‹‹ጥልንም በመስቀሉ ገደለ›› ኤፌ.፪፥፲፮

የዓለም ሰላም የተሰበከውና የተረጋገጠው በመስቀል ላይ በተደረገው የክርስቶስ ቤዛነት ነው፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ‹‹ጥልን በመስቀሉ ገድሎ ርቃችሁ ለነበራችሁ ሰላምና የምሥራችን ሰበከ›› ያለው….

መስቀል

መስቀል ነገር በመጀመሪያ የተገለጸው በመላእክት ዓለም ነበር፡፡

መስቀል የሰላም መሠረት ነው

መስቀል  የሰላም መሠረት፤ ሰላምም የመስቀል ፍሬ ነው፡፡ በግእዝ ሰላም የሚለው ቃል ትርጉም ‹‹ፍጹም ጤና፣ ዕረፍት፣ እርቅ፣ ሰላምታ፣ የቡራኬና የምርቃት ቃል፣ ሰው ሲገናኝና ሲለያይ የሚናገረው›› ነው፡፡ መስቀልና ሰላም አንዱ የአንዱ መሠረት አንዱ የአንዱ ፍሬ ሆነው የተሳሰሩትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡

ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነት

ክርስትና የሕይወት መንገድ ነው፡፡ መንገዱም ደግሞ ወደ ዘላዓለማዊ ክብር የሚያደርስ የሕይወት የድኅነትና የቅድስና መንገድ ነው፡፡ ክርስቲያን ለመሆን በ፵ እና በ፹ ቀን በመጠመቅ የሥላሴ ልጅነትን ማግኘት የቤተ ክርስቲያን አባል መሆን ያስፈልጋል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ መወለድ ማለትም ነው፡፡

ዘመነ ፍሬ

ከመስከረም ፱ እስከ ፲፭ ያሉት ዕለታት ዘመነ ፍሬ ተብለው ይጠራሉ፡፡ በእነዚህ ወቅት የሚዘመረው መዝሙርም ሆነ የሚነበቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እግዚአብሔር ለምድር ፍሬንና ዘርን የሚሰጥ የዓለም መጋቢ መሆኑን የሚያስገነዝቡ ናቸው፡፡

ዘመነ ቅዱስ ዮሐንስ

ርእሰ ዐውደ ዓመት

ዲያቆን ዘክርስቶስ ፀጋዬ

የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት መስከረም አንድ ቀን ይከበራል፡፡ ስያሜው ቅዱስ ዮሐንስ በመባል ሲታወቅ ከመስከረም አንድ እስከ ስምንት ድረስ ያሉት ዕለታትንም ያካትታል፡፡ በዚህ ወቅት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚዘመረው መዝሙር ክብረ ቅዱስ ዮሐንስንና ርእሰ ዐውደ ዓመትን የሚያወሳ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ያስተማረውን ትምህርትና ገድሉን የሚያመለክት ስብከት ይሰበካል፤ ትምህርቱም ይሰጣል፡፡ አዲስ ዓመት ዘመን መለወጫ በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ስም የተሰየመበት ምክንያት፡-

፩. የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ተግባር ለዘመነ ወንጌል መነሻ በመሆኑ

ቅዱስ ማርቆስ በወንጌሉ ‹‹እነሆ÷ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ፡፡ የእግዚአብሔርን መንገድ ጥረጉ፤ ጥርጊያውንም አስተካክሉ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ የአዋጅ ነጋሪ ድምጽ፤ ዮሐንስም በምድረ በዳ ያጠምቅ ነበር፤ ኃጢአትንም ለማስተስረይ የንስሓ ጥምቀትን ይሰብክ ነበር፡፡ የይሁዳና የኢየሩሳሌምም ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ይሄዱ ነበር፤ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ሁሉንም ያጠምቃቸው ነበር»  (ማር.፩፥፪-፭) ብሎ ጽፎልናል፡፡ የካህኑ ዘካርያስ ልጅ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በዘመነ ብሉይ መጨረሻና በዘመነ ሐዲስ መጀመሪያ ላይ ተነስቶ «መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ›› እያለ ስለ ክርስቶስ አዳኝነት በምድረ በዳ እያስተማረና የንስሓ ጥምቀት እያጠመቀ በዘመነ ወንጌል መጀመሪያ ምዕራፍ ተገኝቷል፡፡ እንዲሁም መጥምቁ ዮሐንስ በነቢያት መጨረሻ በሐዋርያት መጀመሪያ ተገኝቶ ዘመነ ሐዲስን እንደሰበከና ከዘመነ ብሉይ ወደ ዘመነ ሐዲስ መሸጋገሪያ ጊዜ ላይ ስለነበረ ያለፈውን ዘመን የምንሸጋገርበት የዘመን መለወጫ ቀን የቅዱስ ዮሐንስ መታሰቢያ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

፪. መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የጻድቃን የሰማዕታት ርእስ ነውና

በቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል ላይ ‹‹እውነት እላችኋለሁ፤ ሴቶች ከወለዱአቸው ወገን ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም›› (ማቴ.፲፩፥፲፩) ብሎ ጌታችን ስለ ዮሐንስ በተነገረለት መሠረት የጻድቃን የሰማዕታት ርእስ እንደመሆኑ አዲስ ዓመትም የበዓላት ሁሉ በኩር ርእስ ነውና በስሙ ተጠርቷል፡፡ እንደዚሁም ጌታ ባረገ በ፻፹ ዘመን በእስክንድርያ ፲፪ ሊቀ ጳጳሳት ሁኖ የተሾመው ቅዱስ ድሜጥሮስ  ባሕረ ሐሳብን ሲደርስ ከዮሐንስ ጀምሮ ደርሶታል፤ ሲጨርስም ለኢየሩሳሌም፣ ለሮም፣ ለኤፌሶንና ለአንጾኪያ ሊቃነ ጳጳሳት ልኳል፡፡ በእስክንድርያ /ግብጽ/ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በዓላት የሚከበሩትና አጽዋማት የሚገቡት ከመስከረም አንድ ተነስቶ በመቁጠር ነው፡፡  በቤተ ክርስቲያናችን የበዓላቱና የአጽዋማቱ መደብ የሚታወቅበትና የዘመናቱ ሂደት ተቀምሮ የሚታወጅበት መስከረም አንድ በመሆኑ ርእሰ ዐውደ ዓመት ይባላል፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም የዘመን መለወጫን አዲስ ዓመት በዓል አስመልክቶ እንደነገረን ‹‹ርእሰ ዐውደ ዓመት ዮሐንስ ወላዴ መጥቅዕ ወአበቅቴ፤›› የዓመት በዓል ራስ ዮሐንስ መጥቅዕና አበቅቴን የምትወልድ ነህ›› እየተባለ ይዘመርለታል፡፡

ጎሐ፤ ጽባሕ

ዲያቆን ዘክርስቶስ ፀጋዬ

ጎሐ ፤ ጽባሕ ከነሐሴ ፳፱ እስከ ጳጉሜ ፭ ድረስ ያሉት ቀናት የሚጠሩበት ነው፤ ጎሐ ማለት ነግህ ሲሆን ጽባሕ ደግሞ ብርሃን ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ በድጓው «ዘመናትን የምታፈራርቅ፤ የብርሃንን ወገግታ የምታመጣ አንተ ነህ» እያለ በመግለጽ ዓለምን ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣው፣ ከመኖርም ወደ አለመኖር የሚያሳልፍ፣ በጨለማ መካከል ብርሃንን ያደረገ እርሱ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ብርሃን እና ቀን የልደት፣ ሌሊትና ጨለማን የሞት ምሳሌዎች ሆነው ያገለግላሉ፡፡

ከነሐሴ ፳፱  እስከ ጳጉሜ ፭ ድረስ ያለው ወቅት የክረምቱ ጨለማ የሚወገድበት፣ የፀሐይ ብርሃን ወለል ብሎ የሚወጣበት፣ ጉምና ደመና በየቦታቸው ተሰብስበው፣ ሰማይ በከዋክብት አሸብርቆ የሚታይበት ነው፡፡

በክረምቱ ውኃ ሙላት ምክንያት ግንኙነት አቋርጠው የነበሩ ወገኖች ሁሉ በዚህ ክፍለ ጊዜ ብርሃን ስለሚያዩ፤ መገናኛ መንገዶችም ስለሚያገኙ፣ ክረምቱን እንደ ሌሊት በመመልከት ይህን ወቅት እንደ ንጋት መታየቱን ለመግለጽ ቤተ ክርስቲያን ‹‹ጎሐ፤ ጽባሕ›› በሚለው ስያሜ ትጠራዋለች፡፡ በዚህ ወቅት የሚዘመሩ መዝሙራት ‹‹አቤቱ ወደ አንተ እጸልያለውና በማለዳ ድምፄን ስማ›› (መዝ.፭፥፪)፤ በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ብርሃንን አየ፣ በሞት ጥላ ሥር ለተቀመጡት ብርሃን ወጣላቸው (ማቴ.፬፥፲፮) የሚሉትና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

ማእከለ ክረምት

ዲያቆን ዘክርስቶስ ፀጋዬ

ዘመነ ክረምት የሚጋመስበት ወቅት ማዕከለ ክረምት ይባላል፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ሁለት  ንኡስ ክፍል ይገኛሉ፤ እነርሱም ዕጒለ ቋዓት እና ደሰያት / ዐይነ ኩሉ/ በመባል ይታወቃሉ፡፡ ይህም ወቅት ከነሐሴ ፲፩ – ፳፯ ቀን ድረስ ያለውን ፲፯ ዕለታት ያካትታል፡፡ ፍጥረታትና በባሕር የተከበቡ ደሴቶች የሚታወሱበት ወቅትም ነው፡፡

ዕጒለ ቋዓት- የሚለው ቃል ቁራን ያመለክታል፤ ቁራ ከእንቁላሉ ተቀፍቅፎ ሲወጣ ያለ ፀጉር በሥጋው ብቻ ይወጣል፡፡ እናትና አባቱም እነርሱን ባለመምሰሉ ደንግጠው ይሸሹታል፤ በዚህ ጊዜ የሚንከባከበው ሲያጣ እግዚአብሔር በረድኤት አፉን ከፍቶ ምግብ ሲሻ ተሐዋስያንን ብር ብር እያደረገ ከአፉ ያስገባለታል፡፡ (ኢዮ. ፴፰፥፵፩) «ለቁራ መብል የሚሰጠው ማን ነው?›› ብሎ እንደገለጸው እግዚአብሔር የሰጠውን እየተመገበ ቆይቶ ሲጠነክር እንደ እናትና አባቱ ያለ ፀጉር ያወጣል፡፡ በዚህ ጊዜ ግን አባቱና እናቱ ቀርበው ይንከባከቡታል፡፡ ቁራ በሥነ ፍጥረት አቆጣጠር በክንፍ ከሚበሩ አዕዋፍ ነው፡፡ ይህም አምላካችን እግዚአብሔር ለፍጥረቱ የሚያስብ በመሆኑ ይህን ዘመን ርኅራኄ ለተመላው ሥራው መታሰቢያ እንዲሆን ቤተክርስቲያን ዕለ ቋዓት በማለት ታስታውሳለች፡፡

ደሰያት – የሚለው ቃል በውኃ የተከበቡ ቦታዎችን ያመለክታል፡፡ እነዚህን ቦታዎች በውኃ እንዲሸፈኑ አድርጎ በውስጣቸው ያሉትን ሰዎች እንስሳት፤ አራዊትና አዕዋፍ ሁሉ የሚጠብቃቸው፣ በተስፋና በእምነት አበርትቶ የሚያኖራቸው እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህም ሰዎች እግዚአብሔርን በዚህ ያመሰግኑታል፡፡ ደሴት የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፤ አንዲት ደሴት በውስጧ ብዙ ፍጥረታትን ትይዛለች፡፡ ከደሴት የተጠጉ ድኅነትን እንደሚያገኙ ሁሉ ወደ ቤተክርስቲያን የተጠጉ ሁሉ ከሞተ ሥጋ ከሞተ ነፍስ ይጠበቃሉ፡፡

በዚህ ዕጒለ ቋዓትና ደሰያት ወቅት ክፍለ ክረምቱ እየተገባደደ፣ ውኃው እየጠራ፣ መሬቱ እየረጋ፣ ደመናውና ጉሙ እየተቃለለ፣ የወንዝ ሙላት እየቀነሰ፣ የክረምት ምግባቸውን ይዘው በየዋሻው የከረሙ ጭልፊቶችና አሞራዎች ድምጻቸውን እየሰሙ ምግብ ፍለጋ ሲወጡ የሚታይበት ወቅት ነው፡፡

‹‹ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት፣ ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት›› እንዳለው፤ ዝናብ ይቀንሳል፣ ምድሪቱም መቀዝቀዝና መጠንከር የምትጀምርበት ወቅት ነው፡፡

ቅድስት ቤተክርስቲያን በዚህ ወቅት እግዚአብሔር አምላክ ለሥጋ ሁሉ ምግብን የሚሰጥ ምሕረቱም ለዘላለም የሆነውን የሰማይን አምላክ መሆኑንና ፍጥረታትም ሁሉ እርሱን ተስፋ የሚያደርጉ መሆናቸውን የሚገልጡ መዝሙራት፣ ትምህርት፣ ስብከት ይሰጣል፣ ይነበባል፡፡ (መዝ.፻፵፬፥፲፮-፲፯)

በተጨማሪ በዚህ በማእከለ ክረምት ‹‹ዕረፍተ አበው›› ከነሐሴ ፳፯ እስከ ነሐሴ ፳፱ ድረስ ባለው ጊዜ ይታሰባል፡፡ ከ፳፪ቱ አርዕስተ አበው አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ የቤተሰቦቻቸው ዕረፍት ይታሰባል፡፡ የአብርሃም ታዛዥነት እና የይስሐቅ ቤዛነት ይታሰባል፡፡ የተቀበሉትም ቃልኪዳን ‹‹ወተዘከረ ሣህሉ ዘለዓለም ዘሠርዓ ለአብርሃም መመሐለ ለይስሐቅ ወዐቀመ ስምዐ ለያዕቆብ ያረኁ ክረምተ ይገብር ምሕረተ እምሰማይ ይሁብ ወእምድር በረከተ ያጸግብ ነፍሰ ርኅብተ›› በማለት ይዘመራል፡፡

ምልአተ ባሕር

ዲያቆን ዘክርስቶስ ፀጋዬ

የበአተ ክረምት ሁለተኛው ክፍል ምልአተ ባሕር ይባላል፡፡ ይህም ከሐምሌ ፲፱ እስከ ነሐሴ ፲ ድረስ ያለው ወቅት ሲሆን ዝናም ምድርን የሚያለመልምበት፤ የተዘራው የሚበቅልበት፤ በፀሐይ ሐሩር የደረቁ ዛፎች ሁሉ የሚያቆጠቁጡበት ወቅት ነው፡፡ በተለይ ከሐምሌ ፲፱ እስከ ሐምሌ ፳፱ መባርቅት የሚበርቁበት፤ ባሕርና አፍላጋት የሚሞሉበት ወቅት ነው፡፡

መብረቅና ነጎድጓድ

መብረቅ ማለት የእሳት ሰይፍ፤ የእሳት ፍላፃ፤ በዝናም ጊዜ ከደመና አፍ የሚመዘዝ የሚወረወር ነው፡፡ (ራእ ፬፥፭፤ ኤር ፲፥፲፫፤ ኢዮ. ፴፯፥፬) የመብረቅ ተፈጥሮ ውሃው በደመና አይበት ተቋጥሮ ሲመጣ በነፋስ ወደል ጋዝ ተጭኖ ፤ ደመናና ደመና በተጋጨ ጊዜ የሚፈጠር ነው፡፡ ወተት ሲገፋ ቅቤ እንደሚወጣው አይነት ማለት ነው፡፡

ነጎድጓድ ማለት ታላቅ ግሩም ድምፅ፤ የሚያስፈራ፤ የሚያስደነግጥና የሚያንቀጠቅጥ ሲሆን (መዝ. ፸፮፥፲፰፤ ኢዮ. ፵፥፬)፤ መብረቅ ከወረደ በኋላ የሚሰማ ድምፅም ነው፡፡ (ኢዮ. ፴፯፥፪-፭፤ መዝ. ፳፰፥፫) ነገር ግን ለማስደንገጥ ወይም ለመዓት ብቻ የተፈጠረ አይደልም፤ ማኅፀነ ምድርን በመክፈት ውኃው ሠርፆ እንዲገባና አዝርዕትና አትክልት እንዲበቅሉ፤ እንዲያብቡና እንዲያፈሩ የሚያደርግ ጭምር ነው፡፡(ሄኖ.፮፥፩)

የክረምትን ኃይልና ብርታት ጥግ አድርገው የሚከሠቱ የተፈጥሮ ኃይላት ዑደትም ይጸናበታል፡፡ መብረቅ፤ ነጎድጓድ፤ ባሕርና አፍላጋት (ወንዞች) ይሠለጥናሉ፡፡ጥልቅ የሆኑ ቦታዎች መጠናቸው ያድጋል፤ ምንጮች ይመነጫሉ፤  የወንዞች ሙላት ይጨምራል፡፡

በቅድስት ቤተክርስቲያን በዚህ ክፍለ ክረምትና ንኡስ ክፍል ዘርዕን፤ ደመናን፤ ዝናምን የሚያዘክሩ እና የመብረቅን፤ የነጎድጓድን፤ የባሕርን፤ የአፍላጋትን፤ የጠልን ጠባይዓት የሚያመለክቱ መዝሙራት ይዘመራሉ፤ ምንባባት ይነበባሉ፤ ስብከት ይሰበካል፡፡

ኢትዮጵያዊ ቅዱስ ያሬድም ይህን ወቅት አስመልክቶ በድጓው ላይ በገለጸው መሠረት ‹‹ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ሶበ ይዘንም ዝናም ይትፌሥሑ ነዳያን፤ ይጸግቡ ርኁባን ምድርኒ ርእየቶ ወአእኰተቶ ባሕርኒ ሰገደት ሎቱ፡፡ የዝናም ድምፅ ተሰማ፤ ዝናብም በዘነመ ጊዜ ድሆች ደስ ይሰኛሉ፤ ረኃብተኞችም ይጠግባሉ፤ ምድር አየችው፤ አመሰገነችውም፤ ባሕርም ሰገደችለት›› የሚለው ዜማ ይዜማል፡፡

ቅዱስ ዳዊት ደግሞ በመዝሙሩ ‹‹ዘይገለብቦ ለሰማይ በደመና፤ ወያስተዴሉ ክረምተ ለምድር፡፡ ዘያበቊል ሣዕረ ውስተ አድባር፡፡ ወሐመልማለ ለቅኔ እጓለ እመሕያው፡፡ ‹‹ሰማይን በደመና የሚሸፍን፤ ለምድርም ዝናምን የሚያዘጋጅ፣ ሣርን በተራሮች ላይ ልምላሜውንም ለሰው ልጆች አገልግሎት የሚያበቅል›› (መዝ.፻፵፮፥፰፤መዝ.፻፴፬፥፮፤መዝ.፸፮፥፲፰፤ መዝ.፷፬፥፱) ሲል ዘምሯል፡፡

እግዚአብሔር በነጎድጓድና በመብረቅ፤ በባሕርና በሐይቅ ሁሉ ላይ ሥልጣን ያለው አምላክ መሆኑን፤ የሚታዩና የማይታዩ ፍጥረታት ሁሉ የኃይሉ መገለጫዎች እንደሆኑ የሚያስተምሩ መዝሙራት ይዘመራሉ፡፡ ምንባባትም ከቅዱስ ወንጌልና ከቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት እንዲሁም ከሐዋርያት ሥራ ክረምቱን በተመለከተ የተዘጋጁት ይነበባሉ፡፡