ዕረፍተ አቡነ ሀብተ ማርያም
ዲያቆን መልአኩ ይፍሩ
ኅዳር ፳፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
በተከበረች በኅዳር ፳፮ ቀን ንዑድ ክቡር ንጹሕ መነኰስ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ አባታችን አቡነ ሀብተ ማርያም የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው። ይህም ቅዱስ አባት የትውልድ ሀገሩ የራውዕይ በምትባል በስተ ምሥራቅ ባለች ሀገር ውስጥ ሲሆን በዚያም ስሙ ፍሬ ቡሩክ የሚባል አንድ ደግ ሰው ነበረ። ይህም ከክቡራን ሰዎች ወገን የሆነ ሰው እጅግ ሀብታምም የነበረ ሲሆን በሕጋዊ ጋብቻ ያጋቡት ቡርክት የሆነች ስሟ ዮስቴና የምትባል ሚስት ነበረችው። እርሷም በበጎ ምግባርና ሥራ የተጌጠች ናት። ይህችውም ደግ እናታችን በሕግ ተወስና ሳለች በጽኑዕ ገድል፣ በጾም በጸሎት በምጽዋትና በስገድትም ትጋደል ነበር።
በኋላም ጌታችን ስለመንኖ ዓለምና መንኖ ይሪት የተናገረውን አስባ ለምናኔ ሀብቷን ሁሉንም ነገር ጥላ በቅርብ ወዳለ በረሃ ሄደች። በዚያም ወደሚገኝ አንድ ዋሻ ብትገባ ድንገት አንድ ደግ ባሕታዊን አገኘች። ያም ባሕታዊ ስለአመጣጧ በተግሣጽ መልክ ቢጠይቃት እርሷ የመጣችው በዚያ ሰው እንደሌለ አስባ እንደሆነ ነገረችውና ከዚያ ወጥታ ወደ ሌላ ዋሻ ልትሄድ ስትል በመንፈስ ቅዱስ ተገልጦለት ከእርሷ ደግ የሆነ ቅዱስ ፍሬ እንደሚወጣ ነግሮ ወደ ዓለም እንድትመለስ አዘዛት። እርሷም እግዚአብሔር የወደደው ይሁን ብላ እያመሰገነች ተመልሳ ሳለ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ይህን ታላቅ ጻድቅ ፀንሳ ወለደች። በዚህም ሁላቸውም እጅግ ተሰኙ። እንደሥርዓቱም ሲጠመቅ የመጽሐፍ ስሙን ሀብተ ማርያም አሉት። እርሱ በሕግ በሥርዓት እያደገ ሄደ። ወደ ቤተ ክርስቲያንም ሲወስዱት እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ የሚለውን ጸሎት ቢሰማ እጅጉን ወደዳት። እርሷንም ይዞ ከቤቱ ሌሊቱን የሚጸልይና የሚጋደል ሆነ።
በኋላም አባቱ እረኝተን ሰዶት ሳለ በዚያ በጎቹን ሲጠብቅ ሳለ የበግ ጠባቂዎቹን ዛሬ ዝናም ይዘንማልና እንግባ አላቸው። እነርሱም ምን ደመና አለና ነው፤ ቀኑ ብራ ነው አሉት። ባልሰሙትም ጊዜ እርሱ በጎቹን ይዞ ወደ ቤቱ እንደገባ ኃይለኛ ዝናም፣ ነፋስና መብረቅ የቀላቀለ ዘነመ። በሌላም ጊዜ እንዲሁ አንድ እረኛ በጉልበት በአባ ሀብተ ማርያምን በትሩን ነጠቀው። መልስልኝ ብሎ በስመ እግዚአብሔር ቢያምለውም እምቢ አለው። ኋላም በተወው ጊዜ እግዚአብሔር ያን እረኛ በአየር ላይ ሠቅሎ አዋለው። እረኞቹም አባ ሀብተ ማርያምን በለመኑት ጊዜ እግዚአብሔር ነውና ስለስሙ ብሎ የቀጣው መሐሪው እርሱ ከወደደ ይማረው ሲል ያእረኛ ተፈታና ወረደ። መጥቶም ከአባታችን እግር ወደቀ፡፡
ከብዙ ዘመናት በኋላም ስሟ እለ አድባር ወደምትባል ገዳም ገብቶ ከአባ መልከ ጼዴቅ እጅ መነኰሰ። ታላቅ ተጋድሎንም ይጋደል ጀመር። በባሕር መካከልም በመቆም መዝሙረ ዳዊትን ይደግምና ግንባሩም የባሕሩን አሸዋ እስኪነካ አምስት መቶ ጊዜ ይሰግዳል። እህልም መቅመስን ትቶ ልክ እንደ ዋልያዎች የዱር ቅጠል የሚመገብ ሆነ። ዐርባ ዐርባ፣ ሰማንያ ሰማንያ ቀንም የሚያከፍል ሆነ። በሌሊትም ቁሞ በማደር (በትጋሃ ሌሊት) በቀንም አራቱን ወንጌላት ዘወትር ይጸልያል። ይህን ጽኑዕ ተጋድሎውንም ያየ አምላካችን ተገለጠለት። አባ ሀብተ ማርያምም ከግርማው የተነሣ ደንግጦ በግንባሩ ተደፋ። ጌታችንም እፍ ብሉ አጽናንቶ ኃይል ጽንዕ ሰጥቶ አሥነሳውና ‹‹ወዳጄ ሀብተ ማርያም ላጠፋህ ሳይሆን ኃይል ጽንዕ ቃል ኪዳንም ልሰጥህ ነውና የመጣሁት አትፍራ›› አለው።
ጽኑዕ ተጋድሎው በሰማያት ስለመጻፉ፣ የቅዱስ ማቴዎስንና የማርቆስን ወንጌል በሚያነብ ጊዜ ከሌሎች ሥውራን አበው ጋር የሚገናኝበትን የብርሃን ሠረገላ እብደሰጠው፣ የቅዱስ ሉቃስንና የቅዱስ ዮሐንስን ወንጌል በሚያነብ ጊዜ ደግሞ ሥጋውን ደሙን ለመቀበል ወደ ኢየሩሳሌም የሚሄድበትን የእሳት ሠረገላ እንደሰጠው ቃል ኪዳን ገባለት። ሰባት እጅግ የሚያስደንቁ አክሊላትንም አቀዳጀው። አንዱ ስለድንግልናው፣ ሁለተኛው ዓለምንና በውስጡ ያለውን ስለመመነኑ፣ ሦስተኛው ፍጹም ስለሆነው ምንኲስናው፣ አራተኛው አራቱን ወንጌላት አዘውትሮ በማንበቡ፣ አምስተኛው ስለፍቅሩ ሲል ረኃብና ጥምን በመታገሡ፣ ስድስተኛው በልቡ ቂምንና በቀልን ባለማኖሩ፣ ሰባተኛው ደግሞ ስለንጹሕ የክህነት አገልግሎቱና በንጽሕና ስለሚያሣርገው መሥዋዕቱ መሆኑን ነገረው። መታሰቢያውን ለሚያደርጉና በስሙ ለሚዘክሩ፣ ከእነርሱ ጋር የሚኖርበትን አምስት መቶ የወርቅ አምዶስ ያሏትን ቦታ ሰጠሁህ አለው። ቅዱሳን መላእክትም ሁላቸው እየተደሰቱ ወንድማችን ወደማያልቀው ሰማያዊ ደስታ ልንወስድህ መጥተናል አሉት።
ይህንንም በተናገረ ጊዜ ጌታችን በሦስትነቱ ተገልጦ ታየው። መታሰቢያህን ለሚያደርግ፣ በስምህ ለቤተ ክርስቲያን መባ ለሚሰጥ፣ ወደዚህች አገር አገባዋለሁ። አራቱን ወንጌልም እያነበብህ ስለኖርህ የየአንዲቱን ቃል ፍሬዋን አንዳንድ ሺህ አደረግሁልህ። ይኸውም ከአንተ በኋላ ለሚመጡት ልጆችን መጽሐፈ ገድልህን ለሚያነቡና በእምነት ለሚሰሙ፣ የገድልህን መጽሐፍ በተነበበበት ውኃ ለሚረጩ፣ ለሚነከሩበት ይህ ቃልኪዳን ሰጥቼሃለሁ። ከዚህም በኋላ ጌታችን ሦስት ጊዜ ሳመው። ነፍሱም ከሥጋው በሰላም ተለየች። ቅዱሳን መላእክትም በታላቅ ደስታ እያመሰገኑ አሣረጓት።
እግዚአብሔር አምላካችን በዚህ ታላቅ ጻድቅ ጸሎት ይማረን፤ በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር፤ ለዘላለሙ አሜን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን