁ እንደ እንግዳ ደርሶ የመጣ ሳይሆን አስቀድሞ በነቢያት ትንቢት የተነገረ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ዳግመኛም ክርስቶስ በነቢያት እንደተነገረለት ሞቶ ከሙታን እንደተነሣ ሰበከላቸው፡፡ የሚሰሙት ሕዝቡ እርሱ የተናገራቸው ከልባቸው ስለገባ ምን እናድርግ አሉ (ሐዋ 2፡37)፡፡ ነስሑ ወተጠመቁ ኩልክሙ በስሙ ለኢየሱስ ክርስቶስ፤ ንስሐ ግቡ ሁላችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምናችሁ ተጠመቁ(ሐዋ 2፡38) ብሎ ቅዱስ ጴጥሮስ መለሰ፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ ነፍሳት ወደ ቤተክርስቲያን እየተደመሩ ቤተክርስቲያን ከኢየሩሳሌም እስከ ዓለም ዳርቻ ምሥክርነቷን አደረሠች፡፡ እንዲሁ ሰው የክርስትናን ጥምቀት ተጠምቆ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ገንዘብ ካደረገ ከሚኖርበት ከቤቱ ጀምሮ ምሥክር ሆኖ ወደ ዓለም መውጣት እንዳለበት መገንዘብ ይቻላል፡፡ 

ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ምሥጢራት ተሳትፋ ጸጋ ነሣእነ ወሕይወተ ረከብነ፤ ጸጋን ተቀበልን ሕይወትንም አገኘን፡፡ብላ በዚያው ባለችበት አትቀመጥም፡፡ ምእመናን ይህን የእግዚአብሔርን ቸርነት እንደቀምሱ ለዓለሙ ሁሉ ምሥክር እንዲሆኑ በቅዳሴ ምክንያት ወደ ሰማይ በሕሊና የወጣችው እትዉ በሰላም፤ በሰላም ወደቤታችሁ ግቡ ትላቸዋለች፡፡ በዓለም ሲኖሩ ከፈቃዱ ባይተባበሩ እንደ ክርስቶስ በፍቅር ያገለግሉ ዘንድ፡፡ የቀመሱትን የእግዚአብሔር ፍቅር በምግባራቸው ለዓለም ይመሠክራሉ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 20

ሚያዝያ 17 ቀን 2007 ዓ.ም.

ስለ ሰማዕታት፤ ስለ አማንያን፤ ስለ ከሃድያን

ቍ.744፡- ብፁዕ ኤጲስ ቆጶስ ያዕቆብና ቅዱስ እስጢፋኖስ በእኛ ዘንድ የከበሩ እንደሆኑ ሰማዕታት በእናንተ ዘንድ የከበሩ ይሁኑ፡፡ እነዚህም በእግዚአብሔር ዘንድ የተመሰገኑ ናቸው፡፡ ትሩፋታቸውም የማይገኝ ነው፡፡

ቍ.747፡- ሰማዕታትም እኔን በሰው ፊት ያመነኝን ሰው ግን እኔም በሰማይ አባቴ ፊት አምነዋለሁ ብሎ ክርስቶስ ስለእነርሱ የተናገረላቸው እነዚህ ናቸው፡፡/ማቴ.10፤32/ በመከራቸው ጊዜ ብትመስሏቸው ስለ ቁርጥ አሳባችሁ ሰማዕትነት ይቆጠርላችኋል፡፡

ቍ.748፡- ሰማዕታትን ከሚረዱዋቸው ወገን አንዱ መከራ ቢያገኘው ብፁዕ ነው፡፡ እርሱ የሰማዕታት ተባባሪያቸው ነውና፡፡ በመከራዎቹም ክርስቶስን መስለው እኛንም ከካህናት ብዙ መከራ አገኘን፡፡ ከእነርሱም ዘንድ ደስ እያለን ወጣን፡፡ ስለመድኃኒታችን ስለ ክርስቶስ መከራን እንቀበል ዘንድ አድሎናልና፡፡ /የሐዋ. 5፤41/ እናንተም እንደዚህ መከራ በተቀበላችሁ ጊዜ ደስ ይበላችሁ፡፡ እናንተ በፍርድ ቀን ትመሰግናላችሁና፡፡

ቍ.749፡- ስለሃይማኖት የሚያሳድዷቸውን ስለጌታችን ትእዛዝ ከአገር ወደ አገር የሚሸሹትን ተቀበሏቸው፤ አሳርፏቸውም፤ ጥቀሟቸውም፤ እንደ ሰማዕታትም አድርጋችሁ አክብሯቸው፡፡ በተቀበላችኋቸውም ጊዜ እናንተ ደስ ይበላችሁ፡፡ ጌታ ክርስቶስ ስለ እኔ ባሳደዷችሁ ጊዜ እናንተ ብፁዓን ናችሁ፤ ፈጽሞ ደስ ይበላችሁ፤ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና፡፡ እንደዚሁም ከእናንተ አስቀድመው የነበሩ ነቢያትን አሳደዷቸው፡፡ እኔን ካሳደዱ ግን ዳግመኛ እናንተን ያሳድዷችኋል፡፡ ከዚች አገር ቢያሳድዷችሁ ወደ ሌላይቱ አገር ሂዱ ብሏልና፡፡ /ማቴ. 5፤11-12፣ ማቴ. 10፤23/

ቍ.750፡- ዳግመኛም እንዲህ አለ፤ በዚህ ዓለም መከራና ኀዘን ያገኛችኋል፡፡ ወደ አደባባይ ያገቧችኋል፡፡ ለእናንተ ምስክር ሊሆንላችሁ ስለ እኔ ወደ ነገሥታቱና ወደ መኳንንቱ ያደርሷችኋል፡፡ እስከ መጨረሻው የታገሠ እርሱ ይድናል፡፡ ለክርስቶስ እንዳልሆነ የሚክድ ከእግዚአብሔርም ይልቅ ፈጽሞ ራሱን የወደደ ሰው ግን ይቅርታን አያገኝም፡፡ የእግዚአብሔር ጠላት የሰዎች ወዳጅ ሊሆን ወድዷልና፡፡ ስለተባረከችውም መንግሥት ፈንታ የዘለዓለም እሳትን ወድዷልና፡፡ /ማቴ. 10፤17-23/ ስለእርሱም ጌታችን በሰው ፊት የካደኝን ስሜንም የለወጠውን እኔም በሰማያዊ አባቴ ፊት እክደዋለሁ፡፡ እለውጠዋለሁም አለ፡፡ /ሉቃ. 12፤8-9/

ቍ.751፡- እንደዚህም ለእኛ ለደቀ መዛሙርቱ ከእኔ ይልቅ አባቱንና እናቱን ወይም ወንድ ልጁንና ሴት ልጁን የሚወድ እኔን አይመስለኝም፡፡ የሞቱንም መከራ ተሸክሞ ያልተከተለኝ እኔን አይመስለኝም አለ፡፡ ሰውነቱን የሚወድ ይጣላት፤ ሰውነቱን የጣላ ግን በእኔ ዘንድ ያገኛታል፡፡ ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ነፍሱን ካጣ ምን ይጠቅመዋል? ሰው ለነፍሱ ቤዛ ምን በሰጠ ነበር፡፡ /ማቴ. 10፤37-39፣ ማቴ. 16፤22-27/ ዳግመኛም ሥጋችሁን የሚገድሉትን ሰዎች አትፍሯቸው፡፡ ነፍሳችሁን ግን መግደል አይቻላቸውም፡፡ ነፍስና ሥጋን አንድ አድርጎ በገሃነም እሳት መቅጣት የሚቻለውን ፍሩት እንጂ አለ፡፡ /ሉቃ. 12፤4-5፣ ማቴ. 10፤28/

ቍ.754፡- ብንጨነቅም ኃላፊውን ዘመን ስለመፍራት ሃይማኖታችንን አንለውጥ፡፡ አንዱስ እንኳ አለኝታውን ቢክድ ይኸውም የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ለጥቂትም ዘመን ከሚሆነው ሞት የተነሣ ቢፈራ ድኅነት በሌለበት በጸና ደዌ ነገ ቢያዝ ከዚች ሕይወት የተለየ ይሆናል፡፡ የወዲያውንም ዓለም ያጣል፡፡ ልቅሶ፤ ጥርስ ማፋጨት ባለበት በጨለማ ውስጥ ለዘለዓሙ ይኖራል፡፡ /ማቴ. 8፤13/

ቍ.755 እና 756፡- ያልተጠመቀ ሰውም ልቡ አይዘን፡፡ ስለ ክርስቶስ የተቀበለው መከራ የተመረጠ ጥምቀት ይሆንለታልና፡፡ የሞቱን ምሳሌ በተቀበለ ጊዜ በጌታ አምሳል ሞቷልና፡፡ ሁለት ልብ አይሁን፡፡ እነርሱ ቢገድሉት እርሱም ቢገደል ይጸድቃልና፤ በደሙ ብቻ ተጠምቋልና፡፡

ቍ.761፡- በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው ደማቸውን ላፈሰሱ ሁሉ ባረፉበት ቀን መታሰቢያቸውን ያድርጉላቸው፡፡

ቍ.765:- በሰማዕታት በዓል የሚሰበሰቡትን ሰዎች የሚንቃቸው ሰው ትዕቢትን የተመላ ነውና የተወገዘ /የተለየ/ ይሁን፡፡

ቍ.766፡- ምእመናን የክርስቶስን ሰማዕታት ትተው ዓላውያን ሰማዕታ ወደሚሏቸው ቦታ መሄድ አይገባቸውም፡፡ ስለ ክርስቶስ ፍቅር መጋደላችን እንዴት መሆን እንደሚገባው እነሆ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጻፈ፤ ወደ ሮሜ ሰዎች በላከው መልእክቱ እንዲህ አለ፤ የክርስቶስን ፍቅር ማን ያስተወናል? መከራ ነውን፤ እስራት ነውን፤ ስደት ነውን ረሃብ ነውን፤ መራቆት ነውን መጣላት ነውን፤ ሰይፍ ነውን፤ ስለአንተ ዘወትር ይገደላሉና እንደሚታረዱም በጎች ን ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ በዚህ ሁሉ መከራ የወደደን በመውደዳችን እኛ ድል እንነሳለን፤ እኔም ሊለየኝ የሚችል እንደሌለ አምናለሁ፡፡ ሞት ቢሆን፤ ሕይትም ቢሆን፤ መላእክት ቢሆኑ፤ አለቆችም ቢሆኑ፤ አሁን ያለውም ይመጣም ዘንድ ያለው ሥራ ሁሉ ቢሆን ኃይለኞችም ቢሆኑ፤ ላይኛውም ቢሆን፤ ታችኛውም ቢሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየኝ አይችልም፡፡ /ሮሜ. 8፤35-39/

ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? (ሮሜ 8፡35)

ሚያዝያ 17 ቀን 2007 ዓ.ም.

በዲ/ን ያረጋል አበጋዝ

መጽሐፍ ቅዱስ ከጥንት ጀምሮ የሚነግረንን የሰውና የእግዚአብሔር ግንኙነት ስንመለከት ጎልተው የሚወጡ ሁለት መሠረታዊ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህም በአንድ በኩል እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለው ታላቅ በጎ ሃሳብና ልዩ አባታዊ ቸርነት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የሰው ልጆች ለዚህ አምላካዊ ጥሪና ቸርነት የሚሰጡት የአጸፌታ መልስ ነው፡፡ የሰዎች አጸፌታዊ መልስም ሁለት ዓይነት ነው፡፡ ይህም ጥቂቶቹ ለአምላካቸው በጎ ምላሽ ሲሰጡ ቀሪዎቹ (በታሪክ ሲታይ ብዙዎቹ) ለአምላካቸው መታዘዝን እምቢ ማለታቸውንና ማመጻቸውን ነው፡፡ የሰው ልጅ ታሪክ የሚያሳየን ከመጀመሪያዎቹ የሰው ልጆች ከአዳምና ከሔዋን ጀምሮ የዲያብሎስን የጎዮንሽ ክፉ ምክር ሰምተው በአምላካቸው ላይ ሲያምጹ፣ ከዚያም የተነሣ ከጸጋ ተራቁተው በራሳቸው ላይ ተደራራቢ ዕዳ በደል ማምጣታቸውን ነው፡፡ ከዚያም ዐመጽ የተጀመረው የሰው ሕይወት እየቀጠለ ክፉው ቃየን የራሱን ወንድም አቤልን በግፍ ደሙን ሲያፈስሰውና ሲገድለው እናያለን፡፡

በሰው ልጆች የመጀመሪያ ጥፋትና ዐመጽ የመጣውን ዕዳና በደል፣ አጠቃላይ በሰው ዘር ላይ የወደቀውን ብዙ ጉዳትና ጥፋት ለማስወገድና ሰውን ወደ ሕይወትና ክብር ለመመለስ ራሱ እግዚአብሔር ሰውን ፍለጋ ልዩ በሆነ አመጣጥ አካላዊ ቃል ሰው ሆኖ ወደ ፈጠራቸው የሰው ልጆች ባሕርያችንን ባሕርዩ አድርጎ ሲገለጥ ደግሞ በደስታ እንደ መቀበል ፋንታ አሁንም ብዙዎች ተቃወሙት፡፡ ነገሩ ድንገት የደረሰባቸውና ያልጠበቁት እንዳይሆንባቸው እግዚአብሔር ከገነት ሲባረሩ ጀምሮ በትንቢት፣ በራዕይ፣ በተምሳሌትና በመሳሰለው ሁሉ ሰው ሆኖ ወደዚህ ዓለም እንደሚመጣ ደግሞ ደጋግሞ ሲናገር ነበር፡፡ ሆኖም ግን ያ ሁሉ ትንቢትና ሱባኤ የተነገራቸው አይሁድ ለማመን የመጀመሪያዎቹ ሊሆኑ ሲገባቸው የእግዚአብሔርን እውነትና ልዩ ጸጋ ለመቀበል አልፈለጉም፡፡ ቅዱስ ወንጌል ውስተ እሊአሁ መጽአ ወእሊአሁሰ ኢተወክፍዎ – የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፣ የገዛ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም በማለት ይህን አሳዛኝ እውነታ ይነግረናል፡፡ ዮሐ. 1፡12

እውነትን የሚቃወሙ አይሁድ ተቃውሟቸውና ጥላቻቸው እያደገ ሄዶ ጫፍ ሲደርስም ምንም እንኳ እርሱ በፈቃዱ ወዶ ቢያደርገውም እነርሱ ግን እናጠፋዋለን መስሏቸው በመስቀል ሰቀሉት፡፡ በመቃብር ለማስቀረትና ከዚያ ወዲያ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም ነገር እንዳይነገርና ታሪክ ብቻ ሆኖ እንዲቀር ለማድረግ በማሰብ መቃብሩን ጥቂት ሰዎች ብቻቸውን ሊያንከባልሉት የማይችሉት ታላቅ ደንጊያ ገጥመው ዘጉት፡፡ ይህም አልበቃቸው ብሎ ከሮማውያን ወታደሮች እንዲመደቡ አድርገው ዙሪያውን እንዲጠብቁ አደረጓቸው፡፡ በገዢው ማኅተምም አተሙት፡፡ ሆኖም ግን ያ ሁሉ ጥረትና ጥበቃ ሥግው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብሩን ክፈቱልኝ ደንጊያውን አንሡልኝ ሳይል መቃብሩ እንደ ታተመ ሞትን ድል አድርጎ ከመነሣት አላገደውም፡፡ ቅዱሳን መላእክት ወደ መቃብሩ የሄዱትን ቅዱሳት አንስት ምንተ ተኃሥሣሁ ለሕያው ምስለ ምውታን ተንሥአ ኢሀሎ ዝየሰ – ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቷል እንጂ በዚህ የለም? በማለት የሞትንና የመቃብርን ይዞ የማስቀረትና የማፍረስ የማበስበስ ኃይል ድል አድርጐ መነሣቱን የምሥራች አበሠራቸው፡፡ ሉቃ. 24፡5 ሞትንና የክፋ ኃይልን ሁሉ ድል አድርጎ ለተነሣው ለመድኃኒታችንና ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ምስጋና ለእርሱ ይሁን!

እርሱ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ያ በዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ መከራ የተቀበለውና የሞተው፣ ወደ መቃብር የወረደው እርሱ አሁን ሕያው ሆኖ መነሣቱን በመካከላቸው እየተገኘ የተወጋ ጎኑን፣ የተቸነከሩ እጆቹንና እግሮቹን በማሳየት የተነሣው ያው እርሱ መሆኑን ደጋግሞ አረጋገጠላቸው፡፡ ከዚህም በኋላ እነርሱ ወደ ዓለም ሁሉ ሄደው ይህን የሞትን በክርስቶስ ትንሣኤ መወገድና በእርሱ ለሚያምኑ ሁሉ ሕይወት፣ ልጅነት፣ መንግሥተ ሰማያት በእርሱ ዘንድ የተዘጋጀ መሆኑን እንዲመሰክሩ መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁብሎ ላካቸው፤ ። የሐዋ. 1፡8

መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን የሕይወትን ቃል እንዲሰብኩ ወደ ዓለም ሲልካቸው ምን እንደሚጠብቃቸው ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ፣ . . . እያለ አስቀድሞ ደግሞ ደጋግሞ እውነታውን ነግሯቸዋል፣ አስጠንቅቋቸዋል፡፡ ማቴ. 10፡28 እንዲሁም እነርሱን የሚያሳድዷቸው እምነት አያስፈልግም ወይም በእግዚአብሔር መኖር አናምንም የሚሉ ብቻ ሳይሆኑ ይልቁንም እግዚአብሔርን ያገለገሉና ለእርሱ የቀኑ የሚመስላቸው ሃይማኖተኞች ነን ባይ የሆኑ ሰዎችም እንደሚሆኑ እንዳትሰናከሉ ይህን ተናግሬያችኋለሁ። ከምኵራባቸው ያወጧችኋል፤ ከዚህ በላይ ደግሞ የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል። ይህንም የሚያደርጉባችሁ አብንና እኔን ስላላወቁ ነው በማለት በሚገባ አስቀድሞ አስጠንቅቋቸዋል፣ አስተምሯቸዋል፡፡ ዮሐ. 16፡1-3 እምነት የለኝም ከሚለው ባላነሰ በተሳሳተ እምነት ውስጥ ያሉም እውነተኛ ክርስቲያኖችን በጽኑ ጭካኔ ሲጨፈጭፉ ኖረዋል፡፡ ማንም ሰው የመሰለውን ማመን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ችግር የሚሆነው ሌላውን ሰው ግድ እኔ የማምነውን ካላመንክ በስተቀር በዚህች ምድር ላይ የመኖር መብት የለህም ሲል ነው፡፡ በምድራችን ላይ ብዙ ግፍ ሲፈጸም የኖረውና አሁንም እየተፈጸመ ያለው ከዚህ የተሳሳተ እምነትና አስተሳሰብ የተነሣ ነው፡- እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ሰው የሰጠውን ነጻነትና መብት በመጋፋት ሰዎችን በማስተማርና በሳመንና ሳይሆን በኃይልና በጉልበት በማስገደድ የራስን እምነት በሌላው ላይ መጫን፡፡ ይህም ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ በእግዚአብሔር እናምናለን የሚሉት ብቻ ሳይሆኑ በእግዚአብሔር መኖር አናምንም፣ ሃይማኖት የለንም የሚሉትም (ይህም በራሱ እምነት ስለሆነ) ሌሎችን እንደ እኛ ካልሆናችሁ በማለት ብዙ ግፍ ሲያደርሱ ኖረዋል፣ ዛሬም ያው ሁኔታ መልኩንና ቅርጹን ቢቀይር እንጂ ጨርሶ አልቀረም፡፡

እንግዲህ የክርስቶስ ተከታዮች (ክርስቲያኖች) ከቅዱሳን ሐዋርያት ጀምሮ በየዘመናቱ የየጊዜውን መስቀል ሲሸከሙና ከመስቀሉ በኋላ የሚገኘውን አክሊል ሲቀበሉ ኖረዋል፡፡ በዘመናት የሚኖሩ ክርስቲያኖች የሚሸከሙት መስቀል አንድ ዓይነት አይደለም፤ ለዚህ ነው ጌታችን መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ ያለው፡፡ ማቴ. 16፡24 መስቀሉን ማለቱ ለእርሱ የተዘጋጀለትን መከራ ማለቱ ነው፡፡ በክርስትና የመጀመሪያው ምስክር የሆነው ቅዱስ እስጢፋኖስ ለአይሁድ የኢየሱስ ክርስቶስን እውነተኛ አምላክነትና መድኃኒትነት፣ እነርሱ (አይሁድ) እንቀበላቸዋለን በሚሏቸው የብሉያት መጻሕፍት ሁሉ የተነገረውና በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው መድኃኒት (መሢሕ) መሆኑን፣ እነርሱም ኢየሱስን መስቀላቸው ታላቅ ጥፋት መሆኑን ሲነግራቸው ተከራክረው መርታት ስላልቻሉ በደንጊያ ወግረው ገደሉት፡፡ . . . ከከተማም ወደ ውጭ አውጥተው ወገሩት። ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በሚሉት በአንድ ጎበዝ እግር አጠገብ አኖሩ። እስጢፋኖስም፡- ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ ነፍሴን ተቀበል ብሎ ሲጠራ ይወግሩት ነበር። ተንበርክኮም፡- ጌታ ሆይ፣ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህንም ብሎ አንቀላፋ። ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር። የሐዋ. 7፡57-60 ስለ ክርስቶስ እየመሰከሩ ይህን እውነትና ሕይወት በሚቃወሙ በክፉዎች እጅ መገደልና ሰማዕትነትን መቀበል አንድ ተብሎ ተጀመረ፡፡ በክርስቶስ መከራና መስቀል የተጀመረው የክርስትና ጉዞም በሕይወት መዝገብ ላይ በደም ቀለም መጻፍ ጀመረ፡፡

በመቀጠልም ከሐዋርያት መካከል ቅዱስ ያዕቆብ በሄሮድስ እጅ በሠይፍ በመገደል ሰማዕት ሆነ፡፡ በዚያም ዘመን ንጉሡ ሄሮድስ መከራ ያጸናባቸው ዘንድ ከቤተ ክርስቲያኑ በአንዳንዶቹ ላይ እጁን ጫነባቸው። የዮሐንስንም ወንድም ያዕቆብን በሰይፍ ገደለው። የሐዋ. 12፡1-2 ከዚያ በኋላ ክርስቲያኖችን መግደልና ማሰቃየት እየሰፋና ተቋማዊ መልክ እየያዘ ሄዶ በተለይ በሮማ ግዛት ግዛት ክርስትና በዐዋጅ ሕገ ወጥ ሃይማኖት ነው ተባለ፡፡ በፋርስ ግዛትም እንዲሁ ክርስትና በመንግሥት በይፋ የሚሳደድ ሆነ፡፡ ኔሮን ቄሣር የሮም ከተማ ነዋሪ ክርስቲያኖችን በመግደሉ ሂደት እንዲተባበረውና እንዲደግፈው በማሰብ የከተማን የተወሰነ ክፍል ካቃጠለ በኋላ ይህን ያደረጉት ክርስቲያኖች ናቸው አለ፡፡ ከዚያም ክርስቲኖያችን ያገኛቸው ሁሉ እንደ ሀገር ጠላት በመቁጠር ገደላቸው፡፡ በዚህም ቁጥራቸውን እግዚአብሔር ብቻ የሚያውቃቸው የብዙ ብዙ የሆኑ የክርስቲያኖች ደም ፈሰሰ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስም አንዱ በስቅላት ሌላው በምትረተ ሠይፍ ሞቱ፡፡ አንዳንዶቹ የሮም ቄሣሮች ደግሞ ክርስቲያኖችን ማታ ማታ ሰቅለው በእሳት እያነደዱ እንደ ሻማ እንደ መብራት እስኪጠቀሙባቸው ደረሱ፡፡

በዚያን ዘመን ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ብለው ሕይወታቸውን ለሰማዕትነት የሰጡትን ቅዱሳን አባቶችና እናቶች እንዲሁም ሕጻናት ቁጥራቸውን ቀርቶ ግምታቸውን እንኳ ማንም ሊያውቀው አይችልም፡፡ ይህን ለመረዳት አንድ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ ያለውን ብቻ ጠቅሰን እንለፍ፡፡ በዚያን ዘመን ብዙ ሰዎችን በአንድ ጊዜ በቀላሉ ለመግደል የሚያስችሉ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች ባለመኖራቸው ምክንያት በግብጽ እና በሦርያ የነበሩ ክርስቲያኖች የሚገድሏቸው ወታደሮች እጃቸው ከመግደል እየደከመና ሠይፋቸው በደም እየታለለ እነርሱም እስኪያርፉና መሣሪያቸውን እስኪወለውሉ ድረስ ክርስቲያኖች በሰማዕትነት ለመገደል ለብዙ ቀናት ወረፋዎችን ይጠብቁ ነበር ይሏል፡፡

መንገድ ላይ እንደ ወደቀውና በድንጋይ ላይ እንደ በቀለው ዘር የጊዜውን መከራ ፈርተውና የዚህን ዓለም ሕይወት ወድደው ክርስቶስን የካዱ ቢኖሩም ብዙዎቹ ክርስቲያኖች ግን በየጊዜው የሚሆነውን መከራ በጽናት ተቀብለው ለሃይማኖታቸው ለክርስቶስ መስክረዋል፡፡ ሲኖሩም ኑሯቸው ሁሉ የሰማዕትነት ሞትን በመጠበቅ ነበር፡፡ ክርስቲያኖችን ከማሳደድ የተመለሰውና ታላቅ ሐዋርያ የሆነው ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲናገር እንዲህ ያለው ለዚህ ነው፡-

ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼያለሁ። ሮሜ 8፡36-39

እግዚአብሔርም ምእመናን መከራውን በጽናት እንዲቀበሉ በቅዱስ ቃሉ፣ አጽናኝና አበረታች መላእክትን በመላክና በተለያዩ መንገዶች ሥቃዩን ያሥታግሣቸውና ያበረታቸው ነበር፡፡ ለአብነትም በሮማውያን ቄሣሮች በእነ ኔሮንና ድምጥያኖስ ዘመን ይደርስ የነበረውን መከራ በራእየ ዮሐንስ ላይ በታናሽ እስያ የነበሩትን የቤተ ክርስቲያን አባቶች እንዲህ በማለት ያበረታታቸው ነበር፡-

በሰምርኔስም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። ሞቶ የነበረው ሕያውም የሆነው ፊተኛውና መጨረሻው እንዲህ ይላል። . . . ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ። እነሆ፥ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወኅኒ ሊያገባችሁ አለው፥ አሥር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ። እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን፣ የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል የነሣው በሁለተኛው ሞት አይጐዳም። ራ. 2፡8-11

ስለ ክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ወንዶች ብቻ ሳይሆኑ ሴቶችም መከራውን በጽናት ይቀበሉ ነበር፡፡ አንዲት ነፍሰ ጡር የነበረች እናት ሃይማኖቷ ክርስቲያን በመሆኑ ምክንያት ብቻ ታስራ ሳለ በሮማውያን ሕግ ነፍሰ ጡሮች አይገደሉ ስለ ነበር ምነው በውስጤ ያለው ጽንስ ቶሎ ተወልዶልኝ ለሃይማኖቴ መስክሬ በሞትኩ ብላ ጸለየች፡፡ ልትወልድ ስትል ምጡ ሲያስጨንቃት ከጠባቂዎቹ ወታደሮች መካከል አንዱ ባያት ጊዜ ምነው ቶሎ ብዬ ለክርስቶስ መስክሬ በሞትኩ ስትይ አልነበር? ተፈጥሯዊ የሆነው ምጥ ይህን ያህል ካስጨነቀሽ ከእኛ እጅ የምትቀበዪውን መከራማ እንዴት አድርገሽ ትችይዋለሽ? አላት፡፡ እርሷም ይህን (ምጡን) የምቀበለው ብቻዬን ነው፤ ስለ ክርስቶስ የምቀበለውን መከራ ግን የምቀበለው ብቻዬን ሳይሆን ከክርስቶስ ጋር ነው፣ እንዲያውም መከራውን የሚቀበለው ራሱ ነው አለችው፡፡ አዎ፣ ስለ ክርስቶስ ያልተከፈለ ዋጋ የለም፤ ለእርሱ የማይከፈል ውድ ዋጋም የለም!

አሁንም ክፉዎች የመዳንን መንገድና እውነትን አንቀበልም ማለታቸው ሳያንስ ሌሎችንም እንደ እኛ ካልሆናችሁ በማለት ለማስገደድና የራሳቸውን አስተሳሰብና እምነት በሌሎች ላይ በኃይል ለመጫን ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ታጥቀው ክርስቶስን አንክድም የሚሉ ክርስቲያኖችን አንገታቸውን እንደ ከብት አጋድመው በሠይፍ እያረዱ ይገኛሉ፡፡ ራሱን እስላማዊ መንግሥት – Islamic State (IS) ብሎ የሚጠራው ቡድን ከወር በፊት 21 ግብጻውያን ክርስቲያን ወንድሞቻችንን ክርስቶስን አንክድም በማለታቸው ብቻ አንገታቸውን አርደው ገድለዋቸዋል፡፡ በሶሪያና በኢራቅ በየጊዜው ብዙ ክርስቲያኖች በሃይማኖታቸው ምክንያት ብቻ ይገደላሉ፣ ይሠቃያሉ፤ የቀሩትም ሀገር ለቀው ይሄዳሉ፡፡

ሰሞኑንም ይኸው ራሱን እስላማዊ መንግሥት – Islamic State (IS) ብሎ በሚጠራው ቡድን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ታምነው የክርስትና ሃይማኖታቸውን አንክድም በማለታቸው ምክንያት የተወሰኑት በጥይት ተደብድበው፣ ሌሎቹ ደግሞ በአሰቃቂ ሁኔታ በሠይፍ ታርደው የተገደሉትን ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችንን ስናስብ መከራቸውና ስቃያቸው ይሰማናል፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ ለእመ አሐዱ አካል ሐመ የሐምም ምስሌሁ ኩሉ ነፍስትነ – አንድም አካል ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ እንደሚለው የእነርሱ ጭንቀትና ስቃይ የእኛም ጭንቀትና ስቃይ ነውና። 1 ቆሮ. 12፡26-27 እነርሱስ አንድ ጊዜ ተቀብለውት ሄደዋል፣ ለእኛ ግን በየጊዜው የማይረሳና ባስታወሱት ቁጥር ውስጥን የሚያደማ የማይሽር የሕሊና ቁስል ነው፡፡ እነዚህ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች የተቀበሉት መከራና ግፍ የሁላችንም መከራና ግፍ ነው፡፡ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ የሚቀበሉት መከራና የሚጋደሉት ተጋድሎ የቤተ ክርስቲያን ራስ የሆነው የክርስቶስ የመከራው አካል ነው፡፡ ጌታችን የኋላውን ቅዱስ ጳውሎስ የቀደመውን ሳውል በሚያስደንቅ ሁኔታ ሲጠራው ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ? አለው፡፡ እርሱም ጌታ ሆይ ማን ነህ? ባለው ጊዜ አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ ያለው ይህን የሚገልጽ ነው፡፡ የሐዋ. 9፡3-5 ጌታችን የክርስቲያኖችን ስደትና መከራ የራሱ አድርጎ ለምን ታሳድደኛለህ? አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ አለው እንጂ ለምን ታሳድዳቸዋለህ? አላለውም፡፡ ስለሆነም እነዚህ ወንድሞቻችን ስለ ሃይማኖታቸው የተጋደሉት ተጋድሎና የተቀበሉት መከራ የክርስቶስ የመከራው አካል ነው፤ የሰውነት የአካል ክፍሎች የሚሠሩት ሥራ የራስ ሥራ አካል ነውና፡፡

ይህ የወንድሞቻችን መከራና የግፍ ሞት ሁለት ገጽታ ያለው ነው፡፡ በአንድ በኩል የገዳዮቻቸውን ጭካኔና አረመኔነት ስንመለከተውና የወንድሞቻችንን ስቃይ ስናስበው በእጅጉ ይዘገንናል፤ ማንኛውንም ሰው የሆነን ሁሉ ይነካል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የመዳን መንገድ ስለ ሆነችው ስለ ክርስትና እምነታቸው ሲሉ በእግዚአብሔር ኃይል ጨክነው ለክርስቶስ መስክረው መሞታቸውንና እስከ መጨረሻው ድረስ መጽናታቸውን ስናስበው ደግሞ ልዩ የሆነ ደስታ ይፈጥራል፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከጥቂት ቀናት በፊት በግብጽ 21 ክርስቲያኖች እምነታቸውን እንደ መሰከሩ ሁሉ አሁን ደግሞ ከኢትዮጵያ 30 እውነተኛ መስካሪዎችን አገኘች፡፡ እነዚህ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፍሬዎች ናቸውና! እንኳን ወላጆቻቸውንና ከዚህ ሞታቸው አስቀድሞ ያውቋቸው የነበሩት ሰዎች ይቅርና አገዳደላቸውን የሚያሳየውንና አይ ኤስ የለቀቀውን ምስል ወድምፅ የተመለከተን ማንኛውንም ሰው በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ ወንድሞቻችን በቅድስት ሥላሴ ስላላቸው እምነት፣ ስለ ክርስቶስ አምላክነትና መድኃኒትነት፣ በአጠቃላይ ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ስለ ሆነችውና ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ስለ ተሰጠችው አንዲት ሃይማኖት መስክረው መሞታቸው እያሳዘነ የሚያስደስት፣ እያስለቀሰ እልል የሚያሰኝ ነው፡፡ በቀድሞ ዘመን ክርስቲያኖች ለሃይማኖታቸው መስክረው ወደሚገደሉባቸው ቦታዎች ሲወሰዱ እናቶችና አባቶች ልጆቻቸውን፣ ሚስቶች ባሎቻቸውን፣ ወዳጅም ወዳጁን አይዞህ፣ በርታ፣ ጽና፣ ምስክርነትህን ፈጽም፣ የምትሄደው ወደ ክርስቶስ ነው እያሉ አንዱ ሌላውን ያበረታታ ነበር፡፡ ስለዚህ የእነዚህ ወንድሞቻችን ቤተሰቦች ሰው እንደ መሆናቸው ማዘን ባይቀርም የእነዚህ እውነተኛ ክርስቲያን ወላጆች ቤተሰቦች በመሆናቸው ሊደሰቱና እግዚአብሔርን ሊያመሰግኑ ይገባቸዋል፡፡ ይህ ለሁሉ የሚገኝ
ጸጋና ክብር አይደለምና!

መከራው የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን ጎዳት? ወይስ ጠቀማት?

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዘመነ ሰማዕታት በገጠማት በዚያ ሁሉ መከራ እየደከመች ሄደች ወይስ እየጠነከረች? የምእመናን ቁጥርስ እያነሰ ሄደ ወይስ እየበዛ? ታሪክ እንደሚያስረዳን በክርስቶስ በሞቱና በትንሣኤው የተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመከራው እየበዛችና እየጠነከረች ሄደች እንጂ ጠላቶቿ እንዳሰቡት እየደከመችና እየጠፋች አልሄደችም፡፡ ይልቁንም አሳዶጆቿና ገዳዮቿ የነበሩት ቄሣሮች እነ ኔሮን፣ እነ ድምጥያኖስ፣ እነ ትራጃን፣ እነ ዳክዮስ፣ እነ ቫሌንቲኖስ፣ እነ ጋሌሪዮስ፣ እነ መክስምያኖስ፣ እነ ድዮቅልጥያኖስ፣ እነ ሉቅያኖስና መሰሎቻቸው ሞተው የት እንደ ወደቁ መቃብራቸው እንኳ የማይታወቅ ሲሆን እነርሱ የገደሏቸውና ያሰቃዩዋቸው ክርስቲያኖች ግን ስማቸው በዓለም ይታወቃል፣ መቃብራቸውንና ዐጽማቸው ያረፉባቸውን ቤተ ክርስቲያኖች ምእመናን በታላቅ ክብርና ፍቅር ይሰለሟቸዋል፡፡ ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎችንም ያልተጠቀሱትን ገዳዮቻቸውን ግን በመልካም እንኳ የሚያነሳቸው የለም፣ በግፍ የሞቱትን ቅዱሳን ክርስቲያኖች ግን የክርስቲያኑ ዓለም ብቻ ሳይሆን ቅን ሕሊና ያለው ሰው ሁሉ የሚያከብራቸው ናቸው፡፡

ክርስትና በዓለም የተስፋፋው በአፍና በመጽሐፍ በሚደረገው ስብከት ብቻ አልነበረም፤ ክርስቲያኖች ለክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ዓይናቸው እያየ ሞትን ሲንቁትና ፊት ለፊት ሲጋፈጡት በማየትም ነበር እንጂ፡፡ እንደ ሌላው ሰው ሁሉ ሰውነታቸው ሕማምና መከራ የሚሰማውና ስቃይን የማይወድ፣ ለአካላቸው መለዋወጫ፣ ለሕይወታቸውም ምትክ የሌላቸው ሲሆን እንዲህ ሞትን የሚንቁትና ደስ እያላቸው የሚሞቱት በትምህርታቸው እንደሚሉት አምላካቸው በእውነት ሞትን በትንሣኤው ድል ያደረገው በመሆኑና ከዚህ ዓለም ሕይወት በኋላ እርግጠኛ የሆነ ሌላ ሕይወት ቢኖር ነው እያሉ አሕዛብ ከክርስቲያኖች የምስክርነት ዐውድ ሕያው ወንጌልን ይማሩ ነበር፡፡ ከዚህ የተነሣ ክርስቲያኖቹን እንዲገድሉ ከተመደቡት ወታደሮች መካከል እንኳ ሳይቀር በክርስቲያኖች ጽናትና በስቃያቸው ጊዜ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ከሚሠራቸው የተለያዩ ገቢረ ተአምራት የተነሣ እኔም በእነዚህ ሰዎች አምላክ አምኛለሁ እያሉ በደማቸው እየተጠመቁ ሰማዕታት የሆኑ ብዙዎች አሉ፡፡

ለአብነትም በአርብኣ ሐራ ሰማዕታት የተፈጸመውን ብቻ እናስታውስ፡፡ የሮማ የምሥራቁ ክፍለ ግዛት ገዢ በነበረው በሉቅያኖስ ባለ ሥልጣናት ለጣዖታት መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ሲታዘዙ እምቢ በማለታቸው በከተማው ውስጥ በነበረ አንድ በረዷማ የውኃ ኩሬ ላይ የጣሏቸው አርባ ክርስቲያን ወታደሮች ነበሩ፡፡ ከዚያ ከተጣሉበት በረዷማ ኩሬ ፊት ለፊት ደግሞ ለመታጠቢያነት ተስማሚና ምቹ የሆነ የፍል ውኃ መታጠቢያ ነበር፡፡ ከአርባው መካከል አንደኛው ከቅዝቃዜው ጽናት የተነሣ አውጡኝ አለና ወዲያውኑ እየሮጠ በሙቅ ውኃው መታጠቢያ ለመታጠብ ሄደ፡፡ ወዲያውኑ እንደ ገባም ሰውነቱ ብስክስክ ብሎ ሞተ፡፡ የእነዚያን ተጋዳይ ወታደሮች ሥቃያቸውን ሲከታተሉ ከነበሩት አስፈጻሚ ወታደሮች መካከል አንደኛው ራሱን በፍል ውኃው እያሞቀ ይህን እንግዳ ነገር እየተመለከተ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜም መላእክት ከሰማያት ወርደው ለአርባው ተጋዳዮች አክሊል ሲያቀዳጇቸው የአንደኛው አክሊል ግን ተንጠልጥሎ በአየር ላይ ሲቀር ተመለከተ፡፡ ያን ጊዜ ያ ወታደር በወጣው ሰው ቦታ ገብቶ በክርስቶስ ታምኖ ወዲያውኑ የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለ፡፡ (ቅዱስ ባስልዮስ፣ ስለ አርብኣ ሐራ ሰማዕታት፣ ትምህርት፣ ትምህርት 19)

በተለይም ደግሞ በጣም ብዙ ክርስቲያኖችን በመግደልና በማሰቃየት ወደር ያልነበረውን አርያኖስ የተባለውን የግብጽ ገዢ ፍጻሜ ማስታወሱ ለዚህ ሕያው ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ አርያኖስ በሮማ ግዛት ውስጥ ክርስቲያኖችን በማሰቃየትና በእነርሱ ላይ ይፈጽም በነበረው በጭካኔው ወደር የለሽ ነበር፡፡ አንድ ቀንም የእርሱ አጫዋች (አዝማሪ) የነበረው ፈልሞን በፊቱ ቆሞ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምን ክርስቲያን መሆኑ መሰከረ፡፡ ያን ጊዜ አርያኖስ ፊልሞንን እና አብላዮስ የተባለውን ጓደኛውን በፍላጻ እንዲነድፏቸው አዘዘ፡፡ አንዲት ፍላጻም ወደ አርያኖስ ተመልሳ ዓይኑን አወጣችው፣ የፍላጻው ሕማምም እጅግ አሠቃየው፡፡ በጣም እየተሠቃየ ሳለ ከክርስቲያኖቹ አንዱ ከሰማዕታቱ ደም ወስደህ ብትቀባው ትድን ነበር አለው፡፡ እርሱም ይህን ያህል እየጠላኋቸውና እያሰቃየኋቸው ይምሩኛልን? ቢላቸው አዎ፣ በክርስትና ጠላትን መውደድና ለጠላት መጸለይ እንጂ መበቀል የለም አሉት፡፡ እንደ ነገሩት ከሰማዕታቱ ደም ወስዶ ቁስሉን ሲቀባው ወዲያውኑ ተፈወሰ፡፡ ከዚያ በኋላ እርሱም በክርስቲያኖች አምላክ አምኖ ጣዖታቱን ሰባብሮ ክርስቲያኖችን ምሕረት የሌለው ሥቃይ ስላሠቃያቸው ታላቅ ጸጸት ተጸጸተ፡፡ ከዚያም ስለ ክርስቶስ መስክሮ በሌላ ገዢ ተገድሎ ሰማዕትነትን ተቀበለ፡፡ (ስንክሳር መጋት 7 እና 8)

ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ ሞትን ድል ማድረጉና የሞትን ኃይልና አስፈሪነት ማጥፋቱ ለሰዎች ከተገለጠበትና ለዓለምም ከሚገለጥበት አንደኛው መንገድ ይህ የክርስቶስ አካላትና ተከታዮች (ክርስቲያኖች) መከራንና ሞትን በጽናት መቀበላቸው፣ ሞትን መናቃቸውና ፊት ለፊት መጋፈጣቸው ነው፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ የማያምኑ ወይም ስለሚመጣው ሕይወት በሃይማኖታቸው ቁርጠኛ ያልሆኑ ሰዎች እንደ ጦር የሚፈሩትን ሞት፣ እንዲሁም ሌት ተቀን የሚጨነቁለትን የዚህን ዓለም ሕይወት በክርስቶስ ትንሣኤ ያመኑ ክርስቲያን ሰማዕታት ሲንቁትና ፊት ለፊት ሳይፈሩ ስለ ክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ሲጋፈጡት ሲያዩ ብዙዎች ከሞት በላይና ባሻገር ስላለው ሕይወትና እውነት በሰማዕታት ጽናትና ብርታት አማካይነት ተምረዋል፡፡ ከአሕዛብ ወገን፣ ሰማዕታቱን ይገድሉና ያሠቃዩ ከነበሩት ከወታደሮችም ሳይቀር በዚሁ ተስበው ለሰማዕትነት የበቁት በጣም ብዙዎች ናቸው፡፡

እንደዚሁም ደግሞ ክርስቶስ ሞትን ድል ባያደርገው ኖሮ ሰማዕታትም ሞትን መጋፈጥና መናቅ ባልቻሉ ነበር፡፡ የእነርሱ ተጋድሏቸው፣ መከራቸውና ድል አድራጊነታቸው የመስቀሉ ድል፣ የትንሣኤው ኃይል ቀጣይ አካልና ሕያው ምስክር ነው፡፡ የእነርሱ ጽናትና ተጋድሎ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ያደረገው መሆኑን በተግባር የሚመሰክሩ ምስክሮች ናቸው፤ ምስክሮችህ ድንቆች ናቸው፣ ስለዚህም ነፍሴ ፈለገቻቸው እንደ ተባለ፡፡ ቅዱሳን ሰማዕታት ሰማዕታት – ምስክሮች፣ መስካሪዎች የተባሉትም ለዚህ ነው፡፡ መዝ. 118፡129

ስለሆነም መከራ መስቀል ክርስትና የተመሠረተበት፣ ያደገበትና የኖረበት ሕይወት እንጂ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ክርስትናን የሚያዳክመው መከራ ሳይሆን ምንነቱን አለመረዳትና ቁሳውይነት፣ ቅምጥልነትና ሥጋውይነት ናቸው፡፡ ሰማዕትነትማ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሞትን ያህል ከባድ ነገር ስለ ክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ሞትን ባሸነፈው በትንሣኤው ኃይል የናቁትንና ለብዙዎች ኢአማንያን በክርስቶስ ማመንና ሰማዕት እስከ መሆን መድረስ ምክንያት የሆኑ ብዙ መንፈሳዊ ጀግኖችን ያፈራችበት ነው፡፡ ለዚህ ነው በሁለተኛው መቶ ዓመት ማብቂያና በሦስተኛው መቶ ዓመት መጀመሪያ ላይ የነበረው የክርስትና መብት ተሟጋቾችና ጠበቆች መካከል አንዱ የሆነው የሰሜን አፍሪካው የቅርጣግናው ሊቅ ጠርጠሉስ ስለ ክርስትና እምነት ንጹሕነትና እውነተኛነት ለአሳዳጆችና ለመከራ ዳራጊዎች በጻፈው የጥብቅና መጽሐፍ ላይ እንዲህ ሲል የገለጸው፡-

“አሠቃዩን፣ ግደሉን፣ ንቀፉን፣ ኰንኑን፣ አቃጥሉን፣፤ የእናንተ ክፋት፣ ግፍና ጭካኔ የእኛ ንጽሕና ማረጋገጫ ነው፡፡ እናንተ በወገራችሁንና በቆረጣችሁን መጠን ቁጥራችን እልፍ እየሆነ ይሄዳል፤ ደመ ሰማዕታት የክርስቲያኖች ዘር ነው፡፡ – Torture us, condemn us, crucify us, destroy us! Your wickedness is the proof of our innocence. . . . The more we are hewn down by you, the more numerous do we become. The blood of the martyrs is the seed of the Church. Apologeticus, Chapter 50)

አዎ፣ ምንም ያልበደሏቸውንና አንዳችም መከላከያ የሌላቸውን ወንድሞቻችንን በክርስትና ሃይማኖታቸው ምክንያት ብቻ በግፍ መግደላቸው ሁለት እውነታዎችን ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ ከእነዚህም አንደኛው እውነተኛ ክርስቲያኖች ለክርስቶስ ያላቸውን ፍቅርና ጽናት፣ እንዲሁም እውነተኛነት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የገዳዮቹ እምነታቸው ከመሠረቱ ስህተትና ውሸት መሆኑን ነው፡፡ ምክንያቱም እውነትን የያዘ ሰው ያ አምነዋለሁ የሚለውን እውነት በማስረዳት ማሳመን ይገባዋል እንጂ እውነትን በግድ መጫን አይቻልም፡፡ ስለሆነም ገዳዮቹ እምነታቸውና አስተሳሰባቸው ሌላውን ሰው ሊያሳምን የማይችል ደካማና ሐሰት ስለሆነ በኃይልና በመሣሪያ ኃይል ካልሀነ በስተቀር የሰውን አእምሮ ማሳመን የማይችል መሆኑን ራሳቸው ቀርጸው ያሠራጩት ምስልና ድምፅ ይመሰክርባቸዋል፡፡ በዚህም በአንድ በኩል እግዚአብሔርን አምነውና መስክረው የሞቱትን የወንድሞቻችንን አሟሟትና ማንነት እንድናውቅ ስላደረጉን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የራሳቸውን የገዳዮቹን የእምነት አስተሳሰብ ባዶነትና ሐሰትነቱ ከጥንትም የታወቀ ቢሆንም አሁን ደግሞ ከራሳቸው ንግግርና ድርጊት እንዲጋለጥ ያደረገውን ምስል ወድምፅ በማሠራጨታቸው እናመሰግናቸዋለን፡፡ እንደ ገደሏቸው ሳይነግሩን የሆነ ቦታ ጥለዋቸው ብቻ ቢሆን ኖሮ ዓለም ይህን ሁሉ ትምህርት ከየት ያገኝ ነበር?

በመጀመሪያው መቶ ዓመት ማብቂያ ገደማ በተፈጸመው የክርስቲያኖች ጭፍጨፋ ስለ ክርስቶስ መስክረው የሞቱ ቅዱሳን ሰማዕታት ነፍሳቸው እንዲህ ብላ ወደ እግዚአብሔር ፍትሕን ጠይቃ ነበር፡- “አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ። በታላቅ ድምፅም እየጮኹ፡- ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፣ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም? ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ።” በዚህ ጊዜ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጣቸው መልስ “እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪፈጸም ድረስ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው” የሚል ነበር። ራእ. 6፡9-11 እስከዚያው ድረስ ግን “ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፡፡”

እግዚአብሔር ክርስቲያኖችን በግፍ በገደሏቸው ላይ ፍርድን በቶሎ ያልሰጠበት ዋና ምክንያት እንደ እነዚያ ያሉና ስለ ክርስቶስ መስክረው የሚሞቱ በየዘመኑ የሚነሡ ሰማዕታት መኖራቸውን እርሱ በአምላክነቱ ስለሚያውቅ ይህ የሰማዕትነት ዕድል እንዳይቀርባቸው ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን በየጊዜው ለክርስቶስ እየመሠከሩ የሚሞቱ አሉና እርሱ የሚያውቃቸው እነዚያ ሰዎች ለዚህ ክብር ሳይበቁ እንዳይቀሩ የፍርድ ጊዜውን እርሱ ባወቀ አቆይቶታል፡፡ ግፍ ፈጻሚዎችን ቀድሞ በአንደኛው መቶ ዓመት ላይ አጥፍቷቸው ቢሆን ኖሮ ከዚያ በኋላ እስከ ዛሬ ድረስ፣ ወደፊትም እንዲሁ እርሱ የሚያውቃቸው ሰማዕታት ይህን የሰማዕትነት አክሊል አያገኙም ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያንም እነዚህን የመሰሉ ጌጦቿን አታገኝም ነበር፡፡ ሰማዕታት የቤተ ክርስቲያን ጌጦች ናቸውና፤ በከመ ከዋክብት ያሠረግውዎ ለሰማይ በሥኖሙ ከማሁ ሰማዕትኒ ያሠረግውዋ ለቤተ ክርስቲያን በገድሎሙ – ከዋክብት ሰማይን በውበታቸው እንደሚያስውቡት ሰማዕታትም በገድላቸው ቤተ ክርስቲያንን ያስጌጧታል እንዳለ ቅዱስ ያሬድ፡፡ (ጾመ ድጓ ዘቴዎቅሪጦስ)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰማዕትነትን መቀበል ሕይወቷ ነው፡፡ በዮዲት ጉዲት ዘመን፣ በግራኝ አህመድ ዘመን፣ በሱስንዮስ ዘመን ቁጥራቸውን እግዚአብሔር ብቻ የሚያውቃቸው ብዙ ክርስቲያኖች በሰማዕትነት መስክረው ዐርፈዋል፡፡ በሙሶለኒ ፋሽስት ወረራ ዘመንም እንዲሁ የደብረ ሊባኖስ፣ የዝቋላ፣ የማኅበረ ሥላሴ፣ እንዲሁም የሌሎች የብዙ ገዳማት መነኰሳትና ባሕታውያን ስለ ሃይማኖታቸው በግፍ ተጨፍጨው በሰማዕትነት ሞተዋል፡፡ ገዳማቱ ግን አሁንም አሉ፣ መነኰሳትና ባሕታውያንም፣ ምአመናንም እንዲሁ አሉ፡፡ ክፉ ያደረጉት ተጎዱ እንጂ ክፉው የደረሰባቸውን አልጎዷቸውም፡፡ እውነተኛ ጉዳት ማለት በጊዜው ጊዜ አይቀር የነበረውን የሥጋ ሞት በሰው እጅ መቀበል ሳይሆን መልካም ሊሠሩበት በተሰጣቸው ጊዜና አእምሮ በሰዎች ላይ ግፍና ጭካኔ ፈጽሞ ከእግዚአብሔር መለየትና ሊቀር ይችል የነበረውን ሞተ ነፍስ በፈቃድ በራስ ላይ ማምጣት ነውና፡፡

ስለሆነም እንዲህ ለሚያደርጉ ክፉዎች ሰዎች ልናዝንላቸውና ልንጸልይላቸው ይገባል፡፡ ጌታችን እንዲህ ብሎ አስተምሮናልና፡

ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ የሚረግሟችሁንም መርቁ፣ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ፣ ስለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፣ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና። የሚወዷችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ።ማቴ. 5፡43-48

አዎ፣ ክርስትና የሚጠሉንን የምንጠላበትና ክፉ ያደረጉብንን በዚያው በክፋት መንገድ አጸፋ የምንመልስበት ሳይሆን ስለ ክፉ አድራጊዎቹ ጥፋት ከልብ የምናዝንበትና የጥፋታቸውን ምንነት ተረድተው ወደ አእምሯቸው ይመለሱ ዘንድ እግዚአብሔርን የምንለምንበት ሕይወት ነው፡፡ ክርስትና ድንጋይ ለወረወረብን መልሰን የምንወረውርበት፣ ጉድጓድ በማሰብን ላይ ሌላ ጉድጓድ የምንቆፍርበት አይደለም፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰቀሉትና ያ አልበቃቸው ብሎ ተጠማሁ ባለ ጊዜ እንኳ መራራ ሐሞትን በአፉ ላደረጉለት ለክፉዎች አይሁድ እንኳ አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን አያውቁም ይቅር በላቸው ብሎ እንደ ጸለየላቸው እኛም ለክፉ አድራጊዎችና ለጠላቶቻችን የምንጸልይበት ሕይወት ነው፡፡ አለዘበለዚያ የእርሱ ደቀ መዛሙርት ልንሆን አንችልም፡፡ ክፉዎች ክፉ በመሆናቸው በእነርሱ ክፋት ተገፋፍቶ ወይም እልክ ውስጥ ገብቶ እነርሱ በሄዱበት የክፋት መንገድ መሄድ ገና ከጅምሩ መሸነፍና ድል መነሣት ነውና፡፡ ምክንያቱም የክፉ ሰው ድርጊቱና ዓላማው ሌላውንም እንደ እርሱ ክፉ ማድረግና ወደ እርሱ የክፋት አስተሳሰብና ድርጊት እንዲሳብ ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ የእኛ አስተሳሰብና ድርጊት እንደ ክፉዎቹ ሰዎች አስተሳሰብና ድርጊት ከሆነ ብርሃን ወደ ጨለማ፣ ጨው ወደ አልጫ ተለወጠ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ገና ሲጀመር መሸነፍ ነው፤ ክፉው መልካሙን አጠፋው ማለት ነውና፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ መጽሐፍ ክፉውን በመልካም አሸንፉ እንጂ በክፉ አትሸነፉሲል በአጽንዖት የሚያስጠነቅቀን፡፡ ሮሜ 12፡21 በክፉ መሸነፍ ማለት ወደ ክፋ መሳብና ክፉዎቹ እንደሚያደርጉት ለማድረግ መነሣት ነው፡፡ ስለዚህም ነው ክፉውን በመልካም አሸንፉ እንጂ ካለ በኋላ ቀጥሎ በክፉ አትሸነፉ አለ እንጂ “በክፉ አታሸንፉ” አላለም፡፡ ምክንያቱም ክፉን በመልካም ብቻ እንጂ በክፉ
ማሸነፍ አይቻልምና፡፡ ክፉ መሆን ከጀመረ ግን በክፉ ተሸንፏል ማለት ነው፡፡ ሰው በክፉዎች ምክንያት እርሱም የሚከፋ ከሆነ ከጅምሩ ተሸንፏል ማለት ነውና፡፡ ፡፡

ሰማዕቱ ቅዱስ እስጢፋኖስ የድንጋይ ናዳ ሲያወርዱበት ለነበሩት አይሁድ ጌታ ሆይ፣ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ብሎ ጸለየላቸው እንጂ አጥፋቸው አላለም፡፡ ይህ የቅዱስ እስጢፋኖስም ጸሎት እንዲሁ በከንቱ አልቀረም፡፡ እርሱን ሲወግሩ የነበሩትን ሰዎች ሲያስተባብርና ልብሳቸውን ሲጠብቅ የነበረው ሳውል የተባለው ኃይለኛ ጸረ ክርስቲያን ወጣት (የኋላው ቅዱስ ጳውሎስ) የእግዚአብሔር ቸርነት ልቡን እንዲነካውና ወደ ክርስትና እንዲመለስ ታላቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ይህንንም አንድ ሊቅ የቅዱስ እስጢፋኖስ ጸሎት ለቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ጳውሎስን አስገኘላት ብሏል፡፡ በየዘመናቱ የነበሩ ክርስቲያኖች ሁሉ መከራ በሚያደርሱባቸው ላይ እንዲሁ ስህተታቸውን የሚገነዘብ ልቡና እንዲሰጣቸውና ወደ እውነት እንዲመለሱ ጸለዩላቸው እንጂ በክፉው መንገድ እንበቀላቸው ብለው አልተነሡም፡፡ በዘመነ ዲዮቅልጥያኖስ ታላላቅ የቤተ መንግሥት ተወላጆችና መኳንንት ከነበሩት ወገን ሰማዕትነትን የተቀበሉት እነ ቅዱስ ቴዎድሮስ፣ ቅዱስ ፋሲለደስ፣ ቅዱስ ዮስጦስ፣ ቅዱስ አቦሊ፣ ቅዱስ ፊቅጦር . . . በጦር ሜዳ ጀግንነታቸውና አርበኝነታቸው የታወቁ ኃያላን ነበሩ፡፡ ዲዮቅልጥያኖስ ክርስቲያኖችን ማሰቃየት ሲጀምር በመጀመሪያ ያደረጉት ነገር ትጥቃቸውን መፍታትና ስለ ክርስቶስ መክራ ለመቀበል በመዘጋጀት ወደ ፊቱ ቀርበው ሃይማኖታቸውን መመስከር ነበር፡፡ የእነርሱ ታማኝ ሠራዊትና ወዳጆች ከነበሩት ብዙዎች ስለ እነርሱ በመቆጨትና በመቆርቆር ዲዮቅልጥያኖስን ወግተን እናጥፋውና እናንተ ግዙን ሲሏቸው አልተቀበሏቸውም፡፡ እነዚህ ሰማዕታት መጀመሪያ ያደረጉት ነገር በዘመኑ የነበራቸውን አርበኝነት፣ ኃያልነት፣ የወገንና የሠራዊት ድጋፍ ሁሉ ትተው ስለ ክርስቶስ መስክሮ ለመሞት ብቻቸውን መቅረብ ነበር፡፡ ክርስትና በሠይፍ የተመሠረተና ለመስፋፋትም ሠይፍ የሚያስፈል
ገው አይደለምና፡፡ ሠይፍን የሚያነሱማ እነርሱው ራሳቸው በሠይፍ እንደሚጠፉ ባለቤቱ አስቀድሞ ነግሮናል፡፡ ማቴ. 26፡52 ታሪክም ይህንኑ እውነታ ያስተምረናል፡፡

ክርስትና በዚህ ዓለም የድሎትና የቅንጦት ኑሮ የሚመኙበትና የሚኖሩበት ሳይሆን ክርስቶስ በዚህ ዓለም የመስቀል ሞት ስለ እኛ በፈቃዱ እንደ ተቀበለና እንደ ተነሣ ክርስቲያኖችም በዚህ ዓለም የሚደርስባቸውን መከራ በትዕግሥት በጥብዐት በመቀበል በትንሣኤው ኃይል ድል የሚያደርጉበት ነው፡፡ ቅምጥሊቱ ግን በሕይወትዋ ሳለች የሞተች ናት ተብሏልና፡፡ 1 ጢሞ. 5፡6

እነዚህን ወንድሞቻችንን ወደ እግዚአብሔር ፈጥነው እንዲሄዱ አደረጓቸው እንጂ አልጎዷቸውም፡፡ ነፍሳቸውን ከሥጋቸው ለዩዋት እንጂ አልገደሏትም፤ ነፍስን ለመግደል ማንም አይችልምና፡፡ ይህ የሥጋና የነፍስ መለያየት (ሞተ ሥጋ) ደግሞ በሕማምም ሆነ በዕድሜ ብዛት መምጣቱ የማይቀር ነው፡፡ ከዚያ ቀድመው ለክርስቶስ መስክረው ወደ አምላካቸውና መድኃኒታቸው እንዲሄዱ አደረጓቸው እንጂ አንዳችም አልጎዷቸውም፡፡ ራሱ ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስ በማይታበል ቃሉ እንዲህ ብሏልና፡- ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም። ዮሐ. 11፡25-26 ለክርስቶስ መስክሮ መሞት ደግሞ ለአንድ ክርስቲያን እጅግ ታላቅ ጸጋና መታደል ነው፤ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ ተብሏልና፡፡ ማቴ. 10፡32

ቅድስናን (ሰማዕትነትን) እውቅና መስጠትን በተመለከተ

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን የሆኑትን ቅዱሳን ናቸው ስትል ቅድስናቸውን እውቅና የመስጠት ጉዳይ እንጂ ቅዱሳን የማድረግ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህም ማለት እነዚያን ሰዎች ቅዱሳን የሚያደርጋቸው እግዚአብሔር ባሳየው የሕይወት መንገድ መጓዛቸውና እርሱን ደስ ያሰኙ መሆናቸው እንጂ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን ናቸው ብላ በምትሰጠው ውሳኔ አይደለም ማለት ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ቅድስናቸውን የማወቅ ውሳኔ የሚመጣው ከሰዎቹ ቅድስና እንጂ የሰዎቹ ቅድስና ከቤተ ክርስቲያን ውሳኔ የሚመጣ አይደለም ለማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚያውቃቸው የቤተ ክርስቲያን አካላት የሆኑ ቅዱሳን ሁሉ በዚህ ዓለም ያለው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ሁሉንም ሊያውቃቸው መቸም መች አይችልም፡፡ ምክንያቱም በየበረሓው ወድቀው ከእኩያት ፍትወታትና ከክፉ መናፍስት ጋር ተጋድለው እግዚአብሔርን አገልግለው ያለፉና እንኳን ቅድስናቸው መኖራቸው እንኳ ከእግዚአብሔር በቀር በሰዎች ያልታወቀ ብዙ ቅዱሳን ነበሩና፣ ዛሬም ይኖራሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ወበኀቤዬሰ ፈድፋደ ክቡራን አዕርክቲከ እግዚኦ ወፈድፋደ ጸንዑ እምቀደምቶሙ እኄልቆሙ እምኆጻ ይበዝኁ – አቤቱ ወዳጆችህ በእኔ ዘንድ እጅግ ብዙዎች ናቸው፣ ብቆጥራቸውም ከአሸዋ ይልቅ በዙ የሚለው ለዚህ ነው፡፡ መዝ. 138፡17-18

እንደዚሁም በዚህ ዓለም ሲኖሩ ኃጢአተኞች መስለው፣ እብድ መስለው፣ የውሻ አስከሬን እስከ መጎተትና አመንዝራ እስከ መምሰል ደርሰው፣ ሰው እንኳን ቅድስናቸውን ሊያውቀው ይቅርና ጥሩ ሰዎች እንኳ አድርጐ የማይመለከታቸው ብዙ ቅዱሳን እንደ ነበሩ ዜና አበውና መጽሐፈ ገነት፣ እንዲሁም ስንክሳርና የተለያዩ የቤተ ክርስቲያናችን ድርሳናት ይነግሩናል፡፡ ከሰማዕታት መካከልም ታላላቅ ተጋድሎ የተጋደሉና ብዙ ዓይነት ጸዋትወ መከራ የተቀበሉ፣ ብዙ ጊዜ ሞተው የተነሡና እግዚአብሔር ብዙ ተአምራት ያደረገላቸው ብዙ ሰማዕታት አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የሚታወቁት ግን በጣም ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው፡፡ ሆኖም በሰዎች ዘንድ አለመታወቃቸው በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያገኙትን ክብራቸውን በእኛ ዘንድ ከታወቁት ሰማዕታት ያነሰ አያደርገውም፤ የክብራቸው መሠረት በእኛ ዘንድ መታወቅ አለመታወቃቸው፣ በዓል ያላቸውና የሚታሰቡ መሆን አለመሆናቸው አይደለምና፡፡ ይህን በተመለከተ አንድ ሊቅ ሲያስረዳ በሰማይ ባሉ ከዋክብት መስሎ አስረድቷል፡፡ በሰማይ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑና ቁጥራቸው ይህን ያህል ተብሎ የማይታወቁ ከዋክብት አሉ፡፡ ለእኛ የሚያበሩልንና መኖራቸውን የምናውቃቸው ካሉት ከዋክብት እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ብቻ እንደ ሆኑ ከቅዱሳንም እኛ የምናውቃቸው ለአርአያና ለትምህርት ይሆኑን ዘንድ በጣም ጥቂቶቹን ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ከመራቃቸው የተነሣ ለእኛ በጣም ጥቃቅን መስለው የሚታዩንና ከነመኖራቸው የማናውቃቸው ትሪሊዮን ጊዜ ትሪሊዮንና ከዚም በላይ በቁጥር ሊገለጽ የማይቻል የሆኑ ከዋክብት እንዳሉ ሁሉ በቅዱሳንም እንዲሁ ነው፡፡ ለእኛ የሚታዩትና የምናውቃቸውም ሆኑ የማይታዩት የማናውቃቸው ከዋክብት የጋራ መገለጫቸው በሰማይ ያሉ ሰማያውያን መሆናቸው እንደ ሆነ ሁሉ የቅዱሳን የጋራ መገለጫቸው ሁሉም ሰማያውያንና በእግዚአብሔር ዘንድ የከበሩ መሆናቸው ነው፡፡

በእግዚአብሔር ቸርነት የሚገኝ ቅድስና ከሚገኝበት መንገድ አንዱ ሰማዕትነት ነው፡፡ ሰማዕታትም የሰማዕትነት አክሊል የሚቀዳጁት ሰማዕታት ናቸው ተብሎ ሲወሰንላቸው ወይም ዐዋጅ ሲታወጅላቸው ሳይሆን ለአምላካቸው ያላቸውን ጽኑ ፍቅርና ታማኝነት መከራውንና ሞቱን ሳይፈሩ ምስክርነታቸውን በሰጡና ከዚያም የሞትን ጽዋ በጽናት በተቀበሉ ጊዜ ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመዋቅሯ ሰማዕት ብላ እውቅና የምትሰጠው ከእነርሱ ከበረከታቸው ለመሳተፍና ለምስክርነታቸው ዕውቅና ለመስጠትና ለማክበር ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ለሰማዕትነታቸው ዕውቅና የመስጠት አለመስጠቱ ጉዳይ እነርሱ በሚያገኙት ጸጋና በሚሆኑት ላይ አንዳችም ለውጥ የማያመጣ ስለሆነ ብዙም የሚያጣድፍ ጉዳይ አለመሆኑንና ረጋ ብሎ አስተውሎ ቢደረግ የሚያመልጥ ነገር አለመኖሩን ተገንዝቦ በተረጋጋ መንፈስ ማድረጉ መልካም ይሆናል፡፡

በአጠቃላይ ከእነዚህ ሰማዕታት የሚከተሉት ነገሮች እንማራለን፡-

1.ክርስትና ከቅዱሳን ሐዋርያት ዘመን አንሥቶ በየዘመናቱ ዓይነቱና ስፋቱ ይለያይ እንጂ ጉዞው በመስቀል ላይ ማለትም በመከራ ላይ መሆኑን፣

2.ክርስትናን ከምድረ ገጽ ለማጥፋትና በዓለም ላይ የአረመኔ ሥርዓት ለመመሥረት አይ ኤስ እና መሰሎቹ የተለያዩ ቡድኖች ክርስቲያኖቹን በመግደልና አብያተ ክርስቲያናትንና ገዳማትን በማቃጠልና በማፍረስ ላይ መሆናቸውን፣

3.ይህ በቤተ ክርስቲያን ላይ እየሆነ ያለው አደጋ ችላ ሊባል የሚገባው ሳይሆን እያንዳንዱ ክርስቲያን በንቃት ሊከታተለው የሚገባ መሆኑንና ሕሊናዊና መንፈሳዊ ዝግጅት፣ እንዲሁም ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ የልብ ጸሎት የሚያስፈልግ መሆኑን፣ እና

4.በመጨረሻም እነዚህ ክርስቲያን ወንድሞቻችን ለክርስቶስ ታምነው ሞትን በጽናት መቀበላቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁላችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለንን ጽኑ ፍቅር አጽንተን በመከራም እንኳ ቢሆን ጸንተን እንድንቆም የሚያስተምር ሕያው ወንጌል መሆኑን ነው፡፡ እነርሱ በሠይፍ ለመታረድና በጥይት ተደብድበው እስከሚገደሉ ድረስ ለሃይማኖታቸው ከጸኑ እኛ ከዚያ ደረጃ ባልደረሱ ተራና ጥቃቅን ሰበቦችና ምክንያቶች ኢየሱስ ክርስቶስን እንዳንክድና በእርሱ ካለን ሕይወት እንዳንለይ፣ በክርስቶስ ያለንን እውነተኛ ኦርቶዶክሳዊና ሐዋርያዊ እምነት እስ መጨረሻው አጽንተን እንድንጠብቅ የወንድሞቻችን ደም ሕያው ሆኖ ከፊታችን እየጮኸ ያስተምረናል፡፡

እኛም እንደ ወንድሞቻችን መኑ ያኀድገነ ፍቅሮ ለክርስቶስ ሕማምኑ ምንዳቤኑ ተሰዶኑ ረሐብኑ ዕርቃንኑ መጥባሕትኑ ጻዕርኑ -ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፣ ወይስ ጭንቀት፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ራብ፣ ወይስ ራቁትነት፣ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? ልንልና በዚህ ሕይወት ልንኖር ይገባናል፡፡ ሮሜ 8፡35

እግዚአብሔር አምላክ ከእርሱ አንድነትና የአባትነት ፍቅር ከሚለይ ነገር ሁሉ ይጠብቀን፣

እኛንም ፈቃዱ ቢሆን እንደ ወንድሞቻችን በጽናት እንድንቆምና ለአክሊለ ሰማዕት እንድንበቃ ያድርሰን፣ አሜን፡፡

ኩኑ ቅዱሳን እስመ ቅዱስ አነ” ዘሌ.19፡2

 የካቲት 12ቀን 2007 ዓ.ም.

 ፲ቱ ማዕረጋት

ቅዱሳን ማለት የተቀደሱ፣ የከበሩ፣ የተመሰገኑ፣ የተለዩ፣ የተመረጡ፣ ንጹሐንየሆኑ፣ የጠሩ….. ወዘተ ማለት ነው፡፡ ቅዱሳን በዚህ ስም የሚጠሩበት ከሰው ወይም ከምድራዊ ባለሥልጣን የተቸሩት አይደለም፡፡ በሃይማኖት ጸንተው በምግባር ጐልምሰው የሥጋ ምኞታቸውን ጥለው አፍርሰው ሲገኙ የቅድስና ባለቤት ቅዱስ እግዚአብሔር እነሱን /ቅዱሳንን/ መሣሪያ አድርጐ ኃይሉንና ሥልጣኑን ቢገልጽባቸው ማኅደረ እግዚአብሔር መሆናቸው ይገለጻል፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱሳን ይባላሉ፡፡

እሱ እግዚአብሐር ቅዱስ ተብሏልና የጌትነቱ መገለጫ የሆኑ ሁሉ ቅዱሳን ይባላሉ፡፡ ጻድቃን እንደመላእክት ውሉደ እግዚአብሔር ይባላሉ፡፡ /ኢዮ.1፡6/፣ ሮሜ.8፡14/ ቅዱሳን ጻድቃን በግብር መላእክትን መስለው ሆነው የፈጣሪአቸውን ፈቃድ ፈጽመው በመገኘታቸው ከዚህ ዓለም በመለየታቸው ቅዱሳን ሲባሉ የፈጣሪአቸውን ሕያው መንግሥት ወራሾች ናቸውና ውሉደ እግዚአብሔር ይባላሉ፡፡ በሌላም ቃል ውሉደ ብርሃን ይባላሉ፡፡ /ሉቃ.16፡8/ በዓለማቸው ይራቀቃሉና ይህን ዓለም ይጠሉታል፡፡ ውሉደ ሕይወት ይባላሉ ሞትንና የሞት ከተማ ይህን ዓለም ይንቃሉና በክብር ተነሥተው ዳግመኛ ሲሞቱ የማይገባቸው ስለሆነ /ሉቃ.10፡30/ ውሉደ ጥምቀት ተብለዋል ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትናን ተጐናጽፈዋልና፡፡ ውሉደ መንግሥትም ተብለዋል የመንግሥተ ሰማያት ባለቤቶች ናቸውና፡፡ በጸጋ እግዚአብሔር የበለጸጉ በመሆናቸው የእግዚአብሔር አዕይንተ እግዚአብሔር ተብለዋል /መዝ.33፡15/

 

የፈጣሪአቸው ፈቃድ በተግባራቸው ስለሚታይ የእግዚአብሔር አዝነ ፈቃድ ወደ ጻድቃን ነው፡፡ ልመናቸው ጾማቸው እንዲሁም ምጽዋታቸው ሁሉ የተወደደ መሥዋዕት ነው፡፡ ቅዱሳን በዓላማቸው ጾምን ግብዣ /ድግስ/፣ ለቅሶን ዘፈን፣ ደስታን ሐዘን አድርገው በመኖራቸው ይህ ተለዋዋጭ ዓለም በየጊዜው የሚአቀርብላቸው መርዶ በእነሱ ዘንድ ዋጋ የለውም ወይም ዋጋ አይሰጡትም፡፡ ዓለምም ለእነሱ የሚያቀርበው ዓለማዊ የምኞት ስጦታ እንደ ኢምንት የተቆጠረ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ገጸ መዓቱ ወደ ዓለማውያን ሰነፎች እንደሆነ ገጸ ምሕረቱ ወደ ቅዱሳን ነው፡፡ ስለዚህ አማላጅነታቸው ጸሎታቸው በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ “አፍቅርዎ ለእግዚአብሔር ኲልክሙ ጻድቃኑ” ቅዱሳን እውነትን ይዛችሁ ትሕትናን ተላብሳችሁ እግዚአብሔርን ውደዱት “እስመ ጻድቅ የሐስስ እግዚአብሔር” እግዚአብሔር እውነትን ትሕትናን ይወዳልና፡፡ /መዝ.30፡23/ የቅዱሳን ፍሬ ትሕትና ነው፡፡ በዓይነ ሕሊናቸው ፈጣሪአቸውን በዓይነ ሥጋቸው የእነሱን ምንነት እንዲሁም የዓለምን ከንቱነት ይመለከታሉ፡፡

 

ፍሬ የያዘ ተክል ሁሉ ቁልቁል የተደፋ ነው፤ ትሕትናን ያስተምራል፣ የጻድቃን ምሳሌ ነው፡፡ በፈሪሃ እግዚአብሔር ልቡ የተሰበረ እሱነቱን /ምንነቱን/ የመረመረ ሰው በዓይነ ሕሊናው የፈጣሪውን ቸርነት በዓይነ ሥጋው የራሱን ውድቀት ይመለከታል፡፡ ይህ አመለካከት ለጸጋ እግዚአብሔርና ለፍሬ ክብር ያደርሱታል፡፡ በመቅረዝ ላይ ያለች መብራት መሰወር እንዳይቻላት የመቅረዙ ከፍታ የግድ እንደሚገልጻት በተራራ ላይ ያለች ቤትም በእይታ እንደማትሰወር የተራራው ከፍታ እንደሚገልጻት በጥበበ እግዚአብሔር ከብረው በጸጋ እግዚአብሔር ተውበው የሚኖሩ ቅዱሳን ጻድቃንም ደረጃ በደረጃ ማዕረጋትን አልፈው ከመለኮት ባሕርይ ተካፍለው የተአምራት መገለጫ ተካፍለው የተአምራት መገለጫ ይሆናሉ፡፡

 

“መንክር እግዚአብሔር በላዕለ ቅዱሳኑ” /መዝ.67፡35/ “እግዚአብሔር በቅዱሳኑ በወዳጆቹ አድሮ የሚሠራው ሥራ ድንቅ ነውን፡፡ /2ኛጴጥ.1፡3/ ቅዱሳን የጸጋ ተዋሕዶ ተዋሕደው ሲገኙ ሙት ሲሆኑ ሙታንን ማስነሳት እውር ሲሆነ እውርን ማብራት፣ በዓለም ላይ ድንቅ ሥራቸው ይሆናል፡፡ የጸጋና የክብር ተሸላሚዎች ሆነዋልና በዓለም ላይ ሳሉ የሚመጣባቸውን ፈተና ሁሉ ከምንም ባለመቁጠር ተቋቁመው የጸጋ መቅረዝ ተቋሞች ይሆናሉ፡፡ በዚህም በአላሰለሰው ሕይወታቸው የአንበሳ አፍ ዘጉ /ዳን.7፡1-28/ ውኃውን ወደ ኋላው መለሱ /ዘጸ.14፡22/ ሰማይን አዘዙ /1ኛ ነገ.17፡1፣ ያዕ.5፡17/ ነበለባለ እዥሰት አበረዱ /ዳን.3፡1-13/ የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ ወዳጅ እግዚአብሔር ከዘመድ ባዕድ ከሀገር የሚኖሩትን በረድኤት ይቀበላል፣ ሥጋዊ ሀገረ ተድላን ጥለው ሓላፊ ጠፊ ምድራዊ ምቾታቸውን ንቀው ጸጋውን የሚጠባበቁትን ሁሉ አብሮአቸው ይኖራል፡፡ ትዕግስትን የጥዋት ቁርስ የቀን ምሳ የማታ እራት አድርገው የሚመገቡትን ሁሉ ቤተ መቅደስ አድርጓቸው ይገኛል፡፡

 

 

ቅዱሳን በዚህ ዓለም ይጠበቡበታል፣ ወጥተው ወርደው እነሱነታቸውን ከስስት ኃጢአት ጠብቀው ለወዲያኛው ዓለም ደግሞ በትዕግሥት ደጅ ይጠኑበታል፡፡ “አሪሃ እግዚአብሔር ትፍስህተ ልብ ውእቱ ወይሁብ ሐሴተ ወያስተፌስህ ወያነውሀ መዋዕለ ሕይወት፤ እግዚአብሔርን መፍራት የልብ ደስታ ነው፡፡ ፍጹም የሥጋና የነፍስን ደስታ ይሰጣል በሕይወትም ያኖራል፡፡” “ለፈሪሃ እግዚአብሔር ይሴኒ ድሐሪቱ ወይትባረክ አመ እለተ ሞቱ እግዚአብሐርን የሢፈራ ሰው ፍጻሜው ያምርለታል እንደ ኢዮብ ከደዌው ተፈውሶ ልጅ ልጅ አይቶ ይሞታል /ኢዮብ.31፡16/ ይህ ሁሉ በረከት የቅዱሳን የሁልጊዜ ፍሬ ነው፡፡

 

ቅዱሳን ሁል ጊዜ የሚሠሩት ሰማያዊ ድርብ ድርብርብ /እንደ ሐመረ ኖኅ/ በጸጋ ላይ ጸጋ እየተጨመረላቸው ወደ 10ሩ መእረጋት ይወጣሉ፡፡ በያዙት ቀን መንገድም ኢዮባዊ ትዕግስት አብርሃማዊ ሂሩት ይስሐቃዊ ፈቃደኛነት ያዕቆባዊ ቅን አገልግሎት ጠሴፋዊ ሀዳጌ በቀልነት ሙሴአዊ ለወገን ተቆርቋሪነት እየጨመሩ በመኖራቸው ሳያውቁት የፈጣሪአቸውን ኃይል የጌትነቱ የመለኮትነቱን ድንቅ ሥራ መገለጫዎች ይሆናሉ፡፡

 

ማዕረጋቸውን ከዚህ ይናገሩታል፡-

 

የንጽሐ ሥጋ ማዕረጋት 3 ናቸ ው እነሱም፡-

1. ጽማዌ
2. ልባዌ
3. ጣዕመ ዝማሬ ይባላሉ፡፡

 

የንጽሐ ነፍስ ማዕረጋት 4 ናቸው

1. አንብዕ
2. ኲነኔ
3. ፍቅር
4. ሁለት ናቸው፡፡

 

የንጽሐ ልቡና ማዕረጋት ናቸው እነሱም
1. ንጻሬ መላእክት
2. ተሰጥሞ
3. ከዊነ እሳት ናቸው፡፡

የንጽሐ ሥጋ ማዕረጋት

1. ማዕረገ ጽማዌ፡- ይህ ማዕረግ የመጀመሪያው ነውና ማስተዋል ውስጣዊ ትዕግስትን ውስጣዊ ትህትና ውስጣዊ የራስ ሚዛንን ይዞ ማሰላሰል…… ወዘተ ይጀምራል፡፡ ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ እግዚአብሔርን ብቻ መዘከር ይችሉ ዘንድ የዚህን ዓለም ውጣ ውረድ ከማውራት ይከለከላሉ፡፡ በዚህ ማዕረግ መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ ያያሉ፡፡ ነገር ግን ለምን እንደሚወጡና እንደሚወርዱ አያውቁም፡፡ ዮሐንስ ሐጺር የሰፋውን ስፌት ገበያ ላይ ለመሸጥ ተቀምጦ እያለ እርሱ ግን በተመስጦ እነ ቅዱስ ሚካኤልንና ቅዱስ ገብርኤልን እንዲሁም ሌሎችን መላእክት በየማዕረጋቸው እያየ ሲያደንቅ ስፌቱን የሚገዛ ሰው ቁሞ እንቅቡ ዋጋው ስንት ነው ብሎ ሲጠይቀው እርሱ የሚያየውን የሚያይ መስሎት “ሚካኤልኑ የዓቢ ወሚመ አኮ ገብርኤል ሚካኤል ይበልጣል ወይስ ገብርኤል” ብሎ በአንክሮ ጠየቀው፡፡ ይህን ሲለው ሰውየው ይሄስ እብድ ነው ብሎ ትቶት ሄዷል፡፡

 

2. ማዕረገ ልባዌ፡– ደግሞ ማስተዋል ልብ ማድረግ አሰሙኝ እንጂ ስሙኝ አለማለት ልማር እንጂ ላስተምር አለማለት የተነገረው ትንቢትና ተግጻጽ ምዕዳን ሁሉ የራሱ እንደሆኑ መገመት መመርመር ዓይነ ሥጋን ከመጽሐፍ ከስነ ፍጥረት ዓይነ ነፍስን ከምስጢር….. ወዘተ ማዋል ነው፡፡ ወይም የእግዚአብሔርን ቸርነት ማድነቅ ስለሰው ያደረገውን ውለታ ማሰላሰል ከሰማየ ሰማያት መውረዱን ከሰው መወለዱን በገዳም መጾሙን መገረፉን ሥጋውን መቁረሱን ደሙን ማፍሰሱን መሰቀሉን መሞቱን መቀበር መነሳቱን እያሰቡ ልብን በፍቅረ እግዚአበሔር መሰበር አንደበትን በመንፈሳዊ ሕይወት መስበር ዓላማን በገጸ መስቀል/ትዕግሥት/ ማስተካከል የመሳሰሉት ናቸው፡፡

 

3. ማዕረገ ጣዕመ ዝማሬ፡- ከዚህ ደረጃ ሲደርስ አንደበትን ከንባብ ልቡናን ከምስጢር ማቆራኘት ነው፡፡ ቅዱሳን ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ አንደበታቸው ምንም ዝም ቢል በልባቸው ውስጥ ዝም አይሉም፡፡ ከአፍ እስትንፋስ ከአፋፍ ላይ ነፋስ እንደማይለይ ሁሉ ከአንደበታቸው ትዕግስት ከእጃዋው ምጽዋት ከልቡናቸው ትሕትና ከሰውነታቸው ንጽሕና አይለይም፡፡

 

4. የሚጸልዩትና የሚይነቡት ምስጢሩ እየገባቸው ስለሚያደርጉት አይሰለቻቸውም፡፡ ከዚህ ማዕረግ የደረሰ አንደ ባሕታዊ ለብዙ ዘመናት አቡነ ዘበሰማያት /አባታችን ሆይ/ እያለ ብቻ ሲኖር መልአክ መጥቶ ይትቀደስ ስምከ በል እንጁ ቢለው ኧረ ጌታዬ እኔስ አቡነ የሚለው ኃይለ ቃል ምስጢሩና ጣዕሙ በአፌ እንደ ጨሙ እየሟሟ አልጠገበኝ ብሏል እንዴት አድርጌ ወደፊት ልሂድ ብሎታል፡፡

 

የንጽሐ ነፍስ ማዕረጋት

 

1. ማዕረገ አንብዕ፡- ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ ቅዱሳን እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ያደረገውን ፍቅር እስከ ሞትና መቃብር የተጓዘውን የመከራ ጉዞ እያሰቡ በአንጻሩም ምረረ ገሃነመ እሳትን ጣዕመ መንግሥተ ሰማያትን እያሰላሰሉ ውሉደ አዳም ይህን ሁሉ መከራ ባለ መገንዘብ ወደ ሰፊው የፈቃደ ሥጋ ሲጓዝ በማየታቸው ሲአለቅሱ ይታያል፡፡ ያለምንም መሰቀቅ ሲአለቅሱ እንባቸው እንደ ምንጭ ይፈሳል፡፡ እንደ ሰን ውኃ ይወርዳል ይኸውም ለዚህ ዓለም ብለው የሚአለቅሱት ልቅሶ ፊትን ያንጣጣል ዓይንን ይመልጣል የቅዱሳን ልቅሶ ግን ፊትን ያበራል ኃጢአትን ያስወግዳል እርጥብ እንጨት ከእሳት ጋር በተያያዘ ጊዜ እንጨቱ ከነበልባለ እሳት ሲዋሐድ እንጨቱ እርጥብነቱን ትቶ ውኃውን በአረፋ መልክ እያስወገደ ይነዳል፡፡ ቅዱሳንም በግብር/በሥራ/ ከመለኮት ጋር ሲዋሐዱ የዚህ ዓለም ምስቅልቅል ሥራ በሰማያዊ የረጋ ሕይወት ተለውጦ አሠራራቸው አካሄዳቸው ፍጹም ሕይወታቸው መልአካዊ ይሆናል፡፡

 

2. ማዕረገ ኲነኔ፡- ከዚህ ማዕረግ ላይ ሲደርሱ ሥጋዊ ፈቃድ ሁሉ ለነፍስ ፈቃድ ይገዛል ነፍስ በሥጋ ባሕርያት ላይ ትሰለጥናለች ምድራዊ /ሥጋዊ/ ምኞት ሁሉ ይጠፋና መንፈሳዊ /ነፍሳዊ/ ተግባር ሁሉ ቦታውን ይወርሳል ያለምንም ማወላወል መንፈሳዊ ተግባር ሁሉ ይከናወናል፡፡

3. ማዕረገ ፍቅር፡– ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ ውሉደ እግዚአብሔር ቅዱሳን እንደ ፈጣሪአቸው ሁሉን አስተካክለው በመውደድ ይመሳሰላሉ አማኒ መናፍቅ ኃጥእ ጻድቅ ዘመድ ባእድ ታላቅ ታናሽ መሃይም መምህር ሳይሉ አስተካክለው በመውደድ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡

4. ማዕረገ ሁለት፡- ቅዱሳን ከዚህ ማዕረግ ላይ ሲደርሱ ባሉበት ሆነው ሁሉን ማየት መረዳት ይችላሉ፡፡ ጠፈር ደፈር ሳይከለክላቸው ርቀት ሳያግዳቸው ሁሉን በሁሉ ይመለከታሉ፡፡

 

የንጽሐ ልቡና ማዕረጋት

1. ንጻሬ መላእክት
2. ተሰጥሞ
3. ከዊነ እሳት ናቸው፡፡

 

 ማዕረገ ንጻሬ መላእክት፡- ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ የመላእክት መውጣት መውረድ ማየት ተልእኮአቸውን ያለምንም አስተርጓሚ መረዳት ማነጋገርና ማማከር የመሳሰሉትን መፈጸም፤ ለምሳሌ እንደ ዮሐንስ አፈወርቅ መልአኩን 10 ዓመት ማቆም ነው፡፡
 ማዕረገ ተሰጥሞ፡– ከዚህ ማዕረግ ሲደረስ በባህረ ብርሃን መዋኘት ባሉበት ሆኖ ወደ ላይም ወደታችም መመልከት መቻል….. ወዘተ ናቸው፡፡
 ማዕረገ ከዊነ እሳት /ነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ/፡- የፈጣሪ ቤተ መቅደስ ሆኖ ጸጋ በተዋሕዶ ከመላእክት ጋር ሆኖ ረቆ ማመስገን ያሉበትን ሥጋ በብቻው ማየት በአካለ ነፍስ ሰማየ ሰማያትን መጐብኘት ገነት ውስጥ መግባት ናቸው፡፡

 

እነዚህም የቅዱሳን ማዕረጋት 10 ናቸው፡፡ /2ኛ ጴጥ.1፡4-10፣ ዮሐ.1፡40/ የአስሩ ማዕረጋት ምሳሌዎች የአስሩ ቃላት፡፡ /ዘጸ.20፡3-12፣ ዮሐ.13፡17/ በመጨረሻም ቅዱሳን የቅዱስ እግዚአብሔር ቤተ መቅደሶች ናቸው ኑሮአቸውም ቅዱስ ነው፡፡

      የቅዱሳን በረከታቸው አይለየን፡፡ አሜን፡፡

• ምንጭ፡- ዝክረ ቅዱሳን ኅዳር ፮ ቀን ፲፱፻፺፯ ዓ.ም.

 

የነነዌ ሰዎች የንስሐ ምስክሮች

 

ጥር 24 ቀን 2007 ዓ.ም.

በዲ/ን በረከት አዝመራው

የነነዌ ጾም ከሰባቱ የቤተ ክርስቲያን አጽዋማት አንዱና የዐቢይ ጾም ማዘጋጃ ደወል ነው፡፡ ይህ የነነዌ ሰዎች የንስሐ ታሪክ በቤተ ክርስቲያናችን በጣም ታላቅ ዋጋ ያለውና የራሱ መዝሙር የሚዘመርለት፣ ቅዳሴ የሚቀደስበት ታላቅ መታሰቢያ ያለው ታሪክ ነው፡፡

 

ራሱ ጌታችንም የነነዌ ሰዎችን የንስሐ ታሪክ በመጥቀስ አይሁድን ገስጾበታል፤ በፍርድ ቀንም በዚያ ትውልድ ዘንድ እንደሚፈርዱበት ተናግሯል፡፡ ይህም የሆነበት የነነዌ ሰዎች ደስ የሚያሰኝ የንስሐ ታሪክ ስላላቸው ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ይህን አስደሳች የንስሐ ታሪክ በጾመ ነነዌ ከሚነበቡ የቅዳሴ ምንባባት አንጻር ለመመርመር እንሞከራለን፡፡

 

ኃጢአት ከእግዚአብሔር መለየት እንደሆነ ሁሉ ንስሐ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው፡፡  በዚህ ከእግዚአብሔር ሊለዩ የሚችሉ ብዙ ፈተናዎች ባለቡት ዓለም እስካለን ድረስ ሕይወታችን ሁሉ የንስሐ ጊዜ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከሁሉም ጊዜ በተለየ ወደ እግዚአብሔር የምንመለስባቸው የጾም ወቅቶች ሲሆኑ ከእነዚህም ታላቁና ዋነኛው ዐቢይ ጾም ነው፡፡

 

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በዐቢይ ጾም ከእያንዳንዱ ምእመን ልቦና የንስሐ ፍሬን ትፈልጋለች፤ ያለ ትንሣኤ ልቦና /ንስሐ/ የክርስቶስን ትንሣኤ በእውነትና በደስታ ማክበር አይቻልምና፡፡ ለመሆኑ ከንስሐ የሚያሰናክሉን ነገሮች ምን ምን ናቸው? የነነዌ ሰዎች ታሪክ ስለዚህ ምን ያስተምረናል?

 

1.    ቅንጦትን መውደድ
ምንም እንኳን በደፈናው ገንዘብ የኃጢአት ምንጭ ነው ባንልም እንደ ወንጌል ትእዛዝ በክርስቲያናዊ መንገድ ካልተያዘ ግን እግዚአብሔርን ሊያስረሳና የኃጢአት ማስፈጸሚያና ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜም ገንዘብና ባለጸግነት ከእግዚአብሔር በመለየታችን ያጣነውን ሰላምና ደስታ ለማግኘት ተስፋ የምንጥልበት ጣኦት ሆኖ ሊቀየር ይችላል፡፡ በሀብታችን በምናገኘው ጊዜያዊ ደስታና ሰላም ዘላለማዊውንና ፍጹምን የእግዚአብሔር ስጦታ መፈለግ፣ ወደ እግዚአብሔር መመለስን መናፈቅ ልናቆም እንችላለን፡፡ በዚህ መልኩ ብልጽግና ከንስሐ የሚያሰናክል ወጥመድ ይሆናል ማለት ነው፡፡

 

እግዚአብሔር ሀብት እንኳ ቢሰጠን ለተቸገረ በመመጽወት፣ ልጆቻችን በክርስቲያናዊ መንገድ በማሳደግ፣ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት በማፋጠን የእውነተኛ ደስታና የጽድቅ መንገድ እንድናደርገው እንጂ እግዚአብሔርን የተጠማች ነፍሳችንን ጥሪዋን በማደናቀፍና ጩኸቷን በማፈን በሥጋ ድሎት ውስጥ የምንደበቅበት መሣሪያ እንድናደረገው አይደለም፡፡ ለ«ታላቂቷ ከተማ» ነነዌም የጥፋት መንገድ የሆናት በብልጽግናዋና በታላቅነቷ እግዚአብሔርን ረስታ የኃጢአት ከተማ መሆኗ ነው፡፡ በነቢዩ በዮናስ ታሪክ ውስጥ ገንዘብ ለዮናስ ከእግዚአብሔር የመከለያ መሣሪያ ሲሆን እናገኘዋልን፡፡ «. ..  ከእግዚአብሔርም ፊት ኮብልሎ ከእነርሱ ጋር ወደ ተርሴስ ይሔድ ዘንድ ዋጋ ሰጥቶ ወደ እርሷ /ወደ መርከቧ/ ገባ» እንዲል /ዮና፤1-3/፡፡

 

በዚህ ሰዓት ለዮናስ ገንዘብ ባይኖረው ይሻል ነበር፡፡ እኛም ቢሆን ከንስሐ የሚመልስ፣ ለኃጢአት መሣሪያ የሚሆን ሀብት ከሚኖረን በድኅነት ብንኖር ይሻለናል፡፡ ምንም እንኳ በቤተክርስቲያናችን ትውፊት ዐቢይ ጾም አብዝተን የምንጸልይበት፣ በጾም በስግደትና በምጽዋት ልናሳልፈው የሚገባ ወቅት ቢሆንም ፤ አሁን አሁን ግን ገንዘብ ማግበስበሻ እየሆነ እንደሆነ እናያለን፡፡ በመሠረቱ በጾም ወቅት ከሆዳችን የምንቀንሰው ገንዘብ እንድናጠራቅመው ሳይሆን እንድንመጸወተው የሚገባ ነው፡፡ ለማጠራቀምማ የማያምኑ ሰዎችስ ምግብ ይቀንሱ የለ? ለዚህ ነው በነነዌ ጾም በመጀመሪያው ቀን /ሰኞ/ የሚነበበው የቅዱስ ያዕቆብ መልእክት “አሁንም እናንተ ባለ ጠጎች ስለሚደርስባችሁ ጭንቅ ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ፡፡ ሀብታችሁ ተበላሽቷል፣ ልብሳችሁም በብል ተበልቷ፡፡ ወርቃችሁም ብራችሁም ዝጓል፤ ዝገቱም ምስክር ይሆንባችኋል፤ ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላል፡፡ ለኋለኛው ቀን መዝገብን አከማችታችኋል፡፡ እነሆ እርሻችሁን ያጨዱት የሠራተኞች ደመወዝ በእናንተ ተቀምቶ ይጮኻል፣የአጫጆችም ድምፅ ወደ ጌታ ጸባዖት ጆሮ ገብቷል፡፡ በምድር ላይ ተቀማጥላችኋል፤ በሴሰኝነትም ኖራችኋል፤ ለእርድ ቀን እንደሚወፍር ልባችሁን አወፍራችኋል”  በማለት አስፈሪ ተግሳጽ የሚያስተላልፈው፡፡ ስለዚህ በዐቢይ ጾም አብዝተን የምንመጸውትበት፣ ከእግዚአብሔር የሆነውን ስጦታ የምንፈልግበት፣ የንስሐ ጊዜ ሊሆን ይገባል፡፡

 

2.    ለኃጢአት ሌላ ተጠያቂ መፈለግ
ሌላው ከንስሐ ሲያርቀን የሚገኘው ምክንያት በሰዎች መፍረድ ነው፡፡ በሰዎች የሚፈርድ ሰው ራሱን የሚያጸድቅ ነው፡፡ ራሱን ያጸደቀ ደግሞ ንስሐ መግባትና ከኃጢአት መመለስ ዳገት ይሆንበታል፡፡ ከነነዌ ሰዎች የንስሐ ታሪክ ውስጥ ለንስሐ በጣም አስቸጋሪ የነበረው ነቢዩ ዮናስ ነው፡፡ መርከበኞቹና የነነዌ ሰዎች በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ወደ እግዚአብሔር ሲመለሱ ዮናስ ግን ከታሪኩ መጀመሪያ እስከ መጨረሻዋ ጊዜ ድረስ በእግዚአብሔር ያጉረመርም ነበር፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ከእግዚአብሔር መኮብለሉና የነነዌ ሰዎችን ድኅነት መቃወሙን እንደ  ስህተት እንጂ እንደራሱ ስህተት አለመቁጠሩ ነው፡፡  ለዚህ ነበር ከእግዚአብሔር ኮብልሎ ሲሔድ እንኳ ምንም ዓይነት ጭንቀት ሳይሰማው «በከባድ እንቅልፍ» ተኝቶ የነበረው /ዮና.1-5/፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አንዳንድ ሰዎች ለራሳቸው ኃጢአት እግዚአብሔርን ተጠያቂ ሲያደርጉ ሌሎች ደግሞ ሰዎችን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡ በዚህም በራሳቸው ከመፍረድ ይልቅ በሰዎች መፍረድ ይጀምራሉ፤ ወይም የኃጢአታቸው ምክንያት እግዚአብሔርን አድርገው ይገኛሉ፡፡ ነቢዩ ዮናስ የራሱን ክብር ፈላጊነት ሳይሆን የእግዚአብሔርን ምሕረት የኃጢአቱ ምክንያት ማድረጉ የሚያስገርም ነው፡፡ ይህም ለብዙ ጊዜ ከንስሐ እንዳዘገየው ከታሪኩ እንማራለን፡፡ በተቃራኒው ለንስሐ ቅርብ የሆኑት መርከበኞች በዮናስ ላይ ለመፍረድ ምን ያህል እንደተጨነቁ ስናይ ቀድሞውኑ በዮናስ አለመታዘዝ ምክንያትም ቢሆን እግዚአብሔር ወደ ንስሐ ሊመልሳቸው የፈለገ ይህን አይቶ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡

 

በጾመ ነነዌ የመጀመሪያው ቀን /ሰኞ/ የሚነበበው የቅዱስ ጳዉሎስ መልእክትም የሚያስተምረን ይህንኑ ነው፡- “ስለዚህ አንተ የምትፈርድ ሰው ሁሉ ሆይ፣ የምታመካኘው የለህም በሌላው በምትፈርድበት ነገር ራስህን ትኮንናለህና፡፡ አንተም ፈራጁ እነዚያን ታደርጋለህና፡፡ እንደዚህም በሚያደርጉት ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነተኛ እንደሆነ እናውቃለንና፡፡ . . . ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ስታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን? ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቁጣ ቀን ቁጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ” /ሮሜ.2-1-5/፡፡ በተቃራኒው ግን በሰው ላይ ከመፍረድ በራሳቸው ላይ መፍረድን የሚመርጡ ሰዎች ለንስሐ ቅርብ ናቸው፡፡ በሚቀጥለው ቀን ማክሰኞ የሚነበበው የቅዱስ ጳውሎስ መልእክትም የሚያብራራው ይህንኑ ነው/1ቆሮ.4-1/፡፡

 

3.    የእግዚአብሔርን ተግሳጽ አለመቀበል
በነነዌ ሰዎች የንስሐ ታሪክ እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ ሰዎችን ሲገስጽ እንመለከታለን፡፡ ነቢዩ ዮናስን በማዕበል፣ ወደባሕር እንዲወረወር በማድረግ፣ አሳ አንበሪ እንዲውጠው በማድረግ እግዚአብሔር ወደ ትክክለኛ መንገዱ ሊመልሰው ቢጥርም በዚህ ሁሉ ሊመለስ አልቻለም፤ ከአሳ አንበሪ አፍ ወጥቶ ሔዶ ቢሰብክም እግዚአብሔር ይቅር ሲላቸው ግን በእግዚአብሔር ላይ ማጉረምረም ጀምሯልና፡፡ ድሮም ቢሆን በፍርሃት እንጂ ስህተቱን ተቀብሎ አልነበረም ወደ ነነዌ ሔዶ የሰበከው፡፡ ግዕዛን የሌላቸው ፍጥረታት /ነፋስ፣ አሳ አንበሪ፣ ትል፣ ፀሐይ/ እንዴት እንደሚታዘዙለት እርሱ ግን ታላቅ ነቢይ ሲሆን አልታዘዝም ማለቱን በማሳየትም ገስጾታል፡፡ በመጨረሻም ለንስሐ በቅቷል፡፡ መርከበኞቹም በመርከባቸው ላይ የተነሣው ማዕበል ተግሳጽ ሆኗቸው ወደ ንስሐ ተመልሰዋል፡፡ ከዘላለም ሕይወት እንዳንለይ አጥብቆ የሚፈልገው እግዚአብሔር ልዩ ልዩ መከራዎችንም በማምጣት ወደ ንስሐ እንድንመለስ ያደርጋል፡፡ ለዚህ ተግሳጽ ግን በትክክለኛ ወይም በተሳሳተ መንገድ መልስ ልንሰጥ እንችላለን፡፡ ካወቅንባቸውና ከተጠቀምንባቸው ችግሮችና መከራዎች ወደ ንስሐ የሚመሩ መንገዶች ናቸው፡፡ የነነዌ ታሪክም የሚነግረን ይህንኑ ነው፡፡ በነነዌ ጾም በቅዳሴ የሚነበቡት የሚከተሉት ምንባባትም በአጽንኦት የሚገልጹት ይህንኑ ነው፡፡
 

ምስባክ:- “ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ በላዬ አለፈ፡፡
እግዚአብሔር በቀን ቸርነቱን ያዛል በሌሊትም ዝማሬው በእኔ ዘንድ ይሆናል
የእኔ ስዕለት ለሕይወቴ አምላክ ነው፡፡” /መዝ.41-7-8/

መልእክት:- “. .  . ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል. . .” /ሐዋ.14-22/፡፡
 

በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ አሳዛኙ ነገር ሰው ካለፈ ሕይወቱ አለመማሩ ነው፡፡ በነቢዩ በዮናስ ታሪክም የምናገኘው ይህንኑ ነው፡፡ እግዚአብሔር የተሳፈረበትን መርከብ ካናወጠ፣ ዮናስ በአሳ አንበሪ እንዲዋጥ ካደረገ በኋላ እንኳ እግዚአብሔር በነነዌ ሰዎች ላይ ያሳየው ምሕረት ዮናስ ሞትን እስኪመኝ ድረስ እንዲያዝንና በእግዚአብሔር ላይ እንዲያጉረመርም አድርጎታልና፡፡ በእኛም ሕይወት ተመሳሳይ ተግሳጻት ከእግዚአብሔር ዘንድ ቢመጣም ከኃጢአት ባለመመለስ ከዮናስ ያልተለየ መልስ ነው የምንሰጠው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ራሳችንን የምናይበት፣ በሕይወታችን ያደረጋቸውን የእግዚአብሔር ሥራዎች የምንመረምርበት፣ በውስጣችን ያደፈጡትን አውሬዎች የምናድንበት የተረጋጋና ሰፋ ያለ ጊዜ ስለሌለን ነው፡፡ ይህን አጥብቃ የተረዳችው ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በልዩ ልዩ መንገድ የሚጠራንን የእግዚአብሔር ድምፅ የምናዳምጥበት፣ በመልካም ምክንያቶች የተሸፈኑ ነገር ግን መልካም ያልሆኑና መልካም ልንሠራበት የምንችለውን የሕይወት ጊዜዎችን የሚያቃጥሉ ከንቱ ምኞቶቻችን፣ የማይጨበጡና የማይደረስባቸው “ክፉ ተስፋዎቻችን” ሁሉ የምንመረምርበት፣ መልካሟንና እውነተኛዋን ነገር ግን አስቸጋሪዋንና ጠባቧን የሕይወት መንገዳችን አጉልተን “የምናስምርበት” ሰፋ ያለ ጊዜ ሰጥታናለች፤ ይህም ዐቢይ ጾም ነው፡፡ በዚህ ጊዜ በአግባቡ ከተጠቀምንበትም የዚህን አስቸጋሪና አወናባጅ ዓለም በድል የተወጡ ሰዎች የሚያዩትን የዘለዓለማዊን ሕይወት «ቀብድ» የትንሣኤውን ብርሃን እናያለን፡፡ ዐቢይ ጾምን እንደሚገባ ያላሳለፈ ክርስቲያን ግን የትንሣኤን ድግስ በልቶ ሆዱን ይሞላ እንደሆነ እንጂ የትንሣኤን ታላቅ ደስታ መቅመስ አይችልም፡፡ ስለዚህም ዐቢይ ጾም ለክርስቲያን ታላቅ ስጦታ መሆኑን ልናውቅ ይገባል፡፡ ለዚህም ነው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ስለጾም በጻፉት መጽሐፋቸው “በዐቢይ ጾም ሕይወቱን ያልቀየረ ክርስቲያን በሌሎች አጽዋማት ይቀይራል ማለት ይከብዳል” በማለት የጻፉት፡፡

 

4.    ክፉ እኔነት
በዮናስ ታሪክ ውስጥ ከብዙ የዮናስ ስህተቶች ጀርባ የነበረውና ንስሐውን ያዘገየበት ታላቁ መሰናከል ክፉ እኔነት ነው፡፡ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ የነነዌ ሰዎችን ድኀነት ሳይሆን የራሱን ክብር እንዲመለከት ያደረገው በዮናስ ሕይወት ውስጥ በጥልቅ የተተከለ ክፉ እኔነቱ ነው፡፡ በዚያ ሁሉ ታሪክ ውስጥ በርግጥም ዮናስ ስለራሱ እንጂ ስለሰዎች ሲያስብ አልታየም፡፡ ነቢዩ ዮናስ “እኔ ሐሰተኛ ነቢይ ከምባል የነነዌ ሰዎች መጥፋት ይሻላል” “የዮናስ አምላክ ቃሉን ይቀይራል ከምባል የነነዌ ሰዎች ይጥፉ” ብሎ ያስብ እንጂ እግዚአብሔር ግን አላለም፡፡ አመድና ትቢያ የሆነው የሰው ልጅ ስለክብሩ ሲጨነቅ ክብር የባሕሪዩ የሆነ ሩህሩህ አምላክ ግን ማንም እንዲጠፋ አልፈቀደም፡፡

 

በርግጥ የነነዌ ሰዎች በመዳናቸው የዮናስም የእግዚአብሔርም ቃለ አልታበለም፡፡ ዮናስ “ነነዌ በሦስት ቀን ውስጥ ትጠፋለች” ብሎ ሰበከ፡፡ አመጸኛዋ ነነዌ ግን በቁጣ እሳት ከመጥፋቷ በፊት በንስሐ ራሷን አዋረደች፡፡ በዚያን ጊዜ ነነዌ በንስሐ አዲስ ፍጥረት የሆነች፣ እግዚአብሔር የሚያጠፋት ሳትሆን የሚወዳት ሌላ ነነዌ ሆነች፡፡ ዮናስ ሆይ በንስሐ የታደሰችው ነነዌ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ እንደማያጠፋስ ለምን አላሰብክም? ታላቁ

 

የእግዚአብሔር ነቢይ ሆይ ንስሐ የገባችዋን ነነዌን ማጥፋት አምላክህን አያስነቅፈውምን? በነቢዩ በዮናስ ውስጥ ያለው እኔነቱ በርግጥም እግዚአብሔርንም፣ የነነዌ ሰዎችንም እንዳያስብ መጋረጃ ሆኖበት ነበር፡፡

 

በነቢዩ በዮናስ ሕይወት ውስጥ ክፉ እኔነቱ በዚህ መልክ ቢገለጥም፣ በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ግን በተለያየ መንገድ ሊገለጥ ይችላል፡፡ አንዳንዶቻችን “እኔ ቅዱስ ነኝ” የማለት ክፉ እኔነት ተጠናውቶናል፡፡ ኃጢአታችን ለንስሐ አባታችንና ለጓደኞቻችን ስንናገር እንኳ “ኃጢአትን የመናገር ቅድስና” እንጂ ኃጢአተኝነታችን አይሰማንም፡፡ “እኔ ርኩስ ነኝ” ስንልም ራስን በፈቃድ ኃጢአተኛ የማድረግ “ቅድስና” እንጂ ልባዊ የሆነ ንስሐ አይሰማንም፡፡ ሌሎቻችን ደግሞ “እኔ አዋቂ ነኝ” የማለት ክፉ እኔነት ይዞናል፡፡ “እኔ እኮ ምንም አላውቅም” ብለን ስንናገር እንኳን በልባችን ራስን ዝቅ ማድረግን “እያስተማርን” ነው በፍቅር ከተሰባሰቡ መንፈሳውያን ወንድሞችና እኅቶች መካከል እንኳን “ወርቃማ መንፈሳዊ ምክሮችን” ለመለገስ እንጂ መች ፍቅርን ‘ከታናናሾቻችን’ ለመማር እንቀመጣለንና፡፡ በዚህም በባዶነታችን እንኖራለን፡፡

 

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኒት መሆኑ እውነት ነው፤ ነገር ግን “ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች መድኃኒት አያስፈልጋቸውም” ብሏል፡፡ ሕመምተኞች መሆናችን አውቀን በንስሐ ብንቀርብ መድኃንኒት ይሆነናል፤ ራሳችንን አጽድቀንና «ቅዱስ ነኝ» ብለን በውሸት የጤንነት ስሜት መድኃኒት መፈለግ ከተውን ግን ከነኃጢአታችን እንሞታለን፡፡ ጌታችን ለእውራን ብርሃን፣ ዕውቀት ለሌላቸው ሰማያዊ ጥበብን የሚሰጥ ራሱ የእግዚአብሔር ጥበብ መሆኑ እውነት ነው፤ ነገር ግን ራሳችን በአዋቂዎች ተራ ከመደብን መምህር አልፎን ይሔዳል፡፡ ጌታ አለማወቃቸውን ያወቁትን ከእግዚአብሔር ዘንድ ሰማያዊ ጥበብን የሚፈልጉትን ሲያስተምር እንጂ «ምሁራንን» ሊያስተምር አልመጣምና፡፡ በኃጢአት መኖር እንደ ሀሞት መሮት፣ እንደጨለማ ከብዶት ከልቡ የሚጮኽን ተነሣሒ ለመቀደስ፣ እግዚአብሔር የዕውቀት ምንጭ የሕሊና ብርሃን መሆኑን አውቀው ከጥልቅ ከልቦናቸው ዕውቀትን የሚፈልጉትን ለማስተማር መጥቷልና እንደዚሁ ካልሆንን ከዚህ ጸጋ ዕድል ፈንታ አይኖረንም፡፡

 

ይህን ሁሉ የሕይወታችን ውጥንቅጥ እንመረምርበት ዘንድ ታላቁ የቤተክርስቲያን ስጦታ ዐቢይ ጾም እነሆ፡፡

የእውነተኛ ንስሐ ውጤቶች በነነዌ ሰዎች ታሪክ

1.    የዘላለም ሕይወት ተስፋ
ነነዌ የጥፋት ፍርድ ከተፈረደባት በኋላ የመኖር ተስፋ የተሰጣት ከተማ ናት፡፡ በሌላ አነጋገር ነነዌ ሞታ የተነሣች ከተማ ናት ማለት ይቻላል፡፡ ነቢዩ ዮናስም ወደ ባሕር ከተጣለ፣ በአሳ አንበሪ ሆድ ውስጥ ካደረ በኋላ የመኖር ተስፋ የተሰጠው ሰው ነው፡፡ መርከበኞችም መርከባቸው በማዕበል ከተመታች በኋላ፣ ማዕበሉ ካሸነፋቸው በኋላ በእግዚአብሔር ምሕረት ሌላ የመኖር ተስፋ የተሰጣቸው ሰዎች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የነነዌ ታሪክ የተስፋ ታሪክ ነው፡፡

 

ንስሐም በኃጢአት ከሞቱ በኋላ እንደገና የመኖር ተስፋ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች የዘለዓለም ሕይወትን ተስፋ ማድረግ ይከብዳቸዋል፤ ለዚህም ምክንያቱ በንስሐ አለመኖራቸው ነው፡፡ ሰው ያላየውን ነገር እንዴት ይናፍቃል? የማያውቀውን ነገርስ እንዴት ተስፋ ያደርጋል? በንስሐ የሚኖር ሰው ግን የዘለዓለም ሕይወት ቀብድ የሆነ ትንሣኤ ልቦናን ይነሣልና የዘለዓለም ሕይወትን በተስፋ ይናፈቃሉ፡፡ ዐቢይ ጾምንም በንስሐና ራስን በመመርመር ያሳለፈ ሰው በትንሣኤው ትንሣኤን ይቀምሳልና ዘለዓለማዊውን ትንሣኤ በተሰፋ ይናፍቃል፡፡

በነነዌ ጾም የሚነበቡ የቅዳሴ ምንባባትም ይህን እንደሚከተለው ይገልጻሉ፡-

“. . .  ትዕግሥትም ፈተናን፣ ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን በመከራችን ደግሞ እንመካለን፡፡ በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም” /ሮሜ.5-4-5/፡፡

“እናንተ ግን፣ ወዳጆች ሆይ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፣ ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን  ጠብቁ” /ይሁዳ.1-20/፡፡

 

2.    በእግዚአብሔር ዘንድ መከበር
በንስሐ የተመለሰችው ነነዌ በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ ከብራለች፡፡ የነነዌ ሰዎች ንስሐ በማይገቡ ዘንድ በትውልዱ ሁሉ ምስክር ይሆኑ ዘንድ እግዚአብሔር ፈቅዷል፡፡ «የነነዌ ሰዎች በፍርድ ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፣ እነሆም “ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ” እንዲል /ሉቃ.11-32/፡፡ የነቢዩ የዮናስ ታሪክም እንደዚሁ ነው፡፡ የንስሐ ሰባኪ የሆነው ራሱም ከብዙ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኋላ በንስሐ የተመለሰው ዮናስ የክርስቶስ ምልክት እንዲሆን እግዚአብሔር መፍቀዱ እግዚአብሔር ለተነሳሕያን የሚሰውን ክብር ያሳያል፡፡

 

ምንም እንኳን በዚህ ምድር ያለን ሰዎች የተነሣሕያንን ክብር ባናውቅም በሰማይ ያሉ መላእክት ግን በአንድ ኃጢአተኛ ንስሐ መግባት ታላቅ ደስታ ማድረጋቸው የንስሐን ክብር ያሳያል፡፡ ለዚህ ነው ለንስሐ የተዘጋጀ ልብን በማየት እግዚአብሔር አስቀድሞ ነነዌን “ታላቂቷ ከተማ” ብሎ የጠራት /ዮናስ.1-2/፡፡ ተነሣሕያን የእግዚአብሔር ይቅርታና ፍቅር የሚገለጥባቸው ሰዎች ናቸውና በእግዚአብሔርና በቅዱሳኑ ዘንድ የከበሩ ሰዎች ናቸው፡፡

 

3.    የእግዚአብሔርን ኃይል ማየት
በነነዌ ሰዎች የእግዚአብሔር ኃያልነት በግልጥ ተገልጧል፡፡ የእግዚአብሔር ኃያልነትም በትዕግሥቱ፣ በፍቅሩ፣ ፍጥረትን በመግዛቱ፣ ለሰው ልጆች በሰጠው ድንቅ ነፃነት ወዘተ ተገልጧል፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ አንዲትም ነፍስ ሳትጠፋ ሁሉም ይድኑ ዘንድ እግዚአብሔር ያሳየው የትዕግሥቱ ኃያልነት እንዴት ድንቅ ነው! የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያስተምር ዘንድ ነቢይ የሆነው ዮናስ እንኳ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ትቶ ሲኮበልል በሔደበት ሁሉ እየተከተለ በተለያየ መንገድ ወደ መንገዱ እንዲመለስ ይሠራ ነበር፡፡ ምናልባትም ሰው ዮናስን ይህን ያህል አይታገሰውም፡፡ ሰዎች እግዚአብሔርን ‘የመምከር’ ዕድል ቢሰጠን “ጌታ ሆይ አንተ ሁሉን ማድረግ ትችላለህ፤ ከነዚህ ድንጋዮት እንኳ ለአብርሃም ልጆች ማስነሣት ትችላለህ፡፡ ለምን ዮናስን ትለምነዋለህ? ተወው ሌላ ነቢይ ወደ ነነዌ ላክ፡፡ ዮናስን ርግፍ አድርገህ ተወው ከነነዌ ሰዎች የራሱን ክብር አስቀድሟልና” እንል ይሆናል፡፡ በባሕሪዩ ታጋሽ የሆነው እግዚአብሔር ግን ዮናስ በንስሐ ይመለስ ዘንድ ጠብቆታል፤ በመጨረሻም ለክርስቶስ ምሳሌ የሚሆን ታላቅ ነቢይ አድርጎታል፡፡

 

በነነዌ ታሪክ የእግዚአብሔር የፍቅሩ ታላቅነትም ተገልጧል፡፡ የእስራኤል አምላክ ይባል እንጂ ከአሕዛብ መካከል ለንስሐ የተዘጋጀ ሕዝብ ሲያይ ነቢዩን ልኮ ሕዝቡ አድርጓቸዋል፡፡ ቀና ልብ ያላቸው፣ ዮናስ ሲተኛ እንኳ ለማያውቁት አምላክ ሲጸልዩ የነበሩትን መርከበኞችንም በዮናስ  ምክንያት እንዲያውቁት አድርጓል፡፡ በርግጥም እግዚአብሔር ወደርሱ የምታይን ነፍስ፣ እርሱን የተጠማችን ልቦና አይተዋትም፡፡

 

በነነዌ ሰዎች ታሪክ የታየው ሌላው የእግዚአብሔር ኃይል በፍጥረቱ ላይ ያለው ሥልጣን ነው፡፡ ግዕዛን የሌላቸው ፍጥረታት /ፀሐይ፣ ማዕበል፣ ትል፣ ዛፍ፣ አሳ አንበሪ. . . / የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያለምንም ተቃውሞ ሲፈጽሙ እናያለን፡፡ በዚህም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሰጠውን ታላቅ ስጦታ ‘ነፃነትን’ እናደንቃለን፡፡ ፍጥረታት የሚታዘዙለት ኃይል እግዚአብሔር በነፃነት የፈጠረው የሰው ልጅ ፈቃዱን ሲጥስ ይመለስ ዘንድ በሚታዘዙት ፍጥረታት፣ በነቢያት. . . ይናገራል እንጂ ልቦናን በኃይሉ ቀይሮ እንደፈቃዱ እንዲኖር አያደርግም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መቀየር የፈለገን ልብ መቀየር የሚችል የሁሉ ፈጣሪ መሆኑን ፍጥረታቱን በማዘዝ አሳይቷል፡፡

 

ከዚህ ታሪክ ለእኛ የሚሆን ብዙ ነገሮችን እናገኛለን፡፡ የመጀመሪያው በንስሐ የምንኖር ከሆነ ወደዚህ ሕይወት እንደርስ ዘንድ እግዚአብሔር የታገሰባቸውን ያለፉትን የኃጢአት ዘመናት አስተውለን የእግዚአብሔርን የትዕግሥቱን ብርታት በሕይወታችን እናውቃለን፡፡ ከዚህ በኋላ ስለ እግዚአብሔር ታጋሽነት ሰዎች ሊነግሩን አያስፈልግም፤ በሕይወታችን አይተነዋልና፡፡

 

ከዚህም በተጨማሪ ወደ እርሱ እንመለስ ዘንድ በሕይወታችን ውስጥ የሠራውን የፍቅሩን ብርታትም እናውቃለን፡፡ ምንም እንኳ በዚህ ምድር ላይ ከቢሊዮኖች መካከል አንድ ብንሆንም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን በንስሐ መመለሳችን ሁሌ በእግዚአብሔር ሕሊና ውስጥ ሲታሰብ የኖረ፣ በሰማያት ካሉ ቅዱሳን ይልቅ የአንድ ኃጢአተኛ መመለስ ለሰማያትና ለእግዚአብሔር ደስታ የሚሰጥ መሆኑን ስናውቅ በርግጥም እግዚአብሔር እንዴት ሰውን ወዳጅ ነው? ነፍሳችንስ በእግዚአብሔር ዘንድ ምን ያህል የምትወደድ ናት? እንላለን፡፡

 

ከዚህ ሌላ ፍጥረታት የእግዚአብሔር ሁሉን የማድረግ ሥልጣን በመታዘዝ እንዳሳዩ ሁሉ በንስሐ የተመለሰ ኃጢአተኛም የእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት የሚታይበት ይሆናል፡፡ በኃጢአት የኖረን፣ አያሌ ዘመናትን በዲያብሎስ ምክር በጠማማ መንገድ የኖረን ልቦና መቀየር ከኃያሉ ከእግዚአብሔር በቀር ለማን ይቻለዋል? ኃጢአተኛን ‘ቅዱስ’ ማድረግ የእግዚአብሔር የብቻው የኃያልነቱ ውጤት ነውና፡፡ ለዚህ ነው ‘ተነሳሕያን’ ሰማዕታት ናቸው የሚባለው፤ የእግዚአብሔርን ሥራ በሕይወታቸው ይመሰክራሉና፡፡ ጥንታውያን ክርስቲያኖች በደማቸው የእግዚአብሔርን ክብር መስክረው ከሆነ ለዚህ ትውልድ ደግሞ “የንስሐ” ሰማዕትነት ቀርቶለታል፡፡

 

በአጠቃላይ ከነነዌ ሰዎች ታሪክ ስለንስሐ ብዙ እንማራለን፡፡ ለዚህም ነው ከብዙ የንስሐ ታሪኮች መርጣ ቅድስት ቤተክርስቲያን በተለየ ክብር የምታስበው፡፡ ለዚህም ነው ለታላቁ የንስሐ ወቅት ለዐቢይ ጾም ማዘጋጃ መግቢያ ያደረገችው፡፡ እኛም ከዚህ ታሪክ ተምረን፣ የተማረነውንም በንስሐ ወቅታችን /በአሁኑ ጾም/ በተግባር ልናውለው ይገባል፡፡ ለዚህም የተነሳሕያን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን! አሜን፡፡
 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር