የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ከምረቃ በኋላ የሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች
በመ/ር ተመስገን ዘገዬ
ክፍል ፪
የተከበራችሁ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎቻችን በክፍል አንድ ዝግጅታችን ከምረቃ በኋላ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በተመለከተ ሦስት ነጥቦችን ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ እነዚህም፡- እንደተመረቁ ሥራ አለመያዝ፣ አለመረጋጋት እና መወሰን የሚሉ ነጥቦችን አይተናል፡፡ ቀጣዩቹን ነጥቦች ደግሞ በክፍል ሁለት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ክርስትናም በእምነት እያደጉ እየጠነከሩ የሚጓዙበት ሕይወት እንጂ ባለህበት እርገጥ ዓይነት አይደለም፡፡ አንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተመራቂ ከትናንት ዛሬ፣ ከአምና ዘንድሮ አድጎና ጠንክሮ መገኘት አለበት፡፡ ክርስትና ቱቻ ገመድ አይደለም፡፡ ተቹ ገመድ ከሣር የሚዘጋጅ ቆርቆሮ ባልነበረበት ዘመን ለቤት መሥሪያ አገልግሎት ያገለግል ነበር፡፡ቱቻ ገመድ ውኃ ሲያገኝ በጣም ይጠብቃል፡ውኃ ሲያጣ ለመበጠስ ቀላል ነው፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች በግል ሕይወታቸው ሥጋዊውን ኑሯቸውን ከመንፈሳዊ ኑሯቸው ጋር አጣጥመው መጓዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ብዙዎቻችን መንፈሳዊ ሥራን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የጨረስን ይመስል ትተን እንደመጣን በሄድንበት ቦታ በዓለም ፍቅር እንደነዝዛለን፡፡ እንደ ዴማስ በሄድንበት በዓለም ተውጠን እንቀራለን፡፡ “ዴማስ የአሁኑን ዓለም ወዶ ትቶኛልና ወደ ተሰሎንቄም ሄዶአል ቄርቂስም ወደ ገላትያ ቲቶም ወደ ድልማጥያ ሄደዋል “እንዳለ ( ፪ኛ ጢሞ.፬፥፲)
መጾም መጸለይ ከትናንሽ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር በማኀበር ፡ በሰንበት ትምህርት ቤት መቀመጥ ይከብደናል፡፡ ቅዱስ ዳዊት “ወንድሞች በኀብረት ቢቀመጡ እነሆ መልካም ነው፡፡እነሆም ያማረ ነው” ይላል (መዝ.133፥1) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች ከእግዚእበሔር ክብር ይልቅ የራሳችንን ክብር ይታየናል፡፡ ለሥጋችን ምቾት እንጂ ለክርስትና መስፋፋት ግዴለሾችና በእንቅልፍ ማሳለፍ እናበዛለን፡፡
ስለሆነም ከምረቃ በኋላ የምናገኘው የአካባቢና የኑሮ ለውጥ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያመጣ ይችላል፡፡
ስለዚህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች በአካባቢ፣ በጓደኛ፣ በኑሮ ለውጥ ተውጠን የግል ሕይወታችን ተበላሽቶ እንዳይቀር ራሳችን መግለጽ፤ ዘወትር መጸለይ፤ ከእግዚአብሔር አለመራቅ፤ በማይመች አካሄድ አለመጠመድ፤ ከምክንያተኝነት መራቅ፤ ተስፋ አለመቁረጥ፤ ኑሮን በመርሐ ግብር መምራት፤ የምሥጢራት ተካፋይ መሆን ይገባል፡፡
ራስን መግለጽ፦ይህ ሲባል ግን እኔ የማኀበሩ አባል ነኝ፣ እኔ ሰባኪ ነኝ ማለት ሳይሆን በኑሯችን እንግለጸው ለማለት ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” ብሏል፡፡ (ማቴ .፭፥፲፮)
ክርስትና ማስመሰል ሳይሆን ሁኖ መገኘት ይፈልጋል፡፡ መንፈሳዊ ሕይወታችን ጊዜና ቦታ የሚወስነው ሳይሆን የሁል ጊዜ ኑሯችንና መታወቂያችን ነው፡፡ ምክንያቱም ክርስትና የምንተርከው ታሪክ ሳይሆን የምንኖረው ሕይወት ስለሆነ ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት “ተግባር ከቃል የበለጠ ይሰብካል“ ይላሉ፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን አንደበተ ርቱዕ የሆኑ ሰዎች አላጣችም፤ የተቸገረችው በሕይወቱ አርአያና ምሳሌ የሚሆን ሰው ግን ማግኘት በ፳፩ኛ ክፍለ ዘመን እየተቸገርን ነው፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂ ወጥ የሆነ ክርስቲያናዊ ሕይወት ሊኖረው ይገባል፡፡ ከግቢ ጉባኤው ተመረቆ ሲወጣ መንፈሳዊ አገልግሎትን የሚዘነጋ (የሚተው) ከሆነ መንፈሳዊ አገልግሎት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ገና አልገባውም ማለት ይቻላል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ቅዱስ ልጁን ጢሞቴዎስን “ቃሉን ስበክ፣ በጊዜውም አለ ጊዜውም ጽና ፈጽመህ እየታገሥክና እያስተማርክ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም” ብሎታል፡፡ (፪ኛ ጢሞ. ፬፥፪) በነገራችን ላይ ማስተማር በዐውደ ምሕረት አትሮንስ ላይ በመሆን ማስተማር ብቻ አይደለም፡፡ በሕይወት በሥራና በተግባር ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች በምንሄድበት ቦታ ሁሉ፣ በቤታችን ውስጥ፣ በሠፈራችን፣ በሥራ ቦታችን ክርስትናችን በኑሯችን ሊገለጥ ይገባል፡፡ ክርስትናችን የሚነበብ መጽሐፍ መሆን አለበት ፡፡
“…በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም፣ በንጽሕናም ለሚያምኑት ምሳሌ ሁን” (፩ኛ ጢሞ. ፬፥፲፩-፲፪) የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች ከላይ በተጠቀሱት መሠረታዊ ነጥቦች ስንመዘን ምሳሌ የሚሆን ሕይወት ይኖረን ይሆን? አንዳንዶች ራስን መግለጽ ሲባል “ግብዝነት” ይመስላቸዋል፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ተለይተው በዓለም ቀልጠው የቀሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ማንነታችን በሰዎች ዘንድ ከታወቀ ሰዎች ለእኛ ታላቅ ክብር አላቸው፡፡ ይህ ክብር የእግዚአብሔር መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ እንደ ክርስትና የሚስከብር ሌላ ምንም ነገር የለም፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች በጸሎት ሕይወት መበርታት ይኖርባቸዋል፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ “ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች” ይላል (ያዕ. ፭÷፲፯) ማር ይስሐቅ “ዕንባሕ ከመፍሰስ እንዳያቆም ከወደድህ በጸሎት ጽሙድ ሁን” ይላል። “ጸሎት ከልዑል እግዚአብሔር ጋር የሚነጋገራት ናት” (ፍትሐ ነገሥት ንባቡና ትርጓሜው አንቀጽ ፲ ወ፬ቱ)
ጌታችንም በመከራው ሌሊት ፫ ጊዜ ጸለየ ደቀ መዛሙርቱን “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ “አለ፡፡ (ማቴ. ፳፮÷፵፩) የዕውቀት ደጋፊዎችን ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ለጸሎት መትጋት ይኖርብናል። የዲያብሎስ አጽመ ርስት ኃጢአት እንዳይነግስብን በጸሎት ሕይወት ፍኖተ አበውን በመከተል መትጋት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች አንዱ የቤት ሥራ ነው፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች ሕዋሳትን ሰብስበን በሰቂለ ኀሊና:በነቂሐ ልቡና ሁነን ወደ እግዚአብሔር መጮኽ አለብን። ከሌሊቱ ዕንቅልፍ በመቀነስ መጸለይ ብልህነት ነው ። የጸሎት መጽሐፍ፣ ምስለ ፍቁር ወልዳ በሁሉም እንቅስቃሴያችን መለየት የለባቸውም፡፡ ጥሩ የጸሎት ሕይወት ያለው ክርስቲያን አይወድቅም፣ ቢወድቅም ይነሳል፡፡
ነቢዩ “ጠላቴ ሆይ ብወድቅ እነሣለሁና በጨለማም ብቀመጥ እግዚአብሔር ብርሃን ይሆንልኛልና “እንዳለ (ሚክ. ፯፥፰) እኛም በሥራችን፣ በአገልግሎታችን መውደቅ፣ መነሣት መኖሩን መረዳት ይኖርብናል፡፡ ተስፋ መቁረጥ የለብንም፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!