“ጾም የነፍስን ቊስል ትፈውሳለች” (ቅዱስ ያሬድ)
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከሚከናወኑ ዐበይት ክርስቲያናዊ ምግባራት መካከል ጾም አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ጾም “ጾመ” ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ተከለከለ፤ ተወ፤ ታቀበ፤ ታረመ ማለት ነው፡፡ (ጾም እና ምጽዋት ገጽ ፰)
የቤተ ክርስቲያናችን የሕግና የሥርዓት መጽሐፍ የሆነው ፍትሐ ነገሥት ደግሞ በአንቀጽ ፲፭ ላይ ጾምን “ጾምሰ ተከልኦተ ብእሲ እመብልዕ በጊዜ ዕውቅ በውስተ ሕግ፤ ጾምስ በታወቀው ዕለት፤ በታወቀው ሰዓት ከምግብ መከልከል ነው” በማለት ይተረጕመዋል፡፡
እንግዲህ በሃይማኖታዊ ትርጉሙ ጾም ማለት ራስን ከእህል፤ ከውኃ ብሎም አምላካችን እግዚአብሔር ከሚጠላቸው እኩይ ምግባራት ሁሉ ራስን በመከልከል የሥጋን ፈቃድ ለነፍስ በማስገዛት መቆየት ማለት ነው፡፡
ጾም በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን የታወቀ፣ በነቢያት የነበረ፣ በክርስቶስ የጸና፣ በሐዋርያት የተሰበከ እና የተረጋገጠ መንፈሳዊ ሕግ፤ ፈጣሪን መለመኛ መንፈሳዊ መሣሪያ ነው፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ የእግዚአብሔርን ጥሪ ተከትሎ ወደ ተራራ በወጣ ጊዜ ለአርባ ቀንና ሌሊት ምግብና ውኃ እንዳልቀመሰ ይነግረናል፡፡ “ሁለቱን የድንጋይ ጽላት፥ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር የተማማለባቸውን የቃል ኪዳን ጽላት፥ እቀበል ዘንድ ወደ ተራራ በወጣሁ ጊዜ፥ በተራራው ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ተቀምጬ ነበር እንጀራ አልበላሁም፥ ውኃም አልጠጣሁም” ተብሎ እንደተጻፈ። (ዘዳ.፱፥፱) ነቢዩ ዕዝራም “በአምላካችን ፊት ራሳችንን እናዋርድ ዘንድ ከእርሱም የቀናውን መንገድ ለእኛ እና ለልጆቻችን ለንብረታችንም ሁሉ እንለምን ዘንድ በዚያ በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾም አወጅሁ” (ዕዝ. ፰፥፳፩) በማለት ራስን ዝቅ በማድረግ ለአምላክ ፈቃድ መገዛት እንደሚገባ ያስተምረናል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊትም “ጉልበቶቼ በጾም ደከሙ፤ ሥጋዬም ቅባት በማጣት ከሳ” በማለት መጾሙን እንረዳለን፡፡ (መዝ ፻፰፥፳፬)
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ስለ መብልና መጠጥ ከንቱነት እንዲህ በማለት አስተምሮናል፡፡ “ራሳችሁን ጠብቁ፤ በመብልና በመጠጥ፤ በመቀማጠልና የዓለምን ኑሮ በማሰብ ልባችሁን አታደንድኑ፤ ያቺ ቀንም በድንገት ትደርስባችኋለች፡፡”(ሉቃ.፳፩፥፴፬) እንዲል፡፡ ጾም ሰው ሠራሽ ሕግ ሳይሆን ልዑል እግዚአብሔር የመሠረተው፣ ከእግዚአብሔር ለሰው ልጅ የተሰጠ የመጀመሪያው ትእዛዝ ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እከብር አይል ክቡር፣ እነግሥ አይል ንጉሥ፣ እጸድቅ አይል ጽድቅ የባሕርዩ የሆነ አምላክ ነው፡፡ ለእኛ አርአያ ቤዛ ሊሆነን፣ እናንተም ብትጾሙ ብትጸልዩ አጋንንትን ድል ትነሳላችሁ ሲለን፣ ጾምን ለመባረክና ለመቀደስ፤ በመብል ምክንያት ስተን ስለ ነበር ስለ እኛ ኀጢአት እና በደል ሲል ዐርባ ቀንና ሌሊት ጾሟል፡፡
ጾም ከመንፈሳዊ ተጋድሎ አንዱ ነው፤ ለሥጋም መንፈሳዊ ልጓም ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን ፈቃደ ሥጋውን እየገታ ነፍሱን የሚያለመልምበት መንፈሳዊ ስንቅ ነው፡፡ “ጾም ቊስለ ነፍስን የምትፈውስ፤ ኃይለ ፍትወትን የምታደክም፤ የበጎ ምግባራት ሁሉ መጀመሪያ፤ ከእግዚአብሔር ጸጋን የምታሰጥ፤ የወንጌል ሥራ መጀመሪያ፤ የጽሙዳን ክብራቸው፤ የደናግል የንጽሕና ጌጣቸው፤ የዕንባ መፍለቂያዋ፤ አርምሞን (ዝምታን) የምታስተምር፤ ለበጎ ሥራ ሁሉ የምታነቃቃ፤ ሰውነትን በእግዚአብሔር ፊት በማዋረድ ትሕትናን ገንዘብ ለማድረግ የምትረዳ መድኃኒተ ነፍስ ናት፡፡ ” (ማር ይስሐቅ አንቀጽ ፬ ምዕ. ፮)
በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት ጾም በሁለት ይከፈላል፤ የአዋጅ እና የግል ጾም በማለት፡፡ በዚህም መሠረት የአዋጅ አጽዋማት የምንላቸው ሰባት ሲሆኑ እነርሱም፡-
- የነቢያት ጾም
- የገሀድ ጾም
- የነነዌ ጾም
- ዐቢይ ጾም
- የሐዋርያት ጾም
- ጾመ ድኅነት (ረቡዕና ዓርብ)
- ጾመ ፍልሰታ
እነዚህ አጽዋማት በቤተ ክርስቲያናችን በአዋጅ ጊዜ እና ወቅት ተሰጥቷቸው፣ ሥርዓትም ተበጅቶላቸው ከሰባት ዓመት ሕፃናት እስከ አረጋውያን ለተወሰነ ሰዓት ከምግብ እና ከውኃ በመከልከል በጸሎትና በበጎ ምግባራት በትጋት የሚጾሙት ነው፡፡
የግል ጾም የምንለው ደግሞ አንድ ሰው በሠራው ኃጢአት ምክንያት ለንስሓ አባቱ ተናግሮ የሚሰጠው የንስሓ ጾም ሲሆን እንዲሁም አንድ ሰው ስለደረሰበትና በእርሱ ላይ ስለሆነ ነገር ስለሚፈልገው ጉዳይ እግዚአብሔር ተገቢውን መልስ እንዲሰጠው የሚጾመው ጾም ነው፡፡ ነገር ግን በግል ጾም ጊዜ ጾሙ የሁሉ ስላልሆነ ራስን መሰወር እንደሚያስፈልግ ታዟል፡፡
ይህንንም አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ሲል ተናግሯል፡፡ “ስትጾሙም እንደ ግብዞች አትጠውልጉ ለሰዎች ሊታዩ እንደ ጾመኛ ፊታቸውን ያጠወልጋሉና አንተ ግን ስትጾም ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ በስውር የሚያይህ አባትህ በግልጥ ይከፍልሃል” (ማቴ.፮፥፲፮-፲፰) እንዲል፡፡ በዚህም መሠረት የግል ጾምን ከጿሚው ሰው እና ከእግዚአብሔር ውጭ ማንም ማወቅ የለበትም፡፡
የጾም ጥቅም፡-
ቅዱስ ያሬድ የጾምን ጥቅም እንዲህ በማለት ይገልጸዋል፡- “ጾም ትፌውስ ቊስለ ነፍስ፤ ወታጸምም ኵሎ ፍትወታተ ዘሥጋ ፤ ትሜህሮሙ ጽሙና ለወራዙት፤ ጾም የነፍስን ቊስል ትፈውሳለች፤ የሥጋን ፍትወታት ሁሉ ታጠፋለች፤ ለወጣቶችም ትሕትናን ታስተምራለች፡፡” በማለት፡፡
ጾም በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ተገለጸው የሚከተሉት ጥቅሞች አሉት፤ ጥቂቶቹን ስንመለከት፡- የሥጋን ምኞት ያጠፋል፤ የነፍስ ቍስልን ያደርቃል፤ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ያስገዛል (ፍት.ነገ.፲፭፥፭፻፷፬)፤ መላእክትን መስሎ ለመኖር ያስችላል፤ ልዩ ልዩ መከራን ያቃልላል፤ አጋንንትን ያስወጣል (ኢያ.፯፥፮-፱)፤ ሰማያዊ ክብር እና ጸጋን ያስገኛል (፩ኛነገ.፲፱፥፰)፤ በመንግሥተ ሰማያት ለመኖር የሚያስችል ምግባርን ያሠራል (ሉቃ.፮፥፳፩)፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርታ እና ምሕረትን ለማግኘት ይረዳል፤ አጋንንትን ድል ለማድረግ ያግዛል (ማቴ.፬፥፲፩፤ አስ.፯)፤ ፈቃደ እግዚአብሔርን ለመፈጸም ይረዳል (፩ኛነገ.፲፱፥፩)፤ ከእግዚአብሔር ቍጣ ለመዳን ያስችላል (ዮና.፫፥፩)፤ የተደበቀ ምሥጢርን ይገልጣል (ዳን.፲፥፲፬)፤ ከቅዱሳን በረከት ያሳትፋል፤ መንፈሳዊ ኃይልን ያሰጣል (፩ኛሳሙ.፯፥፭)፤ ጥበብን ይገልጣል (ዕዝ. ፯፥፮፤ ዳን.፱፥)/፤ ዕድሜን ያረዝማል፤ ትዕግሥትን ያስተምራል፤ ወዘተ፡፡
ጾም ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ በማስገዛት ከኃጢአት ለመራቅ ይረዳናል፡፡ የሥጋ ፍላጎት በቀዘቀዘ ቊጥር ነፍስ ትለመልማለች፤ ለአምላክ ሕግና ትእዛዛት ሁሉ ተገዢ ትሆናለች፡፡ ስለዚህ እኛም አሁን የጀመርነውን የነቢያት ጾም በሥርዓት በመጾምና በመጸለይ ለክርስቲያን የሚገቡ ምግባራትንም በመፈጸም ከአምላካችን ምሕረትን ቸርነትን እናገኝ ዘንድ እንትጋ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!