‹‹አንተ በጎና ታማኝ አገልጋይ›› ማቴ:25
መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ
ህዳር 15 ቀን 2007 ዓ᎐ም
ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን በክቡር ዳዊት አድሮ፤ “እከሥት በምሳሌ አፉየ፤ ወእነግር አምሳለ ዘእምትካት፤ አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ከቀድሞ ጀምሮ ያለውንም ተምሳሌት እናገራለሁ” ብሏል፡፡ /መዝ. 77፡2/
በዚሁ መሠረት ጌታችን ወንጌለ መንግሥተ ሰማያትን በልዩ ልዩ ምሳሌ አስተምሯል፤ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 25 ሁለት ምሳሌያትና አንድ ትንቢት ቀርበዋል፡፡
ከምሳሌያቱ የመጀመሪያው በዐሥሩ ደናግል አንጻር የቀረበው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ወጥተው ወርደው ነግደው ያተርፉበት ዘንድ ገንዘቡን ስለሰጠ ነጋዴ የሚናገረው ነው፡፡ ትንቢቱም ስለ ኅልቀተ ዓለም የተነገረ ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ ዕትማችን ነግደው እንዲያተርፉበት ከጌታቸው የተሰጣቸውን መክሊት ስለተቀበሉት አገልጋዮች እንመለከታለን፡፡ ፈጣሪያችን ለብዎውን ማስተዋሉን ያድለን፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ያስተማራቸውን ምሳሌያዊ ትምህርቶችን በሰፊው ተጽፎ እናገኛለን፡፡
የእነዚህ ትምህርታዊ ምሳሌዎች መሠረታዊ ሀሳብና ዓላማ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምናገኝበትን የታማኝነትን ሥራን እንዴት መሥራት እንደሚገባንና እንደምንችል ማስተማር ነው፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ መንግሥተ ሰማያት ምሥጢር ያስተማራቸው ብዙ ምሳሌዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ብዙ ምሳሌዊ ትምህርቶች መካከል በማቴዎስ ወንጌልም 25 ላይ እንዲያተርፉበት መክሊት ስለተሰጣቸውና ወጥተው ወርደው ሌላ አትረፈው በጌታቸው ስለተመሰገኑት ቸርና መልካም አገልጋዮች፣ እንዲሁም መክሊቱን በመቅበሩ ምክንያት በጌታው ስለተወቀሰውና ፍርድን ስለተቀበለው ሰው ታሪክ፣ የታሪኩም ምሥጢር ምን እንደሚመስል ነው፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ምሳሌ የተናገረው በሚከተለው መልኩ ነበር ‹‹ወደ ሌላ ሀገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና ለእንዳንዱ እንደ ዓቅሙ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ ሀገር ወዲውኑ ሄደ፡፡ አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄደ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ፡፡ አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቆፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ፡፡
ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው፡፡
አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ፡- ጌታ ሆይ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፡ እነሆ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ፡፡ ጌታውም፡- መልካም አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ:: ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡ ሁለት መክሊት የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፡- ጌታ ሆይ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፡፡ እነሆ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት አለ፡፡ ገታውም፡- መልካም አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ:: ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡
አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፡- ጌታ ሆይ ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት እነሆ መክሊትህ አለህ አለው፡፡ ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው፡- አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ ካልዘራሁበት እንዳጭድ ካልበተንሁባትም እንድሰበስብ ታውቃለህን:: ስለዚህ ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር:: እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር፡፡ ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት አሥር መክሊትም ላለው ስጡት::
ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል:: ከሌላው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል፡፡ የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት:: በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል፡፡›› የሚል ነው፡፡ መክሊት ጥንት የክብደት መለኪያ ነበር:: አንድ መክሊት 30 ኪሎ ግራም ያህል ነው፡፡ በዚህ ምሳሌ ላይ እንደተገለጸውም መክሊት የሚለው ቃል ገንዘብን ያመለክታል፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምሳሌ ውስጥ እርሱን የምናገለግል ሁላችን አንደየዓቅማችን ማድረግ የሚገባንን መንፈሳዊ የአገልግሎት ሥራንና በአገልግሎታችን ውጤታማ በመሆናችንም ከእርሱ የምናገኘውን ዘላለማዊ ክብርና ዋጋን እንዲሁም መሥራት የሚገባንን ባለማድረጋችንም ምክንያት የሚገጥመንን መለኮታዊ ቅጣትን አመልክቶናል፡፡ በዚህ ምሳሌ ውስጥ ባለ አምስት የተባለው ፍጹም ትምህርት ተምሮ ሌላውን መክሮ አስተምሮ ራሱን አስመስሎ ያወጣነው፡፡
በተመሳሳይም ባለሁለት የተባለው ፍጹም ትምህርት ተምሮ ሌላውን መክሮ አስተምሮ ራሱን አስመስሎ ያወጣ ሲሆን ባለአንድ የተባለው ደግሞ ተምሮ ሳያስተምር የቀረ ሰው ነው፡፡ በመሆኑም ባለአምስትና ባለሁለት መክሊት የሆኑት ወጥተው ወርደው ደክመው’ መከራ መስቀልን ሳይሰቀቁና ሳይፈሩ’ ነፍሳቸውን ለታመነው አምላክ አደራ በመስጠት የተማሩትን ፍጹም ትምህርት ለሌላው አስተምረው ሌላውን አንደራሳቸው የተማረ አድርገው ሲያወጡ ባለአንድ የተባለው ግን አላውያን እሳት ስለት አሳይተው ቢያስክዱኝ መናፍቃን ተከራክረው ምላሽ ቢያሳጡኝ ብሎ ፈርቶ ሃይማኖቱን በልቡ ከመያዝ በቀር የተማረውን ትምህርት ለሌላው ሊያስተምርና የተሰጠውን አደራንም ሊወጣ አልወደደም፡፡
በምሳሌው ውስጥ እንደተገለጠው ሌላ አምስትና ሁለት ያተረፉት በተሰጣቸው መክሊት ሌላ ማትረፋቸውን ለጌታቸው በገለጡ ጊዜ የመክሊቱ ባለቤት እጅግ አድርጎ እንዳመሰገናቸው ከላይ አንብበናል፡፡
ይህ የመክሊቱ ባለቤት የተባለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለተወጡት ሁሉ እርሱ ፍጹም ዋጋን የሚሰጣቸው መሆኑን ያመለክታል፡፡ ይህም ሁኔታ ‹‹ መልካም አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ፡፡ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ›› በሚል ተገልጧል፡፡ ይህ ቃል በሃይማኖት ለእግዚአብሔር የታመኑ ሁሉ ወደ ፍጹም ደስታ ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ለሚያደርጉት ጉዞ እጅግ ተስፋ የሆነ ቃል ነው፡፡
በዚህ ላይ እንደተገለጸው እግዚአብሔር አምላክ ለሁላችንም እርሱን የምናገለግልበትንና ለእርሱ በመታመን ዘላለማዊ ክብርን የምናገኝበትን ዕውቀትን ማስተዋልን’ ሀብትን’ ዓቅም ወይም ጉልበትን ሌሎችንም ልዩ ልዩ ስጦታዎችን ለእኛ ለሰው ልጆች እንደየዓቅማችን መጠን ሰጥቶናል፡፡
እነዚህ ሁሉ ነገሮች የሥጋችንን ምኞት እንድንወጣባቸው የተሰጡ ሳይሆኑ ነፍሳችን የምትከብርበትን መልካም ሥራን የምንሠራባቸው ናቸው፡፡
በመሆኑም እርሱ በሰጠን የአገልግሎት ጸጋ በታማኝነት በማገልገል በተሰጠን ነገር ሁሉ መንፈሳዊውን ሀብት የምናተርፍ ልንሆን ይገባናል፡፡ ምክንያቱም እኛ የተጠራ ነው ፍሬ ልናፈራና ሌላውንም ልናተርፍ መልካም ሥራን ልንሠራ እንጅ የሥጋችንን ፈቃድ በመከተል የኃጢኣት ባሮች ልንሆን አይደለም፡፡
ከላይ እንደተመለከትነው በልዑል አምላክ በእግዚአብሔር አንደበት አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ መባልን የመሰለ አስደሳችና አስደናቂ ነገር የለም፡፡ ይህ ደግሞ የሚገኘው ሃይማኖትን በሥራ በመግለጥ እንጅ ሃይማኖትን በልቦና በመያዝ ብቻ አይደለም፡፡ ከእነዚህም እንደ አቅማቸው መክሊት ተሰጥቷቸው ሌላ መክሊት ካተረፉት በጎና ታማኝ አገልጋዮች ከተባሉት የምንማረው እውነታ ይህ ነው፡፡ ስለዚህም በብዙ ለመሾም በጥቂቱ መታመን ግድ ነው፡፡
አንድ መክሊት የተሰጠውን ሰው ስንመለከተው ጌታውን ጨካኝ አድርጎ ከመቁጠር ውጪ በተሰጠው መክሊት ወጥቶ ወርዶ ሊያተርፍ አልወደደም፡፡ መክሊቱንም ባስረከበ ጊዜ በጌታው ላይ የተናገራቸው ቃላት የእርሱን አለመታዘዝና አመጸኝነት ይገልጡ ነበር፡፡
በመሆኑም ይህ ሰው በጥቂቱ መታመን ያቀተውና በአስተሳሰቡ ደካማነት እጅግ የተጎሳቆለ ሰው ነው፡፡ በዚህ ምሳሌ መሠረት ይህ ባለአንድ የተባለው ሰው ዓላውያን እሳት ስለት አሳይተው ቢያስክዱኝ መናፍቃን ተከራክረው መልስ ቢያሳጡኝ በማለት ሃይማኖቱን በልቡ ሸሽጎና ቀብሮ ከመያዙ ባሻገር በጌታ ፊት በድፍረት ቆሞ አንተ ሕግ ሳትሠራ በአዕምሮ ጠባይዕ አውቃችሁ’ መምህርም ሳትሰጥ በሥነ ፍጥረት ተመራምራችሁ በሠራችሁ ብለህ የምትፈርድ ጽኑ ጨካኝ መሆንክን አውቃለሁና ዓላውያን እሳት ስለት አሳይተው ቢያስክዱኝ መናፍቃን ተከራክረው መልስ ቢያሳጡኝ ብየ ፈርቼ ሃይማኖቴን በልቡናየ ይዠዋለው በአዕምሮየ ጠብቄዋለሁ የሚል ሃይማኖቱን ግን በሥራ የማይገልጥ ሰነፍ ሰውን ያመለክታል፡፡
ለዚህ ዓይነት ሰው የጌታ መልስ ደግሞ በምሳሌው መሠረት የሚከተለው ነው፡፡ እኔ ሕግ ሳልሠራ በአዕምሮ ጠባይዕ አውቃችሁ መምህር ሳልሰጥ በሥነ ፍጥረት ተመራምራችሁ አውቃችሁ በሠራችሁት ብየ የምፈርድ ጽኑ ጨካኝ መሆኔን ታውቃለህን? እንዲህስ ካወቅህ ሹመትክን ልትመልስልኝ ይገባኝ ነበር፡፡ ወጥቶ ወርዶ ለሚያስተምር በሰጠሁት ነበር፡፡ አሁንም የእርሱን መምህርነት ሹመት ነሥታችሁ (ወስዳችሁ) ለዚያ ደርቡለት! እርሱን ግን አውጡት የሚል ነው፡፡ ዛሬም እያንዳንዳችን በዓቅማችን መጠን መክሊት ተሰጥቶናል፡፡ በመሆኑም መክሊቱን እንደቀበረው እንደዚያ ሰው የተሰጠንን ቀብረን ለወቀሳና ለፍርድ እንዳንሰጥ በአገልግሎታችን ልንተጋ ይገባናል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንኑ ሲገልጥ ‹‹አገልግሎት ቢሆን በአገልግሎታችን እንትጋ የሚያስተምርም በማስተማሩ ይትጋ የሚሰጥም በልግሥና ይስጥ›› (ሮሜ12፥7) በማለት ተናግሯል፡፡ ለመሆኑ ዛሬ ‹‹አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ…›› ተብሎ በእግዚአብሔር ሊመሰገን የሚችል ማን ይሆን? በእውነት በዘመናችን እንዲህ ተብሎ የሚመሰገን በጎና ታማኝ ካህን’ ታማኝ መምህርና ሰባኪ’ ታማኝ ዘማሪ የመሳሰለውን ማግኘት ይቻል ይሆንን? ትልቅ መሠረታዊ ሊሆን የሚገባው ጥያቄ ቢኖር ይህ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ስለ ታማኝነት የሁላችንንም ሕይወት የሚዳስስና ሁላችንንም የሚመለከት ነውና፡፡
በእርግጥም ዛሬም ቢሆን እንደ አባቶቻችን ማለትም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት በእምነት’ በትዕግስት በፍቅር’ በትህትናና በትጋት በማገልገል የተሰጣቸውን መክሊት የሚያበዙ አገልጋዮች አሉ፡፡ የእነዚህ ክብራቸው በምድርም በሰማይም እጅግ የበዛና ራሳቸውን አስመስለው በትምህርት የወለዷቸው ልጆቻቸውም ለቤተክርስቲያን ውድ ልጆች ናቸው፡፡
ለምሳሌ ቅዱስ ጴጥሮስ ቀሌምንጦስን’ ቅዱስ ጳውሎስም ጢሞቴዎስን አፍርተዋል፡፡
ሌሎችም አበው ቅዱሳን በወንጌል ቃል መንፈሳውያንና ትጉሃን የሆኑ ምእመናንን በሚገባ አፍርተዋል፡፡ ያላመኑትንም አሳምነው ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን በመመለስ ለዘላለማዊ ክብር የበቁ እንዲሆኑ አስችለዋቸዋል፡፡ በመሆኑም በክርስቶስ በደሙ የተከፈለውን ወደር የሌለውን ዋጋ ዓለም አምኖና አውቆ በክርስትና ሃይማኖት እንዲድንበትና እዲጠቀምበት በማድረግ እንዲሁም በታማኝነት ሥራቸው ጥንትም ዛሬም ላለችዋና ወደፊትም ለምትኖርዋ ቅድስት ቤተክርስቲያን ድምቀትም ውበትም የሆኑት ቅዱሳን አበው ሊገኙ የቻሉት ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰውን ደስ ለማሰኘት በመድከማቸው ሳይሆን የተጠሩበትን ዓላማና የጠራቸውን እርሱን በሚገባ አውቀውና ከልብ ተረድተው ለዘላለማዊ ህይወት ተግተው በመሥራታቸው ነው፡፡ (ገላ1፥10)
ዛሬም በዚህ ዘመን ያለንና በክርስቶስ ክርስቲያን ተብለን የተጠራን ሁላችንም የተሰጠንን መክሊት (ጸጋ) አውቀን ለእግዚአብሔር ለአምላካችን በመታመን ወጥተን ወርደን ሌላ ልናተርፍ ይገባናል፡፡ በተለይ ደግሞ በክህነት አገልግሎት ውስጥ ያለ ሰው ከምንም በላይ በከፍተኛ መንፈሳዊ ኃላፊነት ላይ ያለ እንደመሆኑ መጠን በሃይማኖትም በሥነምግባርም ለሌላው ዓርዓያ በመሆን እንደ እርሱ ሃይማኖትን ከምግባር ጋር አስተባብረው የያዙ ምእመናንን ማፍራት አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ብቻ ነው አንተ በጎ ታማኝ ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃልና ወደ ጌታህ ደስታ ግባ ልንባል የምንችለው፡፡
አሁን ባለንበት በዘመናችን ብዙ ፈታኝ የሆኑ ችግሮች አሉ፡፡ የችግሮቹም መሠረታዊ ምንጭ በተጠሩበት ጸንቶ መቆም ፈጽሞ አለመቻልና ለሥጋዊ ጥቅም ብቻ በማድላት ኃላፊነትን መዘንጋት ናቸው፡፡ በሥጋዊ አምሮት ፍላጎትና ምርጫ ውስጥ ደግሞ መንፈሳዊ ጸጋንና በረከትን ለማግኘት የሚያስችለንን የታማኝነት ሥራን መሥራት አይቻልምና ከምናድነው ሰው ይልቅ መክሊታችንን በመቅበር መሰናክል የምንሆንበት ሰው ሊበዛ እንደሚችል አያጠራጥርም፡፡ በመሆኑም ከእርሱ ዘንድ እንደዓቅማችን የተሰጠንን መንፈሳዊ ዕውቀት ለሌላው በማድረስ መክሊታችንን ልናበዛ የምንችለውና አገልግሎታችን ወይም ክርስትናችን ውጤታማ የሚሆነው ምርጫችንን አውቀን እንደ ቃሉ ሆነንና ጸንተን ስንገኝ ብቻ ነው፡፡
ይህ ባለመሆኑ ነው ዛሬ ብዙዎቻችን በህይወታችን ሌላውን ማትረፍ አቅቶን በእግዚአብሔርና በሰውም ዘንድ በሚያስወቅሰን የስንፍና መንገድ ላይ ቆመን የምንገኘው፡፡ ስለዚህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ›› (ማቴ24፥42) ብሎናል፡፡
እንግዲህ ቃሉን የሰማንና የምናውቅ ሁላችን በሞቱ ላዳነን፣ በልጅነት ጸጋም ላከበረን፣ በትንሣኤውም ላረጋጋን፣ በመስቀሉ ጥልን ገድሎ ከራሱ ጋር ላስታረቀን፣ በደሙም መፍሰስ ህይወትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ በረከትንና ዘላለማዊ ደስታን ለሰጠን አምላክ ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በመታመን እርሱ ያዘዘንን ሁሉ ልናደርግ ይገባናል፡፡ ምን ጊዜም ትጉህ ሠራተኛ ደግሞ የሚሠራው መልካም ሥራ ሁሉ ለቤተ ክርስቲያንም ለሀገርም የሚሰጠው ጥቅም እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ በመሆኑም በጎና ታማኝ አገልጋዮች ሆነን እንድንገኝ ጠንክረን ልንሠራ ይገባናል፡፡


ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አማካይነት በምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት በደብረ ገሪዛን ጉንዳጉንዲ ቅድስት ማርያም፤ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሽሬ እንዳሥላሴ ሀገረ ስብከት በአስገደ ጽምባላ ወረዳ በአቡነ ቶማስ ደብረ ማርያም ዘሃይዳ፤ በምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት በማቅናት አጽቢ ወምበርታ ወረዳ በደብረ ቅዱሳን ዲቦ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳማት ያከናወናቸውን ፕሮጀክቶች አስመረቀ፡፡
ገዳሙ ያለበትን ችግር በማጥናት የውኃ ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት የተደረገ ሲሆን፤ መንገዱ በጣም አስቸጋሪና ከ3-4 ሰዓት በእግር የሚያስኬድ በመሆኑ አባቶች በሸክም፤ እንዲሁም ግመሎችን በመጠቀም የግንባታ ቁሳቁስ በማመላለስ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ተችሏል፡፡
በምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት ከተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ደግሞ ለደብረ ገሪዛን ጉንዳጉንዲ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም የተገነባው ሁለገብ ሕንፃ ነው፡፡ ሁለገብ ሕንፃው በአዲግራት ከተማ የተገነባ ሲሆን፤ ለተለያየ አገልግሎት በማከራየት ገቢ ማስገኘት የሚችል ነው፡፡ ሕንፃው በብር 2,326,717.87 /ሁለት ሚሊዮን ሦስት መቶ ሃያ ስድስት ሺሕ ሰባት መቶ ዐሥራ ሰባት ብር ከ87 ሣንቲም/ ተገንብቶ የርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ተከናውኗል፡፡
በተጨማሪም በምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት በማቅናት አጽቢ ወምበርታ ወረዳ በደብረ ቅዱሳን ዲቦ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም ማኅበሩ በብር 225,343.65 /ሁለት መቶ ሃያ አምስት ሺህ ሦስት መቶ አርባ ሦስት ብር ከ65 ሣንቲም/ ተግባራዊ ያደረገውን የሽመና ውጤቶችን መሥሪያ አዳራሽ ሠርቶ በማጠናቀቅ፤ የሽመና ቁሳቁስ በማሟላት፤ እንዲሁም የልብስ ሥፌት መኪናዎችን ገዝቶ በማቅረብ ርክክብ ተደርጓል፡፡
የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር በመተባበር ከ2004- 2007 ዓ.ም. 16,630 አዳዲስ አማንያንን በማስተማር መጠመቃቸውን የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ፡፡
የጂንካ ደብረ ቀራንዮ መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጀማል ዑመር /ዐምደ ሚካኤል/ ባቀረቡት ሪፖርት የቤተ ክርስቲያኑ ሕንፃ ሥራ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ እገዛ ላደረጉ ሁሉ ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን፤ የቤተ ክርስቲያኑን ዲዛይን በተመለከተም ሲገልጹ “የወንጌል አርበኞች የሆኑት የማኅበረ ቅዱሳን ጂንካ ማእከል አባላት የቤተ ክርስቲያኑን ዲዛይን በነጻ በመሥራት እገዛ አድርገዋል” ብለዋል፡፡
በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በደምቢያ ወረዳ በጣና ሐይቅ ውስጥ በ1335 ዓ.ም. ተገድማ የነበረችው የጀበራ ማርያም አንድነት ገዳም ከፈረሰች ከበርካታ ዘመናት በኋላ ዳግም ለማቋቋም ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገዳሙን መልሶ ለማቋቋም በማስተባበር ላይ የሚገኙት አባ ዘወንጌል ገለጹ፡፡
በስድስት ወራት ውስጥ የተጀመረው ግንባታም በመፋጠን ላይ ሲሆን፤ ሠርቶ ለማጠናቀቅም በርካታ ሥራዎች ይቀራሉ፡፡ የጣሪያ ቆርቆሮ፤ የበር፤ የመስኮት፤ የቤተ መቅደስ፤ የማጠናቀቂያ ሥራዎችና ሌሎችም ስለሚቀሩት በባለሙያዎች ተጠንቶ 1.2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንደሚያስፈልገውና ይህንን ለማሟላት የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው በችግር ውስጥ እንደሚገኝ አባ ዘወንጌል ገልጸዋል፡፡ በጎ አድራጊ ምእመናንም ገዳሟ ያለችበትን ሁኔታ በመረዳት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡


ከአጸደ ሥጋ ዓለም በሞት ተለይተው በአጸደ ነፍስ የሚገኙ ቅዱሳን ፓትርያኮችና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ጥቅምት 9 ቀን 2007 ዓ.ም በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጸሎተ ፍትሐት ተደረገላቸው፡፡ ሥርዓተ ጸሎተ ፍትሐቱ በተለይ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ፣ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖትና ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳትን እንዲሁም ቤተክርስቲያንን አገልግለው ያለፉ አበው የታሰቡበትና በረከታቸው በአጸደ ሥጋ ላለነው እንዲደርስ ጸሎት የተደረገበት ነው፡፡
ቅዱስነታቸው አያይዘውም “እናትና አባትህን አክብር የሚለውን የጌታን ትእዛዝ ለመፈጸም በዚህ ቦታ ተገኝተናል በመንፈስ ወልደውና በምግባር አሳድገው ለዚህ ስላበቁን እነሱን ማክበርና ማስታወስ ግዴታችን ነው፡፡ ስለሆነም ይህ መታሰቢያ በዓል በየዓመቱ እንዲከበር በቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑ የሚመሰገን ነው፡፡” በማለት ቀደምት የቤተክርስቲያን አበውን መዘከር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በዚሁ እለት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የመታሰቢያ ሐውልት ተመርቋል፡፡ የመታሰቢያ ሐውልቱ የተሠራው በቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያና ትዕዛዝ ሲሆን፤ ወጭውን ደግሞ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መሸፈኑን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጁና የወላይታ ኮንታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ አስታውቀዋል፡፡ 
የ33ኛው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ማጠቃለያ መርሐ ግብር የተጀመረው ከረፋዱ 2፡46 ነበር፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፖትርያርክ አቡነ ማትያስ ጉባኤውን በጸሎት ከከፈቱ በኋላ ብፁዕ ዶ/ር አቡነ ገብርኤል “ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን” በሚል ርዕስ ከምንጊዜውም በላይ የቤተ ክርስቲያንን
በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ለሦስት ቀናት በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ ውይይት እንዲደረግ ጋብዘዋል፡፡ ሆኖም ግን ቅዱስ ፓትርያርኩ በጉባኤው መክፈቻ ዕለት ማኅበረ ቅዱሳንን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ላይ ብቻ ሰፊና ጠንካራ ውይይቶች ተደርጓል፡፡
በመጨረሻም በበጀት ዓመቱ በልማት፣ ዓመታዊ ገቢ
ሪፖርት አቅራቢ ሥራ አስኪያጆችና የሰሜን አሜሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በ2006 ዓ.ም የሥራ ዘመን ክንውን ሪፖርታቸውን የጉባኤው ታዳሚዎች ሲያቀርቡ የሪፖርቱ ይዘት ጉባኤውን በሐሴት እንዲሞላ፣ አንገት እንዲደፋና የዕንባ ዘለላ እንዲወርድ ያደረገ ነበር፡፡
ዓመታዊ ገቢ ማሳደግን በተመለከተ በርካታ ሀገረ ስብከቶች ካለፈው ዓመት ገቢ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ዕድገት ማሳየት መዘገቡ ይበል የሚያሰኝ ሲሆን ለነዚህ አገልግሎቶች ስኬታነት የማኅበረ ቅዱሳን ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበርና በሥልጠና፣ በስብከተ ወንጌል፣ በሕንፃ ዲዛይን በገዳማትና አብነት ትምህርት ቤት ድጋፍ ወዘተ የተደረገው ድጋፍ ከፍተኛ የነበረ ሲሆን በተለይ በተደረገ ሥልጠና አንዳንድ ሀገረ ስብከቶች የሀገረ ስብከቶች ዓመታዊ ገቢያቸው የሥራ ተነሳሽነታቸው መጨመሩም በሪፖርቱ ተወስቷል፡፡
ጥቅምት 6 ቀን 2007 ዓ.ም እና ጥቅምት 7 ቀን 2007 ዓ.ም ትምህርተ ወንጌል በብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ትምህርተ ወንጌል የጉባኤው ታዳሚ ስለ እናት ቤተ ክርስቲያን ይበልጥ እንዲያስብ፣ እንዲሠራ፣ እንዲተጋ ያሳሰበ ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶስም በተለይ የአጽራረ ቤተ ክርስቲያንን ስውር ተልዕኮ ተረድቶ ቤተ ክርስቲያኒቷን እንዲጠብቅ የሚያሳስብ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡